መሲሕ ያስፈልገናል?
መሲሕ ያስፈልገናል?
“መሲሕ ያስፈልገናል?” የሚለውን ጥያቄ አንተም ታነሳ ይሆናል። መሲሑ በአንተ ላይ ተጽዕኖ ያሳድር እንደሆነ መጠየቅህ ምክንያታዊ ነው።
አንዳንድ የምታከብራቸው ሰዎች፣ እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ አንተም መሲሕ ያስፈልግሃል በማለት ለዚህ ጥያቄህ አጭርና ግልጽ መልስ ይሰጡህ ይሆናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በአይሁዶች ሕግ ሊቅ የሆነ አንድ ሰው መሲሑን አስመልክቶ “በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ ‘አዎን’ የሚሆኑት በእርሱ ነውና” ሲል ጽፏል። ይህ ሰው እንዲህ ብሎ ሲጽፍ ፈጣሪያችን የምድር አሕዛብን ሁሉ ለመባረክ ባለው ዓላማ ውስጥ መሲሑ የሚጫወተውን ሚና ጎላ አድርጎ መግለጹ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 1:20) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በመሲሑ መምጣትና በምድር በሚኖረው ሕይወት ላይ ያተኮረ መሆኑ መሲሑ የሚጫወተው ትልቅ ሚና እንዳለ ያሳያል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ሄንሪ ሃሌይ ባለፉት 70 ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተጠቀሙበት መጽሐፋቸው ላይ “ብሉይ ኪዳን የተጻፈው ሰዎች [የመሲሑን] መምጣት በጉጉት እንዲጠባበቁ ለማድረግና ለመሲሑ መንገድ ጠራጊ እንዲሆን ተብሎ ነው” በማለት ተናግረዋል። የእርሱ መምጣት ግን አስፈላጊ ነው? አንተንስ ሊያሳስብህ የሚገባው ለምንድን ነው?
“መሲሕ” የሚለው ቃል “የተቀባ” ማለት ሲሆን በጣም ታዋቂ የሆነው ተመሳሳይ ቃል “ክርስቶስ” የሚለው ነው። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ በ1970 እትሙ ላይ “ታላቁ አዳኝ” በማለት የጠራው ክርስቶስ ወደ ምድር መምጣት ያስፈለገው የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ጥንዶች በወሰዱት አክብሮት የጎደለው እርምጃ ምክንያት ነው። እነዚህ ባልና ሚስት ምንም እንኳ በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አስደሳች የወደፊት ተስፋ ከፊታቸው የተዘረጋላቸውና ፍጹም ሆነው የተፈጠሩ ቢሆንም ይህን አጋጣሚ አሽቀንጥረው ጥለውታል። ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የተጠራው ዓመጸኛ የሆነ መልአክ ፈጣሪያቸው በጣም ጨቋኝ እንደሆነና ጥሩና መጥፎ የሆነውን ለራሳቸው ቢወስኑ የተሻለ እንደሚሆን ነገራቸው።—ዘፍጥረት 3:1-5
ሔዋን ተታልላ ይህን ውሸት አመነች። አዳምም ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ከመገኘት ይልቅ ከሚስቱ ጋር ያለውን ዝምድና አስበልጦ ስለተመለከተ ሰይጣን ባስነሳው በዚህ ዓመጽ ተባበራት። (ዘፍጥረት 3:6፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:14) ይህ ድርጊታቸው በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን ያሳጣቸው ከመሆኑም ሌላ ወደፊት የሚወለዱት ዘሮቻቸው ኃጢአትንና የእርሱ ውጤት የሆነውን ሞትን እንዲወርሱ አደረገ።—ሮሜ 5:12
ፈጣሪያችን ይሖዋ፣ የመጀመሪያው ዓመጽ ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶች በሙሉ የሚያስወግድ ዝግጅት ለማድረግ ወዲያውኑ ወሰነ። ይሖዋ እርቅ ለመፍጠር ሲል በኋላ በሙሴ ሕግ ውስጥ የተካተተውን መሠረታዊ ሥርዓት በመጠቀም ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ የሚከፈልበት ዝግጅት አደረገ። (ዘዳግም 19:21፤ 1 ዮሐንስ 3:8) ፈጣሪ ለሰብዓዊው ቤተሰብ በነበረው ዓላማ መሠረት ችግር ላይ የወደቁት የአዳምና የሔዋን ዝርያዎች በገነት ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ከተፈለገ ይህ ሥርዓት ተግባራዊ መሆን ነበረበት። ይህ ደግሞ ወደ መሲሑ ያመራል።
ይሖዋ አምላክ በዲያብሎስ ላይ የፍርድ ውሳኔ ባሳለፈበት በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:15) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር “በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሰፍረው የሚገኙት መሲሐዊ ተስፋዎች የሚጀምሩት [በዚህ] ሐሳብ ነው” ብለዋል። ሌላ ምሁር ደግሞ መሲሑ “በሰው ዘሮች ላይ የደረሰውን ውድቀት የሚሽር” የአምላክ መሣሪያ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህንንም ሲያደርግ ለሰው ዘሮች በረከት ያመጣል።—ዕብራውያን 2:14, 15
ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ የሰው ዘር እንደተባረከ የሚያሳይ ምንም ነገር አለመኖሩን እናውቃለን። እንዲያውም የሰው ልጆች በተስፋ መቁረጥ ማጥ ውስጥ ተዘፍቀዋል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “ብዙ አይሁዳውያን ዛሬም ቢሆን ችግሮቻቸውን የሚያስተካክል እንዲሁም የሕዝቡን ጠላቶች ድል የሚያደርግ መሲሕ ይመጣል ብለው ይጠብቃሉ።” መጽሐፍ ቅዱስ ግን መሲሑ አስቀድሞ እንደመጣ ይናገራል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ለማመን የሚያስችል ማስረጃ ይኖራል? የሚቀጥለው ርዕስ መልሱን ይሰጣል።