የዘኍልቍ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የዘኍልቍ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በኋላ በብሔር መልክ ተደራጁ። ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባት ይችሉ የነበረ ቢሆንም አልገቡም። በተቃራኒው ለአራት አሥርተ ዓመታት ገደማ “ጭልጥ ባለና አስፈሪ ምድረ በዳ” እንዲባዝኑ ተወሰነባቸው። (ዘዳግም 8:15) ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘኍልቍ መጽሐፍ ምን እንደተከናወነ ይተርክልናል። ዘገባው ይሖዋ አምላክን የመታዘዝንና ወኪሎቹን የማክበርን አስፈላጊነት ሊያስገነዝበን ይገባል።
ሙሴ የዘኍልቍን መጽሐፍ የጻፈው እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሲጓዙና በሞዓብ ሜዳ ሰፍረው እያለ ሲሆን ዘገባው ከ1512 እስከ 1473 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው የ38 ዓመት ከ9 ወራት ጊዜ ውስጥ የተከናወነውን ታሪክ ይሸፍናል። (ዘኍልቍ 1:1፤ ዘዳግም 1:3) የዘኍልቍ መጽሐፍ ስያሜውን ያገኘው እስራኤላውያን በ38 ዓመት ልዩነት ካደረጓቸው ሁለት የሕዝብ ቆጠራዎች ነው። a (ምዕራፍ 1-4, 26) ትረካው በሦስት የተከፈለ ነው፤ የመጀመሪያው ክፍል በሲና ተራራ ግርጌ ሰፍረው ሳለ የተከናወኑትን ሁኔታዎች ያወሳል። ሁለተኛው ክፍል እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሲጓዙ ባሳለፏቸው ዓመታት ምን እንደተፈጸመ የሚገልጽ ሲሆን የመጨረሻው ክፍል ደግሞ በሞዓብ ሜዳ ሰፍረው እያሉ ያጋጠሟቸውን ነገሮች ይሸፍናል። ይህንን ዘገባ ስታነብ ‘እነዚህ ታሪኮች ምን ያስተምሩኛል? በዘኍልቍ መጽሐፍ ውስጥ በዛሬው ጊዜ ሊጠቅሙኝ የሚችሉ መመሪያዎች አሉ?’ እያልክ ራስህን መጠየቅ ትችላለህ።
በሲና ተራራ ግርጌ
ከሁለቱ የሕዝብ ቆጠራዎች የመጀመሪያው የተካሄደው እስራኤላውያን በሲና ተራራ ግርጌ ሠፍረው እያለ ነበር። በቆጠራው መሠረት ሌዋውያንን ሳይጨምር ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች በአጠቃላይ 603,550 ነበሩ። ቆጠራው የተካሄደው ለወታደራዊ ዓላማ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሴቶችን፣ ልጆችንና ሌዋውያንን ጨምሮ አጠቃላይ ሕዝቡ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ይሆናል።
ከሕዝብ ቆጠራው በኋላ እስራኤላውያን ስለሚጓዙበት ቅደም ተከተል የሚገልጽ መመሪያ እንዲሁም ሌዋውያን ስለሚያከናውኗቸው ተግባሮችና በማደሪያው ድንኳን ስለሚካሄደው አገልግሎት ዝርዝር መግለጫ ተሰጣቸው። ከዚህም በላይ የታመመን ሰው ከሕዝቡ ተገልሎ እንዲቆይ ስለማድረግ፣ በባልና ሚስት መካከል ቅናት ቢፈጠር ምን መደረግ እንዳለበትና ናዝራውያን ስለሚፈጽሙት ስዕለት ተነገራቸው። ምዕራፍ 7 የነገድ አለቆች የመሠዊያውን መቀደስ ምክንያት በማድረግ ስለሚያቀርቡት ስጦታ የሚናገር ሲሆን ምዕራፍ 9 ደግሞ የማለፍ በዓልን አከባበር ይገልጻል። በተጨማሪም ሕዝቡ እንዴት እንደሚሰፍሩና ለጉዞ ሲንቀሳቀሱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
2:1, 2—በሦስት በሦስት ነገዶች የተከፈለው ሕዝብ በምድረ በዳ በሚሰፍርበት ጊዜ የሚጠቀምበት “ምልክት” ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ምልክቶች ምን እንደሆኑ አይገልጽም። ሆኖም ምልክቶቹ እንደ ቅዱስ የሚቆጠሩ ወይም ሃይማኖታዊ ትርጉም ያላቸው አልነበሩም። ምልክቶቹ የተዘጋጁት ሕዝቡ በሚሰፍሩበት ጊዜ እያንዳንዱ ግለሰብ በሰፈሩ ውስጥ ትክክለኛ ቦታውን ለማግኘት እንዲችል ተብሎ ነው።
5:27—አመንዝራ ሆና የተገኘች ሚስት “ጭኗ ይሰልላል” ሲባል ምን ማለት ነው? እዚህ ላይ ‘ጭን’ የሚለው ቃል የተሠራበት የመራቢያ አካላትን ለማመልከት ነው። “ጭኗ ይሰልላል” ሲባል የመራቢያ አካሏ መሥራት እንደሚያቆምና መጸነስ እንደማትችል ያመለክታል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
6:1-7፦ ናዝራውያን የራሳቸውን ፍላጎት መሥዋዕት በማድረግ የወይን ውጤቶችን በሙሉ እንዲሁም ማንኛውንም የሚያሰክር መጠጥ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ ይጠበቅባቸው ነበር። ፀጉራቸውን እንዲያሳድጉ ይፈለግባቸው የነበረ ሲሆን ይህም ሴቶች ለባሎቻቸው ወይም ለአባቶቻቸው እንደሚገዙ ሁሉ እነርሱም ለይሖዋ የሚገዙ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ናዝራውያን የቅርብ ዘመዳቸውን ጨምሮ የማንኛውንም ሰው አስከሬን ባለመንካት የተቀደሱ መሆን ነበረባቸው። በዛሬው ጊዜ ያሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሚፈልጉትን ሁሉ ከማድረግ በመቆጠብና ለይሖዋ እንዲሁም ለዝግጅቶቹ በመገዛት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እንዳላቸው ያሳያሉ። አንዳንድ ጊዜ ርቀው በሚገኙ ቦታዎች እንዲያገለግሉ ይመደቡ ይሆናል። በዚህም ምክንያት የቅርብ የቤተሰባቸው አባል የቀብር ሥርዓት ላይ እንኳ ለመገኘት ወደ አገራቸው መመለስ አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ወይም ጨርሶ ላይገኙ ይችላሉ።
8:25, 26፦ በዕድሜ የገፉት ሌዋውያን እንዲያርፉና ሥራውን በብቃት ማከናወን የሚችሉ ወንዶች በዚህ አገልግሎት እንዲካፈሉ ሲባል ሌዋውያን ከተወሰነ ዕድሜ በኋላ ከመደበኛው አገልግሎት ጡረታ እንዲወጡ ታዝዘው ነበር። ያም ሆኖ ሌሎቹን ሌዋውያን በፈቃደኝነት ማገዝ ይችሉ ነበር። በዛሬው ጊዜ ከመንግሥቱ ስብከት ሥራ ጡረታ ባይወጣም የዚህ ሕግ መሠረታዊ ሥርዓት ጠቃሚ ትምህርት ይዟል። አንድ ክርስቲያን በዕድሜ መግፋት ምክንያት አንዳንድ ግዴታዎቹን መወጣት ካቃተው አቅሙ በሚፈቅድለት የአገልግሎት መስክ መሰማራት ይችላል።
በምድረ በዳ ውስጥ ከቦታ ቦታ መባዘን
ደመናው ከማደሪያው ድንኳን ላይ ሲነሳ እስራኤላውያን ከ38 ዓመታትና ከአንድ ወይም ሁለት ወራት በኋላ በሞዓብ ምድረ በዳ የሚገባደደውን ረጅም ጉዞ ጀመሩ። በይሖዋ ምሥክሮች በታተመው ‘መልካሚቱን ምድር ተመልከቱ’ በተባለው ብሮሹር ገጽ 9 ላይ የሚገኘውን ካርታ በመጠቀም እስራኤላውያን የተጓዙበትን መንገድ ልትቃኝ ትችላለህ።
እስራኤላውያን የፋራንን ምድረ በዳ አቋርጠው ቃዴስ እስኪደርሱ ድረስ ቢያንስ ሦስት ጊዜ አጉረምርመዋል። ሕዝቡ መጀመሪያ ላይ ሲያጉረመርሙ ይሖዋ እሳት ልኮ ጥቂቶቹ እንዲበሉ ስላደረገ ማጉረምረማቸውን አቆሙ። ከዚያ ደግሞ እስራኤላውያን ሥጋ አማረን ብለው ሲያለቅሱ ይሖዋ ድርጭት ሰጣቸው። ማርያምና አሮን በሙሴ ላይ በማጉረምረማቸው ማርያም ለተወሰነ ጊዜ ያህል በለምጽ ተመታች።
እስራኤላውያን በቃዴስ ሰፍረው እያለ ሙሴ ተስፋይቱን ምድር እንዲሰልሉ 12 ሰዎች ላከ። ሰላዮቹም ከ40 ቀናት በኋላ ተመለሱ። ሕዝቡ አሥሩ ሰላዮች ያመጡትን መጥፎ ዜና በማመን ሙሴን፣ አሮንንና ታማኞቹን ሰላዮች ኢያሱና ካሌብን ለመውገር ተነሱ። ይሖዋ ሕዝቡን በቸነፈር እንደሚመታቸው ሲገልጽ ሙሴ ጣልቃ ገብቶ አማለደላቸው፤ ከዚያም አምላክ በሕዝብ ቆጠራው ውስጥ የተካተቱት እስራኤላውያን በሙሉ ሞተው እስኪያልቁ ድረስ ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ እንዲቅበዘበዙ በየነባቸው።
በምድረ በዳ እያሉ ይሖዋ ተጨማሪ መመሪያዎች ሰጣቸው። ቆሬና ግብረ አበሮቹ በሙሴና በአሮን ላይ ሲያምፁ የተወሰኑትን እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጠፋቸው ሲሆን ሌሎቹን ደግሞ መሬት ተሰንጥቃ ዋጠቻቸው። በቀጣዩ ቀን ሕዝቡ በአጠቃላይ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረመ። በዚህም የተነሳ ይሖዋ 14,700 የሚያህሉትን በመቅሰፍት ገደላቸው። አምላክ አሮን ሊቀ ካህን ሆኖ መመረጡን ለማሳወቅ በትሩ እንድታቆጠቁጥ አደረገ። ከዚያም የሌዋውያንን ኃላፊነቶችና ሕዝቡን ማንጻትን አስመልክቶ ተጨማሪ ዕብራውያን 9:13, 14
ሕግጋት ሰጣቸው። ለመንጻት ሥርዓት በቀይ ጊደር አመድ መጠቀማቸው የኢየሱስ መሥዋዕት ከኃጢአት እንደሚያነጻን ያመለክታል።—የእስራኤል ልጆች ወደ ቃዴስ የተመለሱ ሲሆን በዚያም ማርያም ሞተች። እዚያ እያሉ ሕዝቡ ውኃ አጣን ብለው በሙሴና በአሮን ላይ እንደገና አጉረመረመ። በዚህ ወቅት ሙሴና አሮን ተዓምራዊ በሆነ መንገድ ከዐለት ውኃ ሲያወጡ የይሖዋን ስም ባለመቀደሳቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገቡ ተከለከሉ። ሕዝቡ ከቃዴስ ተነስቶ ጉዞውን በመቀጠል ወደ ሖር ተራራ ሲደርስ አሮን በተራራው ላይ ሞተ። እስራኤላውያን በኤዶም ዞረው ሲሄዱ በመዛላቸው በአምላክና በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። ይሖዋ መርዘኛ እባቦች በመላክ ቀጣቸው። በዚህ ጊዜም ሙሴ ጣልቃ ገብቶ ይሖዋን ለመነላቸው፤ አምላክ ሙሴ የናስ እባብ እንዲሠራና በእንጨት ላይ እንዲሰቅለው ከዚያም በእባብ የተነደፉት የናሱን እባብ ተመልክተው እንዲድኑ አደረገ። የናሱ እባብ ኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል እንደሚሰቀል የሚያመለክት ነው። (ዮሐንስ 3:14, 15) እስራኤላውያን የአሞራውያንን ነገሥታት ሴዎንንና ዐግን ድል አድርገው መሬታቸውን ወረሱ።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
12:1—ማርያምና አሮን በሙሴ ላይ ያጉረመረሙት ለምን ነበር? ለማጉረምረም ያነሳሳቸው ዋነኛ ምክንያት ማርያም በሕዝቡ ዘንድ ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት የነበራት ፍላጎት ሳይሆን አይቀርም። በምድረ በዳ እያሉ የሙሴ ሚስት ሲፓራ መጥታ እንደገና አብረው መኖር ሲጀምሩ ማርያም በሰፈሩ ውስጥ የነበራትን ተሰሚነት እንዳታጣ ፈርታ ሊሆን ይችላል።—ዘፀአት 18:1-5
12:9-11—ማርያም ብቻ በለምጽ የተመታችው ለምንድን ነው? ማርያም ዓመፁን በመቆስቆስ አሮንም እንዲተባበራት ሳታግባባው አልቀረችም። አሮን ጥፋቱን በማመን ትክክለኛ ዝንባሌ እንዳለው አሳይቷል።
21:14, 15—እዚህ ላይ የተገለጸው መጽሐፍ ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ለጽሑፋቸው ምንጭ አድርገው የተጠቀሙባቸው የተለያዩ መጻሕፍት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተጠቅሰዋል። (ኢያሱ 10:12, 13፤ 1 ነገሥት 11:41፤ 14:19, 29) ‘የእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ’ ከእነዚህ መጻሕፍት አንዱ ነው። የይሖዋ ሕዝቦች ስላከናወኗቸው ጦርነቶች የሚገልጽ ታሪካዊ ዘገባ ይዟል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
11:27-29፦ ሌሎች በይሖዋ አገልግሎት መብት ሲያገኙ ሊኖረን በሚገባው አመለካከት ረገድ ሙሴ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ሙሴ ለራሱ ክብር በመፈለግ ከመቅናት ይልቅ ኤልዳድና ሞዳድ ትንቢት በመናገራቸው ተደስቷል።
12:2, 9, 10፤ 16:1-3, 12-14, 31-35, 41, 46-50፦ ይሖዋ እርሱ ሥልጣን ለሰጣቸው ሰዎች አክብሮት እንዲኖረን ይፈልጋል።
14:24፦ ዓለም መጥፎ ነገር እንድንፈጽም የሚያደርግብንን ግፊት ለመቋቋም የሚረዳው አንዱ ቁልፍ “የተለየ መንፈስ” ወይም አስተሳሰብ ማዳበር ነው። ከዓለም የተለየ መንፈስ ሊኖረን ይገባል።
15:37-41፦ በእስራኤላውያን ልብስ ላይ ለየት ያለ ዘርፍ የተደረገው ለይሖዋ አምልኮ የተለዩ እንደሆኑና ትእዛዛቱን ሊያከብሩ እንደሚገባ እንዲያስታውሳቸው ተብሎ ነበር። እኛም በአምላክ መሥፈርቶች በመመራት ከዓለም የተለየን መሆን አይገባንም?
በሞዓብ ሜዳ
እስራኤላውያን በሞዓብ ሜዳ ላይ ሲሰፍሩ ሞዓባውያን በፍርሃት ተዋጡ። በዚህም የተነሳ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ እስራኤላውያንን እንዲረግምለት በለዓምን ቀጠረ። ሆኖም ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲመርቃቸው አደረገው። ሞዓባውያን በዚህ ሳይወሰኑ የእስራኤልን ወንዶች በሥነ ምግባር ብልግናና በጣዖት አምልኮ ለማጥመድ በሞዓባውያንና ምድያማውያን ሴቶች ተጠቀሙ። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ኃጢአት የሠሩትን 24,000 የሚያህሉ ሰዎች አጠፋቸው። መቅሰፍቱ ያቆመው ፊንሐስ ለይሖዋ እንደሚቀና የሚያሳይ እርምጃ ከወሰደ በኋላ ነበር።
ሁለተኛው የሕዝብ ቆጠራ ከኢያሱና ከካሌብ በቀር በመጀመሪያው የሕዝብ ቆጠራ ከነበሩት ወንዶች ማንም እንዳልተረፈ የሚያረጋግጥ ነበር። ኢያሱ በሙሴ እግር እንዲተካ ተሾመ። እስራኤላውያን የተለያዩ መሥዋዕቶችን እንዴት እንደሚያቀርቡና ስዕለትን አስመልክቶ መመሪያ ተሰጣቸው። ከዚህም በላይ እስራኤላውያን ምድያማውያንን ተበቀሉ። ሮቤል፣ ጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምስራቅ ርስታቸውን ተቀበሉ። እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ስለሚሻገሩበት መንገድና ምድሪቱን እንዴት እንደሚወርሱ ተነገራቸው። ስለ ተስፋይቱ ምድር ድንበር ዝርዝር መግለጫ የተሰጣቸው ከመሆኑም በላይ የርስት ክፍፍል በዕጣ እንደሚካሄድ ተገለጸ። ለሌዋውያን 48 ከተሞች የተሰጧቸው ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 6ቱ የመማጸኛ ከተሞች እንዲሆኑ ተደረገ።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
22:20-22—ይሖዋ በበለዓም ላይ የተቆጣው ለምን ነበር? ይሖዋ ነቢዩ በለዓም እስራኤላውያንን መርገም እንደሌለበት ነግሮት ነበር። (ዘኍልቍ 22:12) ሆኖም ነቢዩ እስራኤላውያንን ለመርገም በማሰብ ባላቅ ከላካቸው ሰዎች ጋር ሄደ። በለዓም የሞዓባውያኑን ንጉሥ ለማስደሰትና በምላሹ ጥቅም ለማግኘት ፈልጎ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:15, 16፤ ይሁዳ 11) በለዓም እስራኤላውያንን ከመርገም ይልቅ ለመመረቅ ቢገደድም እንኳ የንጉሡን ሞገስ ለማግኘት ሲል በዓል አምላኪ የሆኑት ሴቶች የእስራኤልን ወንዶች እንዲያስቱ ሐሳብ አቀረበ። (ዘኍልቍ 31:15, 16) አምላክ በበለዓም ላይ የተቆጣው ስለራሱ ጥቅም ብቻ የሚያስብ ስግብግብ በመሆኑ ነበር።
30:6-8—አንድ ክርስቲያን ባል የሚስቱን ስዕለት ማስቀረት ይችላል? በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚያደርጉትን ስዕለት የሚመለከተው በግለሰብ ደረጃ ነው። ለአብነት ያህል፣ ራስን ለይሖዋ መወሰን አንድ ሰው በግሉ የሚያደርገው ስዕለት ነው። (ገላትያ 6:5) አንድ ባል እንዲህ ያለውን ስዕለት የማስቀረት ሥልጣን የለውም። ሚስትም ብትሆን ከአምላክ ቃል ወይም ለባሏ ካለባት ኃላፊነት ጋር የሚጋጭ ስዕለት ማድረግ አይኖርባትም።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
25:11፦ ፊንሐስ ለይሖዋ አምልኮ ቅንዓት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! ከባድ የፆታ ብልግና መፈጸሙን ብናውቅ የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ ስንል ጉዳዩን ለክርስቲያን ሽማግሌዎች ልንናገር አይገባንምን?
35:9-29፦ ሳያስበው ነፍስ ያጠፋ ሰው ለተወሰነ ጊዜ ቤቱን ለቅቆ ወደ መማጸኛ ከተማ እንዲሸሽ መደረጉ ሕይወት ቅዱስ እንደሆነና በአክብሮት ልንይዘው እንደሚገባ ያስተምረናል።
35:33፦ በንጹሐን ደም የረከሰች ምድር ስርየት ሊደረግላት የሚችለው ደም ባፈሰሱት ሰዎች ደም ብቻ ነው። ይሖዋ ምድርን ወደ ገነትነት ከመለወጡ በፊት ክፉዎችን የሚያጠፋ መሆኑ ምንኛ ተገቢ ነው!—ምሳሌ 2:21, 22፤ ዳንኤል 2:44
የአምላክ ቃል ኃይል አለው
ለይሖዋና በሕዝቡ መካከል በኃላፊነት ለሾማቸው ሰዎች አክብሮት ሊኖረን ይገባል። የዘኍልቍ መጽሐፍ ይህንን ሐቅ ይበልጥ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ይህም በዛሬው ጊዜ የጉባኤውን ሰላምና አንድነት ለመጠበቅ መጣር እንዳለብን የሚያሳይ ግሩም ትምህርት ነው!
በዘኍልቍ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ዘገባዎች መንፈሳዊነታቸውን ችላ የሚሉ ሰዎች እንደ ማጉረምረም፣ የሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም ጣዖት አምልኮ ባሉት ኃጢአቶች በቀላሉ ሊወድቁ እንደሚችሉ ያሳያሉ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በተገለጹት አንዳንድ ምሳሌዎችና ትምህርቶች ላይ ተመሥርቶ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ በሚካሄደው የአገልግሎት ስብሰባ ፕሮግራም ላይ ለጉባኤው እንደሚያስፈልግ ተጠቀሙበት የሚለውን ክፍል ማቅረብ ይቻላል። በእርግጥም “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና [በሕይወታችን ውስጥ] የሚሠራ ነው።”—ዕብራውያን 4:12
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ይሖዋ በማደሪያው ድንኳን ላይ በተዓምር ደመና እንዲኖር በማድረግ እስራኤላውያን ጉዞ የሚጀምሩበትንና የሚሰፍሩበትን ጊዜ ይጠቁማቸው ነበር
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ልንታዘዘው የሚገባ ከመሆኑም በላይ ወኪሎቹን እንድናከብራቸው ይጠብቅብናል
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በኪዳነ ወልድ ክፍሌ በተዘጋጀው ግዕዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት መሠረት በግዕዝ “ኊልቍ” ማለት “ቍጥር” ማለት ነው።