በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዓለምን የምግብ ችግር ማን ይፈታው ይሆን?

የዓለምን የምግብ ችግር ማን ይፈታው ይሆን?

የዓለምን የምግብ ችግር ማን ይፈታው ይሆን?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረሃብን ለመከላከል ያቋቋመው የዓለም የምግብ ፕሮግራም የተባለው ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት 800 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የረሃብ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተገምቷል፤ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ሕፃናት ናቸው። ይህ ድርጅት በቅርቡ እንደገለጸው ብዙ የበለጸጉ አገሮች ለዚህ ችግር ትኩረት ሰጥተው የገንዘብ እርዳታ እንዳያደርጉ እንደ ሽብርተኝነት ያሉ ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንቅፋት ሆነውባቸዋል። የተላላፊ በሽታዎች መዛመትም ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆኗል። ድርጅቱ ያወጣው ግሎባል ስኩል ፊዲንግ የተሰኘው ሪፖርት ኤድስ በጣም ስለተስፋፋባቸው የአፍሪካ አገሮች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ወላጆች በኤድስ ምክንያት እያለቁ በመሆኑ ልጆቻቸው ራሳቸውን ለመርዳት ተገድደዋል። አብዛኞቹ ልጆች በግብርናው መስክም ይሁን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውንና ከወላጆቻቸው ሊያገኙ ይገባ የነበረውን ሥልጠና ስላላገኙ ይህን ማድረግ ያስቸግራቸዋል።”

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ እቅድ አውጥቷል። እቅዱ ረሃብን ከመቀነስም ባሻገር ለወጣቶች መደበኛ ትምህርታቸውን አስታኮ ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከል የሚያስችሉ ሌሎች ፕሮግራሞችንም ጭምር ለማዘጋጀት ነው።

ይህ እቅድ ሥራ ላይ በዋለባቸው አካባቢዎች ሕፃናት የምግብ አቅርቦት፣ የንጽሕና ሥልጠናና የተለያዩ እርዳታዎችን አግኝተዋል። ከዚህም በላይ ሰዎች የአመለካከት ለውጥ ባደረጉባቸው ቦታዎች የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት መቀነሱ ተስተውሏል።

የሰው ልጆች የሚያደርጉት ጥረት የሚያስገኘው ውጤት ያልተሟላ ከመሆኑም በተጨማሪ ዘላቂ አለመሆኑ ያሳዝናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ረሃብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚጠፋ የሚናገር አጽናኝ ተስፋ ይዟል። መዝሙር 72:16 “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ” ይላል። በአምላክ መስተዳድር ሥር ሰዎች ስለ ይሖዋ አምላክ እንዲህ ለማለት ይችላሉ:- “ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፣ . . . ምግባቸውን አዘጋጀህ፣ እንዲሁ ታሰናዳለህና።”—መዝሙር 65:9 1954 ትርጉም

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

WFP/Y. Yuge