የክርስቶስ መገኘት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
የክርስቶስ መገኘት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
“የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?”—ማቴ. 24:3 NW
1. ሐዋርያቱ ኢየሱስን ምን ትኩረት የሚስብ ጥያቄ ጠየቁት?
ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት ኢየሱስ ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሳለ ከሐዋርያቱ መካከል አራቱ ብቻቸውን ወደ እሱ ቀርበው “እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” በማለት ጠይቀውት ነበር። (ማቴ. 24:3 NW) በዚህ ጥያቄ ላይ ሐዋርያቱ “መገኘትህ” እና “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” የሚሉ ከፍተኛ ትኩረት የሚስቡ አገላለጾችን ተጠቅመዋል። እነዚህ አገላለጾች ምን ያመለክታሉ?
2. “መደምደሚያ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው?
2 “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” የሚለውን አገላለጽ ለመመርመር በመጀመሪያ “መደምደሚያ” የሚለውን ቃል እንመልከት። ይህ ቃል ሲንቴሊያ ከሚለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ነው። በእንግሊዝኛ የተዘጋጀው የአዲስ ዓለም ትርጉም ይህን ቃል በሁሉም ቦታዎች ላይ “መደምደሚያ” ብሎ የተረጎመው ሲሆን ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለውን ቴሎስ የሚለውን ቃል ደግሞ “መጨረሻ” በማለት ተርጉሞታል። በእነዚህ ሁለት ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የሚሰጥን ንግግር እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። የንግግሩ መደምደሚያ የሚባለው ተናጋሪው ሲያብራራ የነበረውን ርዕሰ ጉዳይ የተወሰነ ጊዜ ወስዶ ለአድማጮች የሚከልስበትና ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ የሚገልጽበት የንግግሩ የመጨረሻ ክፍል ነው። ተናጋሪው ንግግሩን ጨረሰ የሚባለው ግን ከመድረክ ሲወርድ ነው። በተመሳሳይም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” የሚለው አገላለጽ መጨረሻውን ወይም ፍጻሜውን ጨምሮ ከዚያ በፊት ያለውን የተወሰነ ጊዜ ያመለክታል።
3. በክርስቶስ መገኘት ወቅት የሚፈጸሙት አንዳንድ ክንውኖች የትኞቹ ናቸው?
3 ሐዋርያቱ “መገኘት” ብለው የጠቀሱት ቃልስ ምን ትርጉም አለው? ይህ ቃል ፓሩሲያ * ከሚለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ነው። የክርስቶስ ፓሩሲያ ወይም መገኘት ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ በሆነበት በ1914 የጀመረ ሲሆን ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ክፉዎችን ለማጥፋት እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል። (ማቴ. 24:21) የዚህ ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ዘመን’፣ ነገሥታት የሚሆኑ ሰዎችን የመሰብሰቡ ሥራ፣ እነዚህ ሰዎች በሰማይ ለመኖር የሚያገኙት ትንሣኤና ሌሎች በርካታ ነገሮች የሚከናወኑት ክርስቶስ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ነው። (2 ጢሞ. 3:1፤ 1 ቆሮ. 15:23፤ 1 ተሰ. 4:15-17፤ 2 ተሰ. 2:1) በመሆኑም “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” (ሲንቴሊያ) ተብሎ የተገለጸው ጊዜና የክርስቶስ መገኘት (ፓሩሲያ) ተብሎ የሚጠራው ጊዜ ተመሳሳይ ናቸው ሊባል ይችላል።
ረዘም ያለ ጊዜን ያመለክታል
4. የክርስቶስ መገኘት ከኖኅ ዘመን ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
4 ፓሩሲያ የሚለው ቃል ረዘም ያለ ጊዜን ያመለክታል መባሉ ኢየሱስ መገኘቱን አስመልክቶ ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ማቴዎስ 24:37-39ን አንብብ።) ኢየሱስ መገኘቱን፣ በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ከተከሰተበት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አጭር ከነበረው ጊዜ ጋር እንዳላመሳሰለው ልብ በል። ከዚህ ይልቅ መገኘቱን ያወዳደረው የጥፋት ውኃው እስከመጣበት ሰዓት ድረስ ከነበረው ረዘም ያለ ጊዜ ጋር ነው። ኖኅ መርከቡን የገነባውም ሆነ የስብከት ሥራውን ያከናወነው የጥፋት ውኃው ከመምጣቱ በፊት በነበረው በዚህ ጊዜ ውስጥ ነው። እነዚህ ክንውኖች በርካታ አሥርተ ዓመታት ፈጅተዋል። በተመሳሳይም የክርስቶስ መገኘት ታላቁን መከራ ጨምሮ ከዚያ በፊት የሚከናወኑትን ነገሮች በሙሉ ያጠቃልላል።—2 ተሰ. 1:6-9
5. በራእይ ምዕራፍ 6 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት ቃላት የክርስቶስ መገኘት ረዘም ያለ ጊዜን እንደሚያመለክት የሚጠቁሙት እንዴት ነው?
5 የክርስቶስ መገኘት፣ ኢየሱስ ክፉዎችን ለማጥፋት የሚመጣበትን ወቅት ብቻ ሳይሆን ረዘም ያለ ጊዜን የሚያመለክት መሆኑን ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም በግልጽ ያሳያሉ። የራእይ መጽሐፍ ኢየሱስን በነጭ ፈረስ ላይ እንደተቀመጠ ጋላቢ አድርጎ የሚገልጸው ከመሆኑም ሌላ አክሊል እንደተሰጠው ይናገራል። (ራእይ 6:1-8ን አንብብ።) ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ “እንደ ድል አድራጊ ድል ለመንሣት” እንደወጣ ተደርጎ ተገልጿል። ከዚያም ትንቢቱ የተለያየ መልክ ባላቸው ፈረሶች ላይ የተቀመጡ ጋላቢዎች እንደተከተሉት ይናገራል። እነዚህ ጋላቢዎች ጦርነትን፣ ረሃብንና ቸነፈርን የሚያመለክቱ ሲሆን ሁሉም የሚከናወኑት ‘መጨረሻው ዘመን’ ተብሎ በሚጠራው ረዘም ያለ ጊዜ ውስጥ ነው። በዘመናችን የዚህን ትንቢት ፍጻሜ እየተመለከትን ነው።
6. ራእይ ምዕራፍ 12 ስለ ክርስቶስ መገኘት ምን እንድንረዳ ያስችለናል?
6 ራእይ ምዕራፍ 12 የአምላክ መንግሥት በሰማይ መቋቋሙን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ይዟል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ በሰማይ ጦርነት እንደተደረገ እናነባለን። ሚካኤል ማለትም በሰማይ ሥልጣኑን የያዘው ኢየሱስ ክርስቶስ እና መላእክቱ ከዲያብሎስና ከአጋንንቱ ጋር ተዋጉ። በመጨረሻም ሰይጣን ዲያብሎስና ግብረ አበሮቹ ወደ ምድር ተጣሉ። በዚህ ጊዜ ዲያብሎስ “ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ” በታላቅ ቁጣ እንደተሞላ ዘገባው ይናገራል። (ራእይ 12:7-12ን አንብብ።) ከዚህ ሁኔታ በግልጽ መረዳት እንደምንችለው የክርስቶስ መንግሥት በሰማይ መቋቋሙን ተከትሎ ለምድርና በላይዋ ለሚኖሩ ሰዎች ከፍተኛ ‘ወዮታ’ የሚያስከትል ጊዜ ይመጣል።
7. ሁለተኛው መዝሙር ስለምን ነገር ይናገራል? በዚህ መዝሙር ውስጥ ምን አጋጣሚ እንደተከፈተ ተገልጿል?
7 በተመሳሳይም ሁለተኛው መዝሙር ኢየሱስ ሰማይ በሚገኘው ምሳሌያዊ የጽዮን ተራራ ላይ ንጉሥ ሆኖ ስለ መሾሙ ትንቢት ይናገራል። (መዝሙር 2:5-9፤ 110:1, 2ን አንብብ።) ይሁን እንጂ ይህ መዝሙር፣ የምድር ገዢዎችና ሕዝቦቻቸው ለክርስቶስ ራሳቸውን ለማስገዛት የሚያስችላቸው አጋጣሚ እንዲያገኙ የተወሰነ ጊዜ እንደተሰጣቸውም ይጠቁማል። እነዚህ ገዢዎች ‘ልብ እንዲሉና እንዲጠነቀቁ’ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። አዎን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ይሖዋንና እሱ የሾመውን ንጉሥ በማገልገል አምላክን “መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ የተባረኩ ናቸው።” በመሆኑም ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ የሚገኝበት ጊዜ ገዢዎችም ሆኑ ተገዢዎቻቸው አስፈላጊውን ለውጥ እንዲያደርጉ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል።—መዝ. 2:10-12
ምልክቱን ማስተዋል
8, 9. የክርስቶስን መገኘት የሚጠቁመውን ምልክትም ሆነ ምልክቱ ያለውን ትርጉም የሚያስተውሉት እነማን ናቸው?
8 ኢየሱስ፣ ፈሪሳውያን መንግሥቱ የሚመጣበትን ጊዜ አስመልክተው ሲጠይቁት እነሱ እንደሚያስቡት ‘በሚታዩ ምልክቶች’ ማለትም በግልጽ በሚታይ ሁኔታ እንደማይመጣ በመንገር መልስ ሰጣቸው። (ሉቃስ 17:20, 21) የማያምኑ ሰዎች ይህን ሁኔታ ፈጽሞ መረዳት አይችሉም። ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ወደፊት ንጉሣቸው እንደሚሆን እንኳ አላስተዋሉም። ታዲያ የክርስቶስን መገኘት የሚጠቁመውን ምልክትም ሆነ ምልክቱ ያለውን ትርጉም የሚያስተውሉት እነማን ናቸው?
9 ቀጥሎ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘መብረቅ በርቆ ሰማዩን ከዳር እስከ ዳር ሲያበራ’ ማየት የሚችሉትን ያህል ምልክቱን በግልጽ መመልከት እንደሚችሉ ተናግሯል። (ሉቃስ 17:24-29ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህንን ሲል መገኘቱን ስለሚጠቁመው ምልክት መናገሩ እንደነበር በማቴዎስ 24:23-27 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ሐሳብ በግልጽ መረዳት ይቻላል።
ምልክቱን የሚያየው ትውልድ
10, 11. (ሀ) በማቴዎስ 24:34 ላይ የተገለጸውን “ትውልድ” የሚለውን ቃል በተመለከተ ከዚህ ቀደም ምን ማብራሪያ ተሰጥቶ ነበር? (ለ) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ትውልድ” የሚለው ቃል እነማንን እንደሚጨምር አስበው መሆን አለበት?
10 ከዚህ ቀደም የወጣ መጠበቂያ ግንብ በማቴዎስ 24:34 ላይ የተጠቀሰው “ይህ ትውልድ” የሚለው አገላለጽ በመጀመሪያው መቶ ዘመን “ኢየሱስ በኖረበት ጊዜ የነበሩትን የማያምኑ አይሁዶች” እንደሚያመለክት ገልጾ ነበር። * በወቅቱ ይህ ሐሳብ ምክንያታዊ ይመስል ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ጥቅሶች ላይ “ትውልድ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው አሉታዊ መልእክት በሚያስተላልፍ መንገድ ነው። ከዚህም በላይ ኢየሱስ በብዙዎቹ ቦታዎች ላይ ትውልድ ለሚለው ቃል “ክፉ” እንደሚለው ያሉ ቅጽሎችን ይጠቀም ነበር። (ማቴ. 12:39፤ 17:17፤ ማር. 8:38) በመሆኑም ኢየሱስ “ትውልድ” ሲል፣ በዘመናችን ‘የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ’ (ሲንቴሊያ) ምልክቶች የሚመለከተውን ብቻ ሳይሆን በሥርዓቱ መጨረሻ (ቴሎስ) ላይ በሕይወት የሚገኘውን ክፉና የማያምን “ትውልድ” የሚያመለክት እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ነበር።
11 ኢየሱስ “ትውልድ” የሚለውን ቃል አሉታዊ ትርጉም በሚያስተላልፍ መንገድ የተጠቀመበት በእሱ ዘመን የነበሩትን ክፉ ሰዎች ለማመልከት እንደሆነ ግልጽ ነው። ይሁንና በማቴዎስ 24:34 ላይ “ትውልድ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው በእርግጥ እነሱን ለማመልከት ነው? አራቱ ደቀ መዛሙርት ስለ ሥርዓቱ መደምደሚያ ኢየሱስን የጠየቁት “ለብቻቸው” እንደነበር አስታውስ። (ማቴ. 24:3) ኢየሱስ በዚያ ወቅት “ይህ ትውልድ” ብሎ ሲናገር አሉታዊ ትርጉም የሚያስተላልፍ ቅጽል ስላልተጠቀመ፣ ሐዋርያቱ እነሱም ሆኑ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ‘ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ’ አያልፍም የተባለው “ትውልድ” ክፍል እንደሚሆኑ አድርገው እንዳሰቡ ምንም ጥርጥር የለውም።
12. ኢየሱስ “ትውልድ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ማንን ለማመልከት እንደሆነ በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ የሚጠቁመው እንዴት ነው?
12 እንዲህ ለማለት የሚያስችል ምን ማስረጃ አለ? በማቴዎስ 24:32, 33 ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ከበለስ ዛፍ ይህን ትምህርት ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደተቃረበ ታውቃላችሁ። እንደዚሁም [እናንተ] እነዚህን ሁሉ ስታዩ፣ እርሱ በደጅ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ።” (ከማርቆስ 13:28-30 እና ከሉቃስ 21:30-32 ጋር አወዳድር።) ከዚያም ማቴዎስ 24:34 “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ይላል።
በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ በጥንቃቄ መመርመራችን እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያስችለናል።13, 14. ኢየሱስ የጠቀሰው “ትውልድ” የሚያመለክተው ደቀ መዛሙርቱን መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው?
13 ኢየሱስ “ይህ ሁሉ” ሲፈጸም በማየት አንድ መደምደሚያ ላይ የሚደርሱት ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ የሚቀቡት ደቀ መዛሙርቱ እንደሆኑ ተናግሯል። በመሆኑም “ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ያለው ደቀ መዛሙርቱን ለማመልከት መሆን አለበት።
14 ከማያምኑ ሰዎች በተለየ መልኩ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምልክቱን ማየት ብቻ ሳይሆን ምን ትርጉም እንዳለው ጭምር ይረዳሉ። ምልክቱ ካሉት የተለያዩ ገጽታዎች “ትምህርት” የሚያገኙ ከመሆኑም ባሻገር ትክክለኛ ትርጉማቸውንም ‘ያውቃሉ።’ ከዚህ በመነሳት የሰው ልጅ “በደጅ እንደ ቀረበ” ሙሉ በሙሉ ይረዳሉ። የማያምኑ አይሁዳውያንም ሆኑ ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ኢየሱስ የተናገራቸው ትንቢቶች በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተወሰነ መጠን ሲፈጸሙ እንደተመለከቱ አይካድም፤ ይሁን እንጂ ከተመለከቷቸው ነገሮች ትምህርት ያገኙት ማለትም የእነዚህን ነገሮች ትክክለኛ ትርጉም ማስተዋል የቻሉት በወቅቱ የነበሩት የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ብቻ ነበሩ።
15. (ሀ) ኢየሱስ የጠቀሰው “ትውልድ” በዘመናችን ማንን ያመለክታል? (ለ) “ይህ ትውልድ” የሚቆይበትን ትክክለኛ የጊዜ ርዝመት ማስላት የማንችለው ለምንድን ነው? (በገጽ 25 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)
15 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ መንፈሳዊ ማስተዋል የሌላቸው ሰዎች የኢየሱስን መገኘት የሚጠቁም በግልጽ ‘የሚታይ ምልክት’ እንደሌለ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ሁሉም ነገር ቀደም ሲል እንደነበረው እንደሚቀጥል ይናገራሉ። (2 ጴጥ. 3:4) በሌላ በኩል ግን ታማኝ የሆኑት የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች ማለትም በዛሬው ጊዜ የሚገኙት የዮሐንስ ክፍል አባላት ይህን ምልክት ልክ እንደ መብረቅ ብልጭታ በግልጽ እየተመለከቱ ከመሆኑም ሌላ የምልክቱን ትክክለኛ ትርጉም ተረድተዋል። ‘ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ’ አያልፍም የተባለው “ትውልድ” በዚህ ዘመን ያሉትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች በቡድን ደረጃ የሚያመለክት ነው። * ይህ ደግሞ ከክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች መካከል አንዳንዶቹ በትንቢት የተነገረው ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ወቅት በምድር ላይ እንደሚኖሩ ይጠቁማል።
“ተግታችሁ ጠብቁ!”
16. ሁሉም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
16 ይሁን እንጂ ምልክቱን ማስተዋል ብቻውን በቂ አይደለም፤ ከዚህም የበለጠ ነገር ያስፈልጋል። ኢየሱስ ቀጥሎ “ለእናንተ የምነግራችሁን ለሰው ሁሉ እናገራለሁ፤ ተግታችሁ ጠብቁ!” ብሏል። (ማር. 13:37) ቅቡዓን ክርስቲያኖችም እንሁን የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ይህ ምክር ለሁላችንም በጣም አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ በ1914 በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ ወደ 90 ዓመታት አልፈዋል። በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም እንኳ ዝግጁ መሆንና ተግተን መጠበቅ አለብን። ክርስቶስ በማይታይ ሁኔታ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ እንደሚገኝ ማወቃችን ነቅተን እንድንጠብቅ የሚረዳን ከመሆኑም በላይ በቅርቡ ጠላቶቹን ለማጥፋት ‘ባላሰብነው ሰዓት’ የሚመጣ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል።—ሉቃስ 12:40
17. ስለ ክርስቶስ መገኘት ያገኘነው እውቀት ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል? ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?
17 የክርስቶስ መገኘት ምን ትርጉም እንዳለው መረዳታችን የጥድፊያ ስሜታችንን እንድናቀጣጥል ይረዳናል። ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ እንደተገኘና ከ1914 ጀምሮ በማይታይ ሁኔታ እየገዛ መሆኑን እናውቃለን። በቅርቡ ክፉዎችን ለማጥፋት የሚመጣ ከመሆኑም በላይ በመላው ምድር ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣል። በመሆኑም ኢየሱስ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው [ቴሎስ] ይመጣል” በማለት በተናገረ ጊዜ በጠቀሰው የስብከት ሥራ በንቃት ለመሳተፍ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ማቴ. 24:14
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 ፓሩሲያ የሚለውን ቃል በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 2 ከገጽ 676-679 ተመልከት።
^ አን.10 የኅዳር 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 11-15, 19, 30, 31ን ተመልከት።
^ አን.15 “ይህ ትውልድ” ተብለው የተጠቀሱት ሰዎች የሚኖሩበት ዘመን፣ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው የመጀመሪያው ራእይ ከሚፈጸምበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም። (ራእይ 1:10 እስከ 3:22) ይህ ራእይ ፍጻሜውን የሚያገኘው በጌታ ቀን ውስጥ ሲሆን፣ ይህም ከ1914 ጀምሮ የመጨረሻው ታማኝ ቅቡዕ ሞቶ ትንሣኤ እስከሚያገኝበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል።—ራእይ ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 24 አንቀጽ 4ን ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የኢየሱስ መገኘት ረዘም ያለ ጊዜን እንደሚያመለክት እንዴት እናውቃለን?
• የኢየሱስን መገኘት የሚጠቁመውን ምልክት የሚያስተውሉትና ምን ትርጉም እንዳለው የሚረዱት እነማን ናቸው?
• በማቴዎስ 24:34 ላይ የተጠቀሰው ትውልድ በዘመናችን ማንን ያመለክታል?
• “ይህ ትውልድ” የሚቆይበትን ትክክለኛ የጊዜ ርዝመት ማስላት የማንችለው ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
“ይህ ትውልድ” የሚቆይበትን የጊዜ ርዝመት ማስላት እንችላለን?
“ትውልድ” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ በአንድ ዘመን ውስጥ የኖሩ ወይም አንድ ክንውን ሲፈጸም የተመለከቱ የተለያየ ዕድሜ ያላቸውን ሰዎች ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘፀአት 1:6 “ከጊዜ በኋላ ዮሴፍና ወንድሞቹ ያም ትውልድ በሙሉ ሞቱ” ይላል። ዮሴፍና ወንድሞቹ በዕድሜ የተለያዩ ቢሆኑም በአንድ ወቅት ላይ የተፈጸሙ ነገሮችን እኩል ተመልክተዋል። እዚህ ላይ በተጠቀሰው “ትውልድ” ውስጥ ከዮሴፍ በፊት የተወለዱ አንዳንድ ወንድሞቹም ይገኙበታል። ከእነዚህ አንዳንዶቹ ዮሴፍ ከሞተ በኋላም በሕይወት ቀጥለዋል። (ዘፍ. 50:24) እንደ ብንያም ያሉ ‘በዚያ ትውልድ’ ውስጥ የሚካተቱ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከዮሴፍ በኋላ የተወለዱት ሲሆኑ እሱ ከሞተም በኋላ በሕይወት መኖራቸውን ቀጥለው ሊሆን ይችላል።
በመሆኑም “ትውልድ” የሚለው ቃል በአንድ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የኖሩ ሰዎችን ለማመልከት ከተሠራበት፣ እነዚህ ሰዎች የኖሩበት ጊዜ መጨረሻ እንዳለውና ከመጠን በላይ ረጅም እንደማይሆን ከመግለጽ ውጪ የጊዜውን ትክክለኛ ርዝመት ማስቀመጥ አንችልም። ስለዚህ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:34 ላይ “ይህ ትውልድ” የሚለውን አገላለጽ ሲጠቀም ደቀ መዛሙርቱ ‘የመጨረሻው ዘመን’ የሚያበቃበትን ትክክለኛ ጊዜ ማስላት የሚችሉበትን ፍንጭ እየሰጣቸው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ አጽንኦት ሰጥቶ የተናገረው “ያን ቀንና ሰዓት” እንደማያውቁት ነው።—2 ጢሞ. 3:1፤ ማቴ. 24:36
[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ ‘ድል እያደረገ’ እንዳለ ተደርጎ ተገልጿል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም”