ይሖዋ የሚመለከተን ለጥቅማችን ነው
ይሖዋ የሚመለከተን ለጥቅማችን ነው
“በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት [የይሖዋ] ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ።”—2 ዜና 16:9
1. ይሖዋ የሚመረምረን ለምንድን ነው?
ይሖዋ ፍጹም የሆነ አባት ነው። እያንዳንዳችንን በሚገባ የሚያውቀን ሲሆን ‘ሐሳባችንን’ እንኳ ጠንቅቆ ያውቃል። (1 ዜና 28:9) ይሁን እንጂ ይሖዋ የሚመረምረን ስሕተት ለማግኘት ብሎ አይደለም። (መዝ. 11:4፤ 130:3) ይልቁንም አፍቃሪ የሆነው አባታችን ይህን የሚያደርገው፣ ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን ሊያሳጣን ከሚችል ከማንኛውም ነገር ሊጠብቀን ስለሚፈልግ ነው።—መዝ. 25:8-10, 12, 13
2. ይሖዋ የሚያበረታው እነማንን ነው?
2 ይሖዋ በኃይሉ ተወዳዳሪ የሌለው ከመሆኑም በላይ ሁሉንም ነገር ይመለከታል። በመሆኑም ታማኝ አገልጋዮቹ በሚጠሩት ጊዜ ሁሉ ሊረዳቸው እንዲሁም መከራ ሲያጋጥማቸው ሊደግፋቸው ይችላል። ሁለተኛ ዜና መዋዕል 16:9 “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት [የይሖዋ] ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ” ይላል። ይሖዋ የሚያበረታው በፍጹም ልባቸው ማለትም በንጹሕና በቅን ልብ ተነሳስተው የሚያገለግሉትን ሰዎች እንደሆነ አስተውል። ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ለሚፈጽሙ አሊያም ግብዝ ለሆኑ ሰዎች እንዲህ ያለ አሳቢነት አያሳይም።—ኢያሱ 7:1, 20, 21, 25፤ ምሳሌ 1:23-33
አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር እናድርግ
3, 4. ‘ከአምላክ ጋር መሄድ’ ሲባል ምን ማለት ነው? ይህንን ለመረዳት የሚያስችሉን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው?
3 ግዙፍ የሆነው ጽንፈ ዓለም ፈጣሪ፣ የሰው ልጆች ዘፍ. 5:24፤ 6:9) ሙሴ “የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቊጠር በሐሳቡ [ጸንቷል]።” (ዕብ. 11:27) ንጉሥ ዳዊትም፣ ትሑት በመሆን አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጓል። ዳዊት፣ ይሖዋ “በቀኜ ስላለ አልናወጥም” ብሏል።—መዝ. 16:8
በምሳሌያዊ ሁኔታ ከእሱ ጋር እንዲሄዱ ይፈቅድላቸዋል የሚለው ሐሳብ ለብዙዎች ጨርሶ የማይታሰብ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይሖዋ ከእሱ ጋር እንድንሄድ ይፈልጋል። በጥንት ዘመን የኖሩት ሄኖክና ኖኅ ‘አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር አድርገዋል።’ (4 እርግጥ ነው፣ ቃል በቃል ከይሖዋ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን መሄድ አንችልም። ሆኖም በምሳሌያዊ ሁኔታ እንዲህ ማድረግ እንችላለን። እንዴት? መዝሙራዊው አሳፍ “ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፤ አንተም ቀኝ እጄን ይዘኸኛል። በምክርህ መራኸኝ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 73:23, 24) ከይሖዋ ጋር መሄድ ሲባል በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ እንዲሁም ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል አምላክ የሚሰጠንን ምክር በጥብቅ መከተል ማለት ነው።—ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም፤ 2 ጢሞ. 3:16
5. ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደ አንድ አፍቃሪ አባት በትኩረት የሚመለከታቸው እንዴት ነው? እኛስ ስለ እሱ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
5 ይሖዋ፣ አካሄዳቸውን ከእሱ ጋር የሚያደርጉ ሰዎችን ስለሚወዳቸው እንደ አንድ አፍቃሪ አባት በትኩረት ይመለከታቸዋል፤ ይህም ሲባል ያስተምራቸዋል እንዲሁም ለእነሱ እንክብካቤና ጥበቃ ያደርግላቸዋል ማለት ነው። አምላክ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።” (መዝ. 32:8) እስቲ ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦ ‘ይሖዋ በፍቅር ዓይን እንደሚመለከተኝ በመገንዘብና የእሱን ጥበብ በማዳመጥ ከእሱ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዤ የምሄድ ያህል ሆኖ ይሰማኛል? አስተሳሰቤ፣ ንግግሬ እንዲሁም ተግባሬ ይሖዋ ከእኔ ጋር መሆኑን እንደማውቅ የሚያሳይ ነው? ስሕተት በምሠራበት ጊዜ ይሖዋን፣ እንደማይቀረብና ጥብቅ እንደሆነ አምላክ አድርጌ ሳይሆን ንስሐ የገቡ ሰዎችን እንደገና በእቅፉ ለመያዝ እንደሚፈልግ አፍቃሪና መሐሪ አባት አድርጌ እመለከተዋለሁ?—መዝ. 51:17
6. ይሖዋ ከሰብዓዊ ወላጆች በተሻለ እኛን ለመርዳት የሚያስችል ምን ችሎታ አለው?
6 አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ በተሳሳተ ጎዳና ላይ መጓዝ ከመጀመራችን በፊትም እንኳ ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ተንኰለኛ የሆነው ልባችን ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን መመኘት እንደጀመረ ያስተውል ይሆናል። (ኤር. 17:9) እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ ይሖዋ ከሰብዓዊ ወላጆችም እንኳ ቀድሞ ሊረዳን ይችላል፤ ምክንያቱም “ዐይኖቹ” ውስጣችንን የማየትና ሐሳባችንን የመመርመር ችሎታ አላቸው። (መዝ. 11:4፤ 139:4፤ ኤር. 17:10) የነቢዩ ኤርምያስ ጸሐፊና የቅርብ ወዳጅ የሆነው ባሮክ ከነበረው ዝንባሌ ጋር በተያያዘ አምላክ የወሰደውን እርምጃ እንደ ምሳሌ እንመልከት።
ለባሮክ እውነተኛ አባት ሆኖለታል
7, 8. (ሀ) ባሮክ ማን ነበር? ምን ዓይነት አደገኛ ዝንባሌ በልቡ ውስጥ ማቆጥቆጥ ጀምሮ ነበር? (ለ) ይሖዋ ለባሮክ እንደ አባት እንደሚያስብለት ያሳየው እንዴት ነበር?
7 ባሮክ፣ ይሖዋ በይሁዳ ላይ የሚወስደውን የፍርድ እርምጃ የማወጁን አስቸጋሪ ሥራ ከኤርምያስ ጋር በመሆን በታማኝነት ያከናወነ የሠለጠነ ጸሐፊ ነበር። (ኤር. 1:18, 19) በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ካለው ቤተሰብ እንደተወለደ የሚታሰበው ባሮክ በአንድ ወቅት ለራሱ “ታላቅ ነገር” መሻት ጀምሮ ነበር። ባሮክ ትልቅ ቦታ ላይ የመድረስ ወይም በቁሳዊ ነገሮች ባለጸጋ የመሆን ፍላጎት አድሮበት ሊሆን ይችላል። ይህ የአምላክ አገልጋይ የፈለገው ነገር ምንም ይሁን ምን ይሖዋ በባሮክ ልብ ውስጥ አደገኛ የሆነ አስተሳሰብ እያቆጠቆጠ መሆኑን ተመልክቶ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ በኤርምያስ አማካኝነት ወዲያውኑ ለባሮክ እንዲህ አለው፦ “አንተ፣ ‘እግዚአብሔር በሕመሜ ላይ ሐዘን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ፤ ከልቅሶዬ ብዛት የተነሣ ደክሜያለሁ፤ ዕረፍትም የለኝም’ ብለሃል። . . . ለራስህ ታላቅ ነገር ትሻለህን? . . . አትፈልገው።”—ኤር. 45:1-5
8 ይሖዋ ለባሮክ ጥብቅ ምክር የሰጠው ቢሆንም ይህን ያደረገው በቁጣ ሳይሆን እንደ አባት እውነተኛ አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ነበር። አምላክ፣ የባሮክ አስተሳሰብ አደገኛ እንደሆነ ቢመለከትም ልቡ ክፉ እንዳልሆነ ተረድቶ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ፣ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ የሚጠፉበት ጊዜ እንደቀረበ ስለሚያውቅ ባሮክ በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ እንዲሰናከል አልፈለገም። በመሆኑም አምላክ፣ አገልጋዩ እውነታውን ማስተዋል እንዲችል ለመርዳት ስለፈለገ “በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ጥፋት” እንደሚያመጣ ነገረው፤ አክሎም ባሮክ ጥበብ የተሞላበት እርምጃ ከወሰደ ሕይወቱ እንደሚተርፍ ገለጸለት። ኤር. 45:5) በሌላ አባባል አምላክ እንዲህ ያለው ያህል ነበር:- ‘ባሮክ፣ እውነታውን ለማየት ሞክር። ኃጢአተኛ በሆኑት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ በቅርቡ ምን እንደሚመጣ አትዘንጋ። ታማኝ በመሆን ሕይወትህን ማትረፍ ትችላለህ። እኔም ጥበቃ አደርግልሃለሁ።’ ባሮክ አስተሳሰቡን በማስተካከል ከ17 ዓመታት በኋላ ኢየሩሳሌም ስትጠፋ በሕይወት መትረፍ መቻሉ ይሖዋ በሰጠው ምክር ልቡ እንደተነካ የሚያሳይ ነው።
(9. በዚህ አንቀጽ ውስጥ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምን መልስ ትሰጣለህ?
9 ስለ ባሮክ በሚናገረው ታሪክ ላይ ስታሰላስል የሚከተሉትን ጥያቄዎችና ጥቅሶች አስብባቸው:- አምላክ ከባሮክ ጋር በተያያዘ ያደረገው ነገር ስለ ይሖዋ እንዲሁም ለአገልጋዮቹ ስላለው ስሜት ምን ይጠቁመናል? (ዕብራውያን 12:9ን አንብብ።) የምንኖረው አስጨናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ ከመሆኑ አንጻር አምላክ ለባሮክ ከሰጠው ምክርና ባሮክ ከወሰደው እርምጃ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሉቃስ 21:34-36ን አንብብ።) ክርስቲያን ሽማግሌዎች የኤርምያስን ምሳሌ በመኮረጅ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለው ዓይነት አሳቢነት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?—ገላትያ 6:1ን አንብብ።
የአባቱ ዓይነት ፍቅር ያለው ልጅ
10. ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንዲሆን የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ብቁ እንዲሆን የሚረዳው ምን ችሎታ ተሰጥቶታል?
10 ከክርስትና በፊት በነበሩት ዘመናት፣ ይሖዋ ለሕዝቦቹ ያለውን ፍቅር በነቢያቱና በሌሎች ታማኝ አገልጋዮቹ አማካኝነት አሳይቷል። በዛሬው ጊዜ ደግሞ ይህንን ፍቅሩን ይበልጥ ያሳየው የክርስቲያን ጉባኤ ራስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው። (ኤፌ. 1:22, 23) በመሆኑም በራእይ መጽሐፍ ላይ ኢየሱስ “ሰባት ዐይኖች” ባሉት በግ የተመሰለ ሲሆን እነዚህ ዓይኖች “ወደ ምድር ሁሉ የተላኩት ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።” (ራእይ 5:6) በእርግጥም ኢየሱስ፣ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሙሉ በሙሉ ስለተሰጠው ፍጹም የሆነ የማስተዋል ችሎታ አለው። እሱም እንደ ይሖዋ ውስጣዊ ማንነታችንን ማየት የሚችል ሲሆን ከእይታው የሚሰወር ምንም ነገር የለም።
11. ክርስቶስ ምን ሚና ይጫወታል? አባቱ ለእኛ ያለው ዓይነት አመለካከት እንዳለው ያሳየውስ እንዴት ነው?
11 እንደ ይሖዋ ሁሉ ኢየሱስም ከሰማይ ሆኖ እኛን የሚመለከት ፖሊስ አይደለም። ኢየሱስ የሚመረምረን በፍቅር ተነሳስቶ ነው። ኢየሱስ ከተሰጡት ስሞች መካከል አንዱ “የዘላለም አባት” የሚል ሲሆን ይህ ስም በእሱ ለሚያምኑ ሰዎች ሁሉ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ረገድ የሚጫወተውን ሚና ያስታውሰናል። (ኢሳ. 9:6) ከዚህም በተጨማሪ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነው ክርስቶስ፣ በመንፈሳዊ የጎለመሱና ፈቃደኛ ልብ ያላቸው ክርስቲያኖችን በተለይም ሽማግሌዎችን እርዳታ ለሚያሻቸው ሰዎች ማጽናኛ ወይም ምክር እንዲሰጡ ሊያነሳሳቸው ይችላል።—1 ተሰ. 5:14፤ 2 ጢሞ. 4:1, 2
12. (ሀ) ኢየሱስ በትንሿ እስያ ወደሚገኙት ሰባት ጉባኤዎች የላካቸው ደብዳቤዎች ስለ እሱ ምን ይጠቁማሉ? (ለ) ሽማግሌዎች፣ ክርስቶስ ለአምላክ መንጋ ያለውን አመለካከት የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?
12 ክርስቶስ በትንሿ እስያ በነበሩት ሰባት ጉባኤዎች ውስጥ ለሚገኙት ሽማግሌዎች የላካቸው ደብዳቤዎች ለመንጋው በጥልቅ እንደሚያስብ ይጠቁማሉ። (ራእይ 2:1 እስከ 3:22) በእነዚህ ደብዳቤዎች ላይ ኢየሱስ በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ የሚከናወኑትን ነገሮች እንደሚያውቅ እንዲሁም ለተከታዮቹ በጥልቅ እንደሚያስብ አሳይቷል። ዮሐንስ የተመለከተው ራእይ ፍጻሜውን የሚያገኘው “በጌታ ቀን” በመሆኑ በዛሬው ጊዜም ኢየሱስ በጉባኤዎች ውስጥ የሚከናወኑትን ነገሮች በሚገባ ያውቃል፤ ከዚህም በላይ ለተከታዮቹ በጥልቅ ያስብላቸዋል። * (ራእይ 1:10) ክርስቶስ ለተከታዮቹ ያለው ፍቅር ብዙውን ጊዜ የሚገለጸው የጉባኤው መንፈሳዊ እረኞች ሆነው በሚያገለግሉት ሽማግሌዎች በኩል ነው። ኢየሱስ እነዚህን “ስጦታ” የሆኑ ወንዶች፣ እርዳታ ለሚያሻቸው ሰዎች ማጽናኛና ማበረታቻ ወይም ምክር እንዲሰጡ ሊያነሳሳቸው ይችላል። (ኤፌ. 4:8፤ ሥራ 20:28፤ ኢሳይያስ 32:1, 2ን አንብብ።) ሽማግሌዎች የሚያደርጉት ጥረት፣ ክርስቶስ በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ያለውን አሳቢነት የሚያሳይ እንደሆነ አድርገህ ትመለከተዋለህ?
በተገቢው ጊዜ የተሰጠ እርዳታ
13-15. አምላክ ጸሎታችንን የሚመልስልን በየትኞቹ መንገዶች ሊሆን ይችላል? ምሳሌዎች ስጥ።
13 እርዳታ ለማግኘት ልባዊ ጸሎት አቅርበህ በመንፈሳዊ የጎለመሰ አንድ ክርስቲያን ከሰጠህ ማበረታቻ ለጸሎትህ መልስ ያገኘህበት ጊዜ አለ? (ያዕ. 5:14-16) አሊያም ደግሞ እርዳታውን ያገኘኸው በአንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ከቀረበ ንግግር ወይም ከጽሑፎቻችን ላይ ካነበብከው ነገር ሊሆን ይችላል። ይሖዋ አብዛኛውን ጊዜ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን በእነዚህ መንገዶች ነው። ለአብነት ያህል፣ አንድ ሽማግሌ በጉባኤ ውስጥ ንግግር ከሰጠ በኋላ አንዲት እህት አነጋገረችው፤ ይህች እህት ከዚያ በፊት በነበሩት ሳምንታት የፍትሕ መጓደል ደርሶባት ነበር። እህት የገጠማትን ችግር አንስታ በምሬት ከመናገር ይልቅ ሽማግሌው በንግግሩ ላይ ያቀረባቸውን አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥቦች በመጥቀስ አመሰገነችው። ወንድም የጠቀሳቸውን ነጥቦች እሷ ከገጠሟት ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ልትሠራባቸው እንደምትችልና በጣም እንዳጽናኗት ነገረችው። ይህች እህት በዚያ ስብሰባ ላይ በመገኘቷ ምንኛ ተደስታ ይሆን!
14 በጸሎት አማካኝነት የምናገኘውን እርዳታ በተመለከተ ደግሞ ሦስት እስረኞች ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት፤ እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያወቁት እስር ቤት ሲሆን ያልተጠመቁ አስፋፊዎች መሆን ችለው ነበር። በአንድ ወቅት በወኅኒ ቤቱ ውስጥ በተነሳው ዓመፅ ሳቢያ እስረኞቹ በሙሉ ተጨማሪ እገዳዎች ተጣሉባቸው። ይህ ደግሞ ዓመፅ እንዲቀሰቀስ አደረገ። እስረኞቹ በቀጣዩ ቀን ቁርስ ከበሉ በኋላ የተመገቡባቸውን ሳሕኖች ባለመመለስ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ተስማሙ። በዚህ ጊዜ ሦስቱ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ። በዓመፁ ከተካፈሉ በሮሜ 13:1 ላይ የሚገኘውን የይሖዋ መመሪያ መተላለፍ ይሆንባቸዋል። በዓመፁ ካልተባበሩ ደግሞ በቁጣ የገነፈሉት እስረኞች ጥቃት ሊሰንዝሩባቸው ይችላሉ።
15 ሦስቱ አስፋፊዎች ተገናኝተው መነጋገር ስላልቻሉ ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጣቸው ጸለዩ። በማግስቱ ሲገናኙ ሦስቱም ተመሳሳይ ውሳኔ እንዳደረጉ አወቁ፤ ሁሉም ቁርስ ላለመቀበል ወስነው ነበር። የወኅኒ ቤቱ ጠባቂዎች ሳሕኖቹን ለመሰብሰብ ሲመጡ ሦስቱ አስፋፊዎች ቁርስ ስላልተቀበሉ የሚመልሱት ሳሕን አልነበራቸውም። ‘ጸሎት የሚሰማው’ አምላክ ቅርባቸው እንደሆነ ማወቃቸው ምንኛ አስደስቷቸው ይሆን!—መዝ. 65:2
የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠበቅ
16. የስብከቱ ሥራ ይሖዋ በግ መሰል ለሆኑ ሰዎች እንደሚያስብላቸው የሚያሳየው እንዴት ነው?
16 ዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ፣ ይሖዋ በየትኛውም ቦታ ለሚኖሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እንደሚያስብላቸው የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ ነው። (ዘፍ. 18:25) ይሖዋ ብዙውን ጊዜ በመላእክት በመጠቀም አገልጋዮቹ በግ መሰል ሰዎችን እንዲያገኙ ሊመራቸው ይችላል፤ እነዚህ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የሚኖሩት ምሥራቹ ገና ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ቢሆንም መልእክቱ እንዲደርሳቸው ያደርጋል። (ራእይ 14:6, 7) ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረውን ፊልጶስ የተባለ ወንጌላዊ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን ጋር እንዲገናኝና ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲያብራራለት በአንድ መልአክ አማካኝነት መርቶታል። ምን ውጤት ተገኘ? ሰውየው ምሥራቹን ተቀብሎ በመጠመቅ የኢየሱስ ተከታይ ሆኗል። *—ዮሐ. 10:14፤ ሥራ 8:26-39
17. ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከልክ በላይ መጨነቅ የማይኖርብን ለምንድን ነው?
17 ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ሲመጣ አስቀድሞ የተነገረው “የምጥ ጣር” እየተባባሰ ይሄዳል። (ማቴ. 24:8 የ1954 ትርጉም) ለምሳሌ የተጠቃሚዎች ፍላጎት መጨመር፣ የአየር ሁኔታ መዛባት ወይም የኢኮኖሚ አለመረጋጋት የምግብ ዋጋ እየናረ እንዲሄድ ሊያደርግ ይችላል። ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሊሆን እንዲሁም ሠራተኞች ረጅም ሰዓት እንዲሠሩ ከፍተኛ ጫና ሊደረግባቸው ይችላል። ሆኖም በዓለም ላይ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢከሰት ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ የሚሰጡ እንዲሁም ‘ጤናማ ዓይን’ ያላቸው ሁሉ ከልክ በላይ መጨነቅ አያስፈልጋቸውም። አምላክ እንደሚወዳቸውና እንደሚያስብላቸው ያውቃሉ። (ማቴ. 6:22-34) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከመጥፋቷ አስቀድሞ በነበሩት ሁከት የነገሠባቸው ዓመታት ይሖዋ ለኤርምያስ የሚያስፈልገውን ነገር እንዴት እንዳሟላለት እንመልከት።
18. ኢየሩሳሌም ተከብባ በነበረበት ወቅት ይሖዋ ለኤርምያስ ያለውን ፍቅር ያሳየው እንዴት ነበር?
18 የባቢሎናውያን ከበባ ወደ መጨረሻው በተቃረበበት ወቅት ኤርምያስ በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ታስሮ ነበር። ታዲያ ኤርምያስ ምግብ ከየት ያገኝ ይሆን? ባይታሰር ኖሮ ወዲያ ወዲህ ብሎ ምግቡን ማግኘት ይችል ነበር። አሁን ግን ምግብ ለማግኘት የሌሎችን እጅ መጠበቅ ነበረበት፤ በወቅቱ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ደግሞ ይጠሉት ነበር! ያም ሆኖ ኤርምያስ የታመነው በሰው ሳይሆን እንደሚንከባከበው ቃል በገባለት በአምላክ ላይ ነበር። ታዲያ ይሖዋ ቃሉን ጠብቆ ይሆን? እንዴታ! ኤርምያስ “በከተማዪቱ ያለው እንጀራ እስኪያልቅ ድረስ . . . በየቀኑ አንድ አንድ እንጀራ” እንዲያገኝ ይሖዋ ዝግጅት አድርጎ ነበር። (ኤር. 37:21) ኤርምያስ፣ ባሮክ፣ አቤሜሌክና ሌሎች ሰዎች በዚያ ወቅት ከነበረው ረሃብና በሽታ እንዲሁም ከሞት መትረፍ ችለዋል።—ኤር. 38:2፤ 39:15-18
19. ከወደፊቱ ጊዜ ጋር በተያያዘ ቁርጥ አቋማችን ምን ሊሆን ይገባል?
19 እውነትም “የጌታ [“የይሖዋ፣” NW] ዐይኖች ጻድቃንን [ይመለከታሉ]፤ ጆሮቹም ጸሎታቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው።” (1 ጴጥ. 3:12) የሰማዩ አባትህ የሚመለከትህ መሆኑ ያስደስትሃል? የሚመለከትህ ለጥቅምህ እንደሆነ ማወቅህስ የመረጋጋትና የደኅንነት ስሜት እንዲሰማህ ያደርግሃል? እንግዲያው ወደፊት ምንም ይምጣ ምን ሁልጊዜም አካሄድህን ከአምላክ ጋር ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ይሖዋ ታማኞቹን በሙሉ ምንጊዜም እንደ አባት በአሳቢነት እንደሚመለከታቸው እርግጠኛ መሆን እንችላለን።—መዝ. 32:8፤ ኢሳይያስ 41:13ን አንብብ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.12 እነዚህ ደብዳቤዎች በዋነኝነት የሚመለከቱት የክርስቶስን ቅቡዓን ተከታዮች ቢሆንም በደብዳቤዎቹ ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ለሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ይሠራል።
^ አን.16 አምላክ የስብከቱን ሥራ እንደሚመራው የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ በሐዋርያት ሥራ 16:6-10 ላይ ይገኛል። ጥቅሱ፣ ጳውሎስና ባልደረቦቹ በእስያና በቢታኒያ እንዳይሰብኩ ‘መንፈስ ቅዱስ እንደከለከላቸው’ ይናገራል። መንፈስ ቅዱስ፣ ቅን ልብ ያላቸው በርካታ ሰዎች ለምሥራቹ ምላሽ ወደሰጡበት ወደ መቄዶንያ እንዲሄዱ መርቷቸዋል።
ልታብራራ ትችላለህ?
• ‘አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር እንዳደረግን’ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
• ይሖዋ ለባሮክ ያለውን ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?
• የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነው ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት ያንጸባረቀው እንዴት ነው?
• በዚህ አስጨናቂ ዘመን በአምላክ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤርምያስ ለባሮክ እንዳደረገለት ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለውን አሳቢነት ይኮርጃሉ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በተገቢው ጊዜ እርዳታ የሚሰጠው እንዴት ሊሆን ይችላል?