የአምላክ መንፈስ እንዲመራችሁ ትፈቅዳላችሁ
የአምላክ መንፈስ እንዲመራችሁ ትፈቅዳላችሁ?
“መልካሙ መንፈስህም፣ በቀናችው መንገድ ይምራኝ።”—መዝ. 143:10
1, 2. (ሀ) ይሖዋ አገልጋዮቹን ለመርዳት መንፈስ ቅዱስን የተጠቀመባቸውን አንዳንድ አጋጣሚዎች ተናገር። (ለ) መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው ልዩ በሆኑ ወቅቶች ብቻ ነው? አብራራ።
መንፈስ ቅዱስ ስለሚሠራበት መንገድ ስታስብ ምን ነገር ወደ አእምሮህ ይመጣል? ጌዴዎንና ሳምሶን ያከናወኗቸው አስደናቂ ነገሮች ትዝ አሉህ? (መሳ. 6:33, 34፤ 15:14, 15) ምናልባትም የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የነበራቸውን ድፍረት ወይም እስጢፋኖስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረበበት ወቅት ያሳየውን የመረጋጋት መንፈስ አስታውሰህ ይሆናል። (ሥራ 4:31፤ 6:15) በዘመናችንስ መንፈስ ቅዱስ ሥራውን ስለሚያከናውንበት መንገድ የምታስታውሰው ነገር አለ? በብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የሚኖረንን ደስታ፣ በገለልተኝነት አቋማቸው የተነሳ እስር ቤት የገቡ ወንድሞቻችን ያሳዩትን ታማኝነት እንዲሁም በስብከቱ ሥራ የታየውን አስደናቂ እድገት አስታውሰህ ይሆናል። እነዚህ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ናቸው።
2 መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው ልዩ በሆኑ ወቅቶች ወይም በጣም አስደናቂ ነገሮችን ለማከናወን ብቻ ነው? አይደለም። የአምላክ ቃል፣ ክርስቲያኖች ‘በመንፈስ መመላለሳቸውን’ እንዲቀጥሉ እንዲሁም ‘በመንፈስ የሚመሩ’ እንዲሆኑና ‘በመንፈስ እንዲኖሩ’ ይመክራል። (ገላ. 5:16, 18, 25) እነዚህ አገላለጾች መንፈስ ቅዱስ ቀጣይ በሆነ መንገድ በሕይወታችን ውስጥ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይጠቁማሉ። ይሖዋ አስተሳሰባችንን፣ አነጋገራችንንና ድርጊታችንን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንዲመራልን በየዕለቱ ልንለምነው ይገባል። (መዝሙር 143:10ን አንብብ።) መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ በነፃነት እንዲሠራ ስንፈቅድ ይህ መንፈስ ለሌሎች እረፍት የሚሰጥ ብሎም ለአምላክ ክብር የሚያመጣ ፍሬ በእኛ ውስጥ ያፈራል።
3. (ሀ) በመንፈስ ቅዱስ መመራት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 በመንፈስ ቅዱስ መመራታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የመንፈስ ቅዱስን አሠራር የሚቃወም ሌላ ኃይል ሕይወታችንን ሊቆጣጠር ስለሚፈልግ ነው። ይህ ኃይል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ሥጋ” ተብሎ የተጠቀሰ ሲሆን ይህ አገላለጽ ሥጋችን ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ እንዳለው የሚያመለክት ነው፤ በሌላ አባባል የአዳም ዘሮች በመሆናችን አለፍጽምናን ወርሰናል። (ገላትያ 5:17ን አንብብ።) ታዲያ የአምላክ መንፈስ እንዲመራን መፍቀድ ምን ማድረግን ይጨምራል? ኃጢአተኛ የሆነው ሥጋችን የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ልንወስዳቸው የምንችላቸው ተግባራዊ እርምጃዎች አሉ? የተቀሩትን ስድስት “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታዎች ማለትም ‘ትዕግሥትን፣ ደግነትን፣ ጥሩነትን፣ እምነትን፣ ገርነትንና ራስን መግዛትን’ ስንመረምር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።—ገላ. 5:22, 23
ገርነትና ትዕግሥት ማሳየት በጉባኤ ውስጥ ሰላም ያሰፍናል
4. ገርነትና ትዕግሥት በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት እንዴት ነው?
4 ቆላስይስ 3:12, 13ን አንብብ። ገርነትና ትዕግሥት በአንድነት ሲቀናጁ በጉባኤ ውስጥ ሰላም ለማስፈን ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። የመንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆኑት እነዚህ ሁለት ባሕርያት ሌሎችን በደግነት እንድንይዝ፣ የሚያስቆጣ ነገር በሚያጋጥመን ጊዜ እንድንረጋጋና ሰዎች ደግነት የጎደላቸው ነገሮች ሲናገሩን ወይም ሲያደርጉብን አጸፋውን እንዳንመልስ ይረዱናል። ትዕግሥትን ወይም ቻይነትን ማዳበራችን ከእምነት ባልንጀራችን ጋር አለመግባባት ቢፈጠር በወንድማችን ወይም በእህታችን ተስፋ እንዳንቆርጥ ከዚህ ይልቅ የተፈጠረውን ቅራኔ ለመፍታት የቻልነውን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል። በጉባኤ ውስጥ ገርነትንና ትዕግሥትን ማሳየታችን በእርግጥ አስፈላጊ ነው? አዎን፣ ምክንያቱም ሁላችንም ፍጽምና ይጎድለናል።
5. በጳውሎስና በበርናባስ መካከል ምን ተፈጥሮ ነበር? ይህስ ምን ያሳያል?
5 በጳውሎስና በበርናባስ መካከል የተፈጠረውን ሁኔታ እንመልከት። ምሥራቹን ለማስፋፋት እጅና ጓንት ሆነው ለዓመታት ሠርተዋል። ሁለቱም ጥሩ ባሕርያት አሏቸው። ያም ሆኖ በአንድ ወቅት “በመካከላቸው ኃይለኛ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ተለያዩ።” (ሥራ 15:36-39) ይህ ሁኔታ ቀናተኛ በሆኑ የአምላክ አገልጋዮች መካከልም እንኳ አንዳንድ ጊዜ አለመግባባት ሊፈጠር እንደሚችል ያሳያል። በሁለት ክርስቲያኖች መካከል አለመግባባት ቢፈጠር በቁጣ ገንፍለው ተገቢ ያልሆነ ነገር እንዳይነጋገሩና ሁኔታው ተባብሶ በቀላሉ ወደማይሽር ደረጃ እንዳይደርስ አንድ ክርስቲያን ምን እርምጃ መውሰድ ይችላል?
6, 7. (ሀ) ከእምነት ባልንጀራችን ጋር የምናደርገው ውይይት ወደ ጋለ ጭቅጭቅ ከመቀየሩ በፊት የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ ልናደርግ እንችላለን? (ለ) አንድ ክርስቲያን “ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ” መሆኑ ምን ጥቅሞች አሉት?
6 “ኃይለኛ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ” የሚለው አገላለጽ በጳውሎስና በበርናባስ መካከል በድንገት የከረረ አለመግባባት መከሰቱን ይጠቁማል። አንድ ክርስቲያን በአንድ ጉዳይ ላይ ከእምነት ባልንጀራው ጋር ሲነጋገር እየተናደደ እንደሆነ ከተሰማው በያዕቆብ 1:19, 20 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጉ የጥበብ እርምጃ ነው፦ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግም።” ይህ ወንድም እንደ ሁኔታው የውይይታቸውን ርዕስ ለመቀየር፣ ውይይቱን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ ወይም ወደ ጋለ ጭቅጭቅ ከመቀየሩ በፊት ከአካባቢው ዘወር ለማለት ሊሞክር ይችላል።—ምሳሌ 12:16፤ 17:14፤ 29:11
7 ይህን ምክር መከተል ምን ጥቅሞች አሉት? አንድ ክርስቲያን ጊዜ ወስዶ ራሱን የሚያረጋጋ፣ ስለ ጉዳዩ የሚጸልይና እንዴት የተሻለ መልስ መስጠት እንደሚችል የሚያስብ ከሆነ የአምላክ መንፈስ እንዲመራው ይፈቅዳል። (ምሳሌ 15:1, 28) በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ገርነትንና ትዕግሥትን ማንጸባረቅ ይችላል። በዚህ መንገድ በኤፌሶን 4:26, 29 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ይሆናል፦ “ተቆጡ፤ ነገር ግን ኃጢአት አትሥሩ፤ . . . እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል ማንኛውም መልካም ቃል እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ።” ገርነትንና ትዕግሥትን እንደ ልብስ ስንለብስ ለጉባኤው ሰላምና አንድነት አስተዋጽኦ እናበረክታለን።
ደግነትና ጥሩነት በማሳየት ቤታችሁ የእረፍት ቦታ እንዲሆን አድርጉ
8, 9. ደግነትንና ጥሩነትን እንዴት ትገልጻቸዋለህ? እነዚህ ባሕርያት በቤት ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ እንዲኖር ያደርጋሉ?
8 ኤፌሶን 4:31, 32ን እና 5:8, 9ን አንብብ። ሞቃት በሆነ ቀን ነፋሻማ አየር ባለው አካባቢ መሆንና ቀዝቃዛ ነገር መጠጣት ደስ እንደሚያሰኝ ሁሉ ደግነትና ጥሩነትም መንፈስን ያድሳሉ። እነዚህ ባሕርያት ቤታችሁ የእረፍት ቦታ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ደግነት ስለ ሌሎች ከልብ ከማሰብ የሚመነጭ ተወዳጅ ባሕርይ ሲሆን እንዲህ ያለ አሳቢነት ሰዎችን የሚጠቅም ነገር በማድረግና መልካም ቃላትን በመናገር ይገለጻል። ጥሩነትም ልክ እንደ ደግነት ሌሎችን የሚጠቅም ተግባር በማከናወን የሚገለጽ ግሩም ባሕርይ ነው። የለጋስነት መንፈስ ማሳየት የጥሩነት ምልክት ነው። (ሥራ 9:36, 39፤ 16:14, 15) ያም ሆኖ ጥሩነት ከዚህ የበለጠ ነገርን ይጨምራል።
9 ጥሩነት የላቀ ሥነ ምግባርን ያመለክታል። ይህ ባሕርይ የሚንጸባረቀው በምናደርገው ነገር ብቻ አይደለም፤ እንዲያውም የበለጠ የሚታየው በማንነታችን ላይ ነው። ለቤተሰቧ ፍራፍሬ ቆራርጣ ለማቅረብ የምታዘጋጅን አንዲት ሴት በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ፤ እያንዳንዱን ፍሬ ስትቆርጥ ሙሉ በሙሉ መብሰሉንና ጣፋጭ መሆኑን እንዲሁም ከውስጡም ሆነ ከውጭው ምንም እንከን አለመኖሩን ትመለከታለች። በተመሳሳይም የመንፈስ ፍሬ የሆነው ጥሩነት የአንድን ክርስቲያን አኗኗር በአጠቃላይ የሚነካ ነው።
10. የቤተሰብ አባላት የመንፈስ ፍሬን ለማፍራት ምን ማድረግ ይችላሉ?
10 በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ የቤተሰቡ አባላት አንዳቸው ሌላውን ደግነትና ጥሩነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ለመያዝ ምን ሊረዳቸው ይችላል? ስለ አምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ትልቅ ሚና ይጫወታል። (ቆላ. 3:9, 10) አንዳንድ የቤተሰብ ራሶች የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ማጥናትን በሳምንታዊው የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ውስጥ አካትተዋል። የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ማጥናት ያን ያህል የሚከብድ ነገር አይደለም። በቋንቋችሁ የሚገኙትን ለምርምር የሚረዱ መሣሪያዎች በመጠቀም ስለ እያንዳንዱ የመንፈስ ፍሬ ገጽታ የሚያወሱ ጽሑፎችን ምረጡ። በየሳምንቱ ጥቂት አንቀጾችን ብቻ በመወያየት ስለ እያንዳንዱ ባሕርይ ለበርካታ ሳምንታት ልታጠኑ ትችላላችሁ። ጽሑፉን በምታጠኑበት ወቅት የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥታችሁ በማንበብ ተወያዩባቸው። የተማራችኋቸውን ነገሮች በተግባር ማዋል የምትችሉባቸውን አጋጣሚዎች አስቡ፤ እንዲሁም ይሖዋ ጥረታችሁን እንዲባርክላችሁ ጸልዩ። (1 ጢሞ. 4:15፤ 1 ዮሐ. 5:14, 15) እንዲህ ያለ ጥናት ማድረግ የቤተሰብ አባላት አንዳቸው ሌላውን በሚይዙበት መንገድ ላይ በእርግጥ ለውጥ ያመጣል?
11, 12. ሁለት ባለትዳሮች ስለ ደግነት በማጥናታቸው የተጠቀሙት እንዴት ነው?
11 አንድ ወጣት ባልና ሚስት ትዳራቸው የሰመረ እንዲሆን ስለፈለጉ የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን በጥልቀት አጠኑ። እንዲህ በማድረጋቸው የተጠቀሙት እንዴት ነው? ሚስትየዋ እንዲህ ብላለች፦ “ደግነት፣ የጋብቻ ቃል ኪዳንን ማክበርንና ታማኝ መሆንን እንደሚጨምር ማወቃችን አሁንም ድረስ የሚጠቅመን ሲሆን አንዳችን ሌላውን በምንይዝበት መንገድ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። እሺ ባዮችና ይቅር ባዮች እንድንሆን አስተምሮናል። እንዲሁም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ‘አመሰግናለሁ’ እና ‘ይቅርታ’ ማለትን እንድንማር ረድቶናል።”
12 በትዳራቸው ውስጥ ችግር የገጠማቸው ሌላ
ክርስቲያን ባልና ሚስት እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ረገድ ደግነት እንደጎደላቸው አስተዋሉ። በመሆኑም ስለ ደግነት ባሕርይ አብረው ለማጥናት ወሰኑ። ውጤቱስ ምን ሆነ? ባልየው እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ደግነት ያጠናነው ነገር፣ አንደኛው ወገን እውነቱን እንደደበቀን አድርገን በማሰብ እሱን በጥርጣሬ ዓይን ከማየት ይልቅ በመልካም ጎኑ ላይ የማተኮርን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ ረድቶናል። አንዳችን ለሌላው ፍላጎት ይበልጥ ትኩረት መስጠት ጀመርን። ደግ መሆን ሲባል ባለቤቴ የውስጧን አውጥታ በግልጽ እንድትናገር መፍቀድንና በምትናገረው ነገር ቅር አለመሰኘትን እንደሚጨምር ተገንዝቤያለሁ። ይህም ኩራቴን ዋጥ ማድረግን ጠይቆብኛል። በትዳራችን ውስጥ ደግነትን ስናሳይ ግትር የመሆንን ባሕርይ እያስወገድን መጣን። ይህም ትልቅ እፎይታ አምጥቶልናል።” የእናንተስ ቤተሰብ የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን በማጥናት ጥቅም ማግኘት ይችል ይሆን?ለብቻችሁ ስትሆኑ እምነት እንዳላችሁ አሳዩ
13. መንፈሳዊነታችንን ከየትኛው አደጋ መጠበቅ አለብን?
13 ክርስቲያኖች በሰዎች ፊትም ሆነ ለብቻቸው ሲሆኑ የአምላክ መንፈስ እንዲመራቸው መፍቀድ አለባቸው። በዛሬው ጊዜ ባለው የሰይጣን ዓለም ውስጥ አስነዋሪ ምስሎችና ወራዳ መዝናኛዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። ይህ ደግሞ ለመንፈሳዊነታችን አደገኛ ነው። ታዲያ አንድ ክርስቲያን ምን ማድረግ ይኖርበታል? የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ይመክረናል፦ “ጸያፍ የሆነውን ነገር ሁሉና በዝቶ የተትረፈረፈውን ነገር ይኸውም ክፋትን አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ሊያድን የሚችለውን በውስጣችሁ የሚተከለውን ቃል በገርነት ተቀበሉ።” (ያዕ. 1:21) ሌላኛው የመንፈስ ፍሬ ገጽታ ይኸውም እምነት በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋማችንን ይዘን ለመቀጠል እንዴት እንደሚረዳን እስቲ እንመልከት።
14. እምነት ማጣት መጥፎ ተግባር ወደ መፈጸም የሚመራው እንዴት ነው?
14 እምነት አለን ሲባል በዋነኝነት ይሖዋ አምላክ እውን ሆኖልናል ማለት ነው። አምላክ እውን ካልሆነልን መጥፎ ተግባር እንዳንፈጽም የሚይዘን ነገር አይኖርም። በጥንት ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ምን እንዳደረጉ እንመልከት። ይሖዋ፣ ሕዝቡ በድብቅ የሚፈጽሙትን አስጸያፊ ነገር ለነቢዩ ሕዝቅኤል ሲነግረው እንዲህ ብሏል፦ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች እያንዳንዳቸው በጣዖታቸው ምስል ጓዳ ውስጥ በጨለማ የሚያደርጉትን አይተሃልን? እነርሱ፣ ‘እግዚአብሔር አያየንም፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአል’ ይላሉ።” (ሕዝ. 8:12) ሕዝቡ እንዲህ ያለውን ድርጊት ወደመፈጸም የመራቸው ምን እንደሆነ አስተዋልክ? ይሖዋ የሚያደርጉትን ነገር እንደሚመለከት አያስቡም ነበር። ይሖዋ ለእነሱ እውን አልነበረም።
15. በይሖዋ ላይ ያለን ጠንካራ እምነት ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?
15 ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የዮሴፍን ምሳሌ እንመልከት። ዮሴፍ ከቤተሰቡና ከወገኖቹ ርቆ ይኖር የነበረ ቢሆንም ከጲጥፋራ ሚስት ጋር ዝሙት ለመፈጸም ፈቃደኛ አልነበረም። ለምን? “እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” ብሏል። (ዘፍ. 39:7-9) አዎን፣ ይሖዋ ለእሱ እውን ነበር። እኛም አምላክ እውን ከሆነልን ርኩስ የሆኑ መዝናኛዎችን አንመለከትም ወይም አምላክን የሚያሳዝን ማንኛውንም ነገር በድብቅ አንፈጽምም። እንደሚከተለው ብሎ እንደዘመረው መዝሙራዊ ዓይነት ቁርጥ ውሳኔ ይኖረናል፦ “በቤቴ ውስጥ፣ በንጹሕ ልብ እመላለሳለሁ። በዐይኔ ፊት፣ ክፉ ነገር አላኖርም።”—መዝ. 101:2, 3
ራስን መግዛትን በማዳበር ልባችሁን ጠብቁ
16, 17. (ሀ) በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የተገለጸው “ማስተዋል የጐደለው” ወጣት በኃጢአት ወጥመድ ውስጥ የወደቀው እንዴት ነው? (ለ) በገጽ 26 ላይ ያለው ፎቶግራፍ እንደሚያሳየው በዛሬው ጊዜም በየትኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመው የሚችለው እንዴት ነው?
16 ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች መካከል የመጨረሻ የሆነው ራስን መግዛት አምላክ የሚያወግዛቸውን ነገሮች ለማድረግ እምቢተኞች እንድንሆን ይረዳናል። ራስን መግዛት ልባችንን እንድንጠብቅ ያስችለናል። (ምሳሌ 4:23) በምሳሌ 7:6-23 ላይ የተገለጸውን ሁኔታ እንመልከት፤ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል “ማስተዋል የጐደለው” አንድ ወጣት በአንዲት ዝሙት አዳሪ ወጥመድ እንደወደቀ ይገልጻል። በወጥመዷ የተያዘው “በቤቷ ማእዘን አጠገብ ባለው መንገድ” ሲያልፍ ነበር። ምናልባትም ወደዚያ አካባቢ የሄደው የማወቅ ጉጉት አድሮበት ሊሆን ይችላል። ነገሮች በቅጽበት ስለተከናወኑ ‘ሕይወቱን የሚያሳጣውን’ የሞኝነት ጎዳና እየተከተለ እንዳለ አላስተዋለም ነበር።
17 ይህ ወጣት እንዲህ ያለውን ከባድ ስህተት ከመፈጸም ሊቆጠብ የሚችለው እንዴት ነበር? “ወደ ስሕተት ጐዳናዋም አትግቡ” የሚለውን ማስጠንቀቂያ በመከተል ነበር። (ምሳሌ 7:25) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት አለ፦ የአምላክ መንፈስ እንዲመራን የምንፈልግ ከሆነ ራሳችንን ለፈተና ከማጋለጥ መቆጠብ አለብን። አንድ ሰው “ማስተዋል የጐደለው” ወጣት የሄደበትን የሞኝነት ጎዳና ሊከተል የሚችልበት አንዱ መንገድ የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን እየለዋወጠ መመልከት ወይም ዝም ብሎ ኢንተርኔት መጎርጎር ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው ግለሰብ ፈልጎትም ይሁን ሳይፈልገው የፆታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ምስሎች ያጋጥሙት ይሆናል። ቀስ በቀስም የብልግና ምስሎችን የመመልከት ርኩስ ልማድ ሊጠናወተው ይችላል፤ ይህም ሕሊናውን የሚያቆሽሽበት ከመሆኑም በላይ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ያበላሽበታል። ድርጊቱ ሕይወቱን ሊያሳጣው ይችላል።—ሮም 8:5-8ን አንብብ።
18. አንድ ክርስቲያን ልቡን ለመጠበቅ ምን እርምጃዎች መውሰድ ይችላል? ይህስ ራስን መግዛትን የሚጠይቀው እንዴት ነው?
18 እርግጥ ነው፣ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ምስል ሲያጋጥመን ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ራስን መግዛትን ማሳየት እንችላለን፤ ደግሞም እንዲህ ልናደርግ ይገባል። ሆኖም መጀመሪያውኑም እንዲህ ካለው ሁኔታ መራቁ ምንኛ የተሻለ ነው! (ምሳሌ 22:3) የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድና ውሳኔያችንን በጥብቅ መከተል ራስን መግዛትን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል፣ ኮምፒውተራችንን ሌሎች ሊያዩት በሚችሉት ቦታ ማስቀመጥ ጥበቃ ሊሆንልን ይችላል። አንዳንዶች፣ ሌሎች ሲኖሩ ብቻ ኮምፒውተር መጠቀም ወይም ቴሌቪዥን መመልከት ከሁሉ የተሻለ እርምጃ ሆኖ አግኝተውታል። ሌሎች ደግሞ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ወስነዋል። (ማቴዎስ 5:27-30ን አንብብ።) ይሖዋን “ከንጹሕ ልብ፣ ከጥሩ ሕሊናና ግብዝነት ከሌለበት እምነት” ለማምለክ እንድንችል ራሳችንንና ቤተሰባችንን ለመጠበቅ ማንኛውንም እርምጃ እንውሰድ።—1 ጢሞ. 1:5
19. መንፈስ ቅዱስ እንዲመራን መፍቀዳችን ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል?
19 መንፈስ ቅዱስ የሚያፈራው ፍሬ ብዙ ጥቅሞች ያስገኝልናል። ገርነትና ትዕግሥት ለጉባኤው ሰላም አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ደግነትና ጥሩነት ደስተኛ የሆነ ቤተሰብ እንዲኖር ያደርጋሉ። እምነትና ራስን መግዛት ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን እንድንኖርና በእሱ ፊት ንጹሕ አቋም እንዲኖረን ይረዱናል። ከዚህም በተጨማሪ ገላትያ 6:8 “ለመንፈስ ብሎ የሚዘራ . . . ከመንፈስ የዘላለም ሕይወት ያጭዳል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። አዎን፣ ይሖዋ በመንፈሱ ለመመራት ፈቃደኞች ለሆኑ ሰዎች በቅዱስ መንፈሱ ተጠቅሞ በክርስቶስ ቤዛ አማካኝነት ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ይሰጣቸዋል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ገርነትና ትዕግሥት ለጉባኤው ሰላም አስተዋጽኦ የሚያበረክቱት እንዴት ነው?
• ክርስቲያኖች በቤታቸው ውስጥ ደግነትንና ጥሩነትን እንዲያንጸባርቁ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
• እምነትና ራስን መግዛት አንድ ክርስቲያን ልቡን እንዲጠብቅ የሚረዱት እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውይይቱ ወደ ጋለ ጭቅጭቅ እንዳይቀየር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ማጥናት ቤተሰባችሁን ሊጠቅም ይችላል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እምነትንና ራስን መግዛትን በማዳበር ከየትኞቹ አደጋዎች መራቅ እንችላለን?