‘ዕለት ዕለት ይከተለኝ’
‘ዕለት ዕለት ይከተለኝ’
“የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።”—1 ጴጥሮስ 2:21
1, 2. ኢየሱስ በማስተማሩ ሥራ የተወልንን ፍጹም ምሳሌ መኮረጅ ከአቅማችን በላይ የማይሆንብን ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዛሬ በምድር ላይ ከተነሱት አስተማሪዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ አስተማሪ ነው። ከዚህም በላይ ሰው ሆኖ በኖረባቸው ዓመታት ሁሉ ኃጢአት ሠርቶ የማያውቅ ፍጹም ሰው ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:22) ታዲያ ይህ ሲባል እኛ ፍጹማን ያልሆንን ሰዎች ኢየሱስ በአስተማሪነቱ የተወልንን ምሳሌ መኮረጅ ከአቅማችን በላይ ይሆንብናል ማለት ነውን? በፍጹም።
2 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው የኢየሱስ የማስተማር ሥራ የተመሠረተው በፍቅር ላይ ነበር። ፍቅር ደግሞ ማናችንም ብንሆን ልናዳብረው የምንችለው ባሕርይ ነው። የአምላክ ቃል ለሌሎች ሰዎች ያለን ፍቅር እያደገና እየጎለበተ እንዲሄድ በጥብቅ ያሳስበናል። (ፊልጵስዩስ 1:9፤ ቆላስይስ 3:14) ይሖዋ ከፍጥረታቱ ከአቅማቸው በላይ አይጠብቅባቸውም። እንዲያውም ‘አምላክ ፍቅር’ ስለሆነና እኛንም በአምሳሉ ስለፈጠረን ፍቅር ማሳየት እንድንችል አድርጎ ሠርቶናል ለማለት ይቻላል። (1 ዮሐንስ 4:8፤ ዘፍጥረት 1:27) ስለሆነም በጭብጡ ጥቅስ ላይ የሚገኙትን የሐዋርያው ጴጥሮስ ቃላት መፈጸም እንደምንችል በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። የክርስቶስን ፈለግ በቅርብ መከተል እንችላለን። እንዲያውም ኢየሱስ ‘ዕለት ዕለት ይከተለኝ’ በማለት የሰጠውን ትእዛዝ መጠበቅ እንችላለን። (ሉቃስ 9:23) እንግዲያው ክርስቶስ ለሚያስተምረው ትምህርትና ለሚያስተምራቸው ሰዎች ያሳየውን ፍቅር እንዴት መኮረጅ እንደምንችል አንድ በአንድ እንመልከት።
ለተማርናቸው እውነቶች ፍቅር ማዳበር
3. አንዳንዶች ጥናት ከባድ ሥራ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው? ሆኖም በምሳሌ 2:1-5 ላይ ምን ማሳሰቢያ ይገኛል?
3 ለሌሎች ሰዎች የምናስተምረውን እውነት ለማፍቀር በመጀመሪያ እኛ ራሳችን እንዲህ ዓይነቱን እውነት የመማር ፍቅር ሊያድርብን ይገባል። በዚህ ዓለም ውስጥ ለትምህርት እንዲህ ያለ ፍቅር ማዳበር ቀላል አይደለም። ብዙ ሰዎች በቂ ትምህርት ስላላገኙና ከልጅነታቸው ጀምሮ ባዳበሯቸው መጥፎ ልማዶች የተነሳ ለጥናት ብዙም ፍቅር የላቸውም። ይሁን እንጂ ከይሖዋ መማራችን በጣም አስፈላጊ ነው። ምሳሌ 2:1-5 እንዲህ ይላል:- “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።”
4. ልብን ‘ማዘንበል’ ሲባል ምን ማለት ነው? እንዲህ ለማድረግ ምን ዓይነት አመለካከት መያዝ ይኖርብናል?
4 ከቁጥር 1 እስከ 4 ባሉት ውስጥ ‘እንድንቀበል’ እና ‘ሸሽገን እንድንይዝ’ ብቻ ሳይሆን አጥብቀን ‘እንድንፈላልግ’ እና ‘እንድንሻ’ ተደጋጋሚ ማበረታቻ መሰጠቱን ልብ ማለት ይገባናል። ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ እንድናደርግ የሚያንቀሳቅሰን ምንድን ነው? “ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ” የሚለውን ሐረግ ልብ በል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዳስቀመጠው ይህ ማሳሰቢያ “ትኩረት እንዲሰጥ ብቻ የቀረበ ጥያቄ አይደለም፤ አንድ ዓይነት ዝንባሌ እንድናዳብር ይኸውም ትምህርቱን በጉጉት የመከታተል ችሎታ እንዲኖረን ትእዛዝ መስጠቱ ነው።” ይሖዋ የሚያስተምረንን ትምህርት በጉጉት የምንከታተል ሰዎች እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል? ይህ በአመለካከታችን ላይ የተመካ ነው። ‘የአምላክን እውቀት’ እንደ “ብር” እና እንደ “ተቀበረ ገንዘብ” መመልከት ይኖርብናል።
5, 6. (ሀ) በጊዜ ሂደት ምን ሊከሰት ይችላል? ይህ እንዳይሆን እንዴት መከላከል እንችላለን? (ለ) ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘውን የእውቀት ሃብት በየጊዜው ማሳደግ የሚገባን ለምንድን ነው?
5 እንዲህ ያለ አመለካከት ማዳበር አስቸጋሪ አይደለም። ለምሳሌ ያህል እስከ አሁን ያገኘኸው ‘የአምላክ እውቀት’ ይሖዋ ታማኝ የሆኑ የሰው ዘሮችን በምድራዊ ገነት ላይ ለዘላለም ለማኖር ያለውን ዓላማ እንደሚጨምር እሙን ነው። (መዝሙር 37:28, 29) ይህን እውነት መጀመሪያ በተማርክበት ጊዜ አእምሮህና ልብህ በተስፋና በደስታ እንዲሞላ የሚያደርግ እውነተኛ ሃብት እንዳገኘህ ተሰምቶህ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። አሁንስ? እንደ ውድ ሃብት ትመለከተው ለነበረው እውቀት ያለህ አድናቆት በጊዜ ሂደት ቀንሶ ይሆን? ከሆነ ሁለት ነገሮችን ለማድረግ ሞክር። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ከብዙ ዓመታት በፊት ያወቅካቸውን ጨምሮ ይሖዋ ያስተማረህን እያንዳንዱን እውነት እንደ ውድ ነገር እንድትመለከተው የሚያደርግህ ምን እንደሆነ ራስህን በመጠየቅ አድናቆትህን እንደገና ለማደስ ሞክር።
6 በሁለተኛ ደረጃ፣ መንፈሳዊ ሃብት ማካበትህን ቀጥል። በቁፋሮ ላይ እያለህ አንድ የከበረ ማዕድን ብታገኝ ምን ታደርጋለህ? ያገኘኸውን ብቻ ይዘህ መንገድህን ትቀጥላለህ? ወይስ ሌላም ለማግኘት ቁፋሮህን ትቀጥላለህ? የአምላክ ቃል በብርና በተቀበረ ሃብት በተመሰሉ ክቡርና ውድ እውነቶች የተሞላ ነው። እስከ አሁን ያገኘኸው የመንፈሳዊ ሃብት መጠን ምንም ያህል ቢሆን ተጨማሪ ማግኘትህ አይቀርም። (ሮሜ 11:33) እውነትን በተመለከተ አዲስ እውቀት በምታገኝበት ጊዜ እንዲህ እያልህ ራስህን ጠይቅ:- ‘ይህን እውቀት እንደ ውድ ሃብት እንድመለከተው የሚያደርገኝ ምንድን ነው? ስለ ይሖዋ ባሕርይ ወይም ስለ ዓላማዎቹ ጥልቅ ማስተዋል እንዳገኝ ረድቶኛል? የኢየሱስን ፈለግ እንድከተል የሚረዳኝ ተግባራዊ መመሪያ ላገኝበት እችላለሁ?’ እንደነዚህ ባሉ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰልህ ይሖዋ ላስተማረህ እውነት ያለህ ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ይረዳሃል።
ለምናስተምረው እውነት ፍቅር ማሳደር
7, 8. ከመጽሐፍ ቅዱስ ለተማርነው እውነት ፍቅር እንዳለን ለሌሎች ሰዎች ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? አንድ ምሳሌ ጥቀስ።
7 ሌሎችን በምናስተምርበት ጊዜ ከአምላክ ቃል ለተማርነው እውነት ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል መጽሐፍ ቅዱስን በስብከቱና በማስተማር ሥራችን ላይ በእጅጉ እንጠቀምበታለን። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች በአገልግሎታቸው ላይ ምንጊዜም በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲጠቀሙ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። ይህንን ሐሳብ ተግባራዊ በምታደርግበት ጊዜ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመህ የቤቱ ባለቤት ለምታካፍለው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ከፍ ያለ ግምት እንዳለህ እንዲገነዘብ ማድረግ ትችላለህ።—ማቴዎስ 13:52
8 ለምሳሌ ያህል፣ ባለፈው ዓመት አሸባሪዎች በኒው ዮርክ ከተማ ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት ተከትሎ አንዲት ክርስቲያን እህት በአገልግሎት ለምታገኛቸው ሰዎች መዝሙር 46:1, 11ን ታነብላቸው ነበር። በመጀመሪያ አደጋው ካሳደረባቸው ጭንቀትና ሐዘን አገግመው እንደሆነ ትጠይቃቸዋለች። የሚሰጡትን መልስ በጥሞና አዳምጣ ስሜታቸውን እንደምትረዳላቸው ከገለጸችላቸው በኋላ “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እኔን በእጅጉ ያጽናናኝን አንድ ጥቅስ ባነብልህ (ባነብልሽ) ደስ ይለኛል” ትላቸዋለች። አልፈልግም ያሉት ከስንት አንድ ሲሆኑ ከብዙዎች ጋር ግን አስደሳች ውይይት ማድረግ ችላለች። ይህች እህት ወጣቶችን በምታነጋግርበት ጊዜ በአብዛኛው እንዲህ ትላለች:- “ላለፉት 50 ዓመታት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ሳስተምር ቆይቻለሁ። በጣም የሚገርመው ነገር ይህ መጽሐፍ ሊፈታው የማይችለው አንድም ችግር አጋጥሞኝ አያውቅም።” ሰዎችን በምናነጋግርበት ጊዜ ከልብ የመነጨና ግለት የታከለበት አቀራረብ በመጠቀም ከአምላክ ቃል ላገኘነው ትምህርት ፍቅርና ከፍ ያለ ግምት እንዳለን ማሳየት እንችላለን።—መዝሙር 119:97, 105
9, 10. እምነታችንን በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 ሰዎች ስለ እምነታችን ጥያቄ በሚጠይቁን ጊዜ ከአምላክ ቃል ላይ ለተማርናቸው ትምህርቶች ያለንን ፍቅር የምናሳይበት ጥሩ አጋጣሚ እናገኛለን። የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በራሳችን አስተሳሰብ ላይ ተመሥርተን መልስ ከመስጠት እንቆጠባለን። (ምሳሌ 3:5, 6) ከዚህ ይልቅ መልስ በምንሰጥበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ እንጠቀማለን። ሰዎች ልመልሰው የማልችለው ከባድ ጥያቄ ይጠይቁኝ ይሆናል ብለህ ፍርሃት ተሰምቶህ ያውቃል? እንዲህ ያለውን ፍርሃት ለማስወገድ ልትወስዳቸው የምትችላቸውን ሁለት ውጤታማ እርምጃዎች ተመልከት።
10 የቻልከውን ያህል ጥሩ ዝግጅት አድርግ። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፣ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 3:15) ስለ እምነትህ የሚቀርብልህን ጥያቄ ለመመለስ ዝግጁ ነህ? ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ልማዶች ወይም ተግባሮች ለምን እንደማትካፈል ቢጠይቅህ “ሃይማኖቴ ስለማይፈቅድልኝ ነው” የሚል መልስ በመስጠት ረክተህ ዝም አትበል። እንዲህ ያለው መልስ የአንድ ሃይማኖት አባል የሆንከው በሌሎች ሰዎች ሐሳብ ተመርተህ እንደሆነና የመናፍቃን ቡድን አባል እንደሆንክ ሊያስቆጥርህ ይችላል። ከዚህ ይልቅ “የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ድርጊት ያወግዛል” ወይም “እንዲህ ማድረጌ አምላኬን ያሳዝነዋል” ማለቱ የተሻለ ይሆናል። ከዚያም ለምን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ምክንያታዊ ማብራሪያ ስጥ።—ሮሜ 12:1 አ.መ.ት
11. ስለ አምላክ ቃል እውነት ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ምንጊዜም ዝግጁ እንድንሆን የሚረዳን መጽሐፍ የትኛው ነው?
11 መልስ መስጠት የማትችል ሆኖ ከተሰማህ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ ጊዜ መድበህ ለምን አታጠናውም? a ሰዎች በአብዛኛው የሚያነሷቸውን ጥቂት ርዕሶች ምረጥና አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥቦችን በአእምሮህ ለመያዝ ሞክር። አገልግሎት ላይ ማመራመር መጽሐፍህንና መጽሐፍ ቅዱስን ከመጠቀም ወደኋላ አትበል። ለተለያዩ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ለማግኘት የሚረዳህ ግሩም መጽሐፍ እንዳለና ከእርሱ ላይ አንዳንድ ሐሳቦች ብትመለከት ደስ እንደሚልህ ልትገልጽለት ትችላለህ።
12. ለአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ መልስ ከሌለን ምን ማለት እንችላለን?
12 ከልክ በላይ አትጨነቅ። ለሚጠየቀው ጥያቄ ሁሉ መልስ መስጠት የሚችል ሰው የለም። ስለሆነም ልትመልሰው የማትችለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ በምትጠየቅበት ጊዜ እንደሚከተለው በማለት መልስ መስጠት ትችላለህ:- “በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸው። እውነቱን ለመናገር መልሱን አላውቀውም። መልሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደሚገኝ ግን እርግጠኛ ነኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስለምወድ በዚህ ጥያቄ ላይ ምርምር አድርጌ መልሱን በሚቀጥለው ጊዜ እነግርሃለሁ።” እንዲህ ያለው ግልጽ የሆነና ትሕትና የታከለበት መልስ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ መንገድ ሊከፍት ይችላል።—ምሳሌ 11:2
የምናስተምራቸውን ሰዎች በፍቅር መያዝ
13. ስለምንሰብክላቸው ሰዎች አዎንታዊ አመለካከት መያዝ የሚገባን ለምንድን ነው?
13 ኢየሱስ ለሚያስተምራቸው ሰዎች ፍቅር አሳይቷል። በዚህ ረገድ የእርሱን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? በአካባቢያችን ለሚኖሩ ሰዎች የግድ የለሽነት ዝንባሌ ማሳየት አይገባንም። ‘ሁሉን የሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እየቀረበ ሲሆን በዚህ ጦርነት በቢልዮን ከሚቆጠሩ የሰው ልጆች መካከል ብዙዎቹ ይጠፋሉ። (ራእይ 16:14፤ ኤርምያስ 25:33) ሆኖም ማን እንደሚተርፍ ማን ደግሞ እንደሚጠፋ አናውቅም። ይህ ፍርድ የሚፈጸመው ወደፊት ሲሆን ፈራጁ ይሖዋ የሾመው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ፍርዱ እስኪሰጥ ድረስ ግን እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱን አስተካክሎ የይሖዋ አገልጋይ ይሆናል የሚል አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ይኖርብናል።—ማቴዎስ 19:24-26፤ 25:31-33፤ ሥራ 17:31
14. (ሀ) የሰዎችን ችግር የምንረዳ መሆን አለመሆናችንን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የሌሎችን ችግር የምንረዳና የምናስብላቸው መሆናችንን ማሳየት የምንችልባቸው ተግባራዊ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
14 እንግዲያው እኛም እንደ ኢየሱስ ለሰዎች አዘኔታ ማሳየት እንፈልጋለን። እንዲህ እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን:- ‘በሃይማኖት፣ በፖለቲካውና በንግዱ ዓለም ድርጅቶች የረቀቁ ውሸቶችና ማጭበርበሪያዎች ለተታለሉ ሰዎች አዝንላቸዋለሁን? ለምንነግራቸው መልእክት ግድ የለሽ እንደሆኑ ከተሰማኝ ለምን እንደዚያ እንደተሰማቸው ለመረዳት እሞክራለሁ? እኔ ወይም ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች በአንድ ወቅት ተመሳሳይ ስሜት እንደነበረን ዘንግቻለሁ? አቀራረቤን እንደሁኔታው እቀያይራለሁ? ወይስ እነዚህ ሰዎች የመለወጥ ተስፋ የላቸውም ብዬ እተዋቸዋለሁ?’ (ራእይ 12:9) ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ተረድተን ከልብ እንደምናዝንላቸው ከተሰማቸው ለመልእክታችን አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ይነሳሱ ይሆናል። (1 ጴጥሮስ 3:8) በተጨማሪም እንዲህ ያለው ባሕርይ በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ይበልጥ እንድናስብላቸው ይገፋፋናል። ጥያቄዎቻቸውንና የሚያሳስቧቸውን ነገሮች በማስታወሻችን ላይ እንይዝና ተመልሰን በምናነጋግራቸው ጊዜ ከዚያ በፊት ባደረግነው ውይይት ላይ የሰጧቸውን አስተያየቶች አስበንባቸው እንደመጣን ልንገልጽላቸው እንችላለን። እንዲሁም በወቅቱ መፍትሔ የሚያሻው ብርቱ ጉዳይ አጋጥሟቸው ከሆነ ተግባራዊ እርዳታ መስጠት እንችል ይሆናል።
15. የሰዎችን በጎ ጎን የመመልከት ባሕርይ ማዳበር የሚገባን ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
15 የኢየሱስን ፈለግ በመከተል እኛም የሰዎችን በጎ ጎን ማየት ያስደስተናል። አንዲት ነጠላ ወላጅ ልጆቿን ለማሳደግ የሚያስመሰግን ጥረት እያደረገች ይሆናል። አንድ አባት የቤተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ከላይ ታች ይዋትት ይሆናል። አንድ አረጋዊ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት ማሳየት ጀምረው ሊሆን ይችላል። የምናገኛቸው ሰዎች ያሏቸውን እንደነዚህ የመሳሰሉ በጎ ባሕርያት አስተውለን እናመሰግናቸዋለን? እንዲህ ማድረጋችን ከሰዎቹ ጋር ለመግባባት የሚያስችል የጋራ ነጥብ አግኝተን ስለ አምላክ መንግሥት እንድንመሰክር መንገድ ይከፍትልናል።—ሥራ 26:2, 3
ፍቅር ለማሳየት ትሕትና በጣም አስፈላጊ ነው
16. ለምንሰብክላቸው ሰዎች የዋህነትና አክብሮት ማሳየታችን አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
16 ለምናስተምራቸው ሰዎች ያለን ፍቅር መጽሐፍ ቅዱስ “እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል” በማለት የሚሰጠውን ጥበብ የታከለበት ማስጠንቀቂያ እንድንታዘዝ ይገፋፋናል። (1 ቆሮንቶስ 8:1) ኢየሱስ ከፍተኛ እውቀት የነበረው ቢሆንም ራሱን ከፍ ከፍ አድርጎ አያውቅም። ስለሆነም ስለ እምነትህ ለሌሎች በምትናገርበት ጊዜ ተከራካሪ ከመሆን ተቆጠብ፤ ወይም የትዕቢት መንፈስ አታንጸባርቅ። ግባችን የሰዎችን ልብ በመንካት ሰዎቹ እኛ በጣም ለምንወደው እውነት ፍቅር እንዲያድርባቸው መርዳት ነው። (ቆላስይስ 4:6) ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ለሚጠየቁት ጥያቄ ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጁ መሆን እንዳለባቸው በሰጣቸው ምክር ላይ ይህንን “በየዋህነትና በፍርሃት [“በአክብሮት፣” አ.መ.ት ]” ማድረግ እንዳለብን መጥቀሱን መዘንጋት አይኖርብንም። (1 ጴጥሮስ 3:15) የዋህና ሰው አክባሪ ከሆንን ሰዎችን እኛ ወደምናገለግለው አምላክ እንዲሳቡ መርዳት እንችላለን።
17, 18. (ሀ) የአምላክ አገልጋይ ለመሆን ባለን ብቃት ላይ ለሚሰነዘርብን ትችት ምላሽ መስጠት የሚኖርብን እንዴት ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መጽሐፉ የተጻፈባቸውን የመጀመሪያዎቹን ቋንቋዎች የግድ ማወቅ የማያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
17 ሰዎች በእውቀታችን ወይም በትምህርት ደረጃችን እንዲያደንቁን ለማድረግ መሞከራችን ምንም ፋይዳ አይኖረውም። በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች አንድ ዓይነት የዩኒቨርስቲ ዲግሪ ወይም ማዕረግ የሌለውን ሰው ለማነጋገር ፈቃደኞች ባይሆኑ ይህ አመለካከታቸው ተስፋ ሊያስቆርጥህ አይገባም። ኢየሱስ በዘመኑ በነበረው የረቢዎች ትምህርት ቤት ገብቶ እንዳልተማረ ለተሰነዘረበት ነቀፋ ጆሮ ሰጥቶ አያውቅም። እንዲሁም በጊዜው ለነበረው አስተሳሰብ በመሸነፍ ያለውን ከፍተኛ እውቀት ለማሳየትና ሰዎችን ለማስደመም አልሞከረም።—ዮሐንስ 7:15
18 ክርስቲያን አገልጋዮች ከፍተኛ ግምት የሚሰጡት ለዓለማዊ ትምህርት ሳይሆን ለፍቅርና ለትሕትና ነው። ለአገልግሎቱ ብቁ እንድንሆን የሚያደርገን ታላቁ አስተማሪ ይሖዋ ነው። (2 ቆሮንቶስ 3:5, 6) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ምንም ይበሉ ምን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ለመሆን መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን የመጀመሪያዎቹን ቋንቋዎች መማር አያስፈልገንም። ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ አማካኝነት ያስጻፈው የያዛቸውን ውድ እውነቶች ማንኛውም ሰው ሊረዳው በሚችል ግልጽና ቀጥተኛ አገላለጽ በመጠቀም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ መቶዎች ወደሚቆጠሩ ቋንቋዎች ቢተረጎምም እንኳን እነዚህ እውነቶች አይለወጡም። ስለሆነም የጥንቶቹን ቋንቋዎች መማር አልፎ አልፎ ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም የግድ አስፈላጊ ነው ማለት ግን አይደለም። ከዚህም በላይ አንድ ሰው በቋንቋ ችሎታው የሚኩራራ ከሆነ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሊኖረው የሚገባውን ለመማር ዝግጁ የመሆን ባሕርይ ሊያጣ ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 6:4
19. ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ጠቃሚ ሥራ የሆነው በምን መንገድ ነው?
19 ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ትሕትና የሚጠይቅ ሥራ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ብዙውን ጊዜ ለተቃውሞ፣ ለግድ የለሽነትና ሌላው ቀርቶ ለስደት እንጋለጣለን። (ዮሐንስ 15:20) ሆኖም አገልግሎታችንን በታማኝነት በመወጣት እጅግ ጠቃሚ ሥራ እናከናውናለን። በዚህ ሥራ አማካኝነት ሌሎችን በትሕትና ማገልገላችንን ከቀጠልን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰዎች ያሳየውን ፍቅር እየኮረጅን ነው ማለት ይቻላል። እስቲ ተመልከት:- በግ መሰል የሆነ አንድ ሰው እንኳን ለማግኘት በሺህ ለሚቆጠሩ ግድ የለሽ ወይም ተቃዋሚ ሰዎች መስበክ ቢጠይቅብን ድካማችን የሚያስቆጭ ይሆናልን? በፍጹም አይሆንም! ስለሆነም ተስፋ ሳንቆርጥ በዚህ ሥራ ላይ መካፈላችንን በመቀጠል እስከ አሁን ያላገኘናቸውን በግ መሰል ሰዎች ለመርዳት በታማኝነት እንዳገለገልን ይቆጠራል። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ይሖዋና ኢየሱስ ሌሎች ብዙ ሰዎች ተገኝተው የሚረዱበትን መንገድ እንደሚያመቻቹ ምንም ጥርጥር የለውም።—ሐጌ 2:7
20. ምሳሌ በመሆን ሌሎችን ማስተማር የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
20 ሌሎችን ለማገልገል እንደምንፈልግ የምናሳይበት ሌላው መንገድ ምሳሌ ሆኖ ማስተማር ነው። ለምሳሌ ያህል “ደስተኛ አምላክ” የሆነውን ይሖዋን ማገልገል ከሁሉ የተሻለውና ከምንም በላይ የሚያረካ የሕይወት መንገድ መሆኑን ለሌሎች ሰዎች ማስተማር እንፈልጋለን። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW ) እነዚህ ሰዎች ጠባያችንን እንዲሁም ከጎረቤቶቻችን፣ በትምህርት ቤት አብረውን ከሚማሩ እንዲሁም ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ሲመለከቱ ደስታና እርካታ የተሞላ ሕይወት እንደምንመራ በግልጽ ይታያቸዋልን? በተመሳሳይም፣ የክርስቲያን ጉባኤ ለሌሎች ደንታ ቢስ በሆነውና ጭካኔ በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ የሚገኝ እርስ በርሱ የሚዋደድ ቤተሰብ መሆኑን ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን እናስተምራቸዋለን። ለእያንዳንዱ የጉባኤው አባል ፍቅር እንዳለንና በመካከላችን ያለው ሰላም እንዳይደፈርስ ብርቱ ጥረት እንደምናደርግ ተማሪዎቻችን በግልጽ ማየት ይችላሉ?—1 ጴጥሮስ 4:8
21, 22. (ሀ) በምናከናውነው አገልግሎት ረገድ ራሳችንን መመርመራችን በየትኞቹ አጋጣሚዎች ለመጠቀም ያንቀሳቅሰናል? (ለ) በሚቀጥለው የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ በሚወጡት ርዕሶች የትኛው ጥያቄ ይብራራል?
21 አገልግሎታችንን የምናከናውንበት የፈቃደኝነት መንፈስ አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን እንድንመረምር ይገፋፋናል። ብዙዎች በሐቀኝነት እንዲህ ማድረጋቸው የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመጀመር ወይም እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ በመሄድ አገልግሎታቸውን የማስፋት አጋጣሚ እንዳላቸው እንዲገነዘቡ አስችሏቸዋል። ሌሎች ደግሞ ከአገራቸው ሳይወጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያደገ ያለውን ከሌላ አገር የመጡ ሰዎች ለመርዳት ሲሉ ቋንቋቸውን ለመማር ተነሳስተዋል። አንተም እንዲህ ያለ አጋጣሚ ካለህ ሁኔታውን ትኩረት ሰጥተህ በጸሎት አስብበት። ይሖዋን በማገልገል የምትመራው ሕይወት ታላቅ ደስታ፣ እርካታና የአእምሮ ሰላም ያስገኝልሃል።—መክብብ 5:12
22 በመሆኑም ለምናስተምረው የእውነት ቃልና ለምናስተምራቸው ሰዎች ያለንን ፍቅር በማሳደግ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ መኮረጃችንን እንቀጥል። በእነዚህ ሁለት ዘርፎች ፍቅራችንን ማዳበራችንና ማንጸባረቃችን ክርስቶስን የምንመስል አስተማሪዎች ለመሆን ጠንካራ መሠረት እንድንጥል ይረዳናል። ይሁን እንጂ በዚያ መሠረት ላይ መገንባት የምንችለው እንዴት ነው? በሚቀጥለው የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ኢየሱስ የተጠቀመባቸውን አንዳንድ የማስተማሪያ ዘዴዎች የሚያብራሩ ተከታታይ ርዕሶች ይወጣሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ኢየሱስ እንድንከተለው የተወልን ምሳሌ ከአቅማችን በላይ እንዳልሆነ ምን ማረጋገጫ አለን?
• ከመጽሐፍ ቅዱስ ለተማርነው እውነት ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
• በእውቀት እያደግን በሄድን መጠን ትሑት መሆን የሚኖርብን ለምንድን ነው?
• ለምናስተምራቸው ሰዎች ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቻልከውን ያህል ጥሩ ዝግጅት አድርግ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘የአምላክን እውቀት’ እንደ ውድ ሃብት የምትመለከተው ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ጥሩ አድርገህ ልትጠቀምበት ትችላለህ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለሰዎች ምሥራቹን በመንገር ለእነርሱ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን