ወደ አዲስ ዓለም ለመግባት የሚደረግ ጉዞ
የሕይወት ታሪክ
ወደ አዲስ ዓለም ለመግባት የሚደረግ ጉዞ
ጃክ ፕራምበር እንደተናገረው
በማዕከላዊ ስዊድን አርቡገ ከምትባል አንዲት ትንሽ ውብ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ ከ80 በላይ ፈቃደኛ ሠራተኞች ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ይገኛል። እኔና ባለቤቴ ካሪን የምንኖረውም ሆነ የምንሠራው እዚህ ነው። በዚህ ቦታ ልንገኝ የቻልነው እንዴት ነው?
ወደ 19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ አንዲት የ15 ዓመት ስዊድናዊት ወጣት በስደት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ትሄዳለች። ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ሳለች ከአንድ ስዊድናዊ ባሕረኛ ጋር ተዋወቀች። ትውውቃቸው ወደ ፍቅር ግንኙነት ተቀየረ፤ በኋላም ተጋቡና አንድ ወንድ ልጅ ወለዱ፤ ያ ልጅ እኔ ነኝ። ይህ የሆነው በ1916 አንደኛው የዓለም ጦርነት ይካሄድ በነበረበት ወቅት በብሮንክስ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩ ኤስ ኤ ነበር።
ብዙም ሳይቆይ ወደ ብሩክሊን ሄደን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ከሚገኝበት ከብሩክሊን ሃይትስ ጥቂት ሕንፃዎች አለፍ ብሎ ባለ አካባቢ መኖር ጀመርን። ከጊዜ በኋላ አባቴ እንደነገረኝ እኔና እሱ ለናሙና በተሠራች መርከብ ላይ ሆነን በብሩክሊን ድልድይ አጠገብ ተጉዘናል። እዚያ አካባቢ ላለ ሰው የቤቴል ሕንፃ በቀላሉ ይታያል። በወቅቱ በዚያ ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ በሕይወቴ ላይ ሊያሳድር ስለሚችለው ተጽዕኖ የማውቀው ነገር አልነበረም።
በ1918 አንደኛው የዓለም ጦርነት
አቆመ፤ ለጊዜውም ቢሆን በአውሮፓ ይደረግ የነበረው ትርጉም የለሽ ፍጅት ቆመ። ወታደሮቹ ለየት ካለ ጠላት ማለትም ከሥራ አጥነትና ከድህነት ጋር ለመፋለም ወደየመኖሪያቸው ተመለሱ። አባቴ ወደ ስዊድን መመለስ የሚያዋጣ እንደሆነ ስለተሰማው በ1923 ወደ አገራችን ተመለስን። ወደዚያ ከተመለስን በኋላ ዳልስላንድ ክልል ውስጥ በአንድ ባቡር ጣቢያ አጠገብ በምትገኝ ኢሪክስታድ በምትባል ትንሽ መንደር ውስጥ መኖር ጀመርን። በዚህ አካባቢ አባቴ ማሽን ቤት ከፍቶ መሥራት ጀመረ። ያደግሁትም ሆነ ትምህርቴን የተከታተልኩት በዚህ አካባቢ ነበር።አንድ ዘር ተዘርቶ ነበር
አባቴ ንግዱ ብዙም ስላላዋጣው በ1930ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ እንደገና ባሕረኛ ሆነ። በዚህ ጊዜ ብቻችንን ቀረን። የተረፈን ነገር ቢኖር ለእናቴ ጭንቀት ለእኔ ደግሞ ማሽን ቤቱን መቆጣጠር ነበር። አንድ ቀን እናቴ፣ ዮሐን የሚባለውን የአክስቴን ባል ልትጠይቀው ሄደች። የዓለም ሁኔታ በጣም ያስጨንቃት ስለነበር “ዮሐን፣ የዓለም ሁኔታ እንዲሁ ይቀጥላል?” ስትል ጠየቀችው።
“አይቀጥልም ሩት” በማለት መለሰላት። ቀጥሎም አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው መንግሥት አማካኝነት ክፋትን እንደሚያስወግድና በምድር ላይ የጽድቅ አገዛዝ እንደሚያመጣ የገባውን ቃል ይነግራት ጀመር። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዳንኤል 2:44) ኢየሱስ ባስተማረን ጸሎት ውስጥ የተጠቀሰው መንግሥት መግዛት ሲጀምር ምድር ገነት እንደምትሆንና የጽድቅ አገዛዝ እንደሚሰፍን ጥሩ አድርጎ አስረዳት።—ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:3, 4
እናቴ በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ልቧ ተነካ። በመንገዷ ሁሉ አምላክን እያመሰገነች ቤት ደረሰች። ነገር ግን አባቴም ሆነ እኔ ሃይማኖተኛ ለመሆን መፈለጓ አላስደሰተንም ነበር። በ1930ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ በምዕራብ ስዊድን ወደምትገኘው ትሮልሃተን ወደምትባል ከተማ ሄድኩ። እዚያም በአንድ ትልቅ መሥሪያ ቤት ውስጥ ሥራ አገኘሁ። ብዙም ሳይቆይ እናቴና የባሕር ሕይወቱን በቅርቡ ያቆመው አባቴ እኔ ወዳለሁበት አካባቢ ለመኖር መጡ። በዚህ ጊዜ ቤተሰባችን እንደገና አንድ ላይ መኖር ጀመረ።
እናቴ መንፈሳዊ ፍላጎቷን ለማርካት ትፈልግ ስለነበር በአካባቢው ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ፈልጋ አገኘች። በወቅቱ ልክ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ይሰበሰቡ የነበረው በየግል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነበር። (ፊልሞና 1, 2) አንድ ቀን ስብሰባው የሚካሄድበት ቤት ተራ ለእናቴ ደረሳት። ፈራ ተባ እያለች ጓደኞቿ ቤት መምጣት ይችሉ እንደሆነ አባቴን ጠየቀችው። “ያንቺ ጓደኞች የእኔም ጓደኞች ናቸው” በማለት መለሰላት።
ስለዚህ ሰዎች ለስብሰባ ወደ ቤታችን መምጣት ጀመሩ። ሰዎች መግባት ሲጀምሩ እኔ እወጣ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ቤት መቆየት ጀመርኩ። የይሖዋ ምሥክሮች ተግባቢ መሆናቸው እንዲሁም ትምህርታቸው አሳማኝ መሆኑ በአእምሮዬ የነበረውን ጭፍን ጥላቻ ሁሉ አስወገደልኝ። የወደፊት ሕይወቴ ተስፋ እንዲኖረው የሚያደርግ ዘር በልቤ ውስጥ ማደግ ጀመረ።
የባሕር ላይ ሕይወት
ባሕረኛ የመሆን ፍላጎት ከአባቴ ወርሼ መሆን አለበት እኔም የባሕር ላይ ሕይወት ጀመርኩ። ከዚህም በላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መንፈሳዊ ነገር እንደሚያስፈልገኝ እየተገነዘብኩ መጣሁ። ጉዟችንን አጠናቅቀን ወደብ ላይ ስንደርስ የይሖዋ ምሥክሮችን ለማግኘት ምንጊዜም ጥረት አደርግ ነበር። በሆላንድ፣ (በዛሬዋ ኔዘርላንድ) አምስተርዳም ከተማ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮችን የት ማግኘት እንደምችል ለመጠየቅ ወደ አንድ ፖስታ ቤት ሄድኩኝ። ጥቂት ከተነጋገርን በኋላ ለመግባባት ቻልን፤ ከዚያም አድራሻውን ተቀብዬ ወዲያውኑ ወደ ሥፍራው አመራሁ። ደጃፍ ላይ አንዲት የአሥር ዓመት ልጅ ሞቅ ባለ ስሜት ተቀበለችኝ። እንግዳ ብሆንም ወዲያውኑ ከልጅቷም ሆነ ከቤተሰቧ ጋር አንድ
ቤተሰብ የሆንን ያህል ተሰማኝ። ይህ አስደሳች የሆነው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ኅብረት ምን እንደሚመስል ለማየት የቻልኩበት አጋጣሚ ነበር!ምንም እንኳ ቋንቋችን አንድ ባይሆንም ቤተሰቡ የቀን መቁጠሪያና የባቡር ጉዞ ፕሮግራም አውጥቶ ካርታ መሥራት ሲጀምር በሐርለም አቅራቢያ በምትገኝ ከተማ ውስጥ ትልቅ ስብሰባ ሊካሄድ እንደሆነ ተረዳሁ። ወደ ስብሰባው የሄድኩ ሲሆን በዚያ ይነገር የነበረው አንዱም ቃል ባይገባኝም እንኳ በጣም ነበር የተደሰትኩት። የይሖዋ ምሥክሮቹ እሁድ በሚደረገው የሕዝብ ንግግር ላይ ሰዎች እንዲገኙ የመጋበዣ ወረቀት ሲሰጡ ስመለከት እኔም በማደሉ ሥራ የመካፈል ፍላጎት አደረብኝ። ስለዚህ ሰዎች የጣሏቸውን የመጋበዣ ወረቀቶች እያነሳሁ እንደገና ማደል ጀመርኩ።
በአንድ ወቅት አርጀንቲና፣ ቦነስ አይረስ ወደብ ከደረስን በኋላ የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮ አገኘሁ፤ ውስጡ ቢሮና መጋዘን ነበረው። ሹራብ የምትሠራ አንዲት ሴት ዴስኩ አጠገብ ተቀምጣለች። ልጇ ሳትሆን አትቀርም አንዲት ትንሽ ልጅ በአሻንጉሊት ትጫወታለች። አንድ ሰው በስዊድንኛ የተዘጋጀ ፍጥረት የተባለ መጽሐፍ ጨምሮ ጥቂት መጽሐፎችን ከመደርደሪያው ላይ እየወሰደ ነበር፤ ጊዜው በጣም መሽቷል። በፈገግታ የተሞላውን ፊታቸውን ስመለከት የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ወሰንኩ።
ወደ አገራችን ስንመለስ መርከባችን በኒውፋውንድላንድ የባሕር ዳርቻ ላይ ተከስክሶ የነበረ የካናዳ የጦር አውሮፕላን ሠራተኞችን ጭኖ ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ ስኮትላንድ አቅራቢያ አንድ የእንግሊዝ ባሕር ኃይል ጀልባ በቁጥጥር ሥር አዋለን። ከዚያም ለምርመራ ኦርክኒ ደሴቶች ላይ ወደምትገኝ ኪርክዎል ወደተባለች ከተማ ተወሰድን። በወቅቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈንድቶ የሂትለር ወታደሮች መስከረም 1939 ፖላንድን ወርረው ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ የተለቀቅን ሲሆን ያለ ምንም ችግር ወደ ስዊድን ተመለስን።
በዚህ ጊዜ ወደ ቤቴ ብቻ ሳይሆን ወደ አምላኬም ጭምር ነበር የተመለስኩት። አሁን ከእነዚህ የአምላክ ሕዝቦች አንዱ መሆን እፈልጋለሁ፤ ከእነሱ ጋር መሰብሰቡን ፈጽሞ ችላ ማለት አልፈልግም። (ዕብራውያን 10:24, 25) ባሕረኛ ሆኜ ያሳለፍኩትን ጊዜ ሳስታውስ ደስ ይለኛል፤ ዘወትር ለሌሎች ባሕረተኞች እሰብክ የነበረ ሲሆን ከመካከላቸውም አንዱ የይሖዋ ምሥክር ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ።
ልዩ ዓይነት አገልግሎት
በ1940 መጀመሪያ ላይ ስቶክሆልም የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ጎበኘሁ። በጊዜው በስዊድን ይደረግ የነበረውን የስብከት ሥራ በበላይነት ይከታተል የነበረው ዮሐን ኢነሮት ጥሩ አቀባበል አደረገልኝ። አቅኚ በመሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በስብከቱ ሥራ መካፈል እንደምፈልግ ስነግረው፣ ትኩር ብሎ ተመለከተኝና “ይህ የአምላክ ድርጅት መሆኑን ታምናለህ?” ሲል ጠየቀኝ።
“አዎን” በማለት መለስኩለት። ሰኔ 22, 1940 ከተጠመቅሁ በኋላ አስደሳች በሆነውና ጥሩ የሥራ ባልደረቦች ባሉበት ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ማገልገል ጀመርኩ። ቅዳሜንና እሁድን በአገልግሎት እናሳልፍ ነበር። በጋ ላይ በብስክሌት ራቅ ወዳሉ ክልሎች እየሄድን ቅዳሜንና እሁድን እዚያ ስናገለግል እንውላለን። ሲመሽ ደግሞ በሣር ክምር ላይ እንተኛ ነበር።
አብዛኛውን ጊዜ ግን በስቶክሆልምና በአቅራቢያው ባሉ አካባቢዎች ከቤት ወደ ቤት በመሄድ እናገለግላለን። አንድ ቀን ወደ አንድ ቤት ስሄድ አንድ ሰው ምድር ቤቱ ውስጥ የውኃ ማሞቂያውን ለመሥራት ሲጣደፍ አየሁ፤ ሰውየው ትንሽ ተረብሾ ነበር። እጅጌዬን ሰብሰብ አድርጌ መርዳት ጀመርኩ። ማሞቂያው ማንጠባጠቡን ሲያቆም በአመስጋኝነት ስሜት ተመለከተኝና “የመጣኸው ለሌላ ጉዳይ ይመስለኛል፤ ስለዚህ ወደ ላይ እንውጣና እጃችንን ታጥበን ቡና እንጠጣ” አለኝ። እንዳለው አደረግንና ቡናችንን እየጠጣን መሠከርኩለት። ይህ ሰው ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።
አገሪቱ የገለልተኝነት አቋም እንደምትከተል በይፋ ብትናገርም የስዊድን ሕዝብ በጦርነቱ መነካቱ አልቀረም። እኔን ጨምሮ በርካታ ወንዶች ለውትድርና አገልግሎት ተጠርተን ነበር። ወታደራዊ ሥልጠና ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆኔ ምክንያት ለአጭር ጊዜ ታሰርኩ። ከጊዜ በኋላ ወደ አንድ የእስረኞች ካምፕ እንድገባ ተፈረደብኝ። ብዙውን ጊዜ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ዳኞች ፊት እንዲቀርቡ የሚያዝ መጥሪያ ይደርሳቸው ነበር። ይህም ስለ አምላክ መንግሥት ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ ከፍቶልናል። ይህ ኢየሱስ “በእኔ ምክንያት ወደ ገዦችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፤ በእነርሱና በአሕዛብም ፊት ምስክር ትሆናላችሁ” በማለት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ነው።—ማቴዎስ 10:18
ሕይወቴ ተለወጠ
በ1945 በአውሮፓ የነበረው ጦርነት አበቃ። በዚያው ዓመት ቆየት ብሎ በወቅቱ ዓለም አቀፉን ሥራ በኃላፊነት
ይመራ የነበረው ወንድም ናታን ኖር ከጸሐፊው ከሚልተን ሄንሼል ጋር በመሆን ከብሩክሊን መጥቶ ጎበኘን። የእነሱ ጉብኝት በስዊድን ውስጥ የሚደረገውን የስብከት ሥራ እንደገና በማደራጀት ረገድ ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቷል፤ እኔም ከዚህ ጉብኝት በግለሰብ ደረጃ ተጠቅሜያለሁ። በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብቶ የመማር አጋጣሚ እንዳለ ስሰማ ወዲያው አመለከትኩ።በቀጣዩ ዓመት በወቅቱ ኒው ዮርክ ውስጥ ከሳውዝ ላንሲንግ ወጣ ብሎ ይገኝ በነበረው ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርቴን መከታተል ጀመርኩ። የወሰድኩት የአምስት ወር ሥልጠና ለመጽሐፍ ቅዱስና ለአምላክ ድርጅት ጥልቅ አድናቆት እንዲኖረኝ አድርጎኛል። ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ በበላይነት የሚመሩት ወንድሞች የሚቀረቡና አሳቢ እንደሆኑ ተገንዝቤያለሁ። ከእያንዳንዳችን ጎን በመሰለፍ ጠንክረው ይሠሩ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ምንም እንኳ ይህ የምጠብቀው ነገር ቢሆንም በገዛ ዓይኖቼ ማየቴ ግን አስደስቶኛል።
ጊዜው ሳይታወቀን አልፎ የጊልያድ ትምህርት ቤት ስምንተኛው ክፍል ተማሪዎች የምንመረቅበት የካቲት 9, 1947 ደረሰ። ወንድም ኖር በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የት አገር እንደተመደብን አሳወቀን። የእኔ ተራ ሲደርስ፣ “ወንድም ፕራምበር በስዊድን ያሉትን ወንድሞች ለመርዳት ወደዚያ ይመለሳል” በማለት ተናገረ። እውነቱን ለመናገር ወደ ስዊድን የመመለሱ ነገር ብዙም አላጓጓኝም ነበር።
አንድ አስቸጋሪ ኃላፊነት መወጣት
ወደ ስዊድን ስመለስ በዓለም ዙሪያ በብዙ አገሮች የሚጀመር አዲስ ዓይነት ሥራ እንዳለ ሰማሁ፤ ይህ ሥራ የአውራጃ የበላይ ተመልካችነት ነበር። በስዊድን የመጀመሪያው የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ የተሾምኩ ሲሆን የተሰጠኝ ክልል መላ አገሪቱን የሚሸፍን ነበር። ስዊድን ውስጥ በሚገኙ ትላልቅና አነስተኛ ከተሞች ውስጥ የሚካሄዱ ከጊዜ በኋላ የወረዳ ስብሰባ ተብለው የተጠሩ ስብሰባዎችን ያደራጀሁ ከመሆኑም በላይ ስብሰባዎቹን በኃላፊነት መርቻለሁ። ይህ ዓይነቱ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ አዲስ ስለነበር እምብዛም መመሪያዎች አልነበሩትም። በመሆኑም እኔና ወንድም ኢነሮት አንድ ላይ ቁጭ ብለን ስብሰባዎችን በተሻለ መንገድ ማካሄድ የምንችልበትን ፕሮግራም አወጣን። የተቀበልኩት ኃላፊነት በጣም አስጨንቆኝ ስለነበር ይሖዋ እንዲረዳኝ በተደጋጋሚ ጊዜያት በጸሎት ተማጽኜዋለሁ። በዚህ የአውራጃ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ለ15 ዓመታት የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።
በእነዚያ ዓመታት ተስማሚ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ብዙ ጊዜ በደንብ የማያሞቁ አንዳንዴ ደግሞ ያረጁ የዳንስ አዳራሾችንና ሌሎች ተመሳሳይ ቦታዎችን መጠቀም ነበረብን። በሮኪዮ፣ ፊንላንድ ተደርጎ የነበረው ስብሰባ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። አዳራሹ ለበርካታ ጊዜያት አስታዋሽ አጥቶ የነበረ የቆየ የሕዝብ ማዕከል ነበር። አመዳይ በረዶ የቀላቀለ ኃይለኛ ነፋስ ስለነበረ ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች 20 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነበር። አዳራሹ ውስጥ በነበሩ ከዘይት በርሜል በተሠሩ ሁለት ትላልቅ ምድጃዎች ላይ እሳት አቀጣጠልን። ይሁን እንጂ የአዳራሹ ጭስ ማውጫ ወፎች በሠሩት ጎጆ ተደፍኖ ስለነበር ቤቱ ጭስ በጭስ ሆነ! ሆኖም ማንም ከተቀመጠበት አልተነሳም። በካፖርታችን የተሸፈንን ሲሆን ዓይኖቻችን ያለቅሱ ነበር። ይህ ሁኔታ ስብሰባውን ልዩ ትዝታ እንዲኖረው አድርጎታል።
እነዚህን የሦስት ቀን የወረዳ ስብሰባዎች ለማደራጀት ከተሰጡን መመሪያዎች መካከል ለተሰብሳቢዎቹ ምግብ ማዘጋጀት ይገኝበት ነበር። መጀመሪያ ላይ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ቁሳቁስም ሆነ ልምዱ አልነበረንም። ሆኖም ይህን ከባድ ኃላፊነት በደስታ የተቀበሉ እጅግ በጣም ጥሩ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ነበሩን። በስብሰባው ዋዜማ በቦታው ብትገኙ ኖሮ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ተሞክሮ እየተጫወቱ አጎንብሰው ደስ እያላቸው
ድንች ሲልጡ መመልከት ትችሉ ነበር። በዚያ ወቅት አብረው በትጋት የሠሩ በርካታ ወንድሞችና እህቶች አሁንም ድረስ የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው።የወረዳ ስብሰባዎችን የሚያስተዋውቁ ሰሌዳዎች ይዘን መዘዋወር ሌላው የሥራችን ክፍል ነበር። በከተማዎች ወይም በመንደሮች ውስጥ በሰልፍ ሆነን በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች በሕዝብ ንግግሩ ላይ እንዲገኙ እንጋብዝ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ሕዝቡ ደግነት ያሳየን የነበረ ከመሆኑም በላይ ለእኛ አክብሮት ነበረው። በአንድ ወቅት ፊንስፖንግ በምትባል ከተማ ውስጥ ስንዘዋወር መንገዱ ከአንድ ፋብሪካ በሚወጡ ሠራተኞች ተጥለቅልቆ ነበር። በድንገት ከመካከላቸው አንዱ ወደ እኛ እያመለከተ:- “ሂትለር ሊያሸንፋቸው ያልቻላቸውን እነዚህን ሰዎች ታያላችሁ!” በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ።
በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው አጋጣሚ
ካሪን ከምትባል አንዲት ደስ የምትል ወጣት ጋር ከተዋወቅኩ በኋላ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ያሳለፍኩት ሕይወት ብዙም ሳይቆይ ተቀየረ። ሁለታችንም ሐምሌ 1953 ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ በያንኪ ስታዲየም በሚደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ተጋበዝን። ሰኞ፣ ሐምሌ 20 በእረፍት ሰዓት ላይ ሚልተን ሄንሼል የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን ፈጸመልን። በዚህ ታዋቂ የስፖርት ስታዲየም ውስጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ መፈጸም ያልተለመደ ነበር። እኔና ካሪን እስከ 1962 ድረስ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አብረን ካገለገልን በኋላ የስዊድን ቤቴል ቤተሰብ አባል እንድንሆን ተጋበዝን። በመጀመሪያ በመጽሔት ክፍል ውስጥ የሠራሁ ሲሆን ከዚያ በኋላ የመካኒክነት ልምድ ስለነበረኝ በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ያሉትን የማተሚያ መሣሪያዎችንና ሌሎች ማሽኖችን እንድከታተል ተመደብኩ። ካሪን የልብስ ንጽሕና ክፍል ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ሠርታለች። ከብዙ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በትርጉም ክፍል ውስጥ እያገለገለች ነው።
ትዳር ከመሠረትን በኋላ ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍናቸው ከ54 የሚበልጡ ዓመታት በብዙ ገጠመኞች የተሞሉ፣ ትርጉም ያላቸውና አስደሳች ነበሩ! ይሖዋ በድርጅቱ ውስጥ የሚያገለግሉ አፍቃሪና ትጉ አገልጋዮቹን በእውነት ባርኳቸዋል። በ1940 በቅርንጫፍ ቢሮ ማገልገል በጀመርንበት ወቅት በስዊድን 1,500 የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ የነበሩ ሲሆን አሁን ግን ከ22,000 በላይ ሆነናል። በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች እድገቱ ከፍተኛ በመሆኑ ዛሬ በመላው ምድር ላይ ከስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ።
ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ሥራችንን እየደገፈው በመሆኑ ወደ አዲሱ ዓለም የሚያደርሰን ምሳሌያዊ መርከብ በተሳፋሪዎች እየሞላ ነው። በሚናወጠው የሰው ዘር ባሕር ላይ ሆነን በእምነት ዓይን ስንመለከት ምንም ስጋት አያድርብንም። መርከባችን ላይ ሆነን አሻግረን ስንመለከት አምላክ የሚያመጣው አዲስ ዓለም ወለል ብሎ ይታየናል። እኔም ሆንኩ ካሪን አምላክ ላሳየን ጥሩነት ሁሉ እናመሰግነዋለን። በተጨማሪም ጽኑ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖርና የመጨረሻ ግባችን ላይ ለመድረስ የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጠን ዘወትር እንጸልያለን፤ ዋነኛው ግባችን የአምላክን ሞገስና የዘላለም ሕይወት ማግኘት ነው!—ማቴዎስ 24:13
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እናቴ አቅፋኝ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1920ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ከአባቴ ጋር ለናሙና በተሠራች መርከብ የተጓዝንበት ቦታ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1946 በጊልያድ ትምህርት ቤት ከኸርመን ሄንሼል (ከሄንሼል አባት) ጋር
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐምሌ 20, 1953 በያንኪ ስታዲየም ተጋባን