አሌካንድራ የጻፈችው ደብዳቤ
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
አሌካንድራ የጻፈችው ደብዳቤ
በደብዳቤ የሚሰጥ ምሥክርነት ውጤታማ ዘዴ ሆኖ ማገልገል ከጀመረ ቆየት ብሏል። ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ የሰዎች ምላሽ ምን እንደሚሆን ማወቅ የማይቻል ቢመስልም በዚህ ዘዴ ተጠቅመው መመሥከራቸውን የቀጠሉ አስፋፊዎች በእጅጉ ተባርከዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠዋት ላይ ዘርህን ዝራ፤ ማታም ላይ እጅህ ሥራ አይፍታ፤ ይህ ወይም ያ፣ ወይም ሁለቱ መልካም ይሁኑ፣ የቱ እንደሚያፈራ አታውቅምና” በማለት የሚሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ እያደረጉ ነው።—መክብብ 11:6
ሜክሲኮ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለአሥር ዓመታት ያህል ስታገለግል የቆየች አሌካንድራ የተባለች ወጣት ባደረባት የካንሰር ሕመም የተነሳ ኬሞቴራፒ የሚባል ሕክምና ትከታተል ነበር። በሽታዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄዱ ዕለታዊ ሥራዎቿን እንኳ ለማከናወን አቅም አጣች። ሆኖም አሌካንድራ አገልግሎቷን መተው ስላልፈለገች በደብዳቤ ለመመሥከር ወሰነች። በደብዳቤዋ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች በነጻ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያስጠኑ ከገለጸች በኋላ የእናቷን የስልክ ቁጥር አከለችበት። ከዚያም እናቷ ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ያላገኘቻቸው ሰዎች ቤት ደብዳቤውን እንድታስቀምጥላት ሰጠቻት።
በዚህ መሃል ዲዮሃኒ የተባለች አንዲት ወጣት በቤት ሠራተኛነት ለመቀጠር ከጓቲማላ ወደ ካንኩን፣ ሜክሲኮ ትመጣለች። በዚያ እያለችም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ትገናኝና ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ማድረግ ትጀምራለች። ከጊዜ በኋላ አሠሪዎቿ ወደ ሜክሲኮ ሲቲ ለመሄድ ስላሰቡ አብራቸው እንድትሄድ ጠየቋት። ዲዮሃኒ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንዳትጠፋፋ ስለፈራች አብራቸው ለመሄድ አመነታች።
አሠሪዎቿ ግን “አታስቢ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የማይገኙበት ቦታ የለም። እዚያ እንደደረስን እንፈልጋቸዋለን” አሏት። ዲዮሃኒ ይህን አስደሳች ተስፋ ስላገኘች ከአሠሪዎቿ ጋር ወደ ሜክሲኮ ሲቲ ለመሄድ ተስማማች። እዚያ ከደረሱ በኋላም የዲዮሃኒ አሠሪዎች የይሖዋ ምሥክሮችን መፈለግ ጀመሩ። የሚያስገርመው ግን በዚያች ከተማ ውስጥ ከ41,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮችና 730 ጉባኤዎች ቢኖሩም የዲዮሃኒ አሠሪዎች ምሥክሮቹን ሊያገኟቸው አልቻሉም።
ዲዮሃኒ ምሥክሮቹን አግኝታ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያደርጉትን ውይይት መቀጠል ባለመቻሏ ተስፋ ቆረጠች። አንድ ቀን አሠሪዋ መጣችና “የምሥራች! አምላክሽ ጸሎትሽን ሰምቶልሻል” አለቻት። ከዚያም አንድ ደብዳቤ ሰጠቻትና “የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን ደብዳቤ አስቀምጠውልሻል” አለቻት። ደብዳቤው ከአሌካንድራ የተላከ ነበር።
ዲዮሃኒ ከአሌካንድራ እናትና ከእህቷ ከብላንካ ጋር ተገናኘችና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ከአሌካንድራ ጋር የተገናኘች ሲሆን ደስ የሚል ጊዜ አሳለፉ። አሌካንድራም ዲዮሃኒ ጥናቷን በመቀጠል መንፈሳዊ እድገት እንድታደርግ አበረታታቻት።
ይህ ከሆነ ከጥቂት ወራት በኋላ ማለትም በሐምሌ ወር 2003 አሌካንድራ በሞት ብታንቀላፋም ባሳየችው እምነትና ድፍረት ለእምነት ባልንጀሮቿ ግሩም አርዓያ ሆናለች። በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ ብዙዎች ዲዮሃኒን በማግኘታቸውና ለአሌካንድራ ያላትን አድናቆት ስትናገር በመስማታቸው ልባቸው በጥልቅ ተነክቷል። ዲዮሃኒ እንዲህ ብላ ነበር:- “አሌካንድራና ቤተሰቧ ለእኔ ግሩም ምሳሌ ሆነውልኛል። ይሖዋን ለማገልገልና በቅርቡ ለመጠመቅ ወስኛለሁ። በመጪዋ ገነት አሌካንድራን እንደገና ለማግኘት በጣም እጓጓለሁ!”
ደብዳቤ ከቁም ነገር የማይገባ ትንሽ ነገር ሊመስል ይችላል። ቢሆንም ዘላቂና አስደሳች ውጤት ሊያስገኝ ይችላል!