‘በይሖዋ ሕግ’ ደስ ትሰኛለህ?
‘በይሖዋ ሕግ’ ደስ ትሰኛለህ?
‘በይሖዋ ሕግ ደስ የሚሰኝ ሰው ደስተኛ ነው።’—መዝሙር 1:1, 2
1. የይሖዋ አገልጋዮች መሆናችን ደስታ ያስገኘልን እንዴት ነው?
ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን ይደግፈናል እንዲሁም ይባርከናል። እርግጥ የተለያዩ መከራዎች ያጋጥሙናል፤ ሆኖም እውነተኛ ደስታ አለን። የምናመልከው ‘ደስተኛውን አምላክ’ በመሆኑና ቅዱስ መንፈሱ ይህን ባሕርይ እንድናፈራ ስለሚረዳን ደስተኛ መሆናችን የሚያስደንቅ አይደለም። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW፤ ገላትያ 5:22) ደስታ ጥሩ ነገር በማግኘት ወይም አገኛለሁ ብሎ ተስፋ በማድረግ የሚፈጠር ከልብ የመነጨ ስሜት ነው። በሰማይ የሚኖረው አባታችን ደግሞ በጎ ወይም ጥሩ ስጦታዎችን እንደሚሰጠን የታወቀ ነው። (ያዕቆብ 1:17) በእርግጥም ደስተኛ መሆናችን ምንም አያስገርምም!
2. የትኞቹን መዝሙራት እንመረምራለን?
2 በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ደስታ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። መዝሙር 1 እና 2 ለዚህ ምሳሌ ይሆኑናል። የኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያዎቹ ተከታዮች ሁለተኛውን መዝሙር ያቀናበረው የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት መሆኑን ገልጸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 4:25, 26) በስም ያልተጠቀሰው የመጀመሪያው መዝሙር አቀናባሪ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈውን ይህን መዝሙር የከፈተው “በክፉዎች ምክር የማይሄድ . . . ሰው ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” በማለት ነበር። (መዝሙር 1:1) በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ በመዝሙር 1 እና 2 ላይ የሚገኙትን ለደስታ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች እንመረምራለን።
ደስታ የሚገኝበት ምስጢር
3. በመዝሙር 1:1 መሠረት የአምላክን ሕግ የሚጠብቅ ሰው ደስተኛ እንዲሆን የሚያስችሉት አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
3 መዝሙር 1 የአምላክን ሕግ የሚጠብቅ ሰው ለምን ደስተኛ እንደሚሆን ይገልጻል። መዝሙራዊው እንዲህ ብሎ በመዘመር አንዳንድ ምክንያቶችን ገልጿል፦ “በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣ በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ ሰው ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው።”—መዝሙር 1:1
4. ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ምሳሌ የሚሆን እንዴት ያለ አካሄድ ተከትለዋል?
4 እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ይሖዋ ያወጣቸውን የጽድቅ መሥፈርቶች መጠበቅ ይገባናል። የመጥምቁ ዮሐንስ ወላጆች የመሆን አስደሳች መብት አግኝተው የነበሩት ዘካርያስና ኤልሳቤጥ “የጌታን ትእዛዝና ሥርዐት ሁሉ ጠብቀው ያለ ነቀፋ የሚኖሩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ።” (ሉቃስ 1:5, 6) እኛም ተመሳሳይ አካሄድ የምንከተል እንዲሁም ‘በክፉዎች ምክር ላለመሄድ’ ቁርጥ አቋም የምንይዝ ወይም በመጥፎ ምክራቸው የማንመራ ከሆነ ደስተኞች እንሆናለን።
5. ‘ከኀጢአተኞች መንገድ’ እንድንርቅ ምን ሊረዳን ይችላል?
5 የክፉዎችን አስተሳሰብ የምንቃወም ከሆነ ‘በኀጢአተኞች መንገድ አንቆምም።’ እንዲያውም ክፉዎች ወደሚያዘወትሩት ሥፍራ ይኸውም ሥነ ምግባር የጎደለው መዝናኛ ወደሚቀርብባቸው ወይም በመጥፎ ስም ወደሚታወቁ ቦታዎች አንሄድም። ኃጢአተኞች የሚያንጸባርቁትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ ባሕርይ እንድንከተል ብንፈተንስ? ከሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዐመፅ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ብርሃንስ ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ተስማምተን ለመኖር አምላክ እንዲረዳን እንጸልይ። (2 ቆሮንቶስ 6:14) በአምላክ ከታመንንና ‘ልባችን ንጹሕ’ ከሆነ የኃጢአተኞችን ዝንባሌና አኗኗር የምንጸየፍ ከመሆኑም በላይ ንጹሕ የልብ ዝንባሌና ፍላጎት እንዲሁም ‘እውነተኛ እምነት’ ይኖረናል።—ማቴዎስ 5:8፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:5
6. ፌዘኞችን በሚመለከት ጥንቃቄ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
6 ይሖዋን ለማስደሰት የምንፈልግ ከሆነ ‘በፌዘኞች ወንበር መቀመጥ እንደማይገባን’ የታወቀ ነው። አንዳንዶች የአምላክን ቃል በሚጠብቁ ሰዎች ላይ ያፌዛሉ። ይሁንና በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ ቀድሞ ክርስቲያን የነበሩ ከሃዲዎች የሚሰነዝሩት ፌዝ ከሁሉ የከፋ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት የእምነት ባልንጀሮቹን አስጠንቅቋል፦ “ወዳጆች ሆይ፤ . . . ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ዕወቁ፤ በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ። እነርሱም ‘“እመጣለሁ” ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል’ ይላሉ።” (2 ጴጥሮስ 3:1-4) ‘በፌዘኞች ወንበር ፈጽሞ የማንቀመጥ ከሆነ’ ከሚደርስባቸው ጥፋት እንድናለን።—ምሳሌ 1:22-27
7. በመዝሙር 1:1 ላይ የሚገኙትን ቃላት ተግባራዊ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
7 የመዝሙር 1 የመክፈቻ ቃላት የያዙትን መልእክት ተግባራዊ የማናደርግ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የገነባነው መንፈሳዊነት የእንቧይ ካብ ሊሆንብን ይችላል። እንዲያውም የባሰ ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን። የክፉዎችን ምክር የምንከተል ከሆነ መንፈሳዊ እድገታችን ማሽቆልቆል ሊጀምር ይችላል። ከዚያም ከእነርሱ ጋር አዘውትረን መገናኘት እንጀምር ይሆናል። ውሎ አድሮ እኛም ራሳችን ከሃዲዎች ሆነን በእውነት ላይ ማፌዝ ልንጀምር እንችላለን። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ከክፉዎች ጋር መወዳጀት በውስጣችን መጥፎ መንፈስ ሊዘራብንና ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ሊያበላሽብን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ያዕቆብ 4:4) እንዲህ ያለ ነገር እንዳይደርስብን እንጠንቀቅ!
8. አእምሯችን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ እንዲያተኩር ምን ሊረዳን ይችላል?
8 ጸሎት አእምሯችን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩርና ከክፉዎች ጋር ባልንጀርነት ከመመሥረት እንድንቆጠብ ይረዳናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” ከዚህም በላይ እውነት፣ ክቡር፣ ትክክል፣ ንጹሕ፣ ተወዳጅና መልካም የሆኑትን እንዲሁም በጎነትና ምሥጋና ያለባቸውን ነገሮች እንድናስብ አበረታቶናል። (ፊልጵስዩስ 4:6-8) ከጳውሎስ ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ እንኑር፤ እንዲሁም ክፉ ሰዎችን አንምሰል።
9. ከክፉ ድርጊቶች የምንርቅ ቢሆንም ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ለመርዳት የምንጥረው እንዴት ነው?
9 ከክፉ ድርጊቶች የምንርቅ ቢሆንም ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮማዊው አገረ ገዥ ለፊልክስ “ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ፍርድ” መሥክሮለት እንደነበረው እኛም ለሌሎች በዘዴ እንመሠክራለን። (የሐዋርያት ሥራ 24:24, 25፤ ቆላስይስ 4:6) የመንግሥቱን ምሥራች ለሁሉም ዓይነት ሰዎች የምንመሠክር ከመሆኑም በላይ ደግነት እናሳያቸዋለን። ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ’ ሰዎች አማኞች እንደሚሆኑና በአምላክ ሕግ ደስ እንደሚሰኙ እርግጠኞች ነን።—የሐዋርያት ሥራ 13:48
በይሖዋ ሕግ ደስ ይሰኛል
10. የምናነበው ነገር በአእምሯችንና በልባችን ላይ እንዲቀረጽ ምን ሊረዳን ይችላል?
10 መዝሙራዊው ደስተኛ የሆነውን ሰው በሚመለከት “ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል [“ድምፁን አውጥቶ ያነባል፣”NW]” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። (መዝሙር 1:2) የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ‘በይሖዋ ሕግ ደስ እንሰኛለን።’ የሚቻል ከሆነ የግል ጥናት በምናደርግበትና በምናሰላስልበት ወቅት ‘ድምፃችንን አውጥተን’ ማንበብ እንችላለን። ማንኛውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በምናነብበት ጊዜ እንደዚህ ማድረጋችን መልእክቱ በአእምሯችንና በልባችን ላይ እንዲቀረጽ ይረዳናል።
11. መጽሐፍ ቅዱስን “በቀንና በሌሊት” ማንበብ የሚገባን ለምንድን ነው?
11 “ታማኝና ልባም ባሪያ” መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንድናነብ ማበረታቻ ሲሰጠን ቆይቷል። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ይሖዋ ለሰው ልጆች ያስጻፈውን መልእክት በጥልቅ የማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ስላለን መጽሐፍ ቅዱስን “በቀንና በሌሊት” አንዳንዴም በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ እንቅልፍ አልወስድ በሚለን ጊዜም እንኳ ማንበባችን ጠቃሚ ነው። ጴጥሮስ “በድነታችሁ እንድታድጉ፣ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ” በማለት አሳስቦናል። (1 ጴጥሮስ 2:1, 2) አንተስ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ እንዲሁም ሌሊት ሌሊት በቃሉና በዓላማዎቹ ላይ ማሰላሰል ያስደስትሃል? መዝሙራዊው የአምላክን ቃል በቀንና በሌሊት ያነብብ ነበር።—መዝሙር 63:6
12. በይሖዋ ሕግ የምንደሰት ከሆነ ምን እናደርጋለን?
12 ለዘላለም ተደስተን መኖራችን የተመካው በአምላክ ሕግ ደስ በመሰኘታችን ላይ ነው። ሕጉ ፍጹምና ትክክል ከመሆኑም በላይ እርሱን መጠበቅ ይህ ነው የማይባል ወሮታ ያስገኛል። (መዝሙር 19:7-11) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ ተመልክቶ የሚጸና፣ የሰማውን የሚያደርግና የማይረሳ ሰው በሥራው የተባረከ ይሆናል” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 1:25) በይሖዋ ሕግ ከልብ የምንደሰት ከሆነ በየዕለቱ ለመንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት እንሰጣለን። በእርግጥም ‘የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ለመመርመርና’ በሕይወታችን ውስጥ ለመንግሥቱ ጉዳዮች ቅድሚያ ለመስጠት እንገፋፋለን።—1 ቆሮንቶስ 2:10-13፤ ማቴዎስ 6:33
እንደ ዛፍ ነው
13-15. ፈጽሞ በማይደርቅ ውሃ ዳር እንደሚገኝ ዛፍ ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?
13 መዝሙራዊው ቀና ስለሆነ ሰው እንዲህ በማለት ተጨማሪ ሐሳብ ተናግሯል፦ “እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” (መዝሙር 1:3) የይሖዋ አገልጋዮች የሆንነው እኛም ፍጽምና እንደሚጎድላቸው ሌሎች ሰዎች ሁሉ በሕይወታችን ውስጥ ችግሮች ያጋጥሙናል። (ኢዮብ 14:1) በእምነታችን ምክንያት ስደትና ሌሎች የተለያዩ መከራዎች ይደርሱብን ይሆናል። (ማቴዎስ 5:10-12) ይሁን እንጂ ጠንካራ ዛፍ ኃይለኛ ንፋስ እንደሚቋቋም ሁሉ እኛም በአምላክ እርዳታ እነዚህን ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ መቋቋም እንችላለን።
14 ውሃ ዳር የተተከለ ዛፍ በሞቃት ወራትም ሆነ በድርቅ ዘመን የመጠውለግ አደጋ አያጋጥመውም። እኛም አምላክን የምንፈራ ከሆነ ይሖዋ አምላክ ፈጽሞ የማይነጥፍ የብርታት ምንጭ ይሆንልናል። ጳውሎስ በአምላክ ይተማመን ስለነበር “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ [በይሖዋ] ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” በማለት ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 4:13) የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ አመራርና መንፈሳዊ ድጋፍ ካገኘን ፍሬ ቢስ ወይም በመንፈሳዊ ሙት ሆነን ከስመን አንጠፋም። በአምላክ አገልግሎት ፍሬያማ ከመሆናችንም በላይ የመንፈሱን ፍሬዎች እናንጸባርቃለን።—ኤርምያስ 17:7, 8፤ ገላትያ 5:22, 23
15 መዝሙራዊው “እንደ” የሚል ትርጉም ያለውን የዕብራይስጥ ቃል በመጠቀም ተመሳሳይ ባሕርይ ያላቸውን ሁለት የተለያዩ ነገሮች አነጻጽሯል። ሰዎችና ዛፎች የተለያዩ ነገሮች ናቸው፤ ሆኖም መዝሙራዊው ውሃ ዳር ያለን አንድ ያማረ ዛፍ ሲያይ ‘በይሖዋ ሕግ ደስ የሚሰኙ’ ሰዎች የሚያገኙትን መንፈሳዊ ብልጽግና አስታውሶ ሊሆን ይችላል። እኛም በአምላክ ሕግ የምንደሰት ከሆነ ዕድሜያችን እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናል። እንዲያውም ለዘላለም እንኖራለን።—ዮሐንስ 17:3
16. ‘የምንሠራው ሁሉ የሚከናወንልን’ ለምንድን ነው?
16 ቀና በሆነ ጎዳና ላይ መጓዛችንን በቀጠልን መጠን ይሖዋ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንድንቋቋም ይረዳናል። ይሖዋን ማገልገላችን ደስታና ፍሬ አስገኝቶልናል። (ማቴዎስ 13:23፤ ሉቃስ 8:15) በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛው ግባችን የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ስለሆነ ‘የምንሠራው ሁሉ ይከናወንልናል።’ የይሖዋ ዓላማ ምንጊዜም ፍጻሜውን ስለሚያገኝና እኛም በትእዛዛቱ ደስ ስለምንሰኝ በመንፈሳዊ እንበለጽጋለን። (ዘፍጥረት 39:23፤ ኢያሱ 1:7, 8፤ ኢሳይያስ 55:11) የተለያዩ መከራዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—መዝሙር 112:1-3፤ 3 ዮሐንስ 2
ክፉዎች የተሳካላቸው ይመስላሉ
17, 18. (ሀ) መዝሙራዊው ክፉዎችን በምን መስሏቸዋል? (ለ) ክፉዎች በቁሳዊ ነገሮች ቢበለጽጉም ዘላቂ ዋስትና የሌላቸው ለምንድን ነው?
17 የክፉዎች ዕጣ ፈንታ ከጻድቃን ምንኛ የተለየ ነው! ክፉዎች ለጊዜው በቁሳዊ ነገሮች የተሳካላቸው መስለው ይታዩ ይሆናል፤ በመንፈሳዊ ግን ድሆች ናቸው። መዝሙራዊው ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት ይህን በግልጽ ያሳያሉ፦ “ክፉዎች ግን እንዲህ አይደሉም፤ ነገር ግን ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው፣ ገለባ ናቸው። ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ ፊት፣ ኀጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር መቆም አይችሉም።” (መዝሙር 1:4, 5) መዝሙራዊው “ክፉዎች ግን እንዲህ አይደሉም” እንዳለ ልብ በል። ይህን ሲል ክፉዎች ፍሬያማ በሆነ እንዲሁም ረጅም ዕድሜ ባለው ዛፍ እንደተመሰሉትና የአምላክን ትእዛዛት እንደሚወዱት ሰዎች አይደሉም ማለቱ ነው።
18 ክፉዎች በቁሳዊ ቢበለጽጉም ዘላቂ ዋስትና የላቸውም። (መዝሙር 37:16፤ 73:3, 12) እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ኢየሱስ ውርስ እንዲያከፋፍል በተጠየቀ ጊዜ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ ከጠቀሰው ማስተዋል የጎደለው ሃብታም ሰው ጋር ይመሳሰላሉ። ኢየሱስ በዚያ የነበሩትን ሰዎች “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ ስላልሆነ፣ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ራሳችሁን ጠብቁ” አላቸው። ከዚያም ይህን ነጥብ ግልጽ ለማድረግ አንድ ሀብታም ሰው እርሻው እጅግ ፍሬያማ ስለሆነለት የነበሩትን ጎተራዎች አፍርሶ ሌሎች ሰፋፊ ጎተራዎች ለመሥራት እንዳቀደ የሚገልጽ ምሳሌ ተናገረ። ሰውየው ቁጭ ብሎ ሲበላና ሲጠጣ እንዲሁም ራሱን ሲያስደስት ታየው። አምላክ ግን “አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊ[ወ]ስዱ ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል?” አለው። ኢየሱስ ነጥቡን ለማጉላት ስለፈለገ አክሎ እንዲህ አለ፦ “ስለዚህ ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።”—ሉቃስ 12:13-21
19, 20. (ሀ) በጥንቷ እስራኤል እህል የሚወቃውና ፍሬው ከገለባው የሚለየው እንዴት እንደሆነ ግለጽ። (ለ) ክፉዎች በገለባ የተመሰሉት ለምንድን ነው?
19 ክፉዎች “በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም” አይደሉም። በመሆኑም ከገለባ የተሻለ ደኅንነትና መረጋጋት የላቸውም። በጥንቷ እስራኤል እህል ከታጨደ በኋላ ብዙውን ጊዜ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ወደሚዘጋጅ አውድማ ይጋዛል። ከዚያም አገዳው እንዲሰባበርና እህሉ ከገለባው እንዲለቅ ከብቶች ተጠምደው ሹል ድንጋይ ወይም ጥርስ ያለው ብረት እንዲጎትቱበት ይደረጋል። ቀጥሎ የተወቃው እህል በመንሽ ወደ ላይ እየተበተነ ለነፋስ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 30:24) ፍሬው ተመልሶ አውድማው ላይ ሲያርፍ ጭዱን ግን ነፋሱ ወደ ጎን ገለል ያደርገዋል፤ ገለባውን ደግሞ ጠራርጎ ይወስደዋል። (ሩት 3:2) በመጨረሻ እህሉ ተነፍቶ ወይም ተበጥሮ አፈር ወይም ሌሎች የማይፈለጉ ነገሮች ከወጡለት በኋላ ጎተራ ይገባል አሊያም ይፈጫል። (ሉቃስ 22:31) ገለባው ግን በነፋስ ተወስዷል።
20 ገለባው በነፋስ ሲወሰድ እህሉ እንደሚቀር ሁሉ ክፉዎች ሲጠፉ ጻድቃን ይተርፋሉ። እንደነዚህ ያሉ ክፉ አድራጊዎች በቅርቡ ለዘላለም እንደሚወገዱ ማወቃችን እንደሚያስደስተን የታወቀ ነው። እነርሱ ከተወገዱ በኋላ በይሖዋ ሕግ ደስ የሚሰኙ ሰዎች ታላቅ በረከት ያገኛሉ። በእርግጥም ታዛዥ የሆኑ ሰዎች የአምላክ የጸጋ ስጦታ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ይወርሳሉ።—ማቴዎስ 25:34-46፤ ሮሜ 6:23
‘የጻድቃን መንገድ’ የተባረከ ነው
21. ይሖዋ ‘ጻድቃንን የሚያውቃቸው’ እንዴት ነው?
21 የመጀመሪያው መዝሙር የሚደመደመው “እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ይጠብቃልና [“ያውቃልና፣” የ1954 ትርጉም]፤ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች” በሚሉት ቃላት ነው። (መዝሙር 1:6) አምላክ ‘የጻድቃንን መንገድ የሚያውቀው’ እንዴት ነው? ቀና በሆነው መንገድ ላይ የምንጓዝ ከሆነ በሰማይ የሚኖረው አባታችን ሕጎቹን በሕይወታችን ተግባራዊ ስናደርግ እንደሚመለከተንና አገልጋዮቹ አድርጎ እንደሚቆጥረን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንግዲያው እርሱ በእርግጥ እንደሚያስብልን በመተማመን የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል እንችላለን፤ ደግሞም እንደዚያ ማድረግ ይኖርብናል።—ሕዝቅኤል 34:11፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7
22, 23. ክፉዎች ምን ይደርስባቸዋል? ጻድቃንስ ምን ያገኛሉ?
22 ‘የጻድቃን መንገድ’ ለዘላለም ይኖራል፤ ፈጽሞ የማይታረሙ ክፉ ሰዎች ግን ይሖዋ ስለሚፈርድባቸው ይጠፋሉ። ‘መንገዳቸውም’ ወይም አኗኗራቸውም እንዲሁ አብሯቸው ያከትማል። የሚከተሉት የዳዊት ቃላት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ትምክህት ሊኖረን ይችላል፦ “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:10, 11, 29
23 ክፉዎች ከተወገዱ በኋላ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር መብት ስናገኝ ምንኛ እንደሰታለን! በዚያን ጊዜ ገሮችና ጻድቃን ሁልጊዜ ‘በይሖዋ ሕግ’ ደስ ስለሚሰኙ እውነተኛ ሰላም ያገኛሉ። ከዚያ በፊት ግን ‘የይሖዋ ሕግ’ መፈጸም ይኖርበታል። (መዝሙር 2:7ሀ) የሚቀጥለው ርዕስ ይህ ሕግ ምን እንደሆነና ለእኛም ሆነ ለመላው የሰው ዘር ምን ትርጉም እንዳለው እንድንገነዘብ ያስችለናል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የአምላክን ሕግ የሚጠብቅ ሰው ደስተኛ የሆነው ለምንድን ነው?
• የይሖዋ ሕግ ለደስታችን ምክንያት እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?
• አንድ ሰው በውሃ ዳር እንደተተከለ ዛፍ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
• የጻድቃን መንገድ ከክፉዎች የሚለየው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጸሎት ከክፉዎች ጋር እንዳንወዳጅ ይረዳናል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጻድቅ ሰው በዛፍ የተመሰለው ለምንድን ነው?