የወደፊት ዕጣህን የሚወስነው ምንድን ነው?
የወደፊት ዕጣህን የሚወስነው ምንድን ነው?
“የሰው ልጆች እንደ ሌሎች እንስሳት ሁሉ የወደፊት ዕጣቸውን መወሰን አይችሉም” በማለት የዝግመተ ለውጥ አማኝ የሆኑት ጆን ግሬይ ጽፈዋል። ሽሙሊ ቦቴአክ የተባሉ ደራሲ ደግሞ አን ኢንተለጀንት ፐርሰንስ ጋይድ ቱ ጁዳይዝም በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “የሰው ልጅ እንስሳ ባለመሆኑ ምንጊዜም ቢሆን የራሱን ዕጣ ፈንታ መወሰን ይችላል” በማለት ቀደም ብሎ ከተጠቀሰው ፍጹም ተቃራኒ የሆነ አስተያየት ሰጥተዋል።
በርካታ ሰዎች በጆን ግሬይ ሐሳብ የሚስማሙ ሲሆን ከአቅም በላይ የሆኑ የተፈጥሮ ኃይሎች የሰው ልጆችን ዕጣ ፈንታ እንደሚወስኑ ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ አምላክ ሰውን የፈጠረው የወደፊት ዕጣውን የመቆጣጠር ችሎታ እንዲኖረው አድርጎ እንደሆነ ይሰማቸዋል።
የወደፊት ዕጣቸው ኃያላን በሆኑ ሰዎች ላይ የተመካ እንደሆነ የሚሰማቸውም አሉ። ደራሲ ሮይ ዌዘርፈርድ እንደሚሉት ከሆነ “በምድር ላይ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች በተለይም በታሪክ ዘመናት ውስጥ የታዩት በርካታ ሴቶች . . . ከደረሰባቸው ግልጽ ጭቆናና ብዝበዛ አንጻር ሲታይ በገዛ ሕይወታቸው ላይ ሥልጣን የላቸውም ወይም ቁጥጥር ማድረግ አይችሉም።” (ዚ ኢምፕሊኬሽንስ ኦቭ ዲተርሚኒዝም) ብዙዎች አስደሳች ጊዜ የማየት ሕልማቸው በፖለቲካዊ ወይም በወታደራዊ ኃይሎች ሽኩቻ ምክንያት መና ቀርቶባቸዋል።
በታሪክ ዘመናት ሁሉ የኖሩ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከሰብዓዊ ባሕርይ ውጭ የሆኑ ኃይሎች ዕጣ ፈንታቸውን ስለሚወስኑ ሁሉም ነገር ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። ደራሲው ሽሙሊ ቦቴአክ “ጥንታዊ ግሪኮች . . . ሰው አስቀድሞ የተወሰነለትን ዕድል መለወጥ ስለማይችል የወደፊት ተስፋው ሁሉ ከንቱ ነው የሚለው እምነት ያስጨንቃቸው ነበር” ብለዋል።
ግሪካውያን የእያንዳንዱ ሰው ዕጣ ፈንታ ግብታዊነት በሚያጠቃቸው እንስት አማልክት እንደተወሰነ ይሰማቸው ነበር። እነዚህ እንስት አማልክት ሰው የሚሞትበትን ጊዜ እንዲሁም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ምን ያህል ችግርና ሥቃይ እንደሚደርስበት በትክክል ያውቃሉ ብለው ያምኑ ነበር።ዛሬም ቢሆን የሰው ዕጣ ፈንታ ከሰብዓዊ ባሕርይ ውጭ በሆኑ ኃይሎች ተወስኗል የሚለው አስተሳሰብ በሰፊው ይታመንበታል። ለምሳሌ ያህል ብዙዎች በዕድል ያምናሉ። እነዚህ ሰዎች የሰው ልጆች የሚያደርጉት ነገር የሚያስከትለውን ውጤትም ሆነ የሚሞቱበትን ጊዜ አምላክ አስቀድሞ ወስኗል ይላሉ። እንዲሁም “እያንዳንዱ ሰው በስተመጨረሻ የሚያጋጥመው ጽድቅ ወይም ኩነኔ” ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ “አስቀድሞ ተወስኗል” የሚል ዕድልን የሚመለከት ሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርት አለ። ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎችም በዚህ ትምህርት ያምናሉ።
አንተስ ምን ይመስልሃል? ከአንተ በላይ በሆኑ ኃይሎች የወደፊት ዕጣህ አስቀድሞ ተወስኗል? ወይስ እንግሊዛዊው የቲያትር ደራሲ ዊልያም ሼክስፒር “ሰዎች በአንድ ወቅት ላይ ዕድላቸውን መወሰን ይችላሉ” ሲል የጻፋቸው ቃላት በመጠኑም ቢሆን እውነትነት አላቸው? እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል እንመርምር።