የዘፍጥረት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1
የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የዘፍጥረት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1
“ዘፍጥረት” ማለት “ምንጭ” ወይም “ልደት” ማለት ነው። የአጽናፈ ዓለሙን አፈጣጠር፣ ምድር ለሰው ዘር መኖሪያነት እንዴት እንደተዘጋጀችና የሰው ልጅ በምድር ላይ መኖር የጀመረው እንዴት እንደሆነ ለሚተርክ መጽሐፍ ይህ ተስማሚ ስም ነው። ሙሴ ይህንን መጽሐፍ የጻፈው በሲና በረሃ እያሉ ሲሆን መጽሐፉን ጽፎ የጨረሰው በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሳይሆን አይቀርም።
የዘፍጥረት መጽሐፍ ከጥፋት ውኃ በፊት ስለነበረው ዓለም፣ ከጥፋት ውኃው በኋላ ባለው ዘመን ምን እንደተፈጸመ እንዲሁም ይሖዋ አምላክ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅ፣ ከያዕቆብና ከዮሴፍ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ይነግረናል። በዚህ ርዕስ ሥር ከዘፍጥረት 1:1 እስከ 11:9 ማለትም ይሖዋ ከፓትርያርኩ ከአብርሃም ጋር መነጋገር እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ ባሉት ምዕራፎች ውስጥ የሚገኙት ጎላ ያሉ ነጥቦች ይብራራሉ።
ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረው ዓለም
“በመጀመሪያ” የሚለው የዘፍጥረት መጽሐፍ የመክፈቻ ቃል በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተፈጸመ ክንውንን ያመለክታል። በስድስቱ የፍጥረት “ቀናት” ወይም አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች በተከናወኑባቸው ጊዜያት የተፈጸሙት ነገሮች በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈሩት በምድር ላይ ሰው ቢኖር ኖሮ በሚገልጻቸው መንገድ ነው። በስድስተኛው ቀን አምላክ ሰውን ፈጠረ። የሰው ልጅ ባለመታዘዙ ምክንያት ኤደን ገነት ብዙም ሳይቆይ ብትጠፋም ይሖዋ ለሰው ዘር ተስፋ ሰጠ። የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ኃጢአት ያስከተላቸውን መዘዞች ስለሚያስወግድና የሰይጣንን ራስ ስለሚቀጠቅጥ “ዘር” ገለጸ።
ከዚያ በኋላ ባሉት 1,600 ዓመታት ሰይጣን እንደ አቤል፣ ሄኖክና ኖኅ ከመሳሰሉ ጥቂት ታማኝ ሰዎች በስተቀር መላውን የሰው ዘር በአምላክ ላይ ማሳመፅ ቻለ። ለምሳሌ፣ ቃየን ጻድቅ የሆነውን ወንድሙን አቤልን ገደለ። በዚህ ጊዜ “በእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ።” ይህንን ያደረጉት ስሙን በሚያቃልል መንገድ ሳይሆን አይቀርም። ላሜሕ ራሱን ለመከላከል ሲል አንድን ሰው እንደገደለ በመግለጽ ያቀናበረው ግጥም በወቅቱ ዓመጽ ምን ያህል ተስፋፍቶ እንደነበረ ያሳያል። የአምላክን ትእዛዛት የጣሱ መላእክት ሚስቶች ሲያገቡና ኔፊሊም ተብለው የተጠሩ ግዙፍ የሆኑ ዓመጸኛ ልጆች ሲወልዱ ሁኔታዎቹ እየተባባሱ ሄዱ። ያም ሆኖ ታማኙ ኖኅ መርከቡን ከመሥራቱም በላይ ስለመጪው ጥፋት በድፍረት ማስጠንቀቂያ ተናገረ፤ በጥፋቱ ወቅትም ከነቤተሰቡ መትረፍ ቻለ።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
1:16—ብርሃን ሰጪ አካላት የተፈጠሩት በአራተኛው ቀን ከሆነ አምላክ በመጀመሪያው ቀን ብርሃን እንዲኖር እንዴት ማድረግ ይችላል? በቁጥር 16 ላይ “አደረገ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 1, 21 እና 27 ላይ ከተሠራበት “ፈጠረ” ከሚለው ቃል ይለያል። ብርሃን ሰጪ አካላትን የያዘው ‘ሰማይ’ የተፈጠረው ‘አንደኛው ቀን’ ከመጀመሩ ከረዥም ጊዜ በፊት ነው። ሆኖም የእነዚህ አካላት ብርሃን ወደ ምድር አይደርስም ነበር። በመጀመሪያው ቀን “ብርሃንም ሆነ” የተባለው አነስተኛ መጠን ያለው ብርሃን የደመናውን ሽፋን አልፎ በምድር ላይ ስለታየ ነው። በዚህም የተነሳ ምድር ስትሽከረከር ቀንና ሌሊት ይፈራረቁ ጀመር። (ዘፍጥረት 1:1-3, 5) በዚህም ወቅት ቢሆን የብርሃኑ ምንጭ የሆኑት አካላት ምድር ላይ ላለ ተመልካች አይታዩም ነበር። በአራተኛው ቀን ግን ትልቅ ለውጥ ተከናወነ። ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት “በምድር ላይ ያበሩ” ጀመር። (ዘፍጥረት 1:17) ከዚህ በኋላ በምድር ላይ ላለ ተመልካች ስለሚታዩ አምላክ “ብርሃን አደረገ” ሊባል ችሏል።
3:8—ይሖዋ አምላክ አዳምን ያነጋገረው በቀጥታ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው አምላክ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎችን ያነጋግር የነበረው በመላእክት አማካኝነት ነው። (ዘፍጥረት 16:7-11፤ 18:1-3, 22-26፤ 19:1፤ መሳፍንት 2:1-4፤ 6:11-16, 22፤ 13:15-22) የአምላክ ዋነኛ ቃል አቀባይ “ቃል” ተብሎ የተጠራው አንድያ ልጁ ነበር። (ዮሐንስ 1:1) አምላክ አዳምና ሔዋንን ያነጋገራቸው ‘በቃል’ በኩል መሆን አለበት።—ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:16፤ 3:8-13
3:17—ምድር የተረገመችው እንዴት ነበር? እርግማኑ የቆየውስ ለምን ያህል ጊዜ ነው? ምድር መረገሟ ከዚያ በኋላ ለማልማት አስቸጋሪ እንደምትሆን ያመለክታል። ምድር ከተረገመች በኋላ እሾህና አሜከላ የምታበቅል መሆኗ ለአዳም ዘሮች በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ አስከትሎባቸው ስለነበር የኖኅ አባት ላሜህ ‘እግዚአብሔር በረገማት ምድር ልፋታችንና የጉልበታችን ድካም’ በማለት ተናግሯል። (ዘፍጥረት 5:29 አ.መ.ት) ከጥፋት ውኃው በኋላ ይሖዋ ኖኅና ልጆቹን የባረካቸው ከመሆኑም በላይ ምድር በሰው ዘር እንድትሞላ ያለውን ዓላማ ገልጾላቸዋል። (ዘፍጥረት 9:1) በመሆኑም አምላክ በምድር ላይ የተናገረው እርግማን የተነሳ ይመስላል።—ዘፍጥረት 13:10
4:15—ይሖዋ ‘ለቃየን ምልክት ያደረገለት’ በምን መንገድ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በቃየን ሰውነት ላይ በምንም መልኩ ምልክት እንደተደረገ አይናገርም። ምልክቱ በብቀላ እንዳይገደል ለመከላከል የተደነገገ ሌሎች የሚያውቁትና የሚያከብሩት ጠንከር ያለ ትእዛዝ ሳይሆን አይቀርም።
4:17—ቃየን ሚስት ያገኘው ከየት ነው? አዳም ‘ወንዶችንም ሴቶችንም ወልዷል።’ (ዘፍጥረት 5:4) በመሆኑም ቃየን ያገባው ከእህቶቹ አሊያም ከእህቶቹ ወይም ከወንድሞቹ ልጆች አንዷን ሊሆን ይችላል። ቆየት ብሎ አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ በሥጋ ወንድምና እህት መካከል የሚደረገውን ጋብቻ ከልክሏል።—ዘሌዋውያን 18:9
5:24—አምላክ ‘ሄኖክን የወሰደው’ እንዴት ነበር? ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ሄኖክ በሰዎች እጅ የመገደል አደጋ ተደቅኖበት ነበር፤ ሆኖም አምላክ በጠላቶቹ እጅ እንዲሰቃይ አልፈለገም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሄኖክ ሞትን እንዳያይ . . . ተወሰደ” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 11:5) ይህ ሲባል ግን አምላክ ወደ ሰማይ ወስዶት በዚያ መኖር ቀጥሏል ማለት አይደለም። ወደ ሰማይ ያረገው የመጀመሪያው ሰው ኢየሱስ ነው። (ዮሐንስ 3:13፤ ዕብራውያን 6:19, 20) “ሄኖክ ሞትን እንዳያይ . . . ተወሰደ” መባሉ አምላክ፣ ሄኖክ በተመስጦ ትንቢታዊ ራእይ እንዲመለከትና በዚያው እንዲያንቀላፋ አድርጎታል ማለት ሊሆን ይችላል። ይህ ከሆነ ሄኖክ አልተሰቃየም ወይም በጠላቶቹ እጅ ‘ሞትን አላየም።’
6:6—ይሖዋ ሰውን በመፍጠሩ “ተጸጸተ” ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው? እዚህ ላይ “ተጸጸተ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የአመለካከት ወይም የዓላማ ለውጥ ማድረግን ያመለከታል። ይሖዋ ፍጹም በመሆኑ ሰውን በመፍጠሩ አልተሳሳተም። ሆኖም ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረውን ክፉ ኅብረተሰብ በተመለከተ አመለካከቱን ለውጧል። አምላክ የሰው ልጆች በሚሠሩት ክፋት ከማዘኑ የተነሳ ፈጣሪያቸው እንደመሆኑ የነበረውን አመለካከት በመለወጥ አጥፊያቸው ሆኗል። ጥቂት የሰው ዘሮች እንዲተርፉ ማድረጉ ጸጸት የተሰማው በክፉዎቹ ሰዎች ላይ መሆኑን ያሳያል።—2 ጴጥሮስ 2:5, 9
7:2—ንጹህ የሆኑና ያልሆኑ እንስሳትን ለመለየት የተሠራበት መሥፈርት ምንድን ነው? ንጹህ በሆኑና ባልሆኑ እንስሳት መካከል ልዩነት የተደረገው በአምልኮ ለመሥዋዕትነት ለሚቀርቡ እንስሳት እንጂ የሚበሉትንና የማይበሉትን እንስሳት ለመለየት አይደለም። ከጥፋት ውኃው በፊት ሰዎች የእንስሳት ሥጋ አይበሉም ነበር። ከምግብ ጋር በተያያዘ “ንጹህ” እና “ርኩስ” የሚለው ልዩነት የመጣው የሙሴ ሕግ ከተሰጠ በኋላ ሲሆን ሕጉ ሲወገድ ይህ ትእዛዝም ቀርቷል። (የሐዋርያት ሥራ 10:9-16፤ ኤፌሶን 2:15) ኖኅ ለይሖዋ አምልኮ ተስማሚ የሚሆኑትን እንስሳት ያውቅ የነበረ ይመስላል። ልክ ከመርከቡ እንደወጣ “ለእግዚአብሔር መሠውያውን ሠራ፣ ከንጹህም እንስሳ ሁሉ ከንጹሃን ወፎችም ሁሉ ወሰደ፣ በመሠውያውም ላይ መሥዋዕትን አቀረበ።”—ዘፍጥረት 8:20
7:11—ዓለምን ያጥለቀለቀው ውኃ ከየት መጣ? በምድር ዙሪያ ያለው “ጠፈር” በተፈጠረበት በሁለተኛው የፍጥረት “ቀን” ውኃ “ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ” ይገኝ ነበር። (ዘፍጥረት 1:6, 7) “ከጠፈር በታች” ያለው ውኃ በምድር ላይ የነበረው ነው። “ከጠፈር በላይ” የሆነው ውኃ ከምድር በላይ የተንጠለጠለ ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት አዘል አየር ሲሆን ይህም ‘ታላቅ ቀላይ’ ተብሏል። በኖኅ ዘመን ይህ ውኃ በምድር ላይ ዘነበ።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:26፦ የሰው ልጆች በአምላክ አምሳያ የተፈጠሩ በመሆናቸው አምላካዊ ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ አላቸው። እንደ ፍቅር፣ ምሕረት፣ ደግነት፣ ጥሩነትና ትዕግሥት ያሉትን የፈጣሪያችን ባሕርያት ለማዳበር ጥረት ልናደርግ ይገባል።
2:22-24፦ ጋብቻ የአምላክ ዝግጅት ነው። የጋብቻ ጥምረት ዘላቂና ቅዱስ ሲሆን የቤተሰቡ ራስ ባል ነው።
3:1-5, 16-23፦ ደስታ ማግኘታችን የተመካው በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን ሉዓላዊ ገዥነት በመቀበላችን ላይ ነው።
3:18, 19፤ 5:5፤ 6:7፤ 7:23፦ የይሖዋ ቃል ሁልጊዜ ይፈጸማል።
4:3-7፦ ይሖዋ በአቤል መሥዋዕት የተደሰተው አቤል ጻድቅ የእምነት ሰው ስለነበረ ነው። (ዕብራውያን 11:4) በሌላ በኩል ግን፣ ከድርጊቱ ማየት እንደሚቻለው ቃየን እምነት አልነበረውም። ሥራው ክፉ መሆኑ በቅናት፣ በጥላቻና በነፍስ ግድያ ድርጊቱ ታይቷል። (1 ዮሐንስ 3:12) ከዚህም በላይ ለመሥዋዕቱ እምብዛም ትኩረት የሰጠው አይመስልም፤ መሥዋዕቱን ያቀረበው እንዲያው ለይስሙላ ያህል ነበር። ለይሖዋ የምናቀርበው የምስጋና መሥዋዕት ከልብ የመነጨ እንዲሁም በተገቢ የልብ ዝንባሌና ትክክለኛ ድርጊት የተደገፈ ሊሆን አይገባም?
6:22፦ ኖኅ መርከቡን ለመሥራት በርካታ ዓመታት ቢወስድበትም አምላክ ያዘዘውን በትክክል ፈጽሟል። በመሆኑም ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃው ሊተርፉ ችለዋል። ይሖዋ የሚያነጋግረን በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ አማካኝነት ሲሆን በድርጅቱ በኩል ደግሞ መመሪያ ይሰጠናል። መመሪያውን ሰምተን መታዘዛችን ጥቅሙ ለእኛው ነው።
7:21-24፦ ይሖዋ ጻድቃንን ከክፉዎች ጋር አያጠፋም።
የሰው ዘር ወደ አዲስ ዘመን ተሸጋገረ
ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረው ዓለም ከጠፋ በኋላ የሰው ዘር ወደ አዲስ ዘመን ተሸጋገረ። ሰዎች ሥጋ እንዲበሉ የተፈቀደላቸው ሲሆን ከደም መራቅ ግን ነበረባቸው። ይሖዋ ነፍስ ያጠፋ ሰው እንዲገደል ትእዛዝ አወጣ፤ እንዲሁም ምድርን በድጋሚ በውኃ ላለማጥፋት በቀስተ ደመና አማካኝነት ቃል ኪዳን አደረገ። ሦስቱ የኖኅ ልጆች የጠቅላላው የሰው ዘር ቅድመ አያቶች ሆኑ። የኖኅ የልጅ ልጅ፣ ልጅ የሆነው ናምሩድ ግን “ይሖዋን በመቃወም ኃያል አዳኝ ሆነ።” [NW] ሰዎች ተበታትነው ምድርን ከመሙላት ይልቅ ባቢሎን የተባለች ከተማ እንዲሁም ሰማይ ጠቀስ ግንብ ለመሥራትና ስማቸውን ለማስጠራት ፈለጉ። ይሖዋ ቋንቋቸውን በመዘባረቅ በምድር ላይ እንዲበተኑ ሲያደርጋቸው ዓላማቸው ከሸፈ።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
8:11—በምድር ላይ የነበሩት ዛፎች በጥፋት ውኃ ወድመው ከነበረ ርግቧ የወይራ ቅጠሉን ከየት አገኘች? ሁለት አማራጮች አሉ። ወይራ በቀላሉ እንደገና ማቆጥቆጥ የሚችል ዛፍ በመሆኑ በጥፋት ውኃው ወቅት በውኃ ቢሸፈንም ለተወሰኑ ወራት ሳይበሰብስ ቆይቶ ሊሆን ይችላል። ጎርፉ ሲቀንስ በውኃ ተሸፍኖ የነበረው የወይራ ዛፍ እንደገና ደረቅ መሬት ስለሚያገኝ ሊለመልም ይችላል። ርግቧ ለኖኅ የወሰደችለት የወይራ ቅጠል ውኃው ከቀነሰ በኋላ ካቆጠቆጠ ለጋ የወይራ ተክል የተወሰደ ሊሆንም ይችላል።
9:20-25—ኖኅ ከነዓንን የረገመው ለምንድን ነው? ከነዓን በአያቱ በኖኅ ላይ አንድ ዓይነት አሳፋሪ ድርጊት ሳይፈጽም አልቀረም። የከነዓን አባት ካም ይህንን ቢመለከትም ጣልቃ ገብቶ ለማስቆም አልሞከረም፤ ከዚህ ይልቅ የተፈጸመውን ነገር ለሌሎች አናፈሰው። የኖኅ ሌሎች ሁለት ልጆች፣ ሴምና ያፌት ግን አባታቸውን ለመሸፈን እርምጃ ወሰዱ። ይህንን በማድረጋቸው ኖኅ የባረካቸው ሲሆን ከነዓንን ግን ረግሞታል፤ ካም በልጁ ላይ በደረሰው ሐፍረት ሳይሸማቀቅ አልቀረም።
10:25—በፋሌቅ ዘመን ምድሪቱ ‘የተከፈለችው’ እንዴት ነበር? ፋሌቅ የኖረው ከ2269 እስከ 2030 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ይሖዋ ባቢሎንን ይገነቡ የነበሩትን ሰዎች ቋንቋ አዘባርቆ በምድር ዙሪያ እንዲበተኑ በማድረግ ታላቅ መከፋፈል እንዲፈጠር ያደረገው ‘በፋሌቅ ዘመን’ ነበር። (ዘፍጥረት 11:9) በመሆኑም “ምድር [ወይም የምድር ሕዝብ] በዘመኑ ተከፍላለች” ሊባል ይችላል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
9:1፤ 11:9፦ የትኛውም ሰብዓዊ ዕቅድ ወይም ጥረት የይሖዋን ዓላማ ማጨናገፍ አይችልም።
10:1-32፦ ከጥፋት ውኃ በፊትና በኋላ ያለውን የዘር ሐረግ ዝርዝር የያዙት የምዕራፍ 5 እና 10 ዘገባዎች መላው የሰው ዘር በሦስቱ የኖኅ ልጆች በኩል ከአዳም እንደመጣ ያሳያሉ። አሶራውያን፣ ከለዳውያን፣ ዕብራውያን፣ ሶርያውያንና አንዳንድ የአረብ ነገዶች የሴም ዝርያዎች ናቸው። ኢትዮጵያውያን፣ ግብጻውያን፣ ከነዓናውያንና አንዳንድ የአፍሪካ እና የአረብ ነገዶች የካም ዝርያዎች ሲሆኑ ኢንዶ—አውሮፓውያን የያፌት ዝርያ ናቸው። ሁሉም የሰው ዘሮች እርስ በርስ የሚዛመዱ ሲሆን በአምላክ ዘንድ እኩል ናቸው። (የሐዋርያት ሥራ 17:26) ይህ እውነታ ለሌሎች ሰዎች ያለንን አመለካከት ሊቀርጸው ይገባል።
የአምላክ ቃል ይሠራል
የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ክፍል ስለ ሰው ዘር የመጀመሪያ ታሪክ ትክክለኛ ዘገባ የያዘ ብቸኛው ምንጭ ነው። እነዚህ ምዕራፎች አምላክ ሰውን በምድር ላይ ያስቀመጠበትን ዓላማ እንድንረዳ ያስችሉናል። ናምሩድ እንዳደረገው ዓይነት ማንኛውም ሰብዓዊ ሙከራ የይሖዋ ዓላማ እንዳይሳካ ማድረግ እንደማይችል ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው!
ለቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለመዘጋጀት ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን በምታነብበት ጊዜ “ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የሰፈሩትን ሐሳቦች መመልከትህ አንዳንድ ከበድ ያሉ ጥቅሶችን ለመረዳት ያስችልሃል። “ምን ትምህርት እናገኛለን?” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የሰፈሩት ሐሳቦች ከሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ምን ጥቅም ማግኘት እንደምትችል ያሳዩሃል። ተስማሚ በሚሆንበት ጊዜም በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ለጉባኤው እንደሚያስፈልግ የሚቀርበውን ክፍል በእነዚህ ርዕሶች ላይ ተመሥርቶ ማቅረብ ይቻላል። በእርግጥም የይሖዋ ቃል ሕያው ነው፤ በሕይወታችን ውስጥም ይሠራል።—ዕብራውያን 4:12