ልጆቻችሁ መልስ በመስጠት እንዲሳተፉ አስተምሯቸው
ልጆቻችሁ መልስ በመስጠት እንዲሳተፉ አስተምሯቸው
በሜክሲኮ የምትኖረው ፐርላ ትንሽ ልጅ ሳለች በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት አጫጭር መልሶችን መስጠት እንድትችል እናቷ ታዘጋጃት እንደነበር ታስታውሳለች። በአሁኑ ጊዜ ፐርላ የአምስት ዓመት ወንድ ልጅ አላት። ታዲያ ልጇን የምትረዳው እንዴት ነው? “በመጀመሪያ እኔ ራሴ እዘጋጃለሁ። በምዘጋጅበት ጊዜ ልጄ ተረድቶት በራሱ አነጋገር ሊያብራራው የሚችለውን አንቀጽ እፈልጋለሁ። ከዚያም ልጄ ‘የእኔ አንቀጽ’ ብሎ በሚጠራው በዚህ አንቀጽ ላይ እናተኩራለን። በየዕለቱ ከሚያጋጥሙን ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ቀለል ያሉ ምሳሌዎችን ተጠቅሞ [ነጥቡን] እንዲያብራራልኝ እጠይቀዋለሁ። ከዚያም የሚሰጠውን መልስ ደጋግመን እንለማመደዋለን። [በጉባኤ] መልስ በሚሰጥበት ጊዜ የድምጽ ማጉያውን እንዴት መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ በልምምዳችን ወቅት የድምጽ ማጉያውን የሚያህል ዕቃ እንጠቀማለን። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ሳይመልስ ወይም እጁን ሳያወጣ ቀርቶ አያውቅም፤ ይህም በጣም ያስደስተኛል። ብዙውን ጊዜ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ትምህርቱን ወደሚመራው ወንድም ሄዶ የትኛውን አንቀጽ መመለስ እንደሚፈልግ ይነግረዋል።”
በሂንዲ ቋንቋ በሚመራ ቡድን ውስጥ የሚያገለግል የንስ የተባለ ሽማግሌ የሁለትና የአራት ዓመት ወንዶች ልጆች አሉት። እርሱና ባለቤቱ ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ለስብሰባዎች ሲዘጋጁ የንስ ከወላጆቹ የተማረውን ዘዴ ይጠቀማሉ። የንስ እንዲህ ይላል:- “ከትምህርቱ ውስጥ ልጆቹ ሊረዱት የሚችሉት የትኛውን እንደሆነ አስቀድመን እንወስናለን። ከዚያም አጠቃላይ ሐሳቡ ወይም ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች የትኞቹ እንደሆኑ ከነገርናቸው በኋላ በስብሰባዎች ላይ እንዲመልሷቸው ያሰብናቸውን ጥያቄዎች እንጠይቃቸዋለን። ብዙ ጊዜ በራሳቸው አባባል የሚመልሱትን መልስ ስንሰማ በጣም እንገረማለን። ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መንገድ በእርግጥ ምን እንደተረዱ ያሳያል። በመሆኑም በመልሶቻቸው አማካኝነት ይሖዋን ከማወደሳቸውም ሌላ እምነታቸውን በገዛ አንደበታቸው መግለጽ ይችላሉ።”