አንድ ሆናችሁ ማገልገላችሁን ቀጥሉ
አንድ ሆናችሁ ማገልገላችሁን ቀጥሉ
“አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።”—ሶፎንያስ 3:9
1. በሶፎንያስ 3:9 ፍጻሜ መሠረት ምን ነገር እየተከናወነ ነው?
በመላው ምድር ወደ 6, 000 የሚጠጉ መግባቢያ ቋንቋዎች አሉ። ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ቀበልኛዎች ማለትም በተወሰነ አካባቢ የሚነገሩ ቋንቋዎች አሉ። ሰዎች እንደ አማርኛና እንደ እንግሊዝኛ የመሳሰሉ ፈጽሞ የማይገናኙ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ቢሆኑም እንኳ አምላክ አንድ አስደናቂ ነገር አከናውኗል። በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ብቸኛውንና አንዱን ንጹሕ ቋንቋ እንዲማሩና እንዲናገሩ አስችሏል። ይህ ሊሆን የቻለው በነቢዩ ሶፎንያስ አማካኝነት በተነገረው የተስፋ ቃል ፍጻሜ መሠረት ነው:- “አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን [ቃል በቃል፣ “ንጹሕ ከንፈር፣”] እመልስላቸዋለሁ።”—ሶፎንያስ 3:9
2. ‘ንጹሑ ልሳን’ ምንድን ነው? ምን ነገር እንዲቻል አደርጓል?
2 ‘ንጹሑ ልሳን’ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ እውነት ነው። በይበልጥ ደግሞ የይሖዋን ስም ስለሚያስቀድሰው፣ ሉዓላዊነቱን ስለሚያረጋግጠውና ለሰው ልጆች በረከት ስለሚያመጣው ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው እውነት ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) በመንፈሳዊ ንጹሕ የሆነውና በምድር ላይ የሚነገረው ይህ ቋንቋ አንድ ብቻ ቢሆንም ከሁሉም ብሔራትና ዘሮች የመጡ ሰዎች ይናገሩታል። ይሖዋን “አንድ ሆነው” እንዲያገለግሉት ያስችላቸዋል። ከዚህም የተነሳ በኅብረት ወይም “ተስማምተው” ያገለግሉታል።—አ.መ.ት
በአምላክ ሕዝቦች መካከል አድልዎ መኖር የለበትም
3. ይሖዋን በአንድነት እንድናገለግል የሚያስችለን ምንድን ነው?
3 የተለያየ ቋንቋ የምንናገር ክርስቲያኖች ብንሆንም በመካከላችን ኅብረት በመኖሩ አመስጋኞች ነን። በተለያዩ ቋንቋዎች የመንግሥቱን ምሥራች የምንሰብክ ብንሆንም እንኳ አንድ ሆነን አምላክን እናገለግላለን። (መዝሙር 133:1) ይህ ሊሆን የቻለው በምድር ላይ በየትኛውም ቦታ ብንኖር ንጹሑን ልሳን በመናገር ይሖዋን ስለምናወድስ ነው።
4. በአምላክ ሕዝቦች መካከል አድልዎ መኖር የሌለበት ለምንድን ነው?
4 በአምላክ ሕዝቦች መካከል አድልዎ መኖር የለበትም። ሐዋርያው ጴጥሮስ በ36 እዘአ ከአሕዛብ ወገን በሆነው በመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ቤት በሰበከበትና “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ይህን ጉዳይ ግልጽ አድርጎታል። (ሥራ 10:34, 35) ይህም በመሆኑ የክርስቲያን ጉባኤ አድልዎ የምናደርግበት፣ ጎጠኛ የምንሆንበት ወይም ወገናዊነት የምናሳይበት ቦታ አይደለም።
5. በጉባኤ ውስጥ ቡድን መፍጠር ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
5 አንዲት የኮሌጅ ተማሪ መንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ከተገኘች በኋላ እንዲህ ብላለች:- “አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙት ሰዎች የአንድ ዘር ወይም ጎሣ አባላት ናቸው። . . . የይሖዋ ምሥክሮች የተቀመጡት በወገን ተከፋፍለው ሳይሆን አንድ ላይ ተቀላቅለው ነበር።” በጥንቱ ቆሮንቶስ ጉባኤ የነበሩ አንዳንድ አባላት ግን ወገን ይለያዩ ነበር። በዚህም ምክንያት በመካከላቸው ጠብ እንዲፈጠር ያደረጉ ከመሆኑም በላይ አንድነትና ሰላም የሚያሰፍነው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንዳይሠራ ተቃውመዋል። (ገላትያ 5:22) እኛም በጉባኤ ውስጥ ቡድን የምንፈጥር ከሆነ የመንፈሱን አመራር እንቃወማለን ማለት ነው። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጻፈላቸውን የሚከተሉትን ቃላት እናስታውስ:- “ወንድሞች ሆይ፣ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 1:10) በተጨማሪም ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የአንድነትን አስፈላጊነት አበክሮ ገልጿል።—ኤፌሶን 4:1-6, 16
6, 7. አድልዎን በተመለከተ ያዕቆብ ምን ምክር ሰጥቷል? ምክሩስ የሚሠራው እንዴት ነው?
6 ክርስቲያኖች ምንጊዜም ከአድልዎ እንዲርቁ ይጠበቅባቸዋል። (ሮሜ 2:11) አንዳንድ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤ አባላት ባለጠጋ ለሆኑ ግለሰቦች ያደሉ ስለነበር ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወንድሞቼ ሆይ፣ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፣ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፣ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ:- አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፣ ድሀውንም:- አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፣ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን?”—ያዕቆብ 2:1-4
7 የወርቅ ቀለበትና የጌጥ ልብስ ያደረጉ አማኝ ያልሆኑ ባለጠጎችና ያደፈ ልብስ የለበሱ አማኝ ያልሆኑ ድሆች ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ቢመጡ ልዩ አቀባበል የሚደረገው ለባለጠጎቹ ነበር። ባለጠጎቹ “በመልካም ስፍራ” እንዲቀመጡ ሲደረግ ድሆቹ ግን እንዲቆሙ ወይም በአንድ ሰው እግር ሥር መሬት ላይ እንዲቀመጡ ይነገራቸው ነበር። ሆኖም አምላክ የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት ያቀረበው ያለ አድልዎ ለባለጠጎችም ለድሆችም ነው። (ኢዮብ 34:19፤ 2 ቆሮንቶስ 5:14) ስለዚህ ይሖዋን ማስደሰትና አንድ ሆነን እሱን ማገልገል ከፈለግን አድልዎ ማሳየት ወይም ‘ጥቅም ለማግኘት ሌሎችን መካብ’ አይኖርብንም።—ይሁዳ 4, 16 አ.መ.ት
ከአጉረምራሚነት ራቁ
8. እስራኤላውያን በማጉረምረማቸው ምክንያት ምን ደረሰባቸው?
8 አንድነታችንን ጠብቀን ለመኖርና ያገኘነውን መለኮታዊ ሞገስ እንዳናጣ ጳውሎስ “ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ” ሲል የሰጠውን ምክር መከተል ይኖርብናል። (ፊልጵስዩስ 2:14, 15) ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡት እምነት የለሾቹ እስራኤላውያን በሙሴና በአሮን አልፎ ተርፎም በይሖዋ አምላክ ላይ አጉረምርመዋል። ከዚህም የተነሳ ታማኝ ከነበሩት ከኢያሱና ከካሌብ እንዲሁም ከሌዋውያን በስተቀር 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች በሙሉ ተስፋይቱ ምድር አልገቡም፤ ከዚያ ይልቅ ለ40 ዓመታት በተጓዙበት በምድረ በዳ እንዲያልቁ ተደርገዋል። (ዘኍልቁ 14:2, 3, 26-30፤ 1 ቆሮንቶስ 10:10) አጉረምራሚነታቸው ያስከተለባቸው ቅጣት ምንኛ ታላቅ ነው!
9. ማርያም በማጉረምረሟ ምክንያት ምን ደረሰባት?
9 ዘገባው በብሔር ደረጃ አጉረምራሚ መሆን ምን ሊያስከትል እንደሚችል ያሳያል። አጉረምራሚ የሆኑ ግለሰቦችስ? የሙሴ እህት ማርያም ከወንድሟ ከአሮን ጋር ሆና “በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን?” በማለት አጉረምርማ ነበር። ዘገባው በማከል “እግዚአብሔርም ሰማ” ይላል። (ዘኍልቁ 12:1, 2) ውጤቱስ? በዚህ ጉዳይ ላይ ቀዳሚ ስለነበረች ሳይሆን አይቀርም አምላክ ማርያምን አዋርዷታል። እንዴት? በለምጽ እንድትመታና እስክትነጻ ድረስ ለሰባት ቀናት ያህል ከሰፈሩ ውጪ እንድትቆይ በማድረግ ነው።—ዘኍልቁ 12:9-15
10, 11. ቁጥጥር ያልተደረገለት አጉረምራሚነት ምን ሊያስከትል ይችላል? በምሳሌ አስረዳ።
10 ማጉረምረም ትክክል ባልሆነ በአንድ ጉዳይ ላይ ቅሬታ ማሰማት ማለት ብቻ አይደለም። አጉረምራሚነት የተጠናወታቸው ሰዎች ለስሜታቸው ወይም ለክብራቸው ከልክ በላይ ስለሚጨነቁ የሌሎችን ትኩረት ወደ አምላክ ሳይሆን ወደራሳቸው ይስባሉ። እንዲህ ዓይነቱ ባሕርይ ካልተገታ በወንድሞች መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር ከማድረጉም በላይ አንድ ሆነው ይሖዋን ለማገልገል የሚያደርጉትን ጥረት ያደናቅፋል። እንዲህ የሆነበት ምክንያት አጉረምራሚዎች የሚቆረቆሩላቸው ሌሎች ሰዎች ለማግኘት ቅሬታ ማሰማታቸውን ሥራዬ ብለው ስለሚያያዙት ነው።
11 ለምሳሌ ያህል አንድ ሽማግሌ በጉባኤ ውስጥ ክፍሉን የሚያቀርብበትን ወይም ኃላፊነቶቹን የሚወጣበትን መንገድ በተመለከተ አንድ የጉባኤ አባል ትችት ይሰነዝር ይሆናል። አጉረምራሚውን የምናዳምጥ ከሆነ አስተሳሰቡ ሊጋባብን ይችላል። ቅሬታው በእኛ ልብ ውስጥ ከመዘራቱ በፊት የሽማግሌው ሁኔታ ረብሾን አያውቅ ይሆናል፤ አሁን ግን ይረብሸን ጀምሯል። በመጨረሻም ሽማግሌው የሚያደርገው ማንኛውም ነገር አያስደስተንም። ከዚያም አልፈን በእሱ ላይ ያለንን ቅሬታ መናገር ልንጀምር እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱ ባሕርይ በይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ውስጥ ተቀባይነት የለውም።
12. አጉረምራሚነት ከአምላክ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ምን ውጤት ሊያስከትል ይችላል?
12 የአምላክን መንጋ በእረኝነት የመጠበቅ ኃላፊነት ባላቸው ወንድሞች ላይ ማጉረምረም ወደ ተሳዳቢነት ሊያመራ ይችላል። በሽማግሌዎች ላይ ማጉረምረም ወይም ስማቸውን እያጠፉ መሳደብ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን ይችላል። (ዘጸአት 22:28) ንስሐ የማይገቡ ተሳዳቢዎች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም። (1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 6:10) ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ አጉረምራሚዎችን በተመለከተ “ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ” ሲል ጽፏል። ሥልጣን ያላቸው የተባሉት በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ወንዶች ናቸው። (ይሁዳ 8) እነዚህ አጉረምራሚዎች መለኮታዊ ተቀባይነት አልነበራቸውም። እኛም ከክፉ አካሄዳቸው መራቃችን ጥበብ ነው።
13. ቅሬታ ማሰማት ጨርሶ ተገቢ አይደለም ሊባል የማይችለው ለምንድን ነው?
13 ይሁን እንጂ ይሖዋ የምናሰማውን ማንኛውንም ዓይነት ቅሬታ ይጠላል ማለት አይደለም። የሰዶምና የገሞራን “ጩኸት” በቸልታ ሳያልፍ እነዚህን ኃጢአተኛ ከተሞች አጥፍቷቸዋል። (ዘፍጥረት 18:20, 21፤ 19:24, 25) በኢየሩሳሌም በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ብዙም ሳይቆይ “ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፣ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና።” በዚህም ምክንያት “አሥራ ሁለቱ” ‘በመልካም የተመሰከረላቸውን ሰባት ሰዎች’ ምግብ በማከፋፈሉ አስፈላጊ “ጉዳይ” ላይ በመሾም ለችግሩ መፍትሄ ሰጥተዋል። (ሥራ 6:1-6) በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች መሠረት ያለው ቅሬታ ላለመስማት ‘ጆሯቸውን መድፈን’ የለባቸውም። (ምሳሌ 21:13) ሽማግሌዎችም የእምነት ጓደኞቻቸውን ከመንቀፍ ይልቅ የሚያበረታቱና የሚያንጹ መሆን ይገባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 8:1
14. ከአጉረምራሚነት ለመራቅ በተለይ የትኛው ባሕርይ አስፈላጊ ነው?
14 የተቺነት መንፈስ መንፈሳዊ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ሁላችንም ከአጉረምራሚነት መንፈስ መራቅ ይኖርብናል። እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ አንድነታችንን ያናጋል። ከዚህ ይልቅ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን የፍቅርን ፍሬ እንዲያፈራ እንፍቀድ። (ገላትያ 5:22) ‘የንጉሥ ሕግ’ የተባለውን ‘ፍቅርን’ ማንጸባረቃችን አንድ ሆነን ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።—ያዕቆብ 2:8፤ 1 ቆሮንቶስ 13:4-8፤ 1 ጴጥሮስ 4:8
ስም ከማጥፋት ተጠበቁ
15. በሐሜትና በስም ማጥፋት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
15 አጉረምራሚነት ወደ ጎጂ ሐሜት ሊያመራ ስለሚችል ከአንደበታችን ስለሚወጣው ቃል ጠንቃቆች መሆን ይገባናል። ሐሜት ሰዎችንና ኑሯቸውን በተመለከተ የሚነገር ፍሬ ቢስ ወሬ ነው። ስም ማጥፋት ደግሞ የሌላውን ሰው ስም ለማጉደፍ ሆነ ተብሎ የሚነገር የውሸት ወሬ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ወሬ ተንኰልና ክፋት ያዘለ ነው። ከዚህም የተነሳ አምላክ እስራኤላውያንን “በሕዝብህ መካከል በሸንጋይነት አትዙር” ብሏቸው ነበር።—ዘሌዋውያን 19:16
16. ጳውሎስ አንዳንድ ሐሜተኞችን በተመለከተ ምን ብሏል? ምክሩስ እኛን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
16 ፍሬ ቢስ ወሬ ወደ ስም ማጥፋት ሊያመራ ስለሚችል ጳውሎስ አንዳንድ ሐሜተኛ ክርስቲያኖችን ፊት ለፊት ገስጿቸዋል። ጉባኤው እርዳታ ሊያደርግላቸው የሚገቡ መበለቶች ማሟላት የሚኖርባቸውን ብቃት ከዘረዘረ በኋላ መበለቶችን አስመልክቶ “ቤት ለቤት እየዞሩ ሥራን መፍታት ደግሞ ይማራሉ፣ የማይገባውንም እየተናገሩ ለፍላፊዎችና [“ሐሜተኞችና፣” አ.መ.ት ] በነገር ገቢዎች ይሆናሉ እንጂ፣ ሥራ ፈቶች ብቻ አይደሉም” በማለት ተናግሯል። (1 ጢሞቴዎስ 5:11-15) አንዲት ክርስቲያን እህት ወደ ስም አጥፊነት ሊቀየር የሚችል ወሬ የማውራት ልማድ እንዳለባት ከተገነዘበች ጳውሎስ “ሴቶች ጭምቶች፣ የማያሙ” እንዲሆኑ የሰጠውን ምክር ለመከተል ቆርጣ መነሳት ይኖርባታል። (1 ጢሞቴዎስ 3:11) እርግጥ ነው፣ ክርስቲያን ወንዶችም ጎጂ ሐሜት ከመናገር መቆጠብ አለባቸው።—ምሳሌ 10:19
አትፍረዱ!
17, 18. (ሀ) ኢየሱስ በወንድማችን ላይ መፍረድን በተመለከተ ምን አለ? (ለ) ኢየሱስ ስለ መፍረድ የተናገረውን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
17 የወንድሞችን ስም የምናጠፋ ባንሆንም እንኳ በሌሎች ላይ ፈራጅ ላለመሆን ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርብን ይሆናል። ኢየሱስ የሚከተለውን በመናገር ይህን ባሕርይ አውግዟል:- “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፣ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። በወንድምህም ዓይን ያለውን ጕድፍ ስለ ምን ታያለህ፣ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? ወይም ወንድምህን:- ከዓይንህ ጕድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፣ በዓይንህ ምሰሶ አለ። አንተ ግብዝ፣ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፣ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጕድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።”—ማቴዎስ 7:1-5
18 ትክክለኛ ፍርድ የመስጠት ችሎታችን በምሳሌያዊ “ምሰሶ” ተገድቦ እያለ በወንድማችን ዓይን ላይ ያለችን አንዲትን ትንሽ “ጉድፍ” ለማውጣት ማሰብ አይገባንም። እንዲያውም አምላክ ምን ያህል መሐሪ አንደሆነ ከተገነዘብን በመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ ለመፍረድ አንከጅልም። ሰማያዊ አባታችን እነሱን በሚመለከትበት መንገድ እኛም እነሱን መመልከት የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ” የሚል ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ምንም አያስገርምም! የራሳችንን አለፍጽምና በሐቀኝነት መመልከታችን አምላክ እንደ ኃጢአት አድርጎ ከሚመለከተው በሌሎች ላይ ከመፍረድ እንድንቆጠብ ሊያደርገን ይገባል።
ደካማ የክብር ዕቃ
19. ለእምነት ባልንጀሮቻችን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
19 ከእምነት ጓደኞቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን አምላክን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን በሌሎች ላይ ከመፍረድ በመራቅ ብቻ አንወሰንም። እነሱን በማክበር ረገድ ቀዳሚ እንሆናለን። (ሮሜ 12:10) እንዲያውም የእኛን ሳይሆን የእነሱን ጥቅም ለማስቀደም እንፈልጋለን እንዲሁም ለእነሱ ብለን ትሕትና የሚጠይቁ ሥራዎችን በደስታ እናከናውናለን። (ዮሐንስ 13:12-17፤ 1 ቆሮንቶስ 10:24) ይህን የመሰለ ግሩም ዝንባሌ መያዝ የምንችለው እንዴት ነው? እያንዳንዱ አማኝ በይሖዋ ዘንድ ውድ መሆኑን እንዲሁም እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል በሌላው ላይ ጥገኛ እንደሆነ ሁሉ እርስ በርስ መደጋገፍ እንዳለብን በመገንዘብ ነው።—1 ቆሮንቶስ 12:14-27
20, 21. በ2 ጢሞቴዎስ 2:20, 21 ላይ ያሉት ቃላት ለእኛ ምን ትርጉም አላቸው?
20 ግልጹን ለመናገር ክርስቲያኖች ክብራማ የአገልግሎት መዝገብ በአደራ የተሰጣቸው ደካማ የሸክላ ዕቃዎች ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ይህን ቅዱስ አገልግሎት ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ ማከናወን ከፈለግን በእሱና በልጁ ፊት የሚያስከብር አቋም መያዝ ይገባናል። አምላክ የሚጠቀምብን የክብር ዕቃ ሆነን መቀጠል የምንችለው በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ንጹሕ ከሆንን ብቻ ነው። ይህን በተመለከተ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፣ እኵሌቶቹም ለክብር፣ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፣ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል።”—2 ጢሞቴዎስ 2:20, 21
21 ከመለኮታዊ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው የማይኖሩ ግለሰቦች ‘የውርደት ዕቃ’ ይሆናሉ። እኛ ግን አምላካዊ አኗኗር በመከተል ‘ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ወይም የተለየ ለይሖዋ አገልግሎት የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ እንሆናለን።’ በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን ተገቢ ነው:- ‘“የክብር ዕቃ” ነኝን? በእምነት ባልንጀሮቼ ላይ የማሳድረው ተጽዕኖ በጎ ነውን? ከእምነት ባልንጀሮቼ ጋር አንድ ሆኜ የማገለግል የጉባኤው አባል ነኝን?’
አንድ ሆናችሁ ማገልገላችሁን ቀጥሉ
22. የክርስቲያን ጉባኤ ከምን ጋር ሊመሳሰል ይችላል?
22 የክርስቲያን ጉባኤ ከቤተሰብ ጋር ይመሳሰላል። የአንድ ቤተሰብ አባላት በሙሉ ይሖዋን የሚያመልኩ ከሆኑ በቤተሰቡ ውስጥ የፍቅር፣ የመረዳዳትና የደስታ መንፈስ ይሰፍናል። አንድ ቤተሰብ የተለያየ ባሕርይ ያላቸው በርካታ ግለሰቦችን ያቀፈ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ሁሉም የየራሳቸው ጠቃሚ ድርሻ አላቸው። በጉባኤ ውስጥም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ሁላችንም የተለያየ ባሕርይ ያለንና ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም እንኳ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ወደ ራሱ ስቦናል። (ዮሐንስ 6:44፤ 14:6) ይሖዋ እና ኢየሱስ ይወድዱናል፤ እኛም አንድነት እንዳለው ቤተሰብ እርስ በርሳችን መዋደድ ይኖርብናል።—1 ዮሐንስ 4:7-11
23. ምን ነገር መርሳት አይኖርብንም? ምን ለማድረግስ ቆርጠን መነሳት አለብን?
23 በተጨማሪም የቤተሰብ መልክ ባለው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የታማኝነት ባሕርይ ይንጸባረቃል ብለን እንጠብቃለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለ ቊጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን [“ታማኝ፣” NW ] እጆች እያነሡ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 2:8) በመሆኑም ጳውሎስ ታማኝነትን ክርስቲያኖች በሚሰበሰቡበት “ስፍራ ሁሉ” ከሚቀርብ ሕዝባዊ ጸሎት ጋር አያይዞታል። ጉባኤውን ወክለው ጸሎት ማቅረብ ያለባቸው ታማኝ ወንዶች ብቻ ናቸው። እርግጥ አምላክ ሁላችንም ለእሱም ሆነ አንዳችን ለሌላው ታማኝ እንድንሆን ይጠብቅብናል። (መክብብ 12:13, 14) ስለዚህ በሰውነታችን ላይ እንዳሉ ብልቶች በቅንጅት አንድ ላይ ለመሥራት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲሁም በይሖዋ አምላኪዎች ቤተሰብ ውስጥ በአንድነት የምናገለግል እንሁን። ከሁሉም በላይ እርስ በርስ መደጋገፍ እንዳለብንና አንድ ሆነን ይሖዋን ማገልገላችንን ከቀጠልን መለኮታዊ ተቀባይነትና በረከት እንደምናገኝ እናስታውስ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የይሖዋ ሕዝቦች አንድ ሆነው አምላክን እንዲያገለግሉ የሚያስችላቸው ምንድን ነው?
• ክርስቲያኖች ከአድሏዊነት የሚርቁት ለምንድን ነው?
• ማጉረምረም ትክክል አይደለም የምትለው ለምንድን ነው?
• ለእምነት ባልንጀሮቻችንን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጴጥሮስ ‘አምላክ እንደማያዳላ’ ተገንዝቧል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ማርያምን ያዋረዳት ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታማኝ ክርስቲያኖች አንድ ሆነው ይሖዋን በደስታ ያገለግላሉ