“እንዴት ሊሳካልሽ ቻለ?”
“እንዴት ሊሳካልሽ ቻለ?”
ሚውሪየል የተባለች የሦስት ልጆች እናት ምግብ ቤት ውስጥ ሳለች በዕድሜ የገፉ አንድ የማታውቃቸው ሰው ሳታስበው ከላይ ያለውን ጥያቄ አቀረቡላት። ሚውሪየል ልጆቿን ለማሳከም የሐኪም ቀጠሮ ነበራት፤ በሕክምናው ቦታ ካሰበችው በላይ በመቆየታቸው ምክንያት ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ከመሄዳቸው በፊት ቤት ገብተው ራት ለመብላት ጊዜ አልነበራቸውም። ስለዚህ ልጆቿን ለማብላት በቅርብ ወደሚገኝ ምግብ ቤት ይዛቸው ሄደች።
ተመግበው ሲጨርሱ ሰውየው ወደ ሚውሪየል ጠጋ ብለው እንዲህ አሏት:- “እዚህ ከገባችሁበት ሰዓት ጀምሮ ስመለከታችሁ ነበር። በአንቺ ልጆችና ብዙ ጊዜ በሚያጋጥሙኝ ሌሎች ልጆች መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን አስተውያለሁ። በዛሬው ጊዜ ልጆች የጠረጴዛና የወንበር አጠቃቀማቸው ከሥርዓት ውጪ ነው። እግራቸውን ጠረጴዛ ላይ ይሰቅላሉ። ወንበሮቹን ምስቅልቅል ያደርጋሉ። ያንቺ ልጆች ግን ረጋ ያሉና ጨዋ ናቸው። እንዴት ሊሳካልሽ ቻለ?”
ሚውሪየል “እኔና ባለቤቴ አዘውትረን ከልጆቻችን ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እናጠናለን፤ የተማርናቸውንም ነገሮች በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት እናደርጋለን። እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ነን” በማለት መልስ ሰጠች። በዚህን ጊዜ ሰውየው እንዲህ አሉ:- “እኔ በናዚ ዘመን ከደረሰው እልቂት የተረፍኩ አይሁዳዊ ነኝ። የይሖዋ ምሥክሮች በጀርመን የደረሰባቸውን ስደት አሁን ድረስ አስታውሳለሁ። በዚያን ጊዜ እንኳን ከሌሎች የተለዩ መሆናቸው በግልጽ ይታይ ነበር። የልጆችሽ መልካም ባሕርይ በጥልቅ ነክቶኛል። ስለ ሃይማኖታችሁ በደንብ ማወቅ አለብኝ።”
መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን ለማሳደግ የሚረዳ እጅግ ጠቃሚ መመሪያ ይዟል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት መመሪያዎች ጥቅም እንዲያገኙ የመርዳት ልባዊ ፍላጎት አላቸው። ቀጥሎ የቀረበውን ግብዣ እንዲቀበሉ እናበረታታዎታለን።