የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ሞት “በይሖዋ ፊት ውድ” የሆነው እንዴት ነው?
▪ አንድ መዝሙራዊ በመንፈስ ተመርቶ “የታማኞቹ ሞት በይሖዋ ፊት ውድ ነው” ሲል ዘምሯል። (መዝ. 116:15 NW) ይሖዋ የእያንዳንዱን እውነተኛ አገልጋይ ሕይወት እጅግ ክቡር እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ አንድ ግለሰብ ሞት ብቻ አይደለም።
የአንድን ክርስቲያን ሞት አስመልክቶ የቀብር ንግግር በሚቀርብበት ጊዜ ግለሰቡ ለይሖዋ ታማኝነቱን ጠብቆ የሞተ ቢሆንም እንኳ መዝሙር 116:15 በሟቹ ላይ እንደሚሠራ መናገር ተገቢ አይሆንም። ለምን? ምክንያቱም መዝሙራዊው የተናገረው ሐሳብ ሰፋ ያለ ትርጉም ስላለው ነው። ይህ ጥቅስ የሚያመለክተው አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ በቡድን ደረጃ እንዲጠፉ የማይፈቅድ መሆኑን ነው፤ ምክንያቱም እጅግ ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው አድርጎ ይመለከታቸዋል።—መዝሙር 72:14ን እና 116:8ን ተመልከት።
ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ በቡድን ደረጃ ከምድር ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲወገዱ የማይፈቅድ መሆኑን መዝሙር 116:15 ያረጋግጥልናል። ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ እንደሚያሳየው ከሆነ የይሖዋ ሕዝቦች ከባድ መከራዎችንና ስደቶችን በጽናት ተቋቁመዋል፤ ይህም አምላክ ፈጽመን እንድንጠፋ የማይፈቅድ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።
ይሖዋ ገደብ የለሽ ኃይል ያለውና ዓላማውን ምንጊዜም የሚፈጽም አምላክ በመሆኑ በቡድን ደረጃ ከሕልውና ውጭ እንድንሆን አይፈቅድም። አምላክ እንዲህ ያለውን ነገር ቢፈቅድ ጠላቶቹ ከእሱ የበለጠ ኃይል አላቸው ማለት ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው! በቡድን ደረጃ እንድንጠፋ የሚፈቅድ ከሆነ ምድራችን ታማኝ በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ ያወጣው ዓላማም ሳይፈጸም ይቀራል ማለት ነው፤ ይህም ቢሆን ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። (ኢሳ. 45:18፤ 55:10, 11) በታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ እሱን የሚያመልክ አንድም ሰው ከሌለ በምድር ላይ ለይሖዋ የሚቀርብ ቅዱስ አገልግሎት ሊኖር አይችልም! እንዲሁም “በአዲሱ ሰማይ” አገዛዝ ሥር ለሚኖረው “አዲሱ ምድር” ማለትም በምድራችን ላይ ለሚኖሩት ጻድቅ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ መሠረት የሚሆኑ የሰው ልጆች ሊኖሩ አይችሉም። (ራእይ 21:1) ከዚህም በላይ አንድም ምድራዊ ተገዢ ከሌለ የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት እውን ሊሆን አይችልም።—ራእይ 20:4, 5
አምላክ፣ ጠላቶቹ የእሱን ሕዝቦች በቡድን ደረጃ ከምድረ ገጽ እንዲያጠፉ የሚፈቅድ ከሆነ ይሖዋ የመግዛት መብት ያለው መሆኑ አጠያያቂ ይሆናል፤ መልካም ስሙም ቢሆን ይጎድፋል። በሌላ አባባል ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የመሆን መብቱ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። ከዚህም ባሻገር ይሖዋ ለራሱና ለቅዱስ ስሙ አክብሮት ስላለው ታማኝ አገልጋዮቹ በቡድን ደረጃ እንዲጠፉ አይፈቅድም። አምላክ ‘ፍትሕ የማያዛባ’ መሆኑንም ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ በመሆኑም በታማኝነት ሲያገለግሉት የኖሩ ሕዝቦቹን በቡድን ደረጃ እንደሚጠብቃቸው ምንም ጥርጥር የለውም። (ሮም 9:14፤ ዘፍ. 18:25) ከዚህም በላይ አገልጋዮቹ በጅምላ እንዲጠፉ መፍቀዱ “ስለ ታላቅ ስሙ ሲል እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሕዝቡን አይተውም” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር ይቃረናል። (1 ሳሙ. 12:22) በእርግጥም ይሖዋ ‘ሕዝቡን አይጥልም፤ ርስቱንም አይተውም።’—መዝ. 94:14
የይሖዋ ሕዝቦች ከምድር ላይ ፈጽመው እንደማይጠፉ ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! እንግዲያው ይሖዋ በገባልን ቃል ላይ እምነት በመጣል ምንጊዜም ለእሱ ታማኞች እንሁን፤ ይሖዋ እንዲህ ሲል ቃል ገብቶልናል፦ “በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤ የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፤ ከእኔ የሚያገኙትም ጽድቃቸው ይኸው ነው።”—ኢሳ. 54:17
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አምላክ ሕዝቦቹ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ ፈጽሞ አይፈቅድም