በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

መጽሐፍ ቅዱስ ለመልካም ምኞት መግለጫ ተብሎ ጽዋን ስለማንሳት የሚናገረው ነገር የለም። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ባለው ልማድ የማይካፈሉት ለምንድን ነው?

በወይን ወይም በሌላ የአልኮል መጠጥ የተሞላን ብርጭቆ ወደ ላይ በማንሳት መልካም ምኞትን የመግለጽ ልማድ የሚከናወንበት መንገድ ከቦታ ቦታ ሊለያይ ቢችልም ረጅም ዘመናት ያስቆጠረና በስፋት የሚታወቅ ነው ይህን ልማድ የሚፈጽሙ ሰዎች አንዳንዴ ብርጭቆዎቻቸውን ያጋጫሉ። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ እንዲደረግ የሚጋብዘው ግለሰብ ብርጭቆውን ቀድሞ በማንሳት አንድ ሰው ደስታ፣ ጤና፣ ረጅም ዕድሜና የመሳሰሉትን ነገሮች እንዲያገኝ ያለውን መልካም ምኞት ይገልጻል። በሥርዓቱ የሚካፈሉት ሰዎችም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መስማማታቸውን ሊገልጹ አሊያም ብርጭቆዎቻቸውን ወደ ላይ ካነሱ በኋላ ከወይኑ ሊጎነጩ ይችላሉ። ብዙዎች፣ ይህን ልማድ ምንም ጉዳት እንደሌለው ወይም የጨዋነት ምልክት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ይሆናል። የይሖዋ ምሥክሮች ግን በዚህ ዓይነቱ ሥርዓት የማይካፈሉበት በቂ ምክንያት አላቸው።

ክርስቲያኖች ይህን የማያደርጉት አንድ ሰው ደስተኛ እንዲሆን ወይም ጥሩ ጤንነት እንዲኖረው ስለማይመኙ አይደለም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል ለጉባኤዎች የጻፈውን ደብዳቤ የደመደመበት ቃል “ደኅና ሁኑ”፣ “ጤና ይስጣችሁ” ወይም “ደህና ሰንብቱ” የሚል ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 15:29) በተጨማሪም አንዳንድ እውነተኛ አምላኪዎች ለሰብዓዊ ነገሥታት “ጌታዬ . . . ለዘላለም ይኑር” ወይም “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር” ያሉበት ጊዜ ነበር።—1 ነገሥት 1:31፤ ነህምያ 2:3

ታዲያ ጽዋን በማንሳት መልካም ምኞት የመግለጽ ልማድ የመጣው ከየት ነው? የጥር 1, 1968 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ፣ ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (1910) ጥራዝ 13 ገጽ 121ን በመጥቀስ የሚከተለውን አስፍሮ ነበር:- “‘ለጤናችን’ ብሎ የመጠጣት ልማድ የመጣው የጥንት ሃይማኖቶች ለጣዖታትና ለሙታን በመጠጣት ከሚያከናውኑት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ሳይሆን አይቀርም። ግሪካውያንም ሆኑ ሮማውያን ገበታ ላይ በሚቀርቡበት ወቅት ለጣዖቶቻቸው መጠጥን በመሥዋዕትነት የማፍሰስ፣ እንዲሁም በክብረ በዓሎቻቸው ላይ ለአማልክቶቻቸውና በሞት ለተለዩአቸው ሰዎች ጽዋን የማንሳት ልማድ ነበራቸው።” ኢንሳይክሎፒዲያው አክሎም “በሕይወት ላሉ ሰዎች ጤንነት እንዲኖራቸው በመመኘት የመጠጣት ልማድ እንዲህ ከመሰሉት የመጠጥ መሥዋዕቶች ጋር በተያያዘ ሲሠራበት የቆየ መሆን አለበት” ብሏል።

በአሁኑ ጊዜስ ይህ ሥርዓት የሚከናወነው ለዚሁ ዓላማ ነው? በ1995 የተዘጋጀው ኢንተርናሽናል ሃንድ ቡክ ኦን አልኮሆል ኤንድ ካልቸር የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በአሁኑ ጊዜ [ዋንጫን ማንሣት] ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የሚሠራበት ባይሆንም ለአማልክት እንደ ደምና ወይን የመሰሉ ቅዱስ ፈሳሾች ይቀርቡበት ከነበረው ጥንታዊ የመጠጥ መሥዋዕት የማቅረብ ልማድ ጋር የተቆራኘ ሊሆን ይችላል። የመጠጥ መሥዋዕቱ የሚቀርበው መልካም ምኞትን ለመግለጽ ሲሆን ‘ረጅም ዕድሜ ለእገሌ!’ አሊያም ‘ለጤንነትህ!’ የሚል አጭር ጸሎት ይቀርብ ነበር።”

አንድ ዕቃ ወይም ንድፍ አሊያም አንድ ልማድ የመጣው ከጥንት የሐሰት ሃይማኖት መሆኑ ብቻ እውነተኛ አምላኪዎች በዕቃው ላለመጠቀም ወይም በልማዱ ላለመካፈል ሁልጊዜ ምክንያት ይሆናቸዋል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ የሮማንን ፍሬ እንውሰድ። አንድ ታዋቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፒዲያ “የሮማን ፍሬ በአረማውያን ሃይማኖት ውስጥ ቅዱስ ምልክት ሆኖ ያገለግል የነበረ ይመስላል” በማለት ተናግሯል። ያም ሆኖ አምላክ በሊቀ ካህናቱ መጎናጸፊያ ዘርፍና በሰሎሞን ቤተ መቅደስ የነሐስ አምዶች ዙሪያ የሮማን ፍሬ ቅርጽ እንዲደረግ አዝዞ ነበር። (ዘፀአት 28:33፤ 2 ነገሥት 25:17) ከዚህም በላይ የጋብቻ ቀለበት በአንድ ወቅት ሃይማኖታዊ አንድምታ ነበረው። ይሁንና በዘመናችን ያሉ ብዙ ሰዎች ይህን አያውቁም። እንዲያውም የጋብቻን ቀለበት የሚመለከቱት አንድ ሰው ያገባ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ ብቻ አድርገው ነው።

ወይንን ከሃይማኖታዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ ስለመጠቀምስ ምን ለማለት ይቻላል? ለአብነት ያህል፣ በሴኬም ይኖሩ የነበሩት የበኣል አምላኪዎች በአንድ ወቅት “በአምላካቸው ቤት የደስታ በዓል አደረጉ፤ በዚያም እየበሉና እየጠጡ [የጌዴዎንን ልጅ] አቤሜሌክን ሰደቡ [“ረገሙ፣” NW]።” (መሳፍንት 9:22-28) ለይሖዋ ታማኝ የሆነ አንድ ሰው፣ የሐሰት አማልክቶቻቸው ክፉ እንዲያደርሱበት በመማጸን አቤሜሌክን ሲራገሙ የነበሩት ሰዎች ባዘጋጁት የመጠጥ ግብዣ ላይ የሚገኝ ይመስልሃል? አሞጽ ብዙ እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ ባመጹ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በየመሠዊያው ሥር ይተኛሉ፤ በአምላካቸው ቤት፣ በመቀጫነት የተወሰደውን የወይን ጠጅ ይጠጣሉ።” (አሞጽ 2:8) ወይኑ የቀረበው፣ ለጣኦታት የመጠጥ መሥዋዕት እንዲሆንም ይሁን በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲሁ እንዲጠጣ፣ እውነተኛ አምላኪዎች በዚህ ድርጊት ተካፋይ ይሆኑ ነበር? (ኤርምያስ 7:18) ወይም ደግሞ አንድ እውነተኛ አምላኪ የወይኑን ጽዋ ወደ ላይ በማንሳት አንዳች መለኮታዊ ኃይል በአንድ ሰው የወደፊት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር አሊያም በረከት እንዲያስገኝለት የሚጠይቅ ይመስልሃል?

የሚገርመው፣ የይሖዋ አምላኪዎች እጃቸውን ወደ ላይ ዘርግተው መልካም ነገር ለማግኘት የጠየቁባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሁንና እጃቸውን ወደ ላይ የዘረጉት ወደ እውነተኛው አምላክ ነው። “[ሰሎሞን] በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] መሠዊያ ፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ፣ እንዲህ አለ፤ ‘የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ . . . እንዳንተ ያለ አምላክ ከቶ የለም፤ . . . መኖሪያህ በሆነው በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።’” (1 ነገሥት 8:22, 23, 30) በተመሳሳይም “ዕዝራ . . . እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] አመሰገነ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን በማንሣት፣ ‘አሜን! አሜን!’ ብለው መለሱ፤ ከዚህ በኋላ በግምባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ፣” NW] ሰገዱ” የሚል እናነብባለን። (ነህምያ 8:6፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:8) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ እነዚህ ታማኝ ሰዎች እጃቸውን ወደ ሰማይ የዘረጉት ከዕድል አምላክ በረከት ለማግኘት ፈልገው አይደለም።—ኢሳይያስ 65:11

በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ጽዋቸውን ወደ ላይ በማንሳት መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸው፣ አንድ ጣዖት ምላሽ እንዲሰጣቸው አሊያም እንዲባርካቸው መጠየቃቸው እንደሆነ አድርገው ላያስቡ ይችላሉ። ሆኖም በወይን የተሞላውን ብርጭቋቸውን ወደ ሰማይ የሚያነሱበትን ምክንያት ማስረዳት አይችሉም። እነዚህ ሰዎች ድርጊቱን የሚፈጽሙት በደንብ አስበውበት አለመሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች የእነርሱን ልማድ የመኮረጅ ግዴታ እንዳለባቸው ሆኖ እንዲሰማቸው አያደርግም።

የይሖዋ ምሥክሮች በሌሎች ጉዳዮች ረገድም ቢሆን ብዙዎች የሚጠቀሙባቸውን አካላዊ መግለጫዎች እንደማያሳዩ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ሰዎች ለብሔራዊ አርማ ወይም ለባንዲራ ያላቸውን አክብሮት ለመግለጽ የተለያዩ አካላዊ መግለጫዎች ይጠቀማሉ፤ ይህ ድርጊት አምልኮ እንደሆነ አይሰማቸውም። እውነተኛ ክርስቲያኖች የሌሎችን መብት የማይጋፉ ቢሆኑም እነርሱ ግን በእንዲህ መሰሉ ድርጊት አይካፈሉም። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎችን ላለማስከፋት ሲሉ እንዲህ ዓይነቶቹ ሥርዓቶች በሚካሄዱበት ጊዜ በቦታው ባለመገኘት ጥበብ ያለበት እርምጃ ወስደዋል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያዘው ጋር በመስማማት ብሔራዊ ስሜትን የሚያንጸባርቁ አካላዊ መግለጫዎችን ላለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። (ዘፀአት 20:4, 5፤ 1 ዮሐንስ 5:21) በዛሬው ጊዜ ብዙዎች፣ ጽዋን የማንሳትን ልማድ ከእምነት ጋር ላያያይዙት ይችላሉ። ያም ቢሆን ግን ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ ምንጭ ባለውና በአሁኑ ጊዜም ከሰው በላይ ከሆነ ኃይል እርዳታ ይፈልጉ ይመስል ‘ከሰማይ’ በረከትን እንደመጠየቅ ተደርጎ በሚታየው በዚህ ልማድ የማይካፈሉበት በቂ ምክንያት አላቸው።—ዘፀአት 23:2