ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሰጠው ዘላለማዊ ስጦታ
ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሰጠው ዘላለማዊ ስጦታ
ሳይንቲስቶች በየትኛውም ፕላኔት ላይ ሕይወት እንዲኖር ከተፈለገ፣ መሟላት አለባቸው የሚሏቸው ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተጠቀሱ መሆናቸው አያስደንቅህም? እነዚህ መሟላት ያለባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
ሕይወት እንዲኖር በዘፍጥረት 1:2 ላይ እንደተገለጸው ውኃ በብዛት መኖር አለበት። የሙቀት መጠኑ በፕላኔቱ ላይ ያለው ውኃ ፈሳሽ ሆኖ እንዲቆይ የሚያስችል ሊሆን ይገባዋል። ይህ እንዲሆን ፕላኔቱ ከፀሐዩ ትክክለኛ ርቀት ላይ መገኘት ይኖርበታል። የዘፍጥረት ዘገባ ስለ ፀሐይም ሆነ በምድር ላይ ስለምታሳድረው ተጽዕኖ በተደጋጋሚ ይገልጻል።
አንድ ፕላኔት ለሰዎች መኖሪያነት ምቹ እንዲሆን፣ የተለያዩ ጋዞች በትክክለኛው መጠን የሚገኙበት ከባቢ አየር ያስፈልገዋል። ይህ ወሳኝ ገጽታ በዘፍጥረት 1:6-8 ላይ ተጠቅሷል። በዘፍጥረት 1:11, 12 ላይ የተገለጸው የተክሎች እድገት ከፍተኛ የኦክሲጅን አቅርቦት እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል። አንድ ፕላኔት የተለያዩ ዓይነት እንስሳት እንዲኖሩበት በዘፍጥረት 1:9-12 ላይ ተገልጾ እንደምናገኘው ደረቅና ለም የሆነ መሬት ሊኖረው ይገባል። በመጨረሻም ተስማሚ የአየር ንብረት እንዲኖር አንድ ፕላኔት በትክክለኛው ዲግሪ ጋደል ማለትና ያንን ሳይለቅ መቀጠል ይኖርበታል። ምድር ጋደል ባለችበት እንድትቀጥል በከፊል ምክንያት የሆነው የጨረቃ የስበት ኃይል ነው። የዚህች ሳተላይት መፈጠርና የምትሰጣቸው አንዳንድ ጥቅሞች በዘፍጥረት 1:14, 16 ላይ ተገልጿል።
በጥንት ዘመን የኖረው ጸሐፊ ሙሴ፣ በዘመናዊ ሳይንስ ሳይታገዝ ከላይ ስለተጠቀሱት ነገሮች መናገር የቻለው እንዴት ነው? ሙሴ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች የበለጠ የመረዳት ችሎታ ስለነበረው ነው? ይህን ማድረግ የቻለው የሰማይና የምድር ፈጣሪ ስለገለጠለት ነው። የዘፍጥረት ዘገባ ከሳይንስ አኳያ ትክክል መሆኑን ስንመለከት ይህ ትኩረት የሚስብ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በዙሪያችን ባለው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት አስደናቂ ነገሮች የተፈጠሩበት ዓላማ እንዳላቸው ያረጋግጥልናል። መዝሙር 115:16 “ሰማየ ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” በማለት ይናገራል። ሌላ መዝሙር ደግሞ “ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ አጸናሃት” ይላል። (መዝሙር 104:5) አጽናፈ ዓለምና ውቧ ፕላኔታችን የተሠሩት በፈጣሪ ከሆነ፣ ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግም ችሎታ አለው ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው። ይህም “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚለው ግሩም ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኛ መሆን ትችላለህ ማለት ነው። (መዝሙር 37:29) በእርግጥም አምላክ ‘ምድርን የፈጠራት ባዶ እንድትሆን’ ሳይሆን አድናቂ የሆኑ ሰዎች ለዘላለም ‘እንዲኖሩባት’ ነው።—ኢሳይያስ 45:18
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ስለ አምላክና አምላክ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ስላለው ዓላማ ሊያስተምረን መሆኑን ይናገራል። (ዮሐንስ 3:16) አምላክ በቅርቡ ‘ምድርን የሚያጠፉትን እንደሚያጠፋቸውና’ ለመዳን ያደረገውን ዝግጅት የሚቀበሉ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰላም ወዳድ ሰዎችን ግን እንደሚያድናቸው ዋስትና ተሰጥቶናል። (ራእይ 7:9, 14፤ 11:18) የሰው ልጆች የአምላክን ድንቅ ፍጥረታት ለዘላለም በመመርመር ሲደሰቱ ሕይወት እንዴት ጣፋጭ ይሆናል!—መክብብ 3:11፤ ሮሜ 8:21
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
NASA photo