ጳንጥዮስ ጲላጦስ ማን ነበረ?
ጳንጥዮስ ጲላጦስ ማን ነበረ?
“ዋዘኛና ተጠራጣሪ የነበረው ጲላጦስ በአእምሯችን ላይ ጥያቄ ፈጥሮ ያለፈ የታሪክ ሰው ነው። በአንዳንዶች ዓይን ቅዱስ ተደርጎ ሲታይ በሌሎች ዘንድ ደግሞ የሰብዓዊ ድክመት ፍጹም መገለጫ ነው። በሌላ በኩል፣ ሰላም እንዳይደፈርስ ሲል አንድን ሰው መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ ዓይነተኛ የፖለቲካ ሰው ነበር።”—በአን ሮው የተዘጋጀው ፖንቲየስ ፓይሌት
ከእነዚህ አመለካከቶች መካከል አንዱን ትጋራ ወይም አትጋራ ይሆናል፤ ያም ሆነ ይህ ጳንጥዮስ ጲላጦስ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ካደረገው ነገር የተነሳ በሰፊው ለመታወቅ በቅቷል። ጲላጦስ ማን ነበረ? ስለ እርሱ ምን የሚታወቅ ነገር አለ? የእርሱን ቦታ በሚገባ መረዳታችን በዚያን ወቅት በምድር ላይ የተፈጸሙትን ዐቢይ ክስተቶች በተሻለ ሁኔታ እንድንገነዘብ ያስችለናል።
የነበረው ቦታ፣ ኃላፊነትና ሥልጣን
የሮማው ንጉሠ ነገሥት ጢባርዮስ በ26 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጲላጦስን የይሁዳ ገዥ አድርጎ ሾመው። የምክር ቤት መቀመጫ ካላቸው መኳንንቶች በተለየ እንዲህ ዓይነት ቦታ የሚሰጣቸው ባለ ሥልጣኖች ከዝቅተኛው የገዥ መደብ ክፍል የመጡ ወንዶች ነበሩ። ጲላጦስ ከሠራዊቱ ጋር የተቀላቀለው የበታች አዛዥ ሆኖ ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም በተለያዩ ቦታዎች ግዳጁን ሲወጣ ደረጃ በደረጃ ማዕረግ የተጨመረለት ሲሆን በኋላም 30 ዓመት ሳይሞላው ገዥ ሆኖ ለመሾም በቃ።
ጲላጦስ የደንብ ልብሱን ሲለብስ ከቆዳ የተሠራ እጅጌ ጉርድ ልብስና ከብረት የተሠራ ጥሩር እንደሚያደርግ ይገመታል። ሕዝብ ፊት ሲቀርብ ደግሞ መላ ሰውነቱን የሚሸፍን ወይን ጠጅ ጥለት ያለው ነጭ ልብስ ይለብስ ነበር። አጭር ጸጉር እንዳለውና ጢሙን ሙልጭ አድርጎ እንደሚላጭም ይታሰባል። ምንም እንኳ አንዳንዶች የስፔይን ተወላጅ እንደሆነ ቢያምኑም መጠሪያ ስሙ የፖንቲ ጎሳ (በደቡባዊ ኢጣሊያ የሚኖሩ ሳምናውያን መኳንንቶች) አባል እንደሆነ ይጠቁማል።
የጲላጦስ ዓይነት ሥልጣን የሚሰጣቸው ሹማምት በአብዛኛው የሚላኩት ኋላ ቀር ወደሆኑ ክልሎች ነበር። በሮማውያን አመለካከት ደግሞ ይሁዳ በዚህ መልኩ የምትታይ አገር ነበረች። ጲላጦስ ፀጥታና ሥርዓት ማስከበር ብቻ ሳይሆን ቀጥተኛ ያልሆነ ቀረጥና የዜግነት ግብር የመሰብሰብ ሂደቱንም በበላይነት ይቆጣጠር ነበር። የዕለት ተዕለት ጉዳዮችን መዳኘት የአይሁድ ፍርድ ቤቶች ሥራ ሲሆን ከሞት ቅጣት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ግን የመጨረሻው ፍትሕ አስፈጻሚ አካል ወደሆነው ወደ አገረ ገዥው ይመሩ እንደነበር ግልጽ ነው።
ጲላጦስና ሚስቱ የሚኖሩት የወደብ ከተማ በሆነችው በቂሳርያ ሲሆን አብረዋቸውም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጸሐፊዎች፣ ወዳጆቻቸውና መልእክተኞች ነበሩ። ጲላጦስ እያንዳንዱ ከ500 እስከ 1,000 እግረኛ ወታደሮች ያሉት አምስት ብርጌድ እንዲሁም 500 የሚያህል ፈረሰኛ ጦር ያዝዝ ነበር። ወታደሮቹ ሕግ የሚጥሱ ሰዎችን እንጨት ላይ ሰቅለው የመግደል ልማድ ነበራቸው። በሰላም ጊዜ የሞት ቅጣት የሚፈጸመው ጉዳዩ በአጭሩ ከታየ በኋላ ሲሆን ዓመጽ በተቀሰቀሰበት ወቅት ግን ዓማጺያኑ አንድ ላይ ተይዘው ወዲያውኑ ይገደላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በስፓርታከስ መሪነት የተካሄደውን ዓመጽ ለመደምሰስ ሮማውያን
6,000 ባሮችን እንጨት ላይ ሰቅለው ገድለዋል። በይሁዳ አስጊ ሁኔታ ከተፈጠረ አገረ ገዥው በርካታ ክፍለ ጦሮችን ከሚያዘው በሶርያ ከሚገኘው የንጉሠ ነገሥቱ እንደራሴ እርዳታ መጠየቅ ይችላል። ይሁን እንጂ ጲላጦስ በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት በሶርያ ምንም ዓይነት ክፍለ ጦር ስላልነበረ ማንኛውንም ዓመጽ በአጭሩ ከመቅጨት ሌላ አማራጭ አልነበረውም።በየአገሩ የተሾሙ ገዥዎች ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር በየጊዜው መረጃ ይለዋወጡ ነበር። የንጉሠ ነገሥቱን ክብር የሚነካ ነገር ወይም በሮማውያን አገዛዝ ላይ ስጋት የሚፈጥር ማንኛውም ሁኔታ ለንጉሠ ነገሥቱ ሪፖርት መደረግ የነበረበት ሲሆን ከዚያም ጉዳዩን በተመለከተ ትእዛዝ ይላካል። አንድ አገረ ገዥ ጉዳዩን በተመለከተ ሌሎች አቤቱታ ከማሰማታቸው በፊት በግዛቱ ውስጥ የተፈጸሙ ነገሮችን ቀድሞ ለንጉሠ ነገሥቱ ለማሳወቅ ሳይቻኮል አይቀርም። በይሁዳ ችግር እያንዣበበ ስለነበር እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ጲላጦስን በጣም እንደሚያሳስቡት ግልጽ ነው።
ከወንጌል ዘገባዎች ሌላ ጲላጦስን በተመለከተ ዋነኞቹ የመረጃ ምንጮች ታሪክ ጸሐፊዎቹ ፍላቪየስ ጆሴፈስና ፊሎ ናቸው። ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ ደግሞ ጲላጦስ ክሪስተስን (ክርስቲያኖች ስማቸውን ያገኙት ከእርሱ ነው) እንዳስገደለው ገልጿል።
አይሁዳውያንን ያስቆጣ ድርጊት
ጆሴፈስ፣ በአይሁዳውያን እምነት ምስል መሥራት የተከለከለ ስለሆነ ሮማውያን ገዥዎች ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት የንጉሠ ነገሥቱ ምስል የሚገኝባቸውን ወታደራዊ ዓርማዎች ወደ ኢየሩሳሌም ይዘው ከመምጣት መቆጠባቸውን ገልጿል። ጲላጦስ እንዲህ ዓይነት አሳቢነት ሳያሳይ በመቅረቱ በቁጣ የተሞሉ አይሁዳውያን አቤቱታ ለማቅረብ በአስቸኳይ ወደ ቂሳርያ ሄዱ። ጲላጦስ ለአምስት ቀናት ያህል ምንም ዓይነት እርምጃ ሳይወስድ ቆየ። በስድስተኛው ቀን ወታደሮቹ ዓማጺያኑን እንዲከቡና ካልተበታተኑ እንገድላችኋላን ብለው እንዲያስፈራሯቸው ትእዛዝ ሰጠ። አይሁዳውያኑ ሕጋቸው ከሚጣስ ሞትን እንደሚመርጡ ሲናገሩ ጲላጦስ አቋሙን በመለወጥ ምስሎቹ እንዲነሱ አደረገ።
ጲላጦስ የኃይል እርምጃ የወሰደባቸው ጊዜያትም ነበሩ። ጆሴፈስ፣ አገረ ገዥው ወደ ኢየሩሳሌም በቦይ ውኃ ለማምጣት ግንባታ እንደጀመረና የፕሮጀክቱን ወጪ ለመሸፈን ከቤተ መቅደሱ በተገኘ ገንዘብ እንደተጠቀመ ጽፏል። ጲላጦስ ቤተ መቅደሱን መዝረፍ ርኩስ ተግባር እንደሆነና ጉዳዩ ያስቆጣቸው አይሁዳውያን ከቦታው እንዲያስነሳው ለጢባሪዮስ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ስለሚያውቅ ገንዘቡን በኃይል አልወሰደም። ስለዚህ ጲላጦስ የቤተ መቅደሱን ኃላፊዎች ትብብር ሳያገኝ አልቀረም። “ቁርባን” ተብሎ የሚጠራው ለአምላክ የተሰጠ ገንዘብ ለከተማዋ ነዋሪዎች ጥቅም ተብሎ ለሚከናወን ሥራ ቢውል ምንም ጥፋት የለበትም። ይሁን እንጂ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን በነገሩ መቆጣታቸውን ለመግለጽ ተሰባሰቡ።
ጲላጦስ ወታደሮች ከሰልፈኞቹ ጋር እንዲቀላቀሉና ተቃዋሚዎቹን ሰይፍ ሳይጠቀሙ በቆመጥ ብቻ እንዲመቷቸው ትእዛዝ አስተላለፈ። እንዲህ ያደረገው ዓመጹን ያለ ምንም ደም መፋሰስ መቆጣጠር ስለፈለገ ይሆናል። ምንም እንኳ አንዳንዶች የሞቱ ቢሆንም ስልቱ የተፈለገውን ውጤት ያስገኘ ይመስላል። አንዳንድ ሰዎች ጲላጦስ የገሊላውያንን መሥዋዕት ከደማቸው ጋር እንደቀላቀለው ለኢየሱስ መጥተው የነገሩት ስለዚህ ሁኔታ ሊሆን ይችላል።—ሉቃስ 13:1
“እውነት ምንድን ነው?”
ጲላጦስን የሚያስተቸው ነገር የአይሁድ ካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ኢየሱስ ንጉሥ ነኝ ይላል ሲሉ ያቀረቡትን ክስ የመረመረበት መንገድ ነው። ጲላጦስ የኢየሱስ ተልእኮ ለእውነት መመሥከር መሆኑን ሲሰማ ይህ እስረኛ በሮም መንግሥት ላይ የሚፈጥረው ስጋት እንደሌለ ተገነዘበ። “እውነት ምንድን ነው?” ሲል ያቀረበው ጥያቄ እውነት ለመረዳት የሚያዳግት ጽንሰ ሐሳብ ስለሆነ ያን ያህል ትኩረት ሊሰጠው አይገባም የሚል አስተሳሰብ እንደነበረው በግልጽ ያሳያል። የደረሰበት መደምደሚያ ምን ነበር? ውሳኔውን “እኔ በዚህ ሰው ላይ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም” ሲል ገልጿል።—ዮሐንስ 18:37, 38፤ ሉቃስ 23:4
ማርቆስ 15:7, 10፤ ሉቃስ 23:2) በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ጲላጦስ ከአይሁዳውያን ጋር መጋጨቱ በጢባሪዮስ ዘንድ ያለውን ስም ያጎደፈበት ሲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ደግሞ ብቃት በሚጎድላቸው አገረ ገዥዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ ይታወቃል። በአንጻሩ ደግሞ ለአይሁዳውያኑ ቢሸነፍ የድክመት ምልክት ተደርጎ ሊቆጠርበት ይችላል። ስለዚህ ጲላጦስ ምን እንደሚያደርግ ግራ ተጋባ።
የፍርድ ሂደቱ እዚህ ላይ መቋጨት በተገባው ነበር፤ ሆኖም አይሁዳውያኑ አገሪቱን ለውድቀት እየዳረገ ነው ሲሉ አጥብቀው ተከራከሩ። የካህናት አለቆቹ ኢየሱስን አሳልፈው እንዲሰጡ ያደረጋቸው ቅንዓት ነበር፤ ጲላጦስም ይህን ተረድቷል። ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስን መልቀቅ ችግር እንደሚያስከትል አውቋል፤ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዲፈጠር ደግሞ አይፈልግም። በርባንና ሌሎች ሰዎች ዓመጽ በመቀስቀሳቸውና በነፍስ ግድያ የታሰሩ በመሆናቸው ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው። (ጲላጦስ፣ ኢየሱስ የመጣው ከየት መሆኑን ሲሰማ ጉዳዩን የገሊላ አውራጃ ገዥ ወደሆነው ወደ ሄሮድስ አስተላለፈው። ይህም ሳይሳካ ሲቀር ጲላጦስ በማለፍ በዓል በሚደረገው አንድ እስረኛ የማስፈታት ልማድ መሠረት ከቤተ መንግሥቱ ውጪ የተሰበሰቡት ሰዎች ኢየሱስን ፍታልን እንዲሉት ለማድረግ ሞከረ። ሆኖም የተሰበሰበው ሕዝብ በርባን እንዲፈታ በጩኸት ገለጸ።—ሉቃስ 23:5-19
ጲላጦስ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ የፈለገ ይመስላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ክብሩን መጠበቅና ሕዝቡን ማስደሰት ፈልጓል። በመጨረሻ፣ ሕሊናውን ከማክበርና ፍትሕን ከማስፈጸም ይልቅ ለቦታው መቆም እንደሚሻል ወሰነ። ውኃ እንዲያመጡለት ጠይቆ እጁን ከታጠበ በኋላ አሁን በሚያስተላልፈው የሞት ፍርድ ተጠያቂ እንዳልሆነ ገለጸ። a ጲላጦስ፣ ኢየሱስ ንጹሕ ሰው መሆኑን ቢያምንም እንኳ እንዲገርፉት ከማድረጉም ሌላ ወታደሮቹ እንዲያሾፉበት፣ እንዲመቱትና እንዲተፉበት አሳልፎ ሰጣቸው።—ማቴዎስ 27:24-31
ጲላጦስ ኢየሱስን ለመልቀቅ አንድ የመጨረሻ ሙከራ አደረገ። ሆኖም ይህ አድራጎት የቄሣር ወዳጅ አለመሆኑን እንደሚያሳይ ሕዝቡ በጩኸት ገለጸ። (ዮሐንስ 19:12) ጲላጦስ ይህን ሲሰማ ለፍላጎታቸው ተሸነፈ። አንድ ምሑር የጲላጦስን ውሳኔ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “መፍትሄው ቀላል ነው፤ ሰውየው ይገደል። ደግሞም እንዲያው ጠፋ ቢባል እዚህ ግባ የማይባል የአንድ አይሁዳዊ ሕይወት ነው። በእርሱ ምክንያት ሁከት እንዲነሳ መፍቀድ ሞኝነት ይሆናል።”
የጲላጦስ መጨረሻ ምን ሆነ?
በጲላጦስ የሥልጣን ዘመን ስለሆነው ነገር የሚናገረው የመጨረሻው ዘገባ ሌላ ግጭት መከሰቱን ያወሳል። ጆሴፈስ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የታጠቁ ሳምራውያን ሙሴ በገሪዛን ተራራ ላይ ቀብሮታል እየተባለ የሚወራውን ሀብት ቆፍረው ለማውጣት በዚያ መሰብሰባቸውን ተናግሯል። ጲላጦስ በጉዳዩ ጣልቃ የገባ ሲሆን ወታደሮቹም ከሕዝቡ መካከል በርካታ ሰዎችን ገድለዋል። ሳምራውያኑ የጲላጦስ የበላይ ለነበረው ለሶርያው ገዥ ለሉኪየስ ቪቴሊየስ አቤቱታ አቀረቡ። ቪቴሊየስ፣ ጲላጦስ ያለቦታው ገብቷል የሚል አቋም ይኑረው አይኑረው የተጠቀሰ ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ አድራጎቱን በተመለከተ ወደ ሮም ሄዶ ለንጉሠ ነገሥቱ መልስ እንዲሰጥ ለጲላጦስ ትእዛዝ ሰጥቶታል። ይሁንና ጲላጦስ እዚያ ከመድረሱ በፊት ጢባሪዮስ ሞተ።
“ከዚህ በኋላ ስለ ጲላጦስ የሚያወሳ የታሪክ መረጃ አይገኝም፤ ሆኖም ስለ እርሱ የሚነገሩ በርካታ አፈ ታሪኮች አሉ” ሲል አንድ ምንጭ ዘግቧል። ይሁንና ብዙዎች የእርሱን መጨረሻ ለመግለጽ ጥረት አድርገዋል። ጲላጦስ ክርስትናን እንደተቀበለ ይወራል። በኢትዮጵያ ያሉ “ክርስቲያኖች” “ቅዱስ” የሚል ማዕረግ ሰጥተውታል። በሦስተኛው መቶ ዘመን መገባደጃና በአራተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ዩሴቢየስ፣ ጲላጦስ እንደ ይሁዳ ራሱን ገድሏል ብለው ከተናገሩት በርካታ ሰዎች መካከል የመጀመሪያው ነበር። ይሁን እንጂ የጲላጦስ መጨረሻ ምን እንደሆነ በትክክል የሚያውቅ ሰው የለም።
ጲላጦስ ግትር፣ ግድ የለሽና ጨቋኝ ነው ሊባል ይችል ይሆናል። ሆኖም የይሁዳ ገዥ ሆኖ ለአሥር ዓመት የቆየ ሲሆን አብዛኞቹ ገዥዎች ግን በዚያ የቆዩት ከዚያ እጅግ ለሚያንስ ጊዜ ነው። ስለዚህ በሮማውያን ዓይን ሲታይ ጲላጦስ ኃላፊነቱን በሚገባ የተወጣ ሰው ነበር። በአንጻሩ ደግሞ ራሱን ለማዳን ሲል ኢየሱስ እንዲገረፍና እንዲገደል ያደረገ ፈሪ ሰው ነው ተብሏል። ሌሎች ጲላጦስ ሰላም የማስከበርንና የሮምን ጥቅም የማስጠበቅን ያህል ለፍትሕ የመቆም ግዴታ አልነበረበትም ብለው ይከራከራሉ።
ጲላጦስ የኖረበት ዘመን እኛ ካለንበት በጣም የተለየ ነው። ሆኖም የትኛውም ዳኛ ቢሆን፣ ፍትሕን አዛብቶ ካልሆነ በስተቀር ጥፋት የሌለበትን ሰው ወንጀለኛ ሊያደርግ አይችልም። ጳንጥዮስ ጲላጦስ ከኢየሱስ ጋር ባይገናኝ ኖሮ ስሙ በታሪክ መጽሐፍ ላይ ብቻ ተጠቅሶ የሚገኝ ሰው በሆነ ነበር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በደም ማፍሰስ ድርጊት አለመካፈልን ለማሳየት እጅ መታጠብ የሮማውያን ሳይሆን የአይሁዳውያን ልማድ ነበር።—ዘዳግም 21:6, 7
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቂሳርያ ውስጥ የተገኘው ይህ የተቀረጸ ጽሑፍ ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ ገዥ እንደሆነ ይገልጻል