የወጣቶችን ልብ ለመንካት የተዘጋጀ ፊልም
የወጣቶችን ልብ ለመንካት የተዘጋጀ ፊልም
ብዙ ወጣቶች የወጣቶች ጥያቄ—እውነተኛ ጓደኞች ማፍራት የምችለው እንዴት ነው? a የተባለውን ፊልም ከተመለከቱ በኋላ አኗኗራቸውን በቁም ነገር ለመመርመር ተነሳስተዋል። ፊልሙ ጥሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች፣ ወጣት ክርስቲያኖች የተናገሯቸውን ሐሳቦችና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው በዲና ታሪክ ላይ የተመሠረተ ዘመናዊ ድራማ ይዟል። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 34) ቪዲዮውን አስመልክቶ ከሜክሲኮ የተላኩ አስተያየቶች ቀጥሎ ቀርበዋል።
ማርታ እንዲህ ትላለች:- “ቪዲዮው ልቤን በጥልቅ ነክቶታል። ለኔ ተብሎ የተዘጋጀ ሆኖ ነው የተሰማኝ። አስተማሪዎቼና አብረውኝ የሚማሩት ልጆች የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ማወቃቸው ብቻ በቂ ነው ብዬ አስብ ነበር። ምሥራቹን በመንገር ይህን በተግባር አላሳየኋቸውም። ይሖዋ ለሚያቀርብልን ትምህርት በጣም አመስጋኝ ነኝ። በተለይ እንደዚህ ቪዲዮ ስሜታችንን በጥልቅ የሚነኩ ትምህርቶች በሚወጡበት ጊዜ እርሱን ለማመስገን እገፋፋለሁ።”
ሁዋን ካርሎስ ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “ቪዲዮው ቆም ብላችሁ እንድታስቡ ያደርጋችኋል። ወጣት እንደመሆኔ መጠን ስህተት የፈጸምኩባቸው ጊዜያት ስለነበሩ በድራማው ላይ የቀረቡት አንዳንድ ገጸ ባሕርያት የራሴ ሕይወት ነጸብራቅ እንደሆኑ ተሰምቶኛል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ሁለት ዓይነት ሕይወት ነበረኝ። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አኗኗር መጥፎ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ተገንዝቤያለሁ። ፊልሙን ከተመለከትኩ በኋላ ይሖዋን በታማኝነት ለማምለክ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ።”
ሱሌም እንዲህ ስትል ሐቁን ተናግራለች:- “ቪዲዮውን ስመለከት ስሜቴ በጣም ተነካ። መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቤን አቁሜ የነበረ ሲሆን ወደ ይሖዋ የምጸልየውም አልፎ አልፎ ነበር። በቪዲዮው ላይ የቀረቡት ወጣቶች የተናገሯቸውን ሐሳቦች ሳዳምጥ በድጋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን ለመጀመርና ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ተገፋፍቻለሁ።”
በዛሬው ጊዜ ወጣቶች በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች የሚያጋጥሟቸው ሲሆን የጓደኛ ምርጫቸው ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በሕይወታቸው ላይ ከባድ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። (መዝሙር 26:4፤ ምሳሌ 13:20) በዚህ ረገድ የወጣቶች ጥያቄ—እውነተኛ ጓደኞች ማፍራት የምችለው እንዴት ነው? የተባለው የቪዲዮ ፊልም በርካታ ወጣቶች ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርጉ እየረዳ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።