በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በይሖዋ ደስ ይበላችሁ’

‘በይሖዋ ደስ ይበላችሁ’

‘በይሖዋ ደስ ይበላችሁ’

“በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፣ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።”መዝሙር 37:4

1, 2. የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ማን ነው? ንጉሥ ዳዊት ይህን እውነታ የገለጸውስ እንዴት ነው?

 “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፣ . . . የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፣ . . . የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው።” እነዚህ ሐሳቦች ደስተኛ ስለሆኑ ሰዎች ከሚናገሩ ከሌሎች ስድስት አባባሎች ጋር ተዳምረው ወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ ባሰፈረው መሠረት የኢየሱስ የተራራ ስብከት መግቢያ ናቸው። (ማቴዎስ 5:3-11) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ደስታ ሊደረስበት የሚችል ነገር እንደሆነ ያረጋግጥልናል።

2 የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት በጻፈው መዝሙር ላይ የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን ገልጿል። “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፣ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል” ብሏል። (መዝሙር 37:4) ሆኖም ይሖዋንና የባሕርዩን የተለያዩ ገጽታዎች ማወቅህ ‘ደስ እንዲልህ’ የሚያደርገው እንዴት ነው? ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ከዚህ ቀደም ያደረጋቸውንና ወደፊት የሚያደርጋቸውን ነገሮች መመርመርህ “የልብህን መሻት” የማግኘት ተስፋ የሚሰጥህ እንዴት ነው? መዝሙር 37 ከቁጥር 1 እስከ 11ን በጥልቅ በመመርመር የጥያቄዎቹን መልስ ማግኘት እንችላለን።

“አትቅና”

3, 4. መዝሙር 37:1 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ዳዊት ምን ምክር ሰጥቷል? በዛሬው ጊዜ ምክሩን መከተላችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

3 የምንኖረው ‘አስጨናቂ በሆነ ዘመን’ ውስጥ ከመሆኑም ሌላ ክፋት በእጅጉ ተስፋፍቶ ይገኛል። “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” የሚሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ሲፈጸሙ ተመልክተናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) ክፉ ሰዎች የተሳካላቸውና ብልጽግና ያገኙ መስለው መታየታቸው ብቻ እንኳ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል! ይህ መንፈሳዊ እይታችን እንዲዛባ በማድረግ አቅጣጫችንን ሊያስተን ይችላል። የመዝሙር 37 የመክፈቻ ቃላት “በክፉዎች ላይ አትቅና [“አትበሳጭ፣” የ1980 ትርጉም]፣ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና” በማለት ይህን ከባድ አደጋ በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ይሰጡናል።

4 የዓለማችን መገናኛ ብዙኃን የፍትሕ መጓደልን በተመለከተ በየዕለቱ በርካታ ዘገባዎች ያቀርባሉ። አጭበርባሪ ነጋዴዎች ከመያዝ ያመልጣሉ። ወንጀለኞች ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሰዎችን መጠቀሚያ ያደርጓቸዋል። ነፍሰ ገዳዮች ሳይያዙ ወይም ሳይቀጡ ይቀራሉ። የፍትሕ መዛባት የሚታይባቸው እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሊያበሳጩንና የአእምሮ እረፍት ሊነሱን ይችላሉ። ክፉዎች የተሳካላቸው መስለው መታየታቸው የቅንዓት ስሜት ሊያሳድርብንም ይችላል። ሆኖም የእኛ መናደድ በሁኔታው ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል? ክፉዎች ባገኙት ስኬት መቅናት አካሄዳቸው በሚያስከትልባቸው መዘዝ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለ? ምንም ለውጥ አያመጣም! ደግሞም ‘የምንበሳጭበት’ ምክንያት የለም። ለምን?

5. ክፉዎች በሣር የተመሰሉት ለምንድን ነው?

5 መዝሙራዊው “እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፣ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና” የሚል መልስ ይሰጣል። (መዝሙር 37:2) ለምለም ሣር ሲያዩት የሚያምር ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ይጠወልግና ይደርቃል። የክፉዎች ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። ያገኙት ብልጽግና አብሯቸው አይዘልቅም። በሚሞቱበት ጊዜ በሸፍጥ ያገኙት ሀብት ምንም ሊጠቅማቸው አይችልም። በመጨረሻ ከፍትሕ የሚያመልጥ ሰው የለም። ጳውሎስ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 6:23) ክፉዎችና ዓመፀኞች በሙሉ የኋላ ኋላ የሚገባቸውን “ደመወዝ” ስለሚቀበሉ ከዚህ ምድር ላይ ይጠፋሉ። ይህ በእርግጥ እርባና የሌለው የሕይወት ጎዳና ነው!—መዝሙር 37:35, 36፤ 49:16, 17

6. ከመዝሙር 37:1, 2 የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?

6 ታዲያ ክፉዎች ባገኙት እርባና የሌለው ብልጽግና መናደድ ይኖርብናል? ከመዝሙር 37 የመጀመሪያ ሁለት ቁጥሮች የምናገኘው ትምህርት አለ:- እነርሱ ያገኙት ስኬት ይሖዋን ለማገልገል ከመረጥከው ጎዳና እንዲያስወጣህ አትፍቀድ። ከዚህ ይልቅ ትኩረትህን በመንፈሳዊ በረከቶችና ግቦች ላይ አድርግ።—ምሳሌ 23:17

‘በይሖዋ ታመን፣ መልካምንም አድርግ’

7. በይሖዋ መታመን ያለብን ለምንድን ነው?

7 መዝሙራዊው “በእግዚአብሔር ታመን፣ መልካምንም አድርግ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። (መዝሙር 37:3ሀ) ጭንቀት ላይ ስንወድቅ ወይም ደግሞ ጥርጣሬ ሲያድርብን በይሖዋ ላይ ጽኑ እምነት ማሳደር ይኖርብናል። የተሟላ መንፈሳዊ ጥበቃ ሊያደርግልን የሚችለው ይሖዋ ነው። ሙሴ “በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 91:1) በዚህ ሥርዓት ውስጥ የዓመፅ መብዛት ሲያስጨንቀን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በይሖዋ መታመን ይኖርብናል። እግራችንን ወለም ሲለን ጓደኛችን ደግፎ ቢይዘን ደስ እንደሚለን ሁሉ በታማኝነት ለመጓዝ በምናደርገው ጥረትም የይሖዋ ድጋፍ ያስፈልገናል።—ኢሳይያስ 50:10

8. በክርስቲያናዊ አገልግሎት መሳተፋችን ክፉዎች በሚያገኙት ስኬት ከልክ በላይ እንዳንበሳጭ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

8 ዓመፀኞች በሚያገኙት ስኬት ላለመበሳጨት መፍትሔው በግ መሰል ሰዎችን ለመፈለግና የይሖዋን ዓላማ በትክክል እንዲያውቁ ለመርዳት በትጋት መሥራት ነው። ክፋት እየተባባሰ ባለበት በዚህ ዘመን ሌሎችን በመርዳቱ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና” ብሏል። ከሁሉ የላቀው “መልካም” ሥራ የአምላክን መንግሥት ታላቅ ምሥራች ለሌሎች ማካፈል ነው። ለሕዝብ የምንሰጠው ምሥክርነት በእርግጥ ‘የምሥጋና መሥዋዕት’ ነው።—ዕብራውያን 13:15, 16፤ ገላትያ 6:10

9. ዳዊት “በምድርም ተቀመጥ” ሲል የሰጠው ማበረታቻ ምን ትርጉም እንዳለው አብራራ።

9 ዳዊት በመቀጠል “በምድርም ተቀመጥ፣ ታምነህም ተሰማራ” ብሏል። (መዝሙር 37:3ለ) በዳዊት ዘመን የነበረው ‘ምድር’ ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ክልል ማለትም ተስፋይቱን ምድር ያመለክታል። በሰሎሞን የንግሥና ዘመን የተስፋይቱ ምድር ድንበር በሰሜን በኩል ከዳን አንስቶ በደቡብ እስከ ቤርሳቤህ የሚደርስ ሲሆን እስራኤላውያን የሚኖሩት በዚህ ክልል ውስጥ ነበር። (1 ነገሥት 4:25) በዛሬው ጊዜ በየትኛውም የምድር ክፍል ብንኖር ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ መላዋ ፕላኔት ገነት የምትሆንበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን። እስከዚያ ድረስ ግን በመንፈሳዊ ሁኔታ ተረጋግተን እንኖራለን።—ኢሳይያስ 65:13, 14

10. ‘ታምነን መሰማራታችን’ ምን ያስገኝልናል?

10 ‘ታምነን መሰማራታችን’ ምን ያስገኝልናል? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ምሳሌ “የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል” ይላል። (ምሳሌ 28:20) በምንኖርበት ቦታ ሁሉ እንዲሁም ለምናገኘው ሰው በሙሉ ምሥራቹን በመስበክ በታማኝነት መጽናታችን ከይሖዋ በረከት እንደሚያስገኝልን የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል ፍራንክና ባለቤቱ ሮዝ በሰሜናዊ ስኮትላንድ በምትገኝ በአንዲት ከተማ አቅኚ ሆነው ማገልገል የጀመሩት ከ40 ዓመታት በፊት ነበር። እነርሱ ወደዚያ ከመሄዳቸው በፊት እውነትን ተቀብለው የነበሩ ጥቂት ሰዎች ከእውነት ወጥተዋል። እነዚህ አቅኚ ባልና ሚስት በዚህ ተስፋ ሳይቆርጡ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ተያያዙት። በአሁኑ ጊዜ በዚያ ከተማ ውስጥ አንድ ትልቅ ጉባኤ ይገኛል። በእርግጥም እነዚህ ባልና ሚስት ያሳዩት ታማኝነት የይሖዋን በረከት አስገኝቶላቸዋል። ፍራንክ “ከሁሉ የላቀው በረከት አሁንም እውነት ውስጥ መሆናችንና ይሖዋ በእኛ መጠቀም መቀጠሉ ነው” ሲል በትሕትና ተናግሯል። አዎን፣ ‘ታምነን ስንሰማራ’ ብዙ በረከት እናገኛለን፤ በዚያም እንደሰታለን።

‘በይሖዋ ደስ ይበልህ’

11, 12. (ሀ) ‘በይሖዋ ደስ ሊለን’ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) የግል ጥናትን በተመለከተ ምን ግብ ማውጣት ትችላለህ? ምን ውጤት ልታገኝበትስ ትችላለህ?

11 ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ለማጠናከርና በእርሱ ላይ ያለንን እምነት ጠብቀን ለመኖር ‘በይሖዋ ደስ ሊለን’ ይገባል። (መዝሙር 37:4ሀ) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም እንኳ ከልክ በላይ በራሳችን ጉዳይ ከመጠመድ ይልቅ ትኩረታችን በይሖዋ ላይ እንዲያርፍ እናደርጋለን። እንዲህ ማድረግ የምንችልበት አንደኛው መንገድ ቃሉን ለማንበብ ጊዜ በመመደብ ነው። (መዝሙር 1:1, 2) መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ደስታ ያስገኝልሃል? ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለመማር ብለህ የምታነብብ ከሆነ ደስታ ሊያስገኝልህ ይችላል። የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ካነበብህ በኋላ ቆም ብለህ ‘ያነበብኩት ክፍል ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?’ ብለህ ለምን ራስህን አትጠይቅም። መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብብ ማስታወሻ ደብተር ወይም ወረቀት መያዝህ ሊጠቅምህ ይችላል። ያነበብከው ክፍል ምን መልእክት እንዳለው ለማሰብ ቆም ባልክ ቁጥር የአምላክን ውድ ባሕርያት ለማስታወስ የሚያስችሉህን ጥቂት ቃላት ጻፍ። ዳዊት በአንድ ሌላ መዝሙር ላይ “አቤቱ፣ ረድኤቴ መድኃኒቴም፣ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 19:14) ለአምላክ ቃል ትኩረት መስጠታችን በይሖዋ ፊት “ያማረ” ሆኖ ይታያል፤ እኛም ደስታ እናገኝበታለን።

12 በማጥናትና በማሰላሰል ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው የቻልነውን ያህል የመማር ግብ ማውጣት እንችላለን። እስከዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው እና ወደ ይሖዋ ቅረቡ a የተባሉት ዓይነት ጽሑፎች በአድናቆት ስሜት ልናሰላስልባቸው የምንችል ብዙ ሐሳቦች ይዘዋል። እንዲህ በማድረግ በጽድቅ የምንመላለስ ከሆነ ይሖዋ ‘የልብህን መሻት ይሰጥሃል’ በማለት ዳዊት ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (መዝሙር 37:4ለ) ሐዋርያው ዮሐንስ የሚከተሉትን ቃላት ለመጻፍ የተነሳሳው እንዲህ ዓይነት ትምክህት ስለነበረው መሆን አለበት:- “በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን።”—1 ዮሐንስ 5:14, 15

13. ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በብዙ አገሮች ውስጥ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ረገድ ምን ዓይነት እድገት ታይቷል?

13 ታማኝ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የይሖዋ ሉዓላዊነት ከነቀፋ ጸድቶ ማየት ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልናል። (ምሳሌ 27:11) ቀደም ሲል ጨቋኝ ወይም አምባገነን አገዛዝ ሰፍኖባቸው በነበሩ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞቻችን ስላከናወኑት ከፍተኛ የስብከት እንቅስቃሴ ስንሰማ ልባችን በደስታ አይሞላም? ይህ ሥርዓት ከማብቃቱ በፊት ምን ዓይነት ተጨማሪ ነፃነት ሊገኝ እንደሚችል አናውቅም። በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ለጊዜው ወደ አገራቸው ለመጡና በነፃነት የማምለክ አጋጣሚ ላገኙ ተማሪዎች፣ ስደተኞችና ሌሎች ሰዎች ምሥራቹን በመስበክ በትጋት ይሳተፋሉ። እነዚህ ሰዎች ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ መንፈሳዊ ጨለማ በዋጠው ማለትም ሥራው በታገደበት አገራቸው ውስጥ የእውነትን ብርሃን ማብራታቸውን እንዲቀጥሉ ከልብ እንመኛለን።—ማቴዎስ 5:14-16

‘መንገድህን ለይሖዋ አደራ ስጥ’

14. በይሖዋ መመካት እንደምንችል የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

14 የሚያስጨንቁንና ከባድ ሸክም የሆኑብን ነገሮች የሚወገዱ መሆናቸውን ማወቁ ምንኛ ያስደስታል! ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ዳዊት “መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፣ በእርሱም ታመን” ካለ በኋላ “እርሱም ያደርግልሃል” ሲል ገልጿል። (መዝሙር 37:5) ይሖዋ አስተማማኝ አለኝታ መሆኑን የሚያሳዩ በጉባኤያችን ውስጥ በቂ ምሥክሮች አሉ። (መዝሙር 55:22) በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ማለትም በአቅኚነት፣ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት፣ በሚስዮናዊነት ወይም በቤቴል የሚያገለግሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሁሉ የይሖዋ እንክብካቤ አስተማማኝ መሆኑን ሊመሰክሩ ይችላሉ። የምታውቃቸው የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ካሉ ቀርበህ በማነጋገር ይሖዋ ምን ዓይነት ድጋፍ እንደሰጣቸው ለምን አትጠይቃቸውም? በአስቸጋሪ ጊዜም እንኳ የይሖዋ እጅ አጭር አለመሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ተሞክሮዎች እንደሚነግሩህ የታወቀ ነው። ይሖዋ ለሕይወት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ምንጊዜም ያሟላልናል።—መዝሙር 37:25፤ ማቴዎስ 6:25-34

15. የአምላክ ሕዝቦች ጽድቅ ደምቆ የሚበራው እንዴት ነው?

15 ይሖዋን አለኝታችን ስናደርገውና ሙሉ በሙሉ በእርሱ ስንታመን መዝሙራዊው ቀጥሎ የተናገረው ይፈጸምልናል:- “ጽድቅህን እንደ ብርሃን ፍርድህንም እንደ ቀትር ያመጣል።” (መዝሙር 37:6) የይሖዋ ምሥክር ስለሆንን ብቻ በአብዛኛው ሰዎች ለእኛ የተሳሳተ አመለካከት አላቸው። ሆኖም ምሥራቹን የምንሰብከው ለአምላክና ለሰዎች ባለን ፍቅር ተገፋፍተን መሆኑን ልበ ቅን ሰዎች መገንዘብ እንዲችሉ ይሖዋ ዓይናቸውን ይከፍትላቸዋል። ከዚህም ሌላ ብዙዎች ለመልካም ባሕርያችን የተሳሳተ ትርጉም ቢሰጡም እንኳ ማንነታችን ከሰዎች ዓይን የተሰወረ አይደለም። ይሖዋ ማንኛውንም ዓይነት ተቃውሞና ስደት እንድንቋቋም ይረዳናል። ከዚህም የተነሳ የአምላክ ሕዝቦች ጽድቅ እንደ ቀትር ፀሐይ ደምቆ ይበራል።—1 ጴጥሮስ 2:12

‘ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቅ’

16, 17. በመዝሙር 37:7 መሠረት አሁን ምን የምናደርግበት ጊዜ ነው? ለምንስ?

16 መዝሙራዊው በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤ መንገዱ በተቃናለት፣ ክፋትንም በሚሸርብ ሰው ልብህ አይሸበር።” (መዝሙር 37:7 አ.መ.ት) እዚህ ላይ ዳዊት ይሖዋ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ እንዳለብን አበክሮ ገልጿል። የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እስካሁን ድረስ አለመምጣቱ ለማጉረምረም ምክንያት ሊሆነን አይችልም። የይሖዋ ምሕረትና ትዕግሥት መጀመሪያ ካሰብነው እጅግ የላቀ መሆኑን አላስተዋልንም? መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምሥራቹን በትጋት እየሰበክን በትዕግሥት እንደምንጠብቅ ማሳየት እንችላለን? (ማርቆስ 13:10) በዚህ ጊዜ ደስታችንንና መንፈሳዊ ደኅንነታችንን የሚያሳጣ የችኮላ እርምጃ ላለመውሰድ መጠንቀቅ አለብን። በዚህ ጊዜ የሰይጣን ዓለም የሚያሳድረውን ጎጂ ተጽዕኖ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በኃይል መዋጋት እንዲሁም መንፈሳዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅና በይሖዋ ፊት ያለንን የጽድቅ አቋም ላለማጉደፍ ተጠንቅቀን መኖር አለብን። የብልግና ሐሳቦችን ከአእምሯችን ለማስወገድና ተቃራኒ ፆታ ላላቸውም ሆነ እንደኛው ዓይነት ፆታ ላላቸው ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ዝንባሌ ላለማሳየት በአቋማችን ጸንተን እንቀጥል።—ቆላስይስ 3:5

17 ዳዊት “ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው” የሚል ምክር ሰጥቶናል። “እንዳትበድል አትቅና። ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።” (መዝሙር 37:8, 9) አዎን፣ ይሖዋ ከምድር ላይ ማንኛውንም ክፋትና የክፋት መንስዔ የሆኑትን ሰዎች የሚያስወግድበትን በጣም እየቀረበ ያለውን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠበቅ እንችላለን።

“ገና ጥቂት”

18, 19. ከመዝሙር 37:10 ምን ማበረታቻ ታገኛለህ?

18 “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም።” (መዝሙር 37:10) ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እንዲሁም ከይሖዋ ርቆ በራስ የመመራት ዝንባሌ ወደሚያከትምበት ጊዜ እየተቃረብን ስንሄድ ይህ ጥቅስ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ሰዎች ያቋቋሙት የትኛውም ዓይነት መንግሥት ወይም አገዛዝ ከንቱ መሆኑ ታይቷል። በመሆኑም የአምላክ አገዛዝ ማለትም እውነተኛ ቲኦክራሲ ዳግመኛ ወደሚቋቋምበት ጊዜ ተቃርበናል። ይህ አገዛዝ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የይሖዋ መንግሥት ነው። ይህ መንግሥት መላውን ዓለም ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠር ከመሆኑም በላይ የሚቃወሙትን ሁሉ ያስወግዳል።—ዳንኤል 2:44

19 የአምላክ መንግሥት በሚያስተዳድረው አዲስ ዓለም ውስጥ ‘ኃጢአተኛ’ ለማግኘት ብትጥርም እንኳ አታገኝም። በእርግጥም በይሖዋ ላይ የሚያምፅ ማንኛውም ሰው ወዲያውኑ ይጠፋል። ሉዓላዊ አገዛዙን የሚቃወም ወይም ለአምላካዊ ሥልጣን ለመገዛት ፈቃደኛ የማይሆን ሰው በዚያ አይገኝም። ጎረቤቶችህ በሙሉ እንደ አንተው ይሖዋን ለማስደሰት ፍላጎት ያላቸው ይሆናሉ። ሰዎች ደኅንነታቸው እንደተጠበቀ ይሰማቸዋል፤ በር መቆለፊያና መቀርቀሪያ አያስፈልግም! ሰዎች በሌሎች ላይ ሙሉ እምነት እንዳይጥሉና ደስተኞች እንዳይሆኑ የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም።—ኢሳይያስ 65:20፤ ሚክያስ 4:4፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

20, 21. (ሀ) መዝሙር 37:11 ላይ የተጠቀሱት “ገሮች” እነማን ናቸው? ‘ብዙ ሰላም’ ማግኘት የሚችሉትስ ከየት ነው? (ለ) የታላቁን ዳዊት አርዓያ የምንከተል ከሆነ ምን በረከቶች እናገኛለን?

20 “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ” የሚለው ጥቅስ ፍጻሜውን ያገኛል። (መዝሙር 37:11ሀ) ይሁንና “ገሮች” የተባሉት እነማን ናቸው? “ገር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ማስጨነቅ፣ ማዋረድ፣ ዝቅ ማድረግ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የተገኘ ነው። አዎን፣ “ገሮች” የተባሉት የደረሰባቸውን የፍትሕ መጓደል በሙሉ ይሖዋ እንዲያስተካክልላቸው ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚጠባበቁ ሰዎች ናቸው። “በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:11ለ) በአሁኑ ጊዜም እንኳ በእውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ ገነት በማግኘታችን ብዙ ሰላም አለን።

21 ምንም እንኳ ገና ከመከራ ያልተገላገልን ቢሆንም እርስ በርሳችን እንደጋገፋለን እንዲሁም ያዘኑትን እናጽናናለን። ከዚህም የተነሳ የይሖዋ ሕዝቦች እውነተኛ ውስጣዊ እርካታ አላቸው። እረኞች ሆነው የተሾሙ ወንድሞች፣ መንፈሳዊ አንዳንድ ጊዜም ሥጋዊ ፍላጎቶቻችንን ለማሟላት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እያገለገሉን ለጽድቅ ስንል የሚደርስብንን መከራ በጽናት እንድንወጣ ይረዱናል። (1 ተሰሎንቄ 2:7, 11፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3) ይህን የመሰለ ሰላም በማግኘታችን ምንኛ ታድለናል! ደግሞም በቅርቡ በሚመጣው ሰላም የሰፈነበት ገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ተስፋ አለን። ለይሖዋ ያለው ቅንዓት እስከ መጨረሻው ድረስ በታማኝነት እንዲያገለግል ያነሳሳውን የታላቁን ዳዊት፣ የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ እንከተል። (1 ጴጥሮስ 2:21) እንዲህ በማድረግ ለደስታችን ምክንያት የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን በማወደስ ደስተኞች ሆነን መቀጠል እንችላለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

ከመዝሙር 37:1, 2 ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• ‘በይሖዋ ደስ ሊልህ’ የሚችለው እንዴት ነው?

• በይሖዋ እንድንታመን የሚያስችል ምን ዋስትና አለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ‘ዓመፃን በሚያደርጉ ላይ አይቀኑም’

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘በይሖዋ ታመን፣ መልካምንም አድርግ’

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ ይሖዋ የቻልከውን ያህል በመማር በእርሱ ደስ ይበልህ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ”