ተባብሮ መሥራት መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ይረዳል
ተባብሮ መሥራት መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ይረዳል
መንፈሳዊ የሆነ ቤተሰብ እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ሁሉ እርስ በርስ ተባብሮ የመሥራት መንፈስ ማዳበራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት በፈጠረበት ወቅት ተባብሮ የመሥራትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ሔዋን፣ የአዳም “ረዳት” በመሆን ከእሱ ጋር ተባብራ መሥራት ነበረባት። (ዘፍ. 2:18) በትዳር ውስጥ ባልና ሚስት ተደጋግፈው በመሥራት አንዳቸው ለሌላው አጋር ሊሆኑ ይገባል። (መክ. 4:9-12) ወላጆችና ልጆችም ይሖዋ የሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዲችሉ የትብብር መንፈስ ማሳየታቸው አስፈላጊ ነው።
የቤተሰብ አምልኮ
ባሪ እና ሃይዲ የተባሉት ባልና ሚስት አምስት ልጆች አሏቸው። የቤተሰቡ አባላት፣ ቋሚ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖራቸው ተባብረው መሥራታቸው መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል። ባሪ እንዲህ ይላል፦ “ልጆቻችን በቤተሰብ ጥናቱ ላይ የሚያቀርቡት ቀለል ያለ ነገር ተዘጋጅተው እንዲመጡ የቤት ሥራ እሰጣቸዋለሁ። አንዳንድ ጊዜ፣ ንቁ! መጽሔት ላይ የሚወጡ ርዕሶችን አንብበው በመምጣት በጥናት ወቅት ሐሳብ እንዲሰጡ እነግራቸዋለሁ። ከዚህም ሌላ አገልግሎት ስንወጣ እንዴት ብለን ሰዎችን እንደምናነጋግር እንለማመዳለን፤ ይህም እያንዳንዱ ልጅ የራሱ መግቢያ እንዲኖረው ይረዳዋል።” ሃይዲም አክላ እንዲህ ብላለች፦ “ሁላችንም ልንደርስባቸው የምንፈልጋቸውን የየራሳችንን መንፈሳዊ ግቦች በጽሑፍ እናሰፍራለን፤ ከዚያም ግቦቻችን ላይ በመድረስ ረገድ ምን ያህል እንደተሳካልን ለማወቅ በቤተሰብ ጥናታችን ላይ በየጊዜው እንነጋገርበታለን።” ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ባልና ሚስት በሳምንት ውስጥ ቴሌቪዥን የማይታይባቸው የተወሰኑ ቀናት እንዲኖሩ ማድረጋቸው ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ጸጥታ በሰፈነበት ሁኔታ ለማንበብ የሚያስችል አጋጣሚ እንዲያገኙ እንደረዳቸው አስተውለዋል።
የጉባኤ ስብሰባዎች
ማይክና ዴኒዝ አራት ልጆችን አሳድገዋል። የቤተሰቡ አባላት ተባብረው መሥራታቸው የጠቀማቸው እንዴት ነው? ማይክ እንዲህ ይላል፦ “ስብሰባዎች ላይ በሰዓቱ ለመገኘት ጥሩ እቅድ ብናወጣም አንዳንድ ጊዜ አይሳካልንም፤ ይሁንና ተባብረን መሥራታችን እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ እንደረዳን ማስተዋል ችለናል።” ዴኒዝም እንዲህ ብላለች፦ “ልጆቻችን ከፍ እያሉ ሲሄዱ ለሁሉም የየራሳቸው ሥራ እንሰጣቸው ነበር። ኪም የተባለችው ልጃችን ምግብ በማብሰልና በማቀራረብ ታግዝ ነበር።” ማይክል የተባለው ልጃቸው ደግሞ ልጅ እያሉ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ብሏል፦ “ማክሰኞ ማታ እኛ ቤት የጉባኤ ስብሰባ ይደረግ ነበር። በመሆኑም ክፍሉን ካስተካከልንና ምንጣፉን ካጸዳን በኋላ ወንበሮች እንደረድር ነበር።” ማቲው የሚባለው ሌላው ልጅ፣ “ስብሰባ በሚደረግበት ምሽት ላይ አባቴ እኛን ለጉባኤ ለማዘጋጀት ሲል በጊዜ ከሥራ ለመምጣት ጥረት ያደርግ ነበር” ብሏል። እንዲህ ማድረጋቸው ምን ውጤት አስገኝቷል?
ጥረታቸው ክሷቸዋል
ማይክ እንዲህ ብሏል፦ “በ1987 እኔና ዴኒዝ አቅኚዎች ሆነን ማገልገል ጀመርን። በወቅቱ ከልጆቻችን መካከል ሦስቱ የሚኖሩት ከእኛ ጋር ነበር። ከጊዜ በኋላ ሁለቱ ልጆቻችንም አቅኚ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ በቤቴል ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ተካፍለዋል። ቤተሰባችን 40 ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወስነው እንዲጠመቁ መርዳት መቻሉም ተጨማሪ ደስታ አስገኝቶልናል። ቤተሰባችን በአገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች በተካሄዱ የግንባታ ሥራዎች ላይ የመካፈል መብትም አግኝቷል።”
በእርግጥም በቤተሰብ ተባብሮ መሥራት የሚክስ ነው። በቤተሰባችሁ ውስጥ የትብብር መንፈስ ማሳየት የምትችሉባቸው ሌሎች መንገዶች ይኖራሉ? የትብብር መንፈስ ማዳበራችሁ ቤተሰባችሁ በመንፈሳዊ ይበልጥ እያደገ እንዲሄድ እንደሚረዳው እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለአገልግሎት የሚረዱ መግቢያዎችን መለማመድ በአገልግሎታችሁ እድገት ለማድረግ ይረዳችኋል