አንድ እውነተኛ የክርስትና እምነት
አንድ እውነተኛ የክርስትና እምነት
ኢየሱስ ክርስቶስ ያቋቋመው አንድ ቤተ ክርስቲያን ወይም ጉባኤ ብቻ ነው። ይህ ጉባኤ አንድ መንፈሳዊ አካል ወይም መንፈሳዊ ቤተሰብ ነበር። ይህን ስንል በአምላክ ቅዱስ መንፈስ የተመረጡና አምላክ እንደ ‘ልጆቹ’ አድርጎ የሚመለከታቸው ሰዎች ስብስብ ማለታችን ነው።—ሮሜ 8:16, 17፤ ገላትያ 3:26
አምላክ ሰዎችን ወደ እውነትና ወደ ሕይወት ለመምራት ያዘጋጀው መንገድ አንድ ብቻ መሆኑን ኢየሱስ አስተምሯል። ይህን ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው እውነት በምሳሌ ሲያስረዳ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን ጎዳና በመንገድ መስሎታል። እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።”—ማቴዎስ 7:13, 14፤ ዮሐንስ 14:6፤ ሥራ 4:11, 12
አንድነት ያለው ጉባኤ
ዘ ኒው ዲክሽነሪ ኦቭ ቲኦሎጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ጉባኤ ‘ዛሬ ካለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አወቃቀርና አደረጃጀት ጋር ልናመሳስለው’ አይገባም ብሏል። ለምን? ‘ምክንያቱም በዚህ ዓይነት መልኩ የተዋቀረ ማኅበረሰብ አልነበረም።’
የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ አወቃቀር ዛሬ ከምናያቸው አብያተ ክርስቲያናት አወቃቀር ጋር ይመሳሰላል ብሎ ማንም ሊከራከር አይችልም። ሆኖም የጥንቱ ክርስቲያን ጉባኤ በሚገባ የተደራጀ አልነበረም ማለት አይደለም። እያንዳንዱ ጉባኤ በተናጠል ከመንቀሳቀስ ይልቅ በኢየሩሳሌም የነበረውን የአስተዳደር አካል ሥልጣን በማክበር ከዚያ የሚሰጠውን መመሪያ ይከተል ነበር። በኢየሩሳሌም ከነበረው ጉባኤ የተውጣጡ ሐዋርያትንና ሽማግሌዎችን ያቀፈው ይህ ኤፌሶን 4:4, 11-16፤ ሥራ 15:22-31፤ 16:4, 5
የአስተዳደር አካል ጉባኤው የክርስቶስ ‘አንድ አካል’ ሆኖ በአንድነት እንዲሠራ አስችሏል።—ይህ እውነተኛ አንድ ጉባኤ አሁን የት ደረሰ? በታላቋ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተተክቶ ይሆን? ዛሬ የምናያቸው በውስጣቸው ብዙ ክፍፍል ያላቸው የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ከዚያ የመጡ ይሆኑ? ወይስ ሌላ ነገር ተከስቶ ይሆን?
‘ስንዴ’ እና ‘እንክርዳድ’
መልሱን ለማግኘት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ምን እንዳለ እንመልከት። ኢየሱስ ይህ ጉባኤ ለተወሰነ ጊዜ ከታሪክ መድረክ እንደሚሰወር ያውቅ እንደነበረና እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታም ለዘመናት እንዲቀጥል እንደሚፈቅድ ስታውቅ ትገረም ይሆናል።
እርሱ ያቋቋመውን ጉባኤ ‘ከመንግሥተ ሰማያት’ ጋር በማመሳሰል እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። የባለቤቱም ባሮች ቀርበው:- ጌታ ሆይ፣ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት። እርሱም:- ጠላት ይህን አደረገ አላቸው። ባሮቹም:- እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት። እርሱ ግን:- እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን:- እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፣ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ።”—ማቴዎስ 13:24-30
ኢየሱስ ‘ዘሪው’ እርሱ ራሱ እንደሆነ፣ ‘መልካሙ ዘር’ እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚያመለክትና ‘ጠላቱ’ ደግሞ ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ አብራርቷል። “እንክርዳዱ” ወደ ጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ሰርገው የገቡትን አስመሳይ ክርስቲያኖች ያመለክታል። ኢየሱስ “በዓለም መጨረሻ” እስከሚሆነው ‘የመከር ወቅት’ ድረስ ‘ስንዴውና እንክርዳዱ’ አብረው እንዲያድጉ እንደሚፈቅድ ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:37-43) የዚህ ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው?
የክርስቲያን ጉባኤ መበከል
ሐዋርያት ከሞቱ ብዙም ሳይቆይ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ከሃዲ አስተማሪዎች ቀስ በቀስ ጉባኤውን መቆጣጠር ጀመሩ። ‘ደቀ መዛሙርትን የራሳቸው ተከታዮች ለማድረግ ጠማማ ነገርን’ ይናገሩ ነበር። (ሥራ 20:29, 30) በዚህም የተነሳ በርካታ ክርስቲያኖች ‘ሃይማኖትን ክደው ወደ ተረት ዘወር’ ብለዋል።—1 ጢሞቴዎስ 4:1-3፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4
ዮሐንስ 17:16፤ ያዕቆብ 4:4) ይኸው መጽሐፍ “ብ[ሉይ] ኪ[ዳንን] ከኒዮፕላቶኒክ ፍልስፍና ጋር ማቀላቀል . . . ያሳደረው ተጽዕኖ” የቤተ ክርስቲያኒቷን አጠቃላይ አወቃቀርና አደረጃጀት እንዲሁም ከዋነኛ ሃይማኖታዊ ትምህርቶቿ አብዛኞቹን እንደለወጠ ይገልጻል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተነበየው የአስመሳይ ክርስቲያኖች መብዛት እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ እንዲዋጡ አድርጓል።
ዘ ኒው ዲክሽነሪ ኦቭ ቲኦሎጂ በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ “የካቶሊክ ክርስትና . . . የሮማ መንግሥት ሃይማኖት ሆኖ ነበር” ይላል። “ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ጥምረት” ፈጥረው የነበረ ሲሆን ይህም ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች እምነት ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነው። (የኢየሱስ አድማጮች በቡቃያነቱ ወቅት እውነተኛውን ስንዴ ከመርዛማው እንክርዳድ መለየት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ያውቃሉ። ስለዚህ ኢየሱስ በምሳሌው ላይ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ከአስመሳይ ክርስቲያኖች መለየት ለተወሰነ ጊዜ አስቸጋሪ እንደሚሆን መናገሩ ነበር። ይህ ማለት ግን የክርስቲያን ጉባኤ ሙሉ በሙሉ ከሕልውና ውጭ ይሆናል ማለት አይደለም። ምክንያቱም ኢየሱስ መንፈሳዊ ወንድሞቹን “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል። (ማቴዎስ 28:20) በተጨማሪም ስንዴው ማደጉን እንደሚቀጥል ተናግሯል። ባለፉት ዘመናት ሁሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከክርስቶስ ትምህርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር የተቻላቸውን ያህል ይጥሩ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም በቀላሉ ለመለየት በሚያስችል ሁኔታ እንደ አንድ አካል ወይም ድርጅት አልተዋቀሩም ነበር። ይህ ሲባል ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲሰደብና እንዲነቀፍ ሲያደርግ ከኖረው ከሃዲ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ጋር ተመሳስለው ነበር ማለት አይደለም።—2 ጴጥሮስ 2:1, 2
‘የዓመፅ ሰው ይገለጣል’
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን አስመሳይ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለይቶ የሚያሳውቅ አንድ ነገር ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው . . . ሳይገለጥ፣ [የጌታ ቀን] አይደርስምና።” (2 ተሰሎንቄ 2:2-4) ይህ “የዓመፅ ሰው” ራሱን “በክርስቲያን” ጉባኤ ላይ ከፍ ከፍ በማድረግ የገዥነት ቦታ ከያዘው የቀሳውስት ቡድን ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። a
ክህደቱ የጀመረው በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን ሲሆን ሐዋርያቱ ከሞቱና የሚያሳድሩት በጎ ተጽዕኖ ካቆመ በኋላ ይበልጥ ተስፋፍቷል። ጳውሎስ ክህደቱ “በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር” እንደሚገለጥ ተናግሯል። (2 ተሰሎንቄ 2:6-12) ይህ አባባል በታሪክ ዘመናት ሁሉ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች ተግባር ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው!
የካቶሊክ መሪዎች የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብቸኛዋ እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ናት የሚለውን ሐሳብ ለመደገፍ አቡኖቻቸው “ክርስትና ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ መስመር ከመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት የሐዋርያነት ሥልጣን እንደተቀበሉ” ይናገራሉ። እውነታው ሲታይ ግን ይህ በሐዋርያት እግር የመተካት ሂደት ታሪካዊም ሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የለውም። የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ የተቋቋመው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ድጋፍ እንዳለው የሚያሳይ አንድም ተጨባጭ ማስረጃ የለም።—ሮሜ 8:9፤ ገላትያ 5:19-21
ሃይማኖታዊ ተሃድሶ ከሚባለው ንቅናቄ በኋላ ብቅ ስላሉት አብያተ ክርስቲያናትስ ምን ለማለት ይቻላል? እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት የጥንቱን የክርስቲያን ጉባኤ አሠራር መከተል ጀምረው ይሆን? መጀመሪያ የነበረው ንጹህ የክርስቲያን ጉባኤ እንደገና እንዲቋቋም ማድረግ ችለዋል? ከተሃድሶ ንቅናቄው በኋላ አብዛኛው ተራ ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን በራሱ ቋንቋ ማግኘት እንደቻለ አይካድም። ሆኖም እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት የተሳሳተ ትምህርት ማስተማራቸውን እንደቀጠሉ ታሪክ ይመሰክራል።—ማቴዎስ 15:7-9
ይሁን እንጂ ልብ ልንለው የሚገባ ጉዳይ አለ። ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም መጨረሻ ብሎ በጠራው ጊዜ እውነተኛ ጉባኤው እንደገና እንደሚቋቋም ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:30, 39) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ እንደሚያሳየው አሁን የምንኖረው በዚህ ጊዜ ውስጥ ነው። (ማቴዎስ 24:3-35) ይህ ከሆነ እያንዳንዳችን ‘ታዲያ እውነተኛ የሆነው አንድ ቤተ ክርስቲያን የትኛው ነው?’ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። ይህ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ሂደት ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መሄድ አለበት።
ምናልባት እውነተኛውን ቤተ ክርስቲያን ወይም ጉባኤ እንዳገኘህ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም እርግጠኛ መሆን ይኖርብሃል። ለምን? ምክንያቱም እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም እውነተኛው ቤተ ክርስቲያን አንድ ብቻ ነው። አንተ ያለህበት ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን የክርስቲያን ጉባኤ አሠራር ይከተልና የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶች በታማኝነት ይታዘዝ እንደሆነ በሚገባ መርምረሃልን? ካልሆነ ለምን አሁን መመርመር አትጀምርም? በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።—ሥራ 17:11
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “የዓመፅ ሰው” ማን እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት መጠበቂያ ግንብ 3-111 ገጽ 10-14 ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ የተናገረው ምሳሌ እውነተኛውን ጉባኤ በተመለከተ ምን ያስተምረናል?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንተ ያለህበት ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በስብከትም ሆነ በጥናት ረገድ የተዉትን አርአያ ይከተላልን?