ይሖዋን ‘በጉባኤ መካከል’ አመስግኑት
ይሖዋን ‘በጉባኤ መካከል’ አመስግኑት
ክርስቲያናዊ ስብሰባ ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ለማጠንከር ያቋቋመው ዝግጅት ነው። ዘወትር በስብሰባዎች ላይ በመገኘት ይሖዋ ላቋቋመው ለዚህ ዝግጅት ያለንን አድናቆት ማሳየት እንችላለን። በተጨማሪም በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ‘ወንድሞቻችንን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድናነቃቃ’ ያስችለናል። ይህም አንዳችን ለሌላው ያለንን ፍቅር ለመግለጽ የሚያስችል ጥሩ መንገድ ነው። (ዕብራውያን 10:24፤ ዮሐንስ 13:35) ይሁንና በስብሰባዎች ላይ ወንድሞቻችንን ማነቃቃት የምንችለው እንዴት ነው?
በሰዎች መካከል እምነታችሁን ግለጹ
ንጉሥ ዳዊት የራሱን ሁኔታ አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፣ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ። በታላቅ ጉባኤ ምስጋናዬ ከአንተ ዘንድ ነው።” “አቤቱ፣ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፣ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ።” “በታላቅ ጉባኤ ጽድቅን አወራሁ፤ እነሆ፣ ከንፈሮቼን አልከለክልም።”—መዝሙር 22:22, 25፤ 35:18፤ 40:9
በሐዋርያው ጳውሎስም ዘመን ክርስቲያኖች ለአምልኮ ሲሰበሰቡ በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት የመግለጽና እሱን የማወደስ ልማድ ነበራቸው። በዚህ መንገድ እርስ በርሳቸው ይበረታቱ የነበረ ከመሆኑም በላይ አንዳቸው ሌላውን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ያነቃቁ ነበር። ዳዊትና ጳውሎስ ከኖሩ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ በዛሬው ጊዜ ‘የይሖዋ ቀን በጣም እንደቀረበ’ ዕብራውያን 10:24, 25) የሰይጣን ሥርዓት ወደ ጥፋት እያመራ ሲሆን በዓለም ውስጥ ያሉት ችግሮችም እየተበራከቱ መጥተዋል። ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ ዛሬ ‘መጽናት ያስፈልገናል።’ (ዕብራውያን 10:36) ከወንድሞቻችን ሌላ እንድንጸና ሊያበረታን የሚችል ማን ይኖራል?
መረዳት እንችላለን። (በጥንት ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ ‘በጉባኤ መካከል’ እምነታቸውን መግለጽ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች አሉ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ተሳትፎ ማድረግ ሁሉም ክርስቲያኖች እምነታቸውን መግለጽ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ነው። በስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ያለውን ጥቅም አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። ለምሳሌ ያህል ችግሮችን እንዴት መቋቋም ወይም ማስወገድ እንደሚቻል የሚገልጹ ሐሳቦች ወንድሞቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመከተል ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክሩላቸዋል። ምዕራፋቸውና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የሚያብራሩ ወይም በግል ምርምር የተገኙ መረጃዎችን ያካተቱ ሐሳቦችን መስጠት ሌሎች ወንድሞችም ጥሩ የጥናት ልማድ እንዲያዳብሩ ሊያበረታታቸው ይችላል።
በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት እኛንም ሆነ ሌሎችን እንደሚጠቅም መገንዘባችን ሁላችንም ፍርሃትን ወይም ዓይናፋርነትን እንድናሸንፍ ሊያነሳሳን ይገባል። በተለይ ደግሞ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በጉባኤ ላይ በመገኘትና ተሳትፎ በማድረግ ረገድ ምሳሌ መሆን ስለሚጠበቅባቸው በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ይሁንና አንድ ክርስቲያን በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ለመስጠት የሚቸገር ከሆነ ይህን ድክመት ማሻሻል የሚችለው እንዴት ነው?
ማሻሻያ ለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦች
ሐሳብ መስጠት ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ክፍል መሆኑን አስታውስ። በጀርመን የምትኖር አንዲት እህት በጉባኤ የምትሰጠው ሐሳብ ‘ሰይጣን የአምላክ ሕዝቦች እምነታቸውን እንዳይገልጹ ለማድረግ ለሚሸርበው ሴራ በግል የምትሰጠው ምላሽ’ እንደሆነ ተናግራለች። በዚያው ጉባኤ የሚሰበሰብ በቅርቡ የተጠመቀ አንድ ወንድም ደግሞ “በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ለመስጠት አዘውትሬ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ” ብሏል።
ጥሩ ዝግጅት አድርግ። ትምህርቱን አስቀድመህ ካልተዘጋጀህ ሐሳብ መስጠት ሊከብድህና የምትሰጣቸውም ሐሳቦች እምብዛም ገንቢ ላይሆኑ ይችላሉ። በስብሰባዎች ላይ መልስ መስጠትን በተመለከተ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም በተባለው መጽሐፍ ገጽ 70 ላይ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች ቀርበዋል። a
በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ቢያንስ አንድ ሐሳብ ለመስጠት ግብ አውጣ። በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ የመስጠት አጋጣሚ ለማግኘት እጅህን ደጋግመህ ማውጣት ሊያስፈልግህ ስለሚችል ከአንድ በላይ መልሶችን መዘጋጀት ይኖርብሃል። እንዲሁም የትኞቹን ጥያቄዎች መመለስ እንደምትፈልግ ስብሰባውን ለሚመራው ወንድም አስቀድመህ ልትነግረው ትችላለህ። በተለይ ደግሞ ሐሳብ በመስጠት ረገድ ብዙም ልምድ ከሌለህ እንዲህ ማድረግህ በጣም ይረዳሃል። ‘በጉባኤ መካከል’ እጅ ማውጣት ሊያስፈራህ ስለሚችል አንተ የተዘጋጀህበት አንቀጽ ሲደርስ ስብሰባውን
የሚመራው ወንድም ወደ አንተ መመልከቱ ስለማይቀር ሐሳብ ለመስጠት ልትደፋፈር ትችላለህ።የመጀመሪያዎቹ አንቀጾች ላይ ሐሳብ ለመስጠት ጥረት አድርግ። አንድን ከባድ ሥራ ለሌላ ጊዜ ስላስተላለፍነው ብቻ ሥራው እንደማይቀልልን የታወቀ ነው። በመጀመሪያዎቹ አንቀጾች ላይ መልስ መስጠትህ በጣም ይጠቅምሃል። እንደምንም ብለህ አንዴ መልስ ከሰጠህ ለሁለተኛ ወይም ለሦስተኛ ጊዜ ሐሳብ መስጠት ይበልጥ ሊቀልህ ይችላል።
ጥሩ ቦታ መርጠህ ተቀመጥ። አንዳንዶች አዳራሹ ውስጥ ከፊት በሚገኙት ወንበሮች ላይ በሚቀመጡበት ጊዜ መልስ ለመስጠት ይቀላቸዋል። ሐሳባቸውን የሚከፋፍል ነገር እምብዛም የማይኖር ከመሆኑም በላይ ስብሰባውን የሚመራው ወንድም እጅ ሲያወጡ በቀላሉ ሊያያቸው ይችላል። ፊት መቀመጥ የምትመርጥ ከሆነና በጉባኤያችሁ ውስጥ ለአድማጮች የሚዞር የድምፅ ማጉያ መሣሪያ ከሌለ የምትሰጠውን ሐሳብ ሁሉም መስማት እንዲችሉ ድምፅህን ከፍ ማድረግ ይኖርብሃል።
በጥሞና አዳምጥ። እንዲህ ማድረግህ ሌላ ሰው የሰጠውን ሐሳብ ደግመህ ከመናገር እንድትቆጠብ ይረዳሃል። በተጨማሪም ሌሎች የሚሰጡት ሐሳብ ውይይት እየተደረገበት ያለውን ነጥብ ለማዳበር የሚረዳ አንድ ጥቅስ ወይም ሐሳብ እንድታስታውስ ሊያደርግህ ይችላል። አንዳንድ ጊዜም ርዕሰ ጉዳዩን የሚያጠናክር አጠር ያለ ተሞክሮ ልትናገር ትችላለህ። እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን መስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በራስህ አባባል የመመለስ ልማድ አዳብር። ከጽሑፉ ላይ እያነበብህ ሐሳብ መስጠትህ ትክክለኛውን መልስ እንዳገኘህ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ለአዲሶች ጥሩ መንደርደሪያ ሊሆን ይችላል። ሆኖም እድገት አድርገህ በራስህ አባባል መልስ መስጠት መቻልህ ፍሬ ነገሩን እንዳስተዋልክ ያሳያል። መልስ በምንሰጥበት ጊዜ በጽሑፉ ላይ ያለውን ሐሳብ ቃል በቃል መድገም አያስፈልገንም። የይሖዋ ምሥክሮች በጽሑፎቻቸው ላይ የሰፈረውን ሐሳብ እንዲሁ ሸምድደው አያስተጋቡም።
ከርዕሱ አትውጣ። ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ወይም እየተብራሩ ካሉት ዋና ዋና ነጥቦች ውጪ የሆኑ ሐሳቦችን መስጠት ተገቢ አይደለም። ይህም ማለት የምትሰጠው ሐሳብ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር የተያያዘ መሆን አለበት። እንዲህ ያሉ ሐሳቦች እየተብራራ ባለው ጭብጥ ላይ በመንፈሳዊ የሚያንጽ ጥሩ ውይይት ለማድረግ ያስችላሉ።
ሌሎችን የማበረታታት ግብ ይኑርህ። በስብሰባ ላይ ሐሳብ የምንሰጥበት አንዱ ምክንያት ሌሎችን ለማበረታታት ስለሆነ የሚያሸማቅቅ ዓይነት ሐሳብ ከመሰንዘር መቆጠብ ይኖርብናል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎችም መሳተፍ እንዲችሉ አንቀጹ ውስጥ ያለውን ሐሳብ በሙሉ ለመሸፈን አትሞክር። ረጅምና ውስብስብ የሆኑ መልሶች ፍሬ ነገሩን ሊሰውሩ ይችላሉ። አጠር ያለ መልስ መስጠት ቁም ነገሩን የሚያስጨብጥ ከመሆኑም በላይ አዲሶች አጫጭር መልሶች ለመስጠት እንዲደፋፈሩ ያደርጋል።
ስብሰባዎችን የሚመሩ ወንድሞች ያለባቸው ኃላፊነት
ስብሰባውን የሚመራው ወንድም አድማጮቹን በማበረታታት ረገድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። አንድ አድማጭ መልስ በሚሰጥበት ጊዜ መሪው ትኩረቱን ሌላ ነገር ላይ ከማድረግ ይልቅ ሐሳብ የሚሰጠውን ሰው እያየ በጥሞና በማዳመጥ መልሱን በሚገባ መከታተል ይኖርበታል። በጥሞና ሳያዳምጥ በመቅረቱ ምክንያት የተሰጠውን መልስ ደግሞ ቢናገር ወይም መልስ የተሰጠበትን ጥያቄ እንደገና ቢጠይቅ ተገቢ አይሆንም!
በተጨማሪም የሚመራው ወንድም የተሰጠው ሐሳብ አጥጋቢ እንዳልሆነ በሚያስመስል ሁኔታ መልሱን ትንሽ ለየት ባለ መንገድ ደግሞ የመናገር ልማድ ካለው
አድማጮች ሐሳብ ለመስጠት እምብዛም ላይነሳሱ ይችላሉ። በሌላ በኩል ግን አንድ ቁልፍ ነጥብ በደንብ እንዲብራራ የሚያስችል ፍንጭ መስጠት አድማጮች ተጨማሪ ሐሳቦች እንዲሰነዝሩ ይጋብዛል። ‘ይህን ሐሳብ በጉባኤያችን ልንሠራበት የምንችለው እንዴት ነው?’ ወይም ‘ይህን ነጥብ የትኛው ጥቅስ ይደግፍልናል?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ገንቢ ሐሳቦች እንዲሰጡ በር በመክፈት ውይይቱ እንዲዳብር ያደርጋሉ።እርግጥ ነው፣ አዲሶች ወይም ዓይናፋር የሆኑ ሰዎች ሐሳብ በሚሰጡበት ጊዜ ማመስገን ያስፈልጋል። ግለሰቡ ሊያፍር ስለሚችል ስብሰባው ካለቀ በኋላ በግል ቀርቦ ማመስገኑ ይመረጣል። ይህም ስብሰባውን የሚመራው ወንድም አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ አንዳንድ ምክሮችን ለመለገስ ያስችለዋል።
ሰዎች አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው በሚጫወቱበት ጊዜ አንደኛው ግለሰብ እኔ ብቻ ልናገር የሚል ዓይነት ከሆነ ሌሎቹ ሐሳባቸውን ለመግለጽ አይገፋፉም። ዝም ብለው ቢሰሙትም እንኳ ከልባቸው ላያዳምጡት ይችላሉ። አንድ ወንድም ስብሰባ በሚመራበት ጊዜም በተደጋጋሚ ሐሳብ በመስጠት ውይይቱን ከተቆጣጠረ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ተጨማሪ ጥያቄዎች በመጠየቅ ተሰብሳቢዎቹ ሐሳብ እንዲሰጡና በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ይበልጥ እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ሆኖም እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች መብዛት የለባቸውም።
ስብሰባውን የሚመራው ወንድም እጁን ቀድሞ ላወጣ ሰው ብቻ ዕድል መስጠት የለበትም። እንዲህ የሚያደርግ ከሆነ ሐሳባቸውን ለማቀናበር ጥቂት ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ተስፋ ሊያስቆርጣቸው ይችላል። ጥያቄ ከጠየቀ በኋላ ትንሽ ጊዜ በመስጠት ተሳትፎ የማድረግ አጋጣሚ ላላገኘ ወንድም ዕድሉን ሊሰጥ ይችላል። በተጨማሪም ከባድ ጥያቄዎችን ለትንንሽ ልጆች ላለመስጠት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።
የተሰጠው መልስ ትክክል ባይሆንስ? ስብሰባውን የሚመራው ወንድም መልሱን የሰጠውን ግለሰብ ከማሳፈር መቆጠብ ይኖርበታል። አብዛኛውን ጊዜ እንደሚታየው የተሳሳቱ መልሶችም እንኳ በተወሰነ ደረጃ እውነታን ያዘሉ ናቸው። በመሆኑም መሪው ጥበብ በተሞላበት መንገድ ትክክለኛውን ሐሳብ ብቻ መርጦ በመውሰድ፣ ጥያቄውን በሌላ መልክ በማቅረብ ወይም ተጨማሪ ጥያቄ በመጠየቅ መልስ የሰጠውን ሰው ሳያሸማቅቅ ትክክለኛው መልስ እንዲመለስ ማድረግ ይችላል።
ስብሰባውን የሚመራው ወንድም ‘ተጨማሪ ሐሳብ ያለው አለ?’ እንደሚሉት ዓይነት ድፍን ያሉ ጥያቄዎችን ማቅረብ የለበትም። ‘እስካሁን ያልመለሳችሁ ካላችሁ ይህ የመጨረሻ ዕድላችሁ ነው!’ የሚለው አባባል አድማጮች መልስ እንዲሰጡ ለማበረታታት ተብሎ የሚነገር ቢሆንም ተሰብሳቢዎቹ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ አይጋብዝም። ወንድሞች ቀደም ባሉት አንቀጾች ላይ ሐሳብ ባለመስጠታቸው እንዲሸማቀቁ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ይልቁንም ሐሳብን ማካፈል የፍቅር መግለጫ ስለሆነ የሚያውቁትን እንዲናገሩ ሊበረታቱ ይገባል። ከዚህም ሌላ መሪው ለአንድ ሰው ዕድል ከሰጠ በኋላ “ከእሱ ቀጥሎ ወንድም እከሌ፣ ቀጥሎ ደግሞ እህት እከሊት ሐሳብ ይሰጣሉ” ማለት አይኖርበትም። ከዚህ ይልቅ በቅድሚያ መልሱን በጥሞና ካዳመጠ በኋላ ተጨማሪ ሐሳብ ያስፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ይኖርበታል።
ሐሳብ መስጠት መብት ነው
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ወሳኝ ነው። በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ደግሞ ትልቅ መብት ነው። በዚህ ወደር የለሽ መብት ተጠቅመን ‘በጉባኤ መካከል’ ይሖዋን ማወደሳችን የዳዊትን ምሳሌ እንደተከተልንና የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ እንዳደረግን ያሳያል። በስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ማድረጋችን ለወንድሞቻችን ፍቅር እንዳለንና የይሖዋ ታላቅ ጉባኤ አካል እንደሆንን ያረጋግጣል። ደግሞስ ‘ቀኑ ሲቀርብ እያየን’ ከክርስቲያን ጉባኤ ሌላ ወዴት እንሄዳለን?—ዕብራውያን 10:25
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቶ ማዳመጥም ሆነ ሐሳብ መስጠት አስፈላጊ ነው
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስብሰባውን የሚመራው ወንድም እያንዳንዱን ሐሳብ በትኩረት ማዳመጥ አለበት