የአምላክ እረፍት ምንድን ነው?
የአምላክ እረፍት ምንድን ነው?
“የአምላክ ሕዝብ የሰንበት እረፍት ይጠብቀዋል።”—ዕብ. 4:9
1, 2. ከዘፍጥረት 2:3 ትክክለኛ አተረጓጎም ምን እንገነዘባለን? የትኞቹ ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?
የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ፣ አምላክ ምሳሌያዊ በሆኑ ስድስት ቀናት ውስጥ ምድርን የሰው ልጆች መኖሪያ እንድትሆን እንዳዘጋጃት ይነግረናል። በእያንዳንዱ ምሳሌያዊ ቀን መጨረሻ ላይ “መሸ፤ ነጋም” የሚል ሐሳብ ሰፍሮ እናገኛለን። (ዘፍ. 1:5, 8, 13, 19, 23, 31) ሰባተኛውን ቀን በተመለከተ ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው በሰባተኛው ቀን [“ከዚያ ቀን አንስቶ፣” NW] ነውና።”—ዘፍ. 2:3
2 “ያረፈው ከዚያ ቀን አንስቶ ነው” የሚለውን ሐሳብ ልብ በል። ይህ ሐሳብ ሰባተኛው ቀን ማለትም አምላክ ያረፈበት “ቀን” ሙሴ በ1513 ዓ.ዓ. የዘፍጥረትን መጽሐፍ በጻፈበት ወቅት ገና እንዳላበቃ ያሳያል። የአምላክ የእረፍት ቀን አሁንም እንደቀጠለ ነው? ከሆነ በዛሬው ጊዜ ወደ እረፍቱ መግባት እንችላለን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን በጣም አስፈላጊ ነው።
ይሖዋ አሁንም ‘እያረፈ’ ነው?
3. ኢየሱስ በዮሐንስ 5:16, 17 ላይ የተናገረው ሐሳብ ሰባተኛው ቀን በመጀመሪያው መቶ ዘመንም እንዳላበቃ የሚጠቁመው እንዴት ነው?
3 ሰባተኛው ቀን በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ቢሆን አላበቃም ብለን እንድንደመድም የሚያደርጉን ሁለት ማስረጃዎች አሉ። በመጀመሪያ ኢየሱስ በሰንበት ቀን የታመሙ ሰዎችን መፈወሱ፣ ሥራ ከመሥራት ተለይቶ እንደማይታይ በማሰብ ተቃዋሚዎቹ ሲነቅፉት የሰጣቸውን መልስ እንመልከት። “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም መሥራቴን እቀጥላለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 5:16, 17) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? ተቃዋሚዎቹ ኢየሱስን በሰንበት ቀን ሠርተሃል ብለው ከሰውታል። ስለዚህ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው” ሲል ለክሱ ምላሽ መስጠቱ ነበር። በሌላ አባባል ኢየሱስ እንዲህ ማለቱ ነበር፦ ‘እኔና አባቴ የምንሠራው አንድ ዓይነት ሥራ ነው። አባቴ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በዘለቀው የሰንበት እረፍቱ እየሠራ ስለሆነ እኔም በሰንበት ቀንም እንኳ መሥራት እችላለሁ።’ በመሆኑም ኢየሱስ ከሰው ልጆችና ከምድር ጋር በተያያዘ፣ ታላቁ የአምላክ የሰንበት እረፍት ማለትም ሰባተኛው ቀን በእሱ ዘመንም እንዳላበቃ ጠቁሟል። *
4. ጳውሎስ የተናገረው ነገር፣ ሰባተኛው ቀን በእሱ ዘመንም እንዳላበቃ የሚያሳይ ምን ተጨማሪ ማስረጃ ይሰጠናል?
4 ሁለተኛው ማስረጃ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረው ነገር ነው። ጳውሎስ የአምላክን እረፍት አስመልክቶ በዘፍጥረት 2:2 ላይ ያለውን ሐሳብ በጠቀሰበት ወቅት “እኛ እምነታችንን በተግባር ያሳየነው ወደዚህ እረፍት እንገባለን” በማለት በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ዕብ. 4:3, 4, 6, 9) ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ሰባተኛው ቀን በጳውሎስ ዘመንም አላበቃም ነበር። ታዲያ ይህ የእረፍት ቀን ለምን ያህል ጊዜ ይቀጥላል?
5. ይሖዋ በሰባተኛው ቀን ምን የማድረግ ዓላማ ነበረው? ይህ ዓላማ ሙሉ በሙሉ የሚፈጸመው መቼ ነው?
5 የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሰባተኛው ቀን ዓላማ ምን እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ዘፍጥረት 2:3 “እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም” ይላል። ይሖዋ ይህን ቀን ‘የቀደሰው’ ወይም የለየው ዓላማውን ከዳር ለማድረስ ነው። የይሖዋ ዓላማ፣ ምድር ታዛዥ በሆኑ ወንዶችና ሴቶች እንድትሞላ እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ምድርንም ሆነ በውስጧ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት እንዲንከባከቡ ነው። (ዘፍ. 1:28) ይሖዋ አምላክና “የሰንበት ጌታ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ‘እስካሁን እየሠሩ’ ያሉት ይህን ዓላማ እውን ለማድረግ ነው። (ማቴ. 12:8) የአምላክ የእረፍት ቀን፣ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ዓላማው ሙሉ በሙሉ እስከሚፈጸምበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል።
“የእነዚያን ያለመታዘዝ ምሳሌ” አትከተሉ
6. የትኞቹ ምሳሌዎች ማስጠንቀቂያ ይሆኑናል? ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
6 አምላክ ለአዳምና ለሔዋን ዓላማውን በግልጽ የነገራቸው ቢሆንም ከዚህ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ አልተመላለሱም። እርግጥ ነው፣ ያለመታዘዝን ጎዳና የተከተሉት አዳምና ሔዋን ብቻ አልነበሩም። ከዚያ በኋላ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የእነሱን አካሄድ ተከትለዋል። የአምላክ ምርጥ ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያንም ጭምር ሳይታዘዙ ቀርተዋል። ጳውሎስ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች ከእነሱ መካከልም እንኳ አንዳንዶቹ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በወደቁበት ወጥመድ ሊወድቁ እንደሚችሉ ያስጠነቀቃቸው መሆኑ ትኩረታችንን የሚስብ ነው። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ስለዚህ ማንም የእነዚያን ያለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ በመፍራት ወደዚያ እረፍት ለመግባት የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።” (ዕብ. 4:11) ጳውሎስ አለመታዘዝን ወደ አምላክ እረፍት ካለመግባት ጋር እንዳያያዘው ልብ በል። ይህ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚጋጭ የሆነ ነገር ብንፈጽም ወደ አምላክ እረፍት አንገባም ማለት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በመሆኑ ይህን ጉዳይ በስፋት እንመለከተዋለን። አሁን ግን እስራኤላውያን የተዉትን መጥፎ ምሳሌ በመመርመር ወደ አምላክ እረፍት መግባትን በተመለከተ ምን ተጨማሪ ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።
“ወደ እረፍቴ ፈጽሞ አይገቡም”
7. ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት የታደገበት ዓላማ ምን ነበር? ከእነሱስ ምን ይጠበቅ ነበር?
7 ይሖዋ እስራኤላውያንን በተመለከተ ያለውን ዓላማ በ1513 ዓ.ዓ. ለአገልጋዩ ለሙሴ ገልጾለታል። አምላክ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈሰው ሰፊና ለም ወደ ሆነችው . . . ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ።” (ዘፀ. 3:8) ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን ‘ከግብፃውያን እጅ የታደገበት’ ዓላማ ለቅድመ አያታቸው ለአብርሃም በገባለት ቃል መሠረት እስራኤላውያንን ሕዝቡ ሊያደርጋቸው ስለፈለገ ነው። (ዘፍ. 22:17) አምላክ ለእስራኤላውያን ከእሱ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለመመሥረት የሚረዷቸውን ሕግጋት ሰጥቷቸዋል። (ኢሳ. 48:17, 18) ይሖዋ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በፍጹም ብትታዘዙኝና [በሕጉ ውስጥ የሰፈረውን] ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ . . . ምድር ሁሉ የእኔ [ናትና]።” (ዘፀ. 19:5, 6) ከዚህ ማየት እንደምንችለው እስራኤላውያን ከአምላክ ጋር ያላቸው ልዩ ዝምድና መቀጠሉ የተመካው እሱን በመታዘዛቸው ላይ ነበር።
8. እስራኤላውያን አምላክን ታዘው ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት ሕይወት ይመሩ ነበር?
8 እስራኤላውያን አምላክን ታዘው ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት ሕይወት ሊመሩ ይችሉ እንደነበር እስቲ አስበው! ይሖዋ እርሻቸውን፣ የወይን ተክላቸውን እንዲሁም የበግና የከብት መንጎቻቸውን ይባርክላቸው ነበር። ከጠላቶቻቸውም ጥበቃ ያደርግላቸው ነበር። (1 ነገሥት 10:23-27ን አንብብ።) መሲሑ በሚመጣበት ጊዜ የእስራኤልን ሕዝብ የሚያገኘው በሮማውያን የጭቆና ቀንበር ሥር እየማቀቀ ሳይሆን ራሱን የቻለ ነፃ ብሔር ሆኖ ነበር። እስራኤል፣ እውነተኛውን አምላክ መታዘዝ መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ በረከት እንደሚያስገኝ ጠንካራ ማስረጃ የምትሆን እንዲሁም በዙሪያዋ ባሉት መንግሥታት ዘንድ እንደ ምሳሌ የምትጠቀስ መንግሥት መሆን ትችል ነበር።
9, 10. (ሀ) እስራኤላውያን ወደ ግብፅ ለመመለስ መፈለጋቸው በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) እስራኤላውያን ወደ ግብፅ መመለሳቸው በአምልኳቸው ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችል ነበር?
9 እስራኤላውያን በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ድርሻ የማበርከት ልዩ መብት አግኝተው ነበር! ሕዝቡ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ውሎ አድሮ ለምድር ሕዝቦች ሁሉ በረከት ማምጣት ይችሉ ነበር። (ዘፍ. 22:18) በጥቅሉ ሲታይ ግን በዚያ ትውልድ የነበሩት ዓመፀኛ ሰዎች በቲኦክራሲያዊ መንገድ የሚመራና በአርዓያነት የሚጠቀስ መንግሥት የመሆን መብታቸውን ከፍ አድርገው አልተመለከቱትም። ይባስ ብለው ደግሞ ወደ ግብፅ ለመመለስ ታጥቀው ተነሱ! (ዘኍልቍ 14:2-4ን አንብብ።) እስራኤላውያን ወደ ግብፅ ከተመለሱ ለሌሎች ብሔራት ምሳሌ የሚሆን መንግሥት እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ? ይህ የማይሆን ነገር ነው። እንዲያውም እስራኤላውያን በአረማውያን አገዛዝ ሥር ከወደቁ የሙሴን ሕግ መታዘዝም ሆነ ይሖዋ ኃጢአታቸውን ይቅር ለማለት ካደረገው ዝግጅት ተጠቃሚ መሆን ጨርሶ የማይታሰብ ነገር ይሆንባቸው ነበር። ሕዝቡ ሰብዓዊ አስተሳሰብ ተጠናውቷቸውና አርቆ ማየት ተስኗቸው ነበር! ይሖዋ እነዚህን ዓመፀኞች በተመለከተ እንደሚከተለው ማለቱ አያስገርምም፦ “በዚህ ትውልድ በጣም ተንገሸገሽኩ፤ እንዲህም አልኩ፦ ‘ልባቸው ሁልጊዜ ይሸፍታል፤ መንገዴንም ሊያውቁ አልቻሉም።’ ስለዚህ ‘ወደ እረፍቴ ፈጽሞ አይገቡም’ ብዬ በቁጣዬ ማልኩ።”—ዕብ. 3:10, 11፤ መዝ. 95:10, 11
10 እነዚህ ዓመፀኛ ሕዝቦች በግብፅ የነበረውን ባሮ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርትና ነጭ ሽንኩርት በመመኘት ወደ ግብፅ ለመመለስ መነሳታቸው ያገኙትን መንፈሳዊ በረከት ከመጤፍ እንዳልቆጠሩት ያሳያል። (ዘኍ. 11:5) አድናቆት እንደጎደለው እንደ ዔሳው እነዚህ ዓመፀኞችም ውድ የሆነውን መንፈሳዊ ውርስ በመብል ለመለወጥ ዝግጁ ነበሩ።—ዘፍ. 25:30-32፤ ዕብ. 12:16
11. በሙሴ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ታማኝ አለመሆናቸው በይሖዋ ዓላማ ላይ ለውጥ አምጥቷል?
11 ግብፅን ለቅቀው የወጡት እስራኤላውያን እምነት የለሽ ቢሆኑም ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ በትዕግሥት ‘መሥራቱን’ ቀጠለ፤ ትኩረቱንም ከእነዚህ ዓመፀኞች በኋላ በሚመጣው ትውልድ ላይ አደረገ። ይህ አዲስ ትውልድ ከአባቶቹ ይልቅ ታዛዥ ነበር። ሕዝቡ፣ ይሖዋ ባዘዛቸው መሠረት ወደ ተስፋይቱ ምድር የገቡ ሲሆን ምድሪቱንም ድል አድርገው መቆጣጠር ጀመሩ። ኢያሱ 24:31 እንዲህ ይላል፦ “ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ከኢያሱም በኋላ በሕይወት በኖሩትና እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ በሚያውቁት ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አመለኩ።”
12. በዛሬው ጊዜ ወደ አምላክ እረፍት መግባት እንደሚቻል እንዴት እናውቃለን?
12 ውሎ አድሮ ግን ታዛዥ የነበረው ያ ትውልድ አለፈና “እግዚአብሔርንም ሆነ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ።” በመሆኑም “እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ የበኣል አማልክትንም አመለኩ።” (መሳ. 2:10, 11) በዚህም ምክንያት ተስፋይቱ ምድር እውነተኛ ‘የእረፍት ቦታ’ ልትሆንላቸው አልቻለችም። እስራኤላውያን ባለመታዘዛቸው ምክንያት ከአምላክ ጋር ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖራቸው አልቻለም። ጳውሎስ ስለ እነዚህ እስራኤላውያን እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ኢያሱ [እስራኤላውያንን] ወደ እረፍት ቦታ እየመራ አስገብቷቸው ቢሆን ኖሮ አምላክ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። ስለዚህ የአምላክ ሕዝብ የሰንበት እረፍት ይጠብቀዋል።” (ዕብ. 4:8, 9) እዚህ ላይ ጳውሎስ “የአምላክ ሕዝብ” ያለው ክርስቲያኖችን ለማመልከት ነበር። ይህ ሲባል ታዲያ ክርስቲያኖች ወደ አምላክ እረፍት መግባት ይችላሉ ማለት ነው? አዎን፣ አይሁዳውያንም ሆኑ አይሁዳዊ ያልሆኑ ክርስቲያኖች መግባት እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም!
አንዳንዶች ወደ አምላክ እረፍት ለመግባት ብቁ ሳይሆኑ ቀርተዋል
13, 14. (ሀ) በሙሴ ዘመን እስራኤላውያን ወደ አምላክ እረፍት ለመግባት ምን ማድረግ ነበረባቸው? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ወደ አምላክ እረፍት ለመግባት ምን ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር?
13 ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈበት ወቅት ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ ካለው የአምላክ ዓላማ ጋር አለመተባበራቸው አሳስቦት ዕብራውያን 4:1ን አንብብ።) ይህን ያደረጉት በምን መንገድ ነው? የሚገርመው ነገር፣ ይህ ጉዳይ የሙሴን ሕግ ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ነበር። ለ1,500 ዓመታት ያህል ማንኛውም እስራኤላዊ ከአምላክ ዓላማ ጋር ተስማምቶ ለመኖር ሕጉን መጠበቅ ነበረበት። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ግን ሕጉ ተወግዷል። ይሁንና ይህን ያልተገነዘቡ አንዳንድ ክርስቲያኖች የተወሰኑ የሕጉን ክፍሎች መጠበቃቸውን ቀጥለው ነበር። *
ነበር። (14 ጳውሎስ፣ ሕጉን ካልጠበቅን ብለው ለሚያስቸግሩ ክርስቲያኖች የኢየሱስ የሊቀ ካህንነት አገልግሎት፣ አዲሱ ቃል ኪዳንና መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ከክርስትና በፊት ለእነዚህ ነገሮች ጥላ ሆነው ካገለገሉት ነገሮች የላቁ እንደሆኑ አብራርቶላቸዋል። (ዕብ. 7:26-28፤ 8:7-10፤ 9:11, 12) ጳውሎስ ወደ ይሖዋ የእረፍት ቀን የመግባት መብት ማግኘትን በተመለከተ ቀጥሎ ያለውን ሐሳብ ጽፎላቸዋል፦ “የአምላክ ሕዝብ የሰንበት እረፍት ይጠብቀዋል። ምክንያቱም ወደ አምላክ እረፍት የገባ ሰው አምላክ ከሥራው እንዳረፈ ሁሉ እሱም ከሥራው አርፏል”፤ ሐዋርያው ይህን ሐሳብ የተናገረው ሳምንታዊውን የሰንበት ሕግ መጠበቅን በአእምሮው ይዞ ሳይሆን አይቀርም። (ዕብ. 4:8-10) እነዚያ ዕብራውያን ክርስቲያኖች በሥራቸው ይኸውም የሙሴን ሕግ በመጠበቃቸው የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንደሚችሉ አድርገው ማሰባቸውን መተው ነበረባቸው። በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ጀምሮ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር ላሳዩ ሁሉ አምላክ በጸጋው አማካኝነት ሞገሱን አሳይቷቸዋል።
15. ወደ አምላክ እረፍት ለመግባት ታዛዥነት አስፈላጊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
15 በሙሴ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሳይገቡ የቀሩት ለምን ነበር? ባለመታዘዛቸው ምክንያት ነበር። በጳውሎስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖችስ ወደ አምላክ እረፍት እንዳይገቡ ያደረጋቸው ምን ነበር? እነሱም ታዛዥ አለመሆናቸው ነበር። ሕጉ፣ የተሰጠበትን ዓላማ እንደፈጸመና ይሖዋ ሕዝቦቹን በተለየ አቅጣጫ እየመራቸው እንደሆነ እነዚህ ሰዎች አልተገነዘቡም ነበር።
በዛሬው ጊዜ ወደ አምላክ እረፍት መግባት
16, 17. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ወደ አምላክ እረፍት መግባት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
16 በዛሬው ጊዜ መዳን ለማግኘት የሙሴን ሕግ መጠበቅ ያስፈልጋል ብሎ የሚያስብ ክርስቲያን የለም። ኤፌ. 2:8, 9) ታዲያ ክርስቲያኖች ወደ አምላክ እረፍት መግባት የሚችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ ሰባተኛውን ቀን የእረፍቱ ቀን አድርጎ የለየው ለምድርና ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ወደ ታላቅ ፍጻሜው ለማድረስ ነው። እኛም በአምላክ ድርጅት በኩል ከሚገለጥልንና ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ በመመላለስ እንዲሁም ታዛዦች በመሆን ወደ ይሖዋ እረፍት መግባት እንችላለን።
ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ምንም የሚያሻማ ነገር የለውም። “በእርግጥም እናንተ የዳናችሁት በእምነት አማካኝነት በዚህ ጸጋ ነው፤ ይህም እናንተ በራሳችሁ ያገኛችሁት ሳይሆን የአምላክ ስጦታ ነው። ማንም ሰው የሚመካበት ምክንያት እንዳይኖር ይህ በፍጹም በሥራ የሚገኝ አይደለም” ብሏቸዋል። (17 በሌላ በኩል ደግሞ በራሳችን ለመመራት የምንመርጥና ታማኝና ልባም ባሪያ የሚሰጠንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር አቅልለን የምንመለከት ከሆነ አካሄዳችን ከይሖዋ ዓላማ ጋር የሚጋጭ ይሆናል። ይህም ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ሰላማዊ ዝምድና አደጋ ላይ ይጥለዋል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የአምላክ ሕዝቦች ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ አንዳንድ የተለመዱ ሁኔታዎችን እንመለከታለን፤ በእነዚህ ሁኔታዎች ረገድ አምላክን ለመታዘዝም ሆነ በራሳችን ለመመራት የምናደርጋቸው ውሳኔዎች በእርግጥ ወደ አምላክ እረፍት በመግባታችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 ካህናቱና ሌዋውያኑ በሰንበት ቀን በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚሠሩ ቢሆንም ‘እንደ በደል አይቆጠርባቸውም’ ነበር። ኢየሱስም የአምላክ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህን እንደመሆኑ መጠን በሰንበት ዕለትም መንፈሳዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይችል ነበር፤ እንዲህ ማድረጉ የሰንበትን ሕግ ጥሷል አያስብለውም።—ማቴ. 12:5, 6
^ አን.13 በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል በኋላ በስርየት ቀን መሥዋዕት ማቅረቡን የቀጠለ አይሁዳዊ ክርስቲያን ይኑር አይኑር የሚታወቅ ነገር የለም። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ቢያደርግ ኢየሱስ ላቀረበው መሥዋዕት አክብሮት እንደጎደለው የሚያሳይ ይሆናል። ይሁንና የተወሰኑ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ ከሕጉ ጋር ከተያያዙ አንዳንድ ልማዶች መላቀቅ አልፈለጉም ነበር።—ገላ. 4:9-11
ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች
• የሰባተኛው ቀን ይኸውም የአምላክ የእረፍት ቀን ዓላማ ምን ነበር?
• ሰባተኛው ቀን በዛሬው ጊዜም እንዳላበቃ የሚጠቁመው ምንድን ነው?
• በሙሴ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ወደ አምላክ እረፍት ሳይገቡ የቀሩት ለምን ነበር?
• በዛሬው ጊዜ ወደ አምላክ እረፍት መግባት የሚቻለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በአምላክ ድርጅት በኩል ከሚገለጥልንና ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ በመመላለስ እንዲሁም ታዛዦች በመሆን በዛሬው ጊዜ ወደ ይሖዋ እረፍት መግባት እንችላለን
[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአምላክ ሕዝቦች ዛሬም ቢሆን ወደ እረፍቱ ለመግባት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?