የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመከተል እርካታና ደስታ ማግኘት
የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመከተል እርካታና ደስታ ማግኘት
አንዲት ድመት ጥቅልል ብላ ተኝታ ስታንኮራፋ ተመልክተህ የቀናህበት ጊዜ የለም? ምን ያህል እርካታ እንደሚሰማት መገመት ትችላለህ! ሁልጊዜ እንደ እርሷ ረክቶ መኖር ቢቻል እንዴት ጥሩ ነበር! ሆኖም ብዙ ሰዎች እርካታም ሆነ ደስታ የራቃቸው ከመሆኑም ሌላ ምናልባት ቢያገኙት እንኳ ዘላቂ አይሆንላቸውም። ምክንያቱ ምን ይሆን?
ፍጽምና ስለሚጎድለን በተደጋጋሚ ጊዜ ስህተት የምንሠራ ከመሆኑም በላይ የሌሎችንም ድክመት መታገሥ ይኖርብናል። ከዚህም በተጨማሪ አሁን የምንገኘው መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስጨንቅ ጊዜ” እንደሚሆን በሚገልጸው “በመጨረሻው ዘመን” ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አብዛኞቻችን በልጅነት ጊዜያችን አስደሳች ትዝታዎችን አሳልፈን ይሆናል፤ አሁን ግን ይህ ‘አስጨናቂ ጊዜ’ የሚያሳድረውን ከፍተኛ ተጽዕኖ በገዛ ሕይወታችን እየተመለከትነው ነው። ታዲያ በዘመናችን እርካታና ደስታ ማግኘት ይቻል ይሆን?
ቅዱሳን ጽሑፎች በዚህ ዘመን መኖር የሚያስጨንቅ እንጂ የማይቻል ነው እንዳላሉ ልብ በል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ይህን አስጨናቂ ዘመን መቋቋም እንችላለን። ሁልጊዜ ችግሮቻችንን መፍታት እንችላለን ማለት ባይሆንም እንኳ በተወሰነ ደረጃ ደስታ ማግኘት እንችላለን። እስቲ ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል ሦስቱን እንመልከት።
ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት ይኑርህ
እርካታና ደስታ ማግኘት ከፈለግን ስለ ራሳችንም ሆነ ስለ ሌሎች ድክመት ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” በማለት እውነታውን አስቀምጧል። (ሮሜ 3:23) የይሖዋ ክብር የሚንጸባረቅባቸው ብዙ መንገዶች ከእኛ የመረዳት ችሎታ እጅግ የላቁ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በዘፍጥረት 1:31 ላይ የሚገኘውን ሐቅ እንውሰድ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ።” ይሖዋ ስላደረገው ነገር ሁሉ መለስ ብሎ ቢያስብ ሁልጊዜም “እጅግ መልካም ነበረ” ማለት ይችላል። በሌላ በኩል ግን ሁልጊዜ እንዲህ ሊሰማው የሚችል አንድም ሰው አይኖርም። ስለዚህ ደስታ ለማግኘት የሚረዳን የመጀመሪያው እርምጃ ድክመቶቻችንን አምነን መቀበል ነው። ሆኖም ሌላም ተጨማሪ ነገር ያስፈልገናል። ይሖዋ ስለ ድክመቶቻችን ያለውን አመለካከት ማወቅና የእርሱን አመለካከት መቀበል ይኖርብናል።
“ኃጢአት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ዒላማን መሳት” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የተገኘ ነው። በምሳሌ ለማስረዳት፣ ቀስት ወርውሮ አንድን ዒላማ በመምታት ሽልማት ለማግኘት የሚፈልግን አንድ ሰው በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ይህ ሰው ሦስት ጊዜ የመወርወር ዕድል ተሰጥቶታል። የመጀመሪያውን ቀስት ሲወረውር በአንድ ሜትር ያህል ዒላማውን ሳተ። በተሻለ ሁኔታ አልሞ ሁለተኛውን ቀስት ቢወረውርም ዒላማውን በ30 ሴንቲ ሜትር ሳተው። ሙሉ ትኩረቱን ዒላማው ላይ በማድረግ ለመጨረሻ ጊዜ ሲወረውር በ2 ሴንቲ ሜትር ብቻ ሳተ። ወደ ዒላማው በጣም ቢቃረብም ቦታው ላይ እስካልመታ ድረስ ስቷል።
እኛ ሁላችን፣ ያሰበው ነገር እንዳልተሳካለት እንደዚህ ቀስት ወርዋሪ ነን። አንዳንድ ጊዜ ‘ከዒላማችን’ በጣም እንርቅ ይሆናል። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ዒላማችንን ለመምታት እጅግ በጣም ብንቃረብም ለጥቂት እንስተዋለን። ባለ በሌለ አቅማችን ጥረት አድርገንም በቂ ውጤት ባለማግኘታችን እንበሳጫለን። አሁን ደግሞ እስቲ ወደ ቀስት ወርዋሪው እንመለስ።
ይህ ቀስት ወርዋሪ ሽልማቱን ለማግኘት ጓጉቶ ስለነበር በጣም አዝኖ ፊቱን አዙሮ መሄድ ጀመረ። በድንገት ሽልማቱን የሚያበረክተው ሰው ጠራውና “ስለወደድኩህ ይህን ልሰጥህ እፈልጋለሁ፤ ደግሞም ምን ያህል እንደለፋህ ተመልክቻለሁ” በማለት ሽልማት ሰጠው። በዚህ ጊዜ ቀስት ወርዋሪው ፍንድቅድቅ አለ!
ፍጹም ሆነው የዘላለም ሕይወት የማግኘት “ስጦታ” ከአምላክ የሚቀበሉ ሁሉ እንደዚህ ፍንድቅድቅ ማለታቸው አይቀርም። (ሮሜ 6:23) ከዚያን ጊዜ በኋላ የሚያደርጉት ነገር ሁሉ ፍጹም ስለሚሆን ዒላማን መሳት የሚባል ነገር አይኖርም። ሙሉ ለሙሉ ደስተኛ ይሆናሉ። እስከዚያው ድረስ ግን ይህን አስተሳሰብ መያዛችን ለራሳችንም ይሁን አብረውን ላሉ ሰዎች ጥሩ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል።
ሁሉም ነገር ጊዜ እንደሚወስድ ተገንዘብ
ሁሉ ነገር ጊዜ እንደሚወስድ የታወቀ ነው። ይሁንና አንድ የምትጓጓለት ነገር ከጠበቅኸው በላይ ሲዘገይብህ ወይም አንድ አሳዛኝ ነገር ካሰብከው በላይ ለረጅም ጊዜ ሲቀጥል ደስተኛ ሆኖ መኖር ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ሳትገነዘብ አልቀረህም። ያም ሆኖ ግን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያሉ እርካታና ደስታ ማግኘት የቻሉ ሰዎች አሉ። ኢየሱስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።
ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ታዛዥ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ነበር። ይህም ሆኖ ‘መታዘዝን የተማረው’ እዚህ ምድር እንደሆነ ተገልጿል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ምድር እያለ ‘የተቀበለው መከራ’ መታዘዝን አስተምሮታል። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የሰው ልጆች መከራ ሲደርስባቸው የተመለከተ ቢሆንም እሱ ግን በሕይወቱ መከራ ገጥሞት አያውቅም ነበር። ወደ ምድር ከመጣ በኋላ፣ በተለይ ደግሞ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀበት ጊዜ አንስቶ በጎልጎታ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። ኢየሱስ በመታዘዝ ረገድ ‘ፍጹም ሆኖ የተገኘው’ እንዴት እንደሆነ ዝርዝር ጉዳዮችን ባናውቅም እንኳ ይህን ለመማር ጊዜ እንደወሰደበት የታወቀ ነው።—ዕብራውያን 5:8, 9
ኢየሱስ፣ በታማኝነት ከቀጠለ ስለሚያገኘው ሽልማት ማለትም “በፊቱ ስላለው ደስታ” ማሰላሰሉ ስኬታማ እንዲሆን ረድቶታል። (ዕብራውያን 12:2) ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ጊዜ “ጸሎትንና ልመናን ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋር” ያቀርብ ነበር። (ዕብራውያን 5:7) እኛም ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ የጸለይንበት ጊዜ ይኖራል። ይሖዋ ይህንን የሚመለከተው እንዴት ነው? ይኸው ጥቅስ፣ ይሖዋ የኢየሱስን ‘ጸሎት እንደሰማ’ ይናገራል። አምላክ የእኛንም ጸሎት ቢሆን ይሰማል። ለምን?
ምክንያቱም ይሖዋ ድክመቶቻችንን ስለሚያውቅ ከጎናችን ሆኖ ይረዳናል። እያንዳንዱ ሰው ሊያሳየው የሚችለው ጽናት ገደብ አለው። ቤኒን በምትባል የአፍሪካ አገር የሚኖሩ ሰዎች “ውኃ ሲበዛ እንቁራሪት እንኳ ትሰምጣለች” ይላሉ። ይሖዋ ገደባችን ላይ ልንደርስ መቃረባችንን ከእኛ ይበልጥ ስለሚያውቅ ‘ምሕረትንና በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ’ ይሰጠናል። (ዕብራውያን 4:16) ለኢየሱስ ያደረገው ይህንኑ ሲሆን ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው ሰዎችም እንዲሁ አድርጓል። ሞኒካ የአምላክን እርዳታ ያገኘችው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ሞኒካ ተጫዋችና ብዙም የማትጨነቅ ደስተኛ ልጅ ነበረች። በ1968 ገና በሃያዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳለች መልቲፕል ስክለሮሲስ በተባለ አብዛኛውን ጊዜ የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎችን ሽባ በሚያደርግ በሽታ መያዟን ስታውቅ በጣም ደነገጠች። ይህም ሕይወቷን ሙሉ ለሙሉ የለወጠው ከመሆኑም ሌላ በሙሉ ጊዜ አገልግሎቷ ላይ ትልቅ ማስተካከያ እንድታደርግ አስገድዷታል። በሽታዋ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ መሆኑን ተገንዝባ ነበር። ከ16 ዓመታት በኋላ እንዲህ ብላለች:- “ለበሽታዬ እስከ አሁን ድረስ መድኃኒት አልተገኘለትም። ምናልባትም
አምላክ በሚያመጣው አዲስ ሥርዓት ሁሉ ነገር እስኪታደስ ድረስ በዚሁ ሊቀጥል ይችላል።” ሞኒካ ሁኔታው ቀላል እንዳልነበር ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “ወዳጆቼ ሁልጊዜ ፍልቅልቅ እንደሆንኩ ቢናገሩም . . . በጣም የምቀርባቸው ጓደኞቼ ግን አንዳንድ ጊዜ ስቅስቅ ብዬ እንደማለቅስ ያውቃሉ።”ያም ሆኖ ግን እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “ትዕግሥተኛ መሆን እንዳለብኝና በጤንነቴ ላይ በማየው መጠነኛ ለውጥም እንኳ መደሰት እንደሚገባኝ ተምሬያለሁ። የሰው ልጅ ከበሽታ ጋር በሚያደርገው ትግል ምን ያህል አቅመ ቢስ መሆኑን መመልከቴ ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና ይበልጥ እንዳጠናክር አድርጎኛል። ፍጹም ፈውስ ማምጣት የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።” ሞኒካ በይሖዋ እርዳታ እርካታና ደስታ ማግኘት በመቻሏ ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ችላለች።
እርግጥ ሞኒካ እንዳጋጠማት ዓይነት ያሉ ሁኔታዎች ቀላል አይደሉም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ነገሮች አንተ ከምትጠብቀው በላይ ጊዜ ሊወስዱ እንደሚችሉ ከተገነዘብክ ይበልጥ ደስተኛ ልትሆን እንደምትችል አትጠራጠር። እንደ ሞኒካ ሁሉ አንተም ይሖዋ ‘በሚያስፈልግህ ጊዜ እንደሚረዳህ’ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
ራስህን ከማንም ጋር ሳታወዳድር ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች አውጣ
ሁላችንም የተለያየን ሰዎች ነን። ልክ እንደ አንተ የሆነ ማንም ሰው የለም። ጋን በተባለ አንድ የአፍሪካውያን ቋንቋ “ሁሉም ጣቶቻችን እኩል አይደሉም” የሚል አባባል አለ። አንደኛውን ጣታችንን ከሌላው ጣታችን ጋር ማወዳደር ሞኝነት ነው። ይሖዋ ከማንም ጋር እንዲያወዳድርህ እንደማትፈልግ የታወቀ ነው፤ እርሱም ፈጽሞ አያደርገውም። ያም ሆኖ ግን በሰው ልጆች ዘንድ እርስ በርስ የመወዳደር መንፈስ እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን ይህ ደግሞ አንድ ሰው ደስታውን እንዲያጣ ሊያደርገው ይችላል። ኢየሱስ ይህንን ሁኔታ በማቴዎስ 20:1-16 ላይ እንዴት በምሳሌ እንዳስቀመጠው ልብ በል።
ኢየሱስ እየተናገረ ያለው በወይኑ የአትክልት ቦታ የቀን ሠራተኞችን ለመቅጠር ስለሚፈልግ አንድ “ባለቤት” ነበር። ሥራ አጥተው የተቀመጡ የተወሰኑ ሰዎችን አገኘና ‘በማለዳ’ ምናልባትም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ ቀጠራቸው። በወቅቱ ለቀን ሠራተኛ በሚከፈለው ደሞዝ መሠረት አሥራ ሁለት ሰዓት ከሠሩ በኋላ አንድ አንድ ዲናር እንዲከፍላቸው ተስማሙ። እነዚህ ሰዎች ሥራ ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን በተለመደው የቀን ደሞዝ መቀጠራቸው ጭምር አስደስቷቸው እንደነበር አያጠያይቅም። በኋላ ላይ ይህ ባለቤት በተለያየ ሰዓት ሲወጣ ሥራ ያጡ ሌሎች ሰዎችን አገኘ። አንዳንዶቹን 3 ሰዓት ላይ፣ ሌሎቹን 6 ሰዓት ላይ እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን 9 ሰዓት ላይ የቀጠረ ሲሆን ሌላው ቀርቶ 11 ሰዓት ላይ እንኳ የቀጠራቸው ነበሩ። ከመጀመሪያዎቹ የቀን ሠራተኞች በኋላ የተቀጠሩት ሁሉ የሙሉ ቀን ሥራ አልሠሩም። የወይኑ ባለቤት “ተገቢውን ክፍያ” እንደሚሰጣቸው የነገራቸው ሲሆን እነርሱም ተስማምተዋል።
በመሸ ጊዜ የወይኑ ባለቤት የሠራተኞቹን ተቆጣጣሪ ጠርቶ ደሞዛቸውን እንዲከፍል አዘዘው። ሠራተኞቹን ሁሉ ከጠራ በኋላ መጨረሻ ከመጡት ጀምሮ እንዲከፍላቸው ነገረው። መጨረሻ ላይ የተቀጠሩት ሰዎች የሠሩት ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የሚደንቀው ነገር የሙሉ ቀን ደሞዝ ተሰጣቸው። በዚህን ጊዜ ጉዳዩ ምን ያህል ሊያነጋግራቸው እንደሚችል መገመት እንችላለን። ሙሉ 12 ሰዓት የሠሩት ሰዎች ላቅ ያለ ክፍያ እንደሚቀበሉ ደምድመዋል። ያም ሆኖ ግን ለእነርሱም የተከፈለው እኩል ነበር።
በዚህ ጊዜ ምን ተሰማቸው? “ክፍያውን ሲቀበሉ በባለቤቱ ላይ በማጕረምረም፣ ‘እነዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩት አንድ ሰዓት ብቻ ሲሠሩ፣ ቀኑን ሙሉ በሥራ ስንደክምና በፀሐይ ስንንቃቃ ከዋልነው ጋር እንዴት እኩል ትከፍለናለህ?’ አሉት።”
ይሁን እንጂ የወይኑ አትክልት ባለቤት ሁኔታውን የተመለከተበት መንገድ ለየት ያለ ነው። የተቀበሉት ገንዘብ ከተስማሙበት ክፍያ ምንም እንዳልጎደለ ነገራቸው። ለሌሎቹ የሙሉ ቀን ደሞዝ ሊሰጣቸው ስለፈለገ ከጠበቁት በላይ እንደተቀበሉ እሙን ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ማናቸውም ቢሆኑ ከተስማሙበት ያነሰ ክፍያ አልተቀበሉም። እርግጥ ነው ብዙዎቹ ከጠበቁት በላይ አግኝተዋል። በመሆኑም መጨረሻ ላይ የወይኑ ባለቤት “ታዲያ በራሴ ገንዘብ የፈለግሁትን ማድረግ አልችልምን?” የሚል ጥያቄ ሰንዝሯል።
ተቆጣጣሪው መጀመሪያ ተቀጥረው ለነበሩት ሰዎች ከሁሉም በፊት ከፍሏቸው ቢሆንና እነርሱም ደሞዛቸውን ተቀብለው ወዲያው ቢሄዱ ኖሮ ሊከሰት የሚችለውን ሁኔታ እስቲ ገምት። ባገኙት ገቢ መደሰታቸው አይቀርም ነበር። ደስታቸውን ያጡት ሌሎች ለትንሽ ጊዜ ሠርተው ከእነርሱ ጋር እኩል እንደተከፈላቸው ስላዩ ብቻ ነው።
ይህም እንዲበሳጩና ይባስ ብሎም በወይን አትክልቱ ባለቤት ላይ እንዲያጉረመርሙ አደረጋቸው፤ መጀመሪያ ላይ ግን የወይኑ ባለቤት ስለቀጠራቸው በጣም ሳያመሰግኑት አልቀሩም።ይህ ምሳሌ ራሳችንን ከሌሎች ጋር በምናወዳድርበት ጊዜ የሚገጥመንን ሁኔታ በትክክል ይገልጻል። ከይሖዋ ጋር ባለህ ዝምድና ላይ ካሰላሰልክና የሰጠህን በረከት የምታደንቅ ከሆነ እርካታም ሆነ ደስታ ይኖርሃል። የራስህን ሁኔታ ሌሎች ካሉበት ሁኔታ ጋር አታወዳድር። ይሖዋ ለሌሎች ሰዎች የላቀ ነገር ሊያደርግላቸው ከወሰነ ከእነርሱ ጋር ደስ ይበልህ።
ሆኖም ይሖዋ ከአንተ የሚጠብቀው ነገር አለ። ምን ይሆን? ገላትያ 6:4 እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ . . . ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል።” በሌላ አባባል ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች አውጣ። ወደ ግብህ የሚያደርስህ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል እቅድ ይኑርህ፤ ከዚያም በእቅድህ መሠረት ተጓዝ። ያወጣኸው ግብ ልትደርስበት የምትችል ከሆነ፣ ግብህን ስትመታ ‘የምትመካበትን ታገኛለህ።’ በዚህ ጊዜ ደስታና እርካታ ይኖርሃል።
ሽልማት ተዘጋጅቶልሃል
ፍጹማን ካለመሆናችንም በላይ የምንኖረው በዚህ የመጨረሻ ዘመን ውስጥ ነው፤ ያም ቢሆን ግን ከላይ ያየናቸው ሦስት መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደሚያሳዩት እርካታና ደስታ ማግኘት እንችላለን። በየዕለቱ በምታደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ ላይ በግልጽ የተቀመጡ ወይም በታሪኮችና በምሳሌዎች ውስጥ በተዘዋዋሪ መንገድ የተገለጹ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት ለምን አትሞክርም?
ደስታህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠፋ እንደመጣ ከተሰማህ ትክክለኛውን መንስኤ ለማግኘት ጣር። ከዚያም ሁኔታህን ለማስተካከል የሚረዱህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት ቁፈራ አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው (2 ዜና መዋዕል—ኢሳይያስ) a የተባለውን ብሮሹር ገጽ 22, 23 መመልከት ትችላለህ። በዚህ ጽሑፍ ላይ የምሳሌ መጽሐፍ የተብራራ ሲሆን በ12 ንዑስ ርዕሶች የተከፋፈሉ ብዙ መሠረታዊ ሥርዓቶችንና ምክሮችን ይዟል። እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ* (እንግሊዝኛ) እና በሲዲ የሚገኘው ዎች ታወር ላይብረሪ* ግሩም ሐሳቦች ይዘዋል። በእነዚህ መሣሪያዎች በተደጋጋሚ ጊዜ መጠቀምህ ተግባራዊ ልታደርጋቸው የምትችላቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በቀላሉ ማግኘት እንድትለምድ ይረዳሃል።
ይሖዋ ለሚገባቸው ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት የሚሰጥበት ጊዜ በጣም ቅርብ ነው። በዚያን ጊዜ የሚኖሩ ሁሉ ሕይወታቸው በደስታ የተሞላ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል።”—ሮሜ 3:23
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ “ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ።”—ዕብራውያን 5:8, 9
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ከሌላ ሰው ጋር ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል።”—ገላትያ 6:4