ጭካኔ በሞላበት ዓለም ውስጥ ርኅራኄ ማሳየት
ጭካኔ በሞላበት ዓለም ውስጥ ርኅራኄ ማሳየት
በቡሩንዲ የሚኖር አንድ ሰው ወባ ይዞት በጠና ታሟል። ሰውየው በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል መወሰድ ያስፈልገዋል። ሆኖም ለመጓጓዣ የሚሆን መኪና የለም። ታዲያ ይህን ሰው ወደ ሆስፒታል ማድረስ የሚቻለው እንዴት ነው? በዚህ ጊዜ ሁለት ጓደኞቹ ሊረዱት መጡ። ሕመምተኛውን በብስክሌት ላይ አስቀምጠው በተራራማ አካባቢ በሚገኝ መንገድ ብስክሌቱን እየገፉ ለአምስት ሰዓታት ያህል አድካሚ ጉዞ አደረጉ። ከዚያም በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል በሚወስደው አውቶቡስ ላይ አሳፈሩት። ከጥቂት ቀናት በኋላ ሰውየው ተሻለው።
በሌላው የዓለም ክፍል ደግሞ በነሐሴ 2005፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የባሕረ ሰላጤ አካባቢ ካትሪና በተባለችው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ከተመታ በኋላ የተወሰኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች ዛፎች የወደቁበት አንድ ቤት ተመለከቱ። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች የቤቱን ባለቤቶች ጨርሶ የማያውቋቸው ቢሆንም ቀኑን ሙሉ ቤቱ ላይ የወደቁትን ዛፎችና ፍርስራሹን ሲያነሱ ዋሉ። የቤቱ ባለቤት “እነዚህን . . . [ሰዎች] ምን ያህል እንደማመሰግናቸው ለመግለጽ . . . ቃላቶች ያጥሩኛል” ብላለች።
በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡት ስሜታችንን የሚረብሹ ዘገባዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚያወሩት ስለግፍና ስለጭካኔ ድርጊቶች ነው። በየዕለቱ የሚፈጸሙ የርኅራኄና የደግነት ድርጊቶች ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ባሉት ዘገባዎች ይሸፈናሉ። ይህ መሆኑ ግን የትም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ፍቅርና ርኅራኄ በጣም የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አይለውጠውም። የሰው ልጆች ርኅራኄ ይርባቸዋል! ብዙዎች ‘ለሰው ሰላምና በጎ ፈቃድ ይሁን’ እያሉ በሚናገሩበት አሊያም በሚዘምሩበት በገና በዓል ሰሞን ከሌላው ሉቃስ 2:14 የ1954 ትርጉም
ጊዜ ይበልጥ ርኅራኄ ማሳየት የተለመደ ሊሆን ይችላል።—ወዳጃዊ መንፈስ እየጠፋ ባለበት ዓለም ውስጥ ርኅራኄ ማሳየት ቀላል ላይሆን ይችላል። አብዛኞቹ ሰዎች ጨካኝና ለሌላው ስሜት ደንታ ቢስ መሆን ለስኬትና ለድል እንደሚያበቃ ይሰማቸዋል። ብዙ ሰዎች ‘ርኅሩኅ ከመሆን ይልቅ ጨካኝ መሆን የበለጠ ብልኅነት ነው’ በሚለው ፈሊጥ ሕይወታቸውን የሚመሩ ይመስላል። ሰዎች ስግብግብና ራስ ወዳድ መሆናቸው ርኅራኄ እንዳያሳዩ ያደርጋቸዋል።
በመሆኑም ብዙዎች ራሳቸውን የሚያስቀድሙ ሲሆን እንዲያውም ይህን የሚያደርጉት በሌሎች ሰዎች ስሜት ወይም ጥቅም ላይ በመረማመድ ነው። ብዙውን ጊዜ በስፖርቱና በመዝናኛው ዓለም ታዋቂ የሆኑ ወንዶች ደግነትና ፍቅር የማያሳዩ “እውነተኛ ወንዶች” (ትምክሕተኞች) እንደሆኑ ተደርገው ይቀርባሉ። አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎችም እንደዚህ ዓይነት ባሕርይ ያሳያሉ።
እንግዲያው እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው:- ‘ርኅሩኅ መሆን የሚኖርብን ለምንድን ነው? ርኅራኄ መልካም እንድናደርግ የሚገፋፋ ባሕርይ ነው? ደግሞስ ርኅራኄ እንድናሳይ ምን ሊረዳን ይችላል?’ የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
• ርኅራኄ ማሳየት ደካማነት ነው?
• ርኅራኄ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል?
• ርኅራኄ ማሳየት የምትችለው በየትኞቹ ተግባራዊ መንገዶች ነው?