ይሖዋ የክህደትን ጎዳና ይጠላል
ይሖዋ የክህደትን ጎዳና ይጠላል
‘አንዳችን በሌላው ላይ ክህደት አንፈጽም።’—ሚልክያስ 2:10 Nw
1. የዘላለም ሕይወት ማግኘት ከፈለግን አምላክ ምን ይጠብቅብናል?
የዘላለም ሕይወት ማግኘት ትፈልጋለህ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው በዚህ ተስፋ የምታምን ከሆነ ‘ምን ጥያቄ አለው’ ብለህ ትመልስ ይሆናል። ይሁን እንጂ አምላክ ወደፊት በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት እንዲሰጥህ ከፈለግህ እሱ ያወጣቸውን ብቃቶች ማሟላት ይኖርብሃል። (መክብብ 12:13፤ ዮሐንስ 17:3) ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ብቃቶቹን ያሟላሉ ብሎ መጠበቁ ምክንያተ ቢስነት ነውን? አይደለም። ምክንያቱም ይሖዋ “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና” በማለት የሚያበረታታ ሐሳብ ተናግሯል። (ሆሴዕ 6:6) ስለዚህ ስህተት ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎች እንኳን የአምላክን ብቃቶች ማሟላት ይችላሉ ማለት ነው።
2. ብዙ እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ ክህደት የፈጸሙት እንዴት ነበር?
2 ይሁን እንጂ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልጉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። ሆሴዕ ሌላው ቀርቶ ብዙ እስራኤላውያን እንኳን ይህን ማድረግ እንዳልፈለጉ ገልጿል። በብሔር ደረጃ የአምላክን ሕግ ለመታዘዝ ቃል ኪዳን ገብተው ወይም ተስማምተው ነበር። (ዘጸአት 24:1-8) ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የአምላክን ሕግ በመጣስ ‘ቃል ኪዳኑን ተላለፉ።’ በዚህም ምክንያት ይሖዋ እነዚያን እስራኤላውያን ‘ክህደት ፈጽመውብኛል’ በማለት ተናግሯል። (ሆሴዕ 6:7 NW ) ከዚያ ወዲህ ሌሎች ብዙ ሰዎች እንደ እነርሱ አድርገዋል። ሆኖም ይሖዋ በእርሱም ላይ ሆነ እርሱን በሚወዱና በሚያገለግሉ ሰዎች ላይ የሚፈጸመውን ክህደት አጥብቆ ይጠላል።
3. በዚህ ጥናት ውስጥ ምን ነገር እንመረምራለን?
3 አምላክ ስለ ክህደት ያለውን አመለካከት አበክሮ የገለጸው ነቢዩ ሆሴዕ ብቻ አይደለም። እኛም ረዥምና አስደሳች ሕይወት ለማግኘት ከፈለግን ይህን ማወቅና መቀበል ያስፈልገናል። ከዚህ በፊት በነበረው ርዕስ ውስጥ የሚልክያስን ትንቢታዊ መልእክት ከመጽሐፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ አንስቶ መመርመር ጀምረናል። አሁን ደግሞ የዚህን መጽሐፍ ሁለተኛ ምዕራፍ አውጥተን አምላክ ስለ ክህደት ያለው አመለካከት እንዴት ትኩረት እንዳገኘ እንመልከት። ሚልክያስ የተናገረው የአምላክ ሕዝቦች ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ በመካከላቸው ሰፍኖ ስለነበረው ሁኔታ ቢሆንም ይህ ሁለተኛ ምዕራፍ ዛሬ ለምንኖረው ለእኛም ትልቅ ትርጉም አለው።
ሊወቀሱ የሚገባቸው ካህናት
4. ይሖዋ ለካህናቱ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው?
4 ሚልክያስ ምዕራፍ 2 የአይሁድ ካህናት ከይሖዋ የጽድቅ መንገዶች በመራቃቸው ምክንያት በተሰነዘረባቸው ወቀሳ ይጀምራል። ምክሩን ካልሰሙና መንገዳቸውን ካላስተካከሉ ከባድ ችግር እንደሚመጣባቸው የተረጋገጠ ነው። የመጀመሪያዎቹን ሁለት ቁጥሮች ልብ በል:- “አሁንም እናንተ ካህናት ሆይ፣ ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው። ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ ባትሰሙ፣ በልባችሁም ባታደርጉት፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እርግማን እሰድድባችኋለሁ፣ በረከታችሁንም እረግማታለሁ።” ካህናቱ የአምላክን ሕግ ለሕዝቡ አስተምረውና ለራሳቸውም ጠብቀው ቢሆን ኖሮ በረከትን ባገኙ ነበር። ሆኖም የአምላክን ፈቃድ ችላ በማለታቸው ምክንያት እርግማንና ኩነኔ ይመጣባቸዋል። ካህናቱ የሚናገሯቸው በረከቶች እንኳን ሳይቀር ወደ እርግማን ይለወጣል።
5, 6. (ሀ) በተለይ ካህናቱ ተነቃፊ የሆኑት ለምን ነበር? (ለ) ይሖዋ ለካህናቱ ያለውን ንቀት የገለጸው እንዴት ነው?
5 በተለይ ካህናቱ ተነቃፊ ሆነው የተገኙት ለምንድን ነው? ሚል 2 ቁጥር 7 አንድ ግልጽ ምክንያት ይጠቁመናል:- “ካህኑ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፣ ሰዎችም ሕግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል።” አንድ ሺህ ከሚበልጡ ዓመታት ቀደም ብሎ በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን የተሰጠው የአምላክ ሕግ ካህናት ‘እግዚአብሔር የነገራቸውን ሥርዓት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች የማስተማር’ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይናገራል። (ዘሌዋውያን 10:11) የሚያሳዝነው ግን በአንድ ሌላ ወቅት ላይ የ2 ዜና መዋዕል 15:3 ጸሐፊ “እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፣ ያለ አስተማሪም ካህን፣ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር” በማለት ዘግቧል።
6 በሚልክያስ ዘመን ይኸውም በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ካህናቱ የሚገኙበት ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነበር። የአምላክን ሕግ ለሕዝቡ ማስተማራቸውን አቁመው ነበር። ስለዚህ እነዚያ ካህናት በአምላክ ፊት መጠየቃቸው የተገባ ነው። ይሖዋ በእነርሱ ላይ የተናገራቸውን ተግሣጽ ያዘሉ ቃላት ልብ በል። ሚልክያስ 2:3 “የመሥዋዕታችሁንም ፋንድያ በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ” በማለት ይገልጻል። እንዴት ያለ ዘለፋ ነው! ለመሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሳት ፈርስ ከሠፈር ውጪ ተወስዶ እንደሚቃጠል የሚታወስ ነው። (ዘሌዋውያን 16:27) ሆኖም ይሖዋ ፈርሱን በፊታቸው ላይ እንደሚበትን መናገሩ የሚያቀርቡለትን መሥዋዕትም ሆነ መሥዋዕቱን ያቀርቡ የነበሩትን ሰዎች በንቀት ዓይን እንደሚመለከታቸውና እንደማይቀበላቸው በግልጽ የሚያሳይ ነው።
7. ይሖዋ በሕጉ አስተማሪዎች ላይ የተቆጣው ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ ከሚልክያስ ዘመን በርካታ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ሌዋውያን የመገናኛውን ድንኳን በኋላም ቤተ መቅደሱንና በዚያ ይከናወን የነበረውን ቅዱስ አገልግሎት በአግባቡ እንዲይዙ ኃላፊነት ሰጥቷቸው ነበር። በተጨማሪም በእስራኤል ብሔር ውስጥ አስተማሪዎች ነበሩ። ይህን ኃላፊነት መወጣታቸው ለራሳቸውም ሆነ ለመላው ብሔር ሕይወትና ሰላም ያስገኝላቸው ነበር። (ዘኁልቊ 3:5-8) ሆኖም ሌዋውያኑ መጀመሪያ የነበራቸውን ፈሪሃ አምላክ አጡ። ስለዚህ ይሖዋ ‘እናንተ ግን ከመንገዱ ፈቀቅ ብላችኋል፤ በሕግም ብዙ ሰዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊንም ቃል ኪዳን አስነውራችኋል፣ . . . ስለዚህ መንገዴን አልጠበቃችሁም’ ብሏቸዋል። (ሚልክያስ 2:8, 9) ካህናቱ እውነቱን ማስተማራቸውን በማቆምና መጥፎ ምሳሌ በመሆን ብዙ እስራኤላውያንን አስተዋል። ስለዚህ ይሖዋ በእነርሱ ላይ መቆጣቱ የተገባ ነበር።
አምላክ ያወጣውን የአቋም ደረጃ መጠበቅ
8. ሰዎች የአምላክን የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች እንዲከተሉ መጠበቁ ምክንያታዊ ነውን? አብራራ።
8 እነዚያ ካህናት ፍጽምና የጎደላቸው ተራ ሰዎች ስለነበሩና የአምላክን የጽድቅ ደረጃዎችና መንገዶች መጠበቅ ከአቅማቸው በላይ ስለሚሆንባቸው ሊታዘንላቸውና ይቅርታ ሊደረግላቸው ይገባ ነበር ብለን አናስብ። ይሖዋ የሚጠብቅባቸው ከአቅማቸው በላይ ስላልሆነ ሰዎች የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ ይችላሉ። በዚያ ዘመን ከነበሩት ካህናት መካከል የአምላክን የጽድቅ ደረጃዎች የጠበቁ ግለሰቦች አይጠፉም። ከዚያ ቆየት ብሎ የመጣው ታላቁ ሊቀ ካህናት ኢየሱስም ጠብቆ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። (ዕብራውያን 3:1) ስለ እርሱ “የእውነት ሕግ በአፉ ውስጥ ነበረች፣ በከንፈሩም ውስጥ በደል አልተገኘበትም፤ ከእኔም ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፣ ብዙ ሰዎችንም ከኃጢአት መለሰ” በትክክል ሊባል ይችላል።—ሚልክያስ 2:6
9. በዘመናችን እውነትን በታማኝነት የሚያዳርሱት እነማን ናቸው?
9 በዘመናችንም ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች ከአንድ መቶ ለሚበልጥ ዓመት “ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት” ያቀርቡ ዘንድ “ቅዱስ ካህናት” ሆነው አገልግለዋል። (1 ጴጥሮስ 2:5) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ለማዳረስ ግንባር ቀደም ሆነው ሠርተዋል። እውነትን ከእነርሱ ስትማር የእውነት ሕግ በቅቡዓኑ አፍ እንደሚገኝ በራስህ ተሞክሮ አልተገነዘብክም? ከሃይማኖታዊ ስህተት እንዲመለሱ ብዙዎችን በመርዳታቸው በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተማሩና ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሊገኙ ችለዋል። እነዚህም በበኩላቸው የእውነትን ሕግ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች የማስተማር መብት አግኝተዋል።—ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:9
ጠንቃቃ የምንሆንበት ምክንያት
10. ጠንቃቆች መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?
10 ይሁን እንጂ ልንጠነቀቅበት የሚገባ አንድ ጉዳይ አለ። በሚልክያስ 2:1-9 አማካኝነት ሊተላለፍ የተፈለገውን መልእክት ልንስት እንችላለን። በከንፈራችን ውስጥ በደል እንዳይገኝ እንጠነቀቃለን? ለምሳሌ ያህል የቤተሰባችን አባሎች የምንናገረው ነገር እውነት መሆን አለመሆኑን ለማመን ይቸገራሉ? በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶችስ? የምንናገረው ነገር ትክክለኛነቱን ሳይለቅ ሆን ብለን ሌሎችን እንዲያሳስት አድርገን የማቅረብ ልማድ ቀስ በቀስ ሊጠናወተን ይችላል። ወይም አንድ ሰው በንግድ ነክ ጉዳዮች ዝርዝር ሁኔታውን ያጋንን ወይም ይሠውር ይሆናል። ይሖዋ እንዲህ ያሉትን ነገሮች መመልከት ያቅተዋል? እንደነዚህ ያሉትን ልማዶች የምንከተል ከሆነ የከንፈራችንን የውዳሴ መሥዋዕት ይቀበላል?
11. በተለይ ጥንቃቄ ማድረግ የሚኖርባቸው እነማን ናቸው?
11 በዛሬው ጊዜ በጉባኤ ውስጥ የማስተማር መብት የተሰጣቸውን ሰዎች በማስመልከት ሚልክያስ 2:7 ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይዟል። ከንፈራቸው ‘እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፣ ሰዎችም ከአፋቸው ሕግን ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል’ ይላል። ያዕቆብ 3:1 “የባሰውን ፍርድ” ይቀበላሉ ስለሚል በእነዚህ አስተማሪዎች ጫንቃ ላይ ከባድ ኃላፊነት ተጭኗል። በቅንነትና በግለት እንዲያስተምሩ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም እንኳ ትምህርታቸው በሙሉ በተጻፈው የአምላክ ቃልና የይሖዋ ድርጅት አዘጋጅቶ በሚያቀርበው ትምህርት ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። በዚህ መንገድ ‘ሌሎችን ለማስተማር’ ብቁ ይሆናሉ። ስለዚህም “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ” ተብለው ተመክረዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:2, 15
12. እንዲያስተምሩ መብት የተሰጣቸው ሰዎች ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል?
12 ጥንቃቄ የማናደርግ ከሆነ በምናስተምርበት ጊዜ የግል አመለካከታችንንና አስተያየታችንን ጨምረን ለማስተማር እንፈተን ይሆናል። በተለይ የእርሱ ሐሳብ የይሖዋ ድርጅት ከሚያስተምረው ጋር በሚጋጭበት ጊዜ እንኳን ከልክ በላይ በራሱ የመተማመን ዝንባሌ ያለው ሰው ለዚህ አደጋ የተጋለጠ ነው። ይሁን እንጂ ሚልክያስ ምዕራፍ 2 የጉባኤው አስተማሪዎች በጎቹን ሊያሰናክል ከሚችለው ከራሳቸው አመለካከት ይልቅ ከአምላክ የሚያገኙትን እውቀት በጥብቅ እንዲከተሉ ልንጠብቅባቸው እንደምንችል ያሳያል። ኢየሱስ “በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፣ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 18:6
የማያምን ሰው ማግባት
13, 14. ሚልክያስ ጎላ አድርጎ የጠቀሰው አንደኛው የክህደት ጎዳና ምንድን ነው?
13 ሚልክያስ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 10 ጀምሮ ስለ ክህደት ይበልጥ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ይገልጻል። ሚልክያስ ‘ክህደት’ የሚለውን ቃል ደጋግሞ በተጠቀመባቸው እርስ በርሳቸው የሚዛመዱ ሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። በመጀመሪያ ግን ሚልክያስ “ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን? የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ለማስነቀፍ እኛ እያንዳንዳችን ወንድማችንን ስለ ምን አታለልን [“በወንድማችን ላይ ስለምን ክህደት ፈጸምን፣” NW ]” በሚሉ ጥያቄዎች ምክሩን እንደጀመረ ልብ በል። ከዚያም ቁጥር 11 እስራኤላውያን የተከተሉት የክህደት መንገድ ‘የይሖዋን ቅድስና’ እንደማርከስ እንደሚቆጠር ይጠቅሳል። ይህን ያህል ከባድ ጥፋት ሆኖ የተቆጠረው ምንድን ነው? ይኸው ቁጥር ከተሳሳተ አካሄዳቸው መካከል አንዱን ይኸውም “የእንግዳውንም አምላክ ልጅ ሚስት” አድርገው መውሰዳቸውን ይገልጻል።
14 በሌላ አነጋገር ራሱን ለይሖዋ ከወሰነው ብሔር መካከል የነበሩ አንዳንድ እስራኤላውያን እርሱን የማያመልኩ ሰዎችን አግብተዋል። ይህ ድርጊት በጣም ከባድ የሆነበትን ምክንያት ከጥቅሱ አገባብ መረዳት እንችላለን። ቁጥር 10 አንድ የጋራ አባት እንዳላቸው ይናገራል። ይህ አባት (ከጊዜ በኋላ እስራኤል የተባለው) ያዕቆብ ወይም አብርሃም አልፎ ተርፎም አዳም አልነበረም። ሚልክያስ 1:6 ‘አንዱ አባታቸው’ ይሖዋ እንደሆነ ያመለክታል። የእስራኤል ብሔር ይሖዋ ከአባቶቻቸው ጋር በገባው ቃል ኪዳን አማካኝነት ከእርሱ ጋር ተዛምደዋል። በዚያ ቃል ኪዳን ከተካተቱት ሕጎች መካከል አንዱ “ከእነርሱም ጋር አትጋባ፤ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፣ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ” የሚለው ነበር።—ዘዳግም 7:3
15. (ሀ) አንዳንዶች የማያምን ሰው ማግባትን በተመለከተ ተገቢ እንደሆነ አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ስለ ጋብቻ ያለውን አመለካከት የገለጸው እንዴት ነው?
15 በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች ‘እኔ የወደድኳት ሴት በጣም ጥሩ ናት። አንድ ቀን እውነተኛውን አምልኮ ትቀበል ይሆናል’ ብለው ያስቡ ይሆናል። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?” የሚለውን በመንፈስ የተነገረ ማስጠንቀቂያ እውነተኝነት ያረጋግጣል። (ኤርምያስ 17:9) አምላክ አንድን የማያምን ሰው ስለማግባት ያለው አመለካከት “እንዲህ የሚያደርገውን ሰው ይሖዋ ያጠፋዋል” በሚለው በሚልክያስ 2:12 [NW ] ላይ ተገልጿል። ስለሆነም ክርስቲያኖች ‘በጌታ ብቻ’ እንዲያገቡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) በክርስትና ዝግጅት ውስጥ አንድ አማኝ የማታምን ሴት አግብተሃል ተብሎ ‘እንዲጠፋ’ አይደረግም። ሆኖም የማያምነው የትዳር ጓደኛ ባለማመኑ ቢጸና እና አምላክ በቅርቡ ይህን ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ሲያመጣው ያ ግለሰብ ምን ይደርስበታል?—መዝሙር 37:37, 38
የትዳር ጓደኛን መበደል
16, 17. አንዳንዶች የተከተሉት የክህደት ጎዳና ምንድን ነው?
16 ሚልክያስ ቀጥሎ ሁለተኛውን የክህደት ዓይነት ይኸውም የትዳር ጓደኛን በተለይም ፍትሐዊ ባልሆነ ምክንያት በመፍታት መበደልን ያነሳል። ምዕራፍ 2 ቁጥር 14 እንዲህ ይላል:- “ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርስዋን አታልለሃታልና [“በእርስዋ ላይ ክህደት ፈጽመሃልና፣” NW ] እግዚአብሔር በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው።” አይሁዳውያን ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ ክህደት በመፈጸም የይሖዋ መሠዊያ ‘በእንባ እንዲርስ’ አድርገው ነበር። (ሚልክያስ 2:13) እነዚህ ወንዶች ወጣት ሴቶችን ወይም የአሕዛብ ሴቶችን ለማግባት ሲሉ በረባ ባልረባው የልጅነት ሚስቶቻቸውን ያላግባብ ይፈቱ ነበር። ምግባረ ብልሹ የሆኑት ካህናትም ይህን በዝምታ ተመልክተዋል! ሆኖም ሚልክያስ 2:16 “መፋታትን እጠላለሁ፣ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር” በማለት ይናገራል። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ፣ በደል የተፈጸመበት የትዳር ጓደኛ ፈትቶ ሌላ ለማግባት የሚያስችለው ብቸኛው ምክንያት የጾታ ብልግና እንደሆነ ተናግሯል።—ማቴዎስ 19:9
17 እስቲ በሚልክያስ ቃላት ላይ አሰላስልና እነዚህ ቃላት የተፈጥሮ ደግነት ያለውን የማንኛውንም ሰው ልብና ስሜት እንዴት እንደሚነኩ ተመልከት። “ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳንህ ሚስት” ብሏል። ይህ መልእክት የተላለፈለት ሰው ሁሉ የአምልኮ ባልንጀራው የሆነች እስራኤላዊት ሴት የተወደደችና የዕድሜ ልክ ባልንጀራው እንድትሆን መርጦ አግብቷል። ምናልባት ይህ ጋብቻ የተፈጸመው ሁለቱም ወጣት በነበሩበት ወቅት ይሆናል። የጊዜያት ማለፍና የዕድሜ መግፋት እርስ በርስ ያስተሳሰራቸውን የጋብቻ ቃል ኪዳን እንዲሻር አያደርገውም።
18. ሚልክያስ ክህደትን አስመልክቶ የሰጠው ምክር በዛሬው ጊዜ የሚሠራው በምን መንገድ ነው?
18 ይህ ምክር ዛሬም ከጥንቱ ባላነሰ ሁኔታ እንደሚሠራ ግልጽ ነው። አንዳንዶች አምላክ በጌታ ብቻ እንዲያገቡ የሰጠውን መመሪያ ችላ ማለታቸው የሚያሳዝን ነው። እንዲሁም አንዳንዶች ጋብቻቸውን ለማጠናከር የሚያደርጉትን ጥረት አለመቀጠላቸው የሚያሳዝን ነው። ከዚህ ይልቅ ሌላ ሰው ለማግባት ሲሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ፍቺ በመፈጸም አምላክ የሚጠላውን ለማድረጋቸው ሰበብ ወይም ማመካኛ ለማግኘት ይጥራሉ። ይህን የመሰለ ነገር በማድረግ ‘ይሖዋን አታክተውታል።’ በሚልክያስ ዘመን መለኮታዊውን መመሪያ ችላ ይሉ የነበሩ ሰዎች የይሖዋ አመለካከት ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸው ነበር። እንዲያውም “የፍርድ አምላክ ወዴት አለ?” እስከማለት ደርሰዋል። እንዴት ያለ የተጣመመ አስተሳሰብ ነው! እንዲህ ባለው ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ።—ሚልክያስ 2:17
19. ባሎችና ሚስቶች የአምላክን መንፈስ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?
19 በአዎንታዊ ጎኑ ደግሞ ሚልክያስ በዘመኑ ከነበሩት ባሎች መካከል አንዳንዶቹ በሚስቶቻቸው ላይ ክህደት እንዳልፈጸሙ አመልክቷል። ‘በትንሹም ቢሆን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ያላቸው’ ነበሩ። (ቁጥር 15) በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ድርጅት ‘ሚስቶቻቸውን በሚያከብሩ’ እንዲህ ባሉ ወንዶች የተሞላ መሆኑ ያስደስታል። (1 ጴጥሮስ 3:7) እነዚህ ባሎች ሚስቶቻቸውን አካላዊ ጥቃት በመፈጸምም ሆነ በንግግር አይበድሉም፣ ወራዳ የሆኑ የሩካቤ ሥጋ ተግባራትን ካልፈጸምን አይሉም እንዲሁም ለሌሎች ሴቶች የፍቅር ስሜት በማሳየት ወይም የብልግና ሥዕሎችን በመመልከት ሚስቶቻቸውን አያቃልሉም። በተጨማሪም የይሖዋ ድርጅት ለአምላክና ለሕጎቹ የታመኑ ብዙ ክርስቲያን ሚስቶችን ያቀፈ በመሆኑ ተባርኳል። እነዚህ ሁሉ ወንዶችና ሴቶች አምላክ ክህደትን እንደሚጠላ ስለሚያውቁ ከዚህ ጋር የሚስማማ አስተሳሰብና ድርጊት አዳብረዋል። አንተም ‘አምላክን በመታዘዝና’ በመንፈስ ቅዱስ በመባረክ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች መሆንህን ቀጥል።—ሥራ 5:29
20. በመላው የሰው ዘር ላይ የትኛው ጊዜ እየደረሰ ነው?
20 በቅርቡ ይሖዋ መላውን ዓለም ወደ ፍርድ ያመጣዋል። እያንዳንዱ ግለሰብ ስለሚያምንበትና ስለሚያደርገው ነገር ለእርሱ መልስ ይሰጣል። “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።” (ሮሜ 14:12) ስለሆነም እዚህ ላይ ከይሖዋ ቀን በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ይነሳል። ሦስተኛውና የመጨረሻው ርዕስ ይህን ጭብጥ የሚያብራራ ይሆናል።
ልታብራራ ትችላለህን?
• ይሖዋ በእስራኤል ይኖሩ የነበሩትን ካህናት የነቀፈበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?
• የይሖዋን የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች መጠበቅ ከሰዎች አቅም በላይ ያልሆነው ለምንድን ነው?
• ስናስተምር ጠንቃቆች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
• ይሖዋ በተለይ ያወገዛቸው ሁለት ድርጊቶች ምንድን ናቸው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሚልክያስ ዘመን ካህናቱ የይሖዋን መንገዶች ባለመጠበቃቸው ተነቅፈዋል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለግል አመለካከቶቻችን ቅድሚያ ሳንሰጥ የይሖዋን መንገዶች ለማስተማር ጠንቃቆች መሆን ይገባናል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በሰበብ ባስባቡ ሚስቶቻቸውን ፈትተው አሕዛብ ሴቶችን ያገቡ እስራኤላውያንን አውግዟል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዛሬ ክርስቲያኖች የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ያከብራሉ