በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘አፈጣጠራችን ድንቅ’ ነው

‘አፈጣጠራችን ድንቅ’ ነው

‘አፈጣጠራችን ድንቅ’ ነው

“ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ።”—መዝሙር 139:14

1. አስተዋይ የሆኑ ብዙ ሰዎች በምድር ላይ ያሉትን አስደናቂ ፍጥረታት የፈጠረው አምላክ ነው ብለው እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

 ዓለማችን አስደናቂ በሆኑ ፍጥረታት የተሞላ ነው። እነዚህ ፍጥረታት ወደ ሕልውና የመጡት እንዴት ነው? አንዳንዶች ጠቢብ ስለሆነ ፈጣሪ ሳይጠቅሱ ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት ይቻላል ብለው ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ ፈጣሪን ከግምት ውስጥ አለማስገባት ተፈጥሮን የመረዳት ችሎታችንን ይገድብብናል የሚል እምነት አላቸው። እነዚህ ሰዎች የምድር ፍጥረታት እጅግ ውስብስብ፣ በጣም የተለያዩና ድንቅ ከመሆናቸው የተነሳ እንዲያው ባጋጣሚ ሊገኙ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። እነዚህ ማስረጃዎች አንዳንድ ሳይንቲስቶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች አጽናፈ ዓለም ጠቢብ፣ ኃያልና አሳቢ የሆነ ሠሪ አለው ብለው እንዲያምኑ አድርገዋቸዋል። a

2. ዳዊት ይሖዋን እንዲያወድስ ያነሳሳው ምንድን ነው?

2 የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ፈጣሪ ድንቅ ለሆኑት ፍጥረታቱ ውዳሴ ሊቸረው ይገባል የሚል እምነት ነበረው። ዳዊት የኖረው ሳይንስ እንደ አሁኑ በተራቀቀበት ጊዜ ባይሆንም በዙሪያው ያሉት አስደናቂ ነገሮች የአምላክ የፍጥረት ሥራዎች መሆናቸውን ተረድቶ ነበር። ዳዊት የአምላክን የመፍጠር ችሎታ ለማድነቅ የገዛ አካሉን አሠራር መመልከቱ ብቻ በቂው ነበር። በመሆኑም “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች” ሲል ጽፏል።—መዝሙር 139:14

3, 4. እያንዳንዳችን ስለ ይሖዋ ሥራዎች በቁም ነገር ማሰባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ዳዊት እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት ሊኖረው የቻለው በጉዳዩ ላይ በቁም ነገር ስላሰበ ነው። በዛሬው ጊዜ ትምህርት ቤቶችና መገናኛ ብዙሃን ስለ ሰው ዘር አመጣጥ እምነት የሚሸረሽር ንድፈ ሐሳብ ያስተምራሉ። እኛም የዳዊት ዓይነት እምነት እንዲኖረን ከፈለግን በጉዳዩ ላይ በቁም ነገር ማሰብ ይኖርብናል። በተለይ ፈጣሪ መኖሩንና ከፍጥረት ጋር በተያያዘ የተጫወተውን ሚና በመሳሰሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የሌሎች አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን መፍቀድ አደጋ አለው።

4 ከዚህም በላይ በይሖዋ ሥራዎች ላይ ማሰላሰላችን ለእርሱ ያለን ፍቅርና አድናቆት እንዲጨምር እንዲሁም በሰጠን ተስፋዎች ላይ እንድንተማመን ያደርገናል። ይህ ደግሞ ይሖዋን የበለጠ እንድናውቀውና እንድናገለግለው ያነሳሳናል። በመሆኑም ዘመናዊው ሳይንስ ዳዊት ‘አፈጣጠራችን ድንቅ’ ስለመሆኑ የተናገረው ሐሳብ ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ድንቅ የሆነው የአካላችን እድገት

5, 6. (ሀ) የሁላችንም ሕይወት የጀመረው እንዴት ነው? (ለ) ኩላሊታችን ምን ሚና ይጫወታል?

5 “አቤቱ፣ አንተ ኵላሊቴን ፈጥረሃልና፣ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል።” (መዝሙር 139:13 የ1954 ትርጉም) ሁላችንም በእናታችን ማሕፀን ውስጥ ማደግ የጀመርነው ከአንዲት ትንሽ ነጥብ ከሚያንስ ነጠላ ሴል ተነስተን ነው። በአጉሊ መነጽር ብቻ የሚታየው ይህ ሴል በጣም ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ ትንሽ ፋብሪካ ነው ሊባል ይችላል። ሴሉ ፈጣን እድገት ያደርጋል። በማሕፀን ውስጥ ሁለት ወር ሲሞላህ ዋና ዋና የአካል ክፍሎችህ ተሠርተው ይጠናቀቃሉ። ከእነዚህ መካከል ኩላሊቶችህ ይገኙበታል። በምትወለድበት ጊዜ ኩላሊቶችህ ቆሻሻና አላስፈላጊ ውኃ በማስወገድ እንዲሁም ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን በማስቀረት ደምህን ለማጣራት ዝግጁ ይሆናሉ። የአንድ አዋቂ ሰው ኩላሊቶች ጤናማ ከሆኑ በደም ውስጥ ከሚገኘው ውኃ አምስት ሊትር ያህሉን በየ45 ደቂቃው ያጣራሉ!

6 በተጨማሪም ኩላሊቶችህ በደም ውስጥ ያለውን የማዕድን ይዘትና የአሲድ መጠን እንዲሁም የደምህን ግፊት ለመቆጣጠር ይረዳሉ። ኩላሊቶችህ ሌሎች አስፈላጊ ሥራዎችንም ያከናውናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ቫይታሚን ዲ ለአጥንት እድገት አስፈላጊ ወደሆነ እንዲሁም ኤሪትሮፖዬቲን የተባለውን ሆርሞን ለማመንጨት ወደሚረዳ ንጥረ ነገር እንዲቀየር ያደርጉታል። ይህ ሆርሞን በአጥንታችን ውስጥ ቀይ የደም ሴሎች የሚመረቱበትን ሂደት ያፋጥናል። ሰዎች ኩላሊት በሚያከናውነው ሥራ በጣም መደነቃቸው አያስገርምም! b

7, 8. (ሀ) አንድ ጽንስ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የሚኖረውን እድገት ግለጽ። (ለ) በማሕፀን ውስጥ በማደግ ላይ ያለ ጽንስ ‘በምድር ጥልቀት ውስጥ በጥበብ እንደተሠራ’ ተደርጎ የተገለጸው ለምንድን ነው?

7 “እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣ ዐጥንቶቼ ከአንተ አልተደበቁም፤ በምድር ጥልቀት ውስጥ በጥበብ በተሠራሁ ጊዜ።” (መዝሙር 139:15) የመጀመሪያው ሴል ለሁለት ከተከፈለ በኋላ አዳዲሶቹ ክፋዮችም እንዲሁ መከፈላቸውን ይቀጥላሉ። ብዙም ሳይቆይ ሴሎቹ የነርቭ ሴል፣ የጡንቻ ሴል፣ የቆዳ ሴልና ወዘተ በመሆን መከፋፈል ይጀምራሉ። ተመሳሳይ የሆኑት ሴሎች በአንድ ላይ ተሰባስበው በመጀመሪያ ሕብረ ህዋስ፣ ከዚያም አንድ የአካል ክፍል ይሠራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በተጸነስክ በሦስተኛው ሳምንት አጥንቶችህ መዋቀር ይጀምራሉ። ሰባት ሳምንት ሲሞላህ ማለትም 2.5 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ብቻ እያለህ፣ ሙሉ ሰው በምትሆንበት ጊዜ የሚኖሩህ 206 አጥንቶች፣ ገና ያልጠኑ ቢሆኑም እንኳ ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ።

8 በእናትህ ማሕፀን ውስጥ የሚከናወነው እንዲህ ያለው አስደናቂ እድገት ከሰው እይታ የተሰወረ ስለሆነ በምድር ጥልቅ ውስጥ የተቀበረ ያህል ነው። በእርግጥም የሰው ልጅ ስለ አካላችን እድገት ብዙ የማያውቀው ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ በሴልህ ውስጥ ያሉት ጂኖች፣ ሴሎቹ የተለያዩ የአካል ክፍሎችን ለመሥራት እንዲከፋፈሉ ያዟቸዋል፤ ሆኖም ጂኖቹ እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? ሳይንስ ውሎ አድሮ መልሱን ሊደርስበት ይችል ይሆናል። ሆኖም ዳዊት ቀጥሎ እንደተናገረው ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ የማያውቀው ነገር የለም።

9, 10. የአንድ ጽንስ እድገት በአምላክ ‘መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቧል’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

9 “ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣ ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣ በመጽሐፍ [“በመጽሐፍህ፣” የ1954 ትርጉም] ተመዘገቡ።” (መዝሙር 139:16) የመጀመሪያው ሴል የመላው አካልህን የተሟላ ንድፍ ይዟል። ይህ ንድፍ በማሕፀን ውስጥ የምትቆይበትን ዘጠኝ ወር ጨምሮ ሙሉ ሰው እስክትሆን ድረስ ባሉት ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት የሚኖርህን እድገት ይቆጣጠራል። በእነዚህ ጊዜያት አካልህ የተለያዩ የእድገት ደረጃዎችን ያልፋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው በዚያች አንዲት ሴል ውስጥ በተቀመጠው መረጃ መሠረት ነው።

10 ዳዊት ስለ ሴሎችም ሆነ ስለ ጂኖች የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ሌላው ቀርቶ አጉሊ መነጽር እንኳ አይቶ አያውቅም። ይሁንና የራሱ አካል የሚያድግበት መንገድ አስቀድሞ የተቀመጠ ንድፍ ለመኖሩ ማስረጃ እንደሆነ ተረድቷል። ዳዊት ስለ ጽንስ እድገት የተወሰነ እውቀት ይኖረው ይሆናል። ስለዚህም እያንዳንዱ የእድገት ደረጃ የሚከናወነው አስቀድሞ በወጣለት ንድፍና የጊዜ ቀመር መሠረት መሆኑን መረዳት ይችላል። ዳዊት ይህን ንድፍ በአምላክ ‘መጽሐፍ ላይ ተመዝግቧል’ በማለት ማራኪ በሆነ መንገድ ገልጾታል።

11. አካላዊ ገጽታችንን የሚወስነው ምንድን ነው?

11 በዛሬው ጊዜ፣ ከወላጆችህና ከቅድመ አያቶችህ የወረስካቸው ባሕርያት ማለትም ቁመትህ፣ የፊትህ ገጽታ፣ የዓይንህና የፀጉርህ ቀለም እንዲሁም ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ባሕርያት የሚወሰኑት በጂኖችህ እንደሆነ ታውቋል። በሰውነትህ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ሴል በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጂኖችን የያዘ ሲሆን እያንዳንዱ ጂን ደግሞ በዲ ኤን ኤ (ዲኦክሲራይቦኑክሊክ አሲድ) የተገነባ ረጅም ሰንሰለት ክፍል ነው። የአካልህ የግንባታ መመሪያ ‘የተመዘገበው’ በአንተ ዲ ኤን ኤ ኬሚካላዊ መዋቅር ውስጥ ነው። ሴሎችህ ሌሎች ሴሎችን ለመፍጠርም ሆነ ያረጁትን ለመተካት በሚከፈሉበት ጊዜ ዲ ኤን ኤ የያዘውን መረጃ ወደ አዳዲሶቹ ሴሎች ያስተላልፋል። በሕይወት መቆየትና ገጽታህ ሳይቀየር መኖር የቻልከው ለዚህ ነው። በሰማይ የሚኖረው ፈጣሪያችን ያለውን ኃይልና ጥበብ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!

አስደናቂ የሆነው አእምሯችን

12. ሰዎችን ከእንስሳት ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?

12 “አቤቱ፣ አሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደ ምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቊጥራቸውም እንደ ምን በዛ! ብቈጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ።” (መዝሙር 139:17, 18ሀ የ1954 ትርጉም) እንስሳትም ቢሆኑ ድንቅ ሆነው ተፈጥረዋል። እንዲያውም የተወሰኑ እንስሳት በአንዳንድ መንገዶች ከሰዎች የላቁ ችሎታዎች አሏቸው። ሆኖም አምላክ ለሰዎች ከማንኛውም እንስሳ በእጅጉ የሚልቅ የማሰብ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። አንድ የሳይንስ መጽሐፍ “እኛ ሰዎች ከሌሎች እንስሳት ጋር በብዙ መንገዶች የምንመሳሰል ብንሆንም በቋንቋና በማሰብ ችሎታችን በምድር ካሉ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ የተለየን ነን። በተጨማሪም ስለ ራሳችን ለማወቅ ባለን ከፍተኛ ጉጉት ከሌሎች እንለያለን። አካላችን የተገነባው እንዴት ነው? እንዴት ተሠራን? እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን እንጠይቃለን።” ዳዊትም በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ያሰላስል ነበር።

13. (ሀ) ዳዊት በአምላክ ሐሳቦች ላይ ለማሰላሰል የቻለው እንዴት ነው? (ለ) እኛስ የዳዊትን ምሳሌ እንዴት መኮረጅ እንችላለን?

13 ከሁሉም በላይ ከእንስሳት የተለየን የሚያደርገን በአምላክ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰል መቻላችን ነው። c ይህ ልዩ ስጦታ ‘በአምላክ መልክ’ መፈጠራችን የሚታይበት አንዱ መንገድ ነው። (ዘፍጥረት 1:27) ዳዊት ይህንን ስጦታ በሚገባ ተጠቅሞበታል። ዳዊት የአምላክን መኖር በሚያሳዩት ማስረጃዎችና በዙሪያው ባሉት ነገሮች ላይ በሚንጸባረቁት የአምላክ ግሩም ባሕርያት ላይ ያሰላስል ነበር። በተጨማሪም ዳዊት፣ አምላክ ስለ ራሱና ስለ ሥራዎቹ የተናገራቸውን ሐሳቦች የያዙት የቅዱሳን መጻሕፍት የመጀመሪያዎቹ ክፍሎች ነበሩት። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት እነዚህ መጻሕፍት የአምላክን ሐሳቦች፣ ባሕርያትና ዓላማ እንዲረዳ አስችለውታል። ዳዊት በቅዱሳን መጻሕፍት፣ በፍጥረት ሥራዎችና ከአምላክ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ማሰላሰሉ ፈጣሪውን እንዲያወድስ ገፋፍቶታል።

እምነት ምንን ይጨምራል?

14. በአምላክ ላይ እምነት እንዲኖረን ስለ እርሱ ሁሉን ማወቅ የማያስፈልገን ለምንድን ነው?

14 ዳዊት በፍጥረት ሥራዎችና በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ይበልጥ ባሰላሰለ መጠን የአምላክን እውቀትና ችሎታ ሙሉ በሙሉ መረዳት ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ተረድቷል። (መዝሙር 139:6) ሁኔታው ለእኛም ተመሳሳይ ነው። ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም። (መክብብ 3:11፤ 8:17) ሆኖም አምላክ በየትኛውም ዘመን የኖሩ እውነት ወዳድ ሰዎች፣ በማስረጃ ላይ የተደገፈ እምነት እንዲኖራቸው ለመርዳት በቅዱሳን መጻሕፍትና በፍጥረት ሥራዎች አማካኝነት በቂ እውቀት ‘ገልጧል።’—ሮሜ 1:19, 20፤ ዕብራውያን 11:1, 3

15. ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና ከእምነት ጋር ምን ግንኙነት እንዳለው በምሳሌ አስረዳ።

15 እምነት ሲባል ሕይወትና አጽናፈ ዓለም እጅግ ጠቢብ ከሆነ አካል የተገኙ መሆናቸውን አምኖ መቀበል ማለት ብቻ አይደለም። ይሖዋ አምላክ እንድናውቀውና ከእርሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንድንመሠርት የሚፈልግ እውን አካል መሆኑን በመገንዘብ በእርሱ መታመንን ይጠይቃል። (ያዕቆብ 4:8) አንድ ልጅ አፍቃሪ በሆነው አባቱ ላይ ያለውን የመተማመን ስሜት እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። አንድ ተጠራጣሪ ሰው አባትህ በችግር ጊዜ አይረዳህም ቢልህ አባትህ እምነት የሚጣልበት ሰው መሆኑን ለማሳመን ትቸገር ይሆናል። ይሁንና አባትህ አፍቃሪ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከተመለከትክ በችግር ጊዜ እንደማያሳፍርህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። በተመሳሳይም ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት፣ በአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ላይ በማሰላሰልና ለጸሎቶቻችን እንዴት መልስ እንደሰጠን በማሰብ ይሖዋን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ በእርሱ ለመታመን እንገፋፋለን። ይሖዋን ማወቃችን ስለ እርሱ የበለጠ እንድንማርና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር ለዘላለም እንድናወድሰው ይገፋፋናል። ይህ ደግሞ አንድ ሰው ከምንም በላይ ግብ ሊያደርገው የሚገባ ነገር ነው።—ኤፌሶን 5:1, 2

የፈጣሪያችንን መመሪያ ለማግኘት ጣር!

16. ዳዊት ከይሖዋ ጋር ከነበረው የጠበቀ ዝምድና ምን እንማራለን?

16 “እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ፤ የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።” (መዝሙር 139:23, 24) ዳዊት የሚያስበውን፣ የሚናገረውን ወይም የሚያደርገውን ሁሉ ይሖዋ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ተገንዝቦ ነበር። (መዝሙር 139:1-12፤ ዕብራውያን 4:13) አንድ ልጅ በሚወዱት ወላጆቹ እቅፍ ውስጥ ሲሆን እንደሚረጋጋ ሁሉ፣ ዳዊት ይሖዋ ስለ እርሱ አበጥሮ የሚያውቅ መሆኑን መገንዘቡ የደህንነት ስሜት እንዲሰማው አድርጎታል። ዳዊት ከይሖዋ ጋር ያለውን የጠበቀ ዝምድና ከፍ አድርጎ ይመለከት ስለነበር በአምላክ ሥራዎች ላይ በማሰላሰልና በመጸለይ ይህ ዝምድናው እንዳይበላሽ ለማድረግ ጥሯል። መዝሙር 139ን ጨምሮ አብዛኞቹ የዳዊት መዝሙሮች የጸሎት ይዘት ያላቸው መሆኑ ይህን የሚያሳይ ነው። እኛም የምናሰላስልና የምንጸልይ ከሆነ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን።

17. (ሀ) ዳዊት ይሖዋ ልቡን እንዲመረምርለት የፈለገው ለምንድን ነው? (ለ) የመምረጥ ነፃነታችንን የምንጠቀምበት መንገድ ሕይወታችንን የሚነካው እንዴት ነው?

17 በአምላክ መልክ ስለተፈጠርን የመምረጥ ነፃነት አለን። ጥሩ ወይም መጥፎ የሆነውን ለማድረግ መምረጥ እንችላለን። ይህ ነፃነት ደግሞ ተጠያቂነትን ያስከትላል። ዳዊት በክፉዎች ጎራ መፈረጅ አልፈለገም። (መዝሙር 139:19-22) እንዲያውም የኋላ ኋላ ሐዘን ሊያስከትሉ የሚችሉ ስህተቶችን ከመፈጸም መራቅ ፈልጓል። በመሆኑም ዳዊት ይሖዋ ሁሉን እንደሚያውቅ በማሰላሰል፣ ውስጣዊ ማንነቱን እንዲመረምርለትና ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ እንዲመራው በትሕትና ተማጽኗል። የአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ለሁሉም ሰው ስለሚሠሩ እኛም ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል። ይሖዋ ሁላችንንም እንድንታዘዘው ያሳስበናል። መታዘዛችን የእርሱን ሞገስና የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልናል። (ዮሐንስ 12:50፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:8) በየዕለቱ ከይሖዋ ጋር መሄዳችን በአሳዛኝ ሁኔታዎች ውስጥ ብንሆንም ውስጣዊ ሰላም እንድናገኝ ይረዳናል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ድንቅ የሆነውን ፈጣሪያችንን ተከተል!

18. ዳዊት በፍጥረት ሥራዎች ላይ ማሰላሰሉ ምን መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል?

18 ዳዊት ልጅ ሳለ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው በጎች በመጠበቅ ነበር። በጎቹ ሣር ለመጋጥ ሲያጎነብሱ፣ እርሱ ዓይኑን ወደ ሰማይ ያነሳ ነበር። ምሽት ላይ ደግሞ አጽናፈ ዓለም ምን ያህል እጹብ ድንቅ እንደሆነና ይህ ሁሉ ምን መልእክት እንደሚያስተላልፍ ያሰላስል ነበር። ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ። ቀን ለሌላው ቀን ይናገራል፤ ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀትን ይገልጣል።” (መዝሙር 19:1, 2) ዳዊት ሁሉን ነገር ውብ አድርጎ የሠራውን አካል ለማግኘት መጣርና እርሱን መከተል እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። እኛም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል።

19. ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ‘አፈጣጠራችን ድንቅ’ መሆኑን ማወቃቸው ምን ያስተምራቸዋል?

19 ዳዊት ልጁ ሰሎሞን እንደሚከተለው በማለት ለወጣቶች የሰጠውን ምክር በተግባር በማዋል ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው:- “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ። . . . እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።” (መክብብ 12:1, 13) ዳዊት ‘ድንቅ ሆኖ መፈጠሩን’ ያስተዋለው ገና በወጣትነቱ ነበር። ከዚህ እውቀቱ ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለሱም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቶለታል። ወጣቶችም ሆን አረጋውያን ታላቁን ፈጣሪያችንን ካወደስንና ካገለገልን የአሁኑም ሆነ የወደፊት ሕይወታችን በደስታ የተሞላ ይሆናል። ይሖዋን የሙጥኝ ብለው የሚኖሩና በጽድቅ መንገዶቹ የሚመላለሱ ሰዎች ስላላቸው ተስፋ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ፤ እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ። ‘እግዚአብሔር ትክክለኛ ነው . . .’ ይላሉ።” (መዝሙር 92:14, 15) አዎን፣ የፈጣሪያችንን ድንቅ ሥራዎች በመመልከት ለዘላለም የምንደሰትበት ጊዜ ከፊታችን ይጠብቀናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የሰኔ 22, 2004 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ተመልከት።

b በተጨማሪም በኅዳር 1998 የንቁ! እትም ላይ “ኩላሊት—ለሕይወትህ የግድ አስፈላጊ የሆነ ማጣሪያ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

c ዳዊት በመዝሙር 139:18ለ ላይ የተናገራቸው ቃላት ከጠዋት ጀምሮ ማታ እስኪተኛ ድረስ የይሖዋን ሐሳቦች ቢቆጥር፣ በማግስቱ ጠዋት ሲነቃም የሚቆጥረው እንደማያጣ የሚያሳዩ ይመስላል።

ልታብራራ ትችላለህ?

• አንድ ጽንስ የሚያድግበት መንገድ ‘አፈጣጠራችን ድንቅ’ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

• በይሖዋ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው?

• ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ከእምነት ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ምንጭ]

ሽል:- Lennart Nilsson

ዲ ኤን ኤ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማሕፀን ውስጥ ያለ ጽንስ አስቀድሞ የተወሰነለትን ንድፍ ተከትሎ እድገት ያደርጋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች አፍቃሪ በሆነ አባታቸው እንደሚተማመኑ ሁሉ እኛም በይሖዋ እንታመናለን

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት በይሖዋ የእጅ ሥራዎች ላይ ማሰላሰሉ እንዲያወድሰው ገፋፍቶታል