ንጽሕና—ትክክለኛ ትርጉሙ ምንድን ነው?
ንጽሕና—ትክክለኛ ትርጉሙ ምንድን ነው?
በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመን በአውሮፓና በዩናይትድ ስቴትስ በንጽሕና አጠባበቅ ረገድ የታየው አስደንጋጭ ሁኔታ በጊዜው የነበሩ ሚስዮናውያን “የንጽሕና ሃይማኖታዊ ትምህርት” እየተባለ የሚጠራ ትምህርት እንዲሰብኩ አነሳስቷቸዋል። ይህ ትምህርት መቆሸሽ በራሱ ኃጢአት እንደሆነና በአንጻሩ ደግሞ ንጽሕና ወደ አምላክ የሚያቀርብ እንደሆነ ይገልጻል። ምናልባትም “ንጽሕና እና መለኮታዊነት ጎን ለጎን የሚሄዱ ናቸው” የሚለውን የተለመደ አባባል ታዋቂ ያደረገው ይህ ሳይሆን አይቀርም።
በዊልያምና ካተሪን ቡዝ መሥራችነት የተቋቋመው ሳልቬሽን አርሚ የተባለው ድርጅት የዚህ ዓይነት አመለካከት ነበረው። ሄልዝ ኤንድ ሜድስን ኢን ዚ ኢቫንጀሊካል ትራዲሽን የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ ከሳልቬሽን አርሚ የቀድሞ መፈክር መካከል “ሳሙና፣ ሾርባና ድነት” የሚለው ይገኝበታል። ከዚያም ሉዊ ፓስተርና ሌሎች ግለሰቦች በበሽታና በባክቴሪያ መካከል ያለውን ግንኙነት በማስረጃ ማረጋገጣቸው የተሻሉ የማኅበራዊ ንጽሕና አጠባበቅ ደንቦች ለማውጣት በር ከመክፈቱም በተጨማሪ ሳይንሳዊ መሠረትም ጥሏል።
በዚህ ረገድ የተወሰደው ፈጣን እርምጃ አንድ ሰው ፍርድ ቤት ለምሥክርነት ሲቀርብ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲስም የሚያስገድደውን ደንብና በትምህርት ቤትም ሆነ በባቡር ጣቢያዎች ኩባያዎችን በጋራ የመጠቀምን ልማድ ማስቀረትን ይጨምራል። በቅዳሴ ሥርዓቶች ላይ ሰዎች በተወሰኑ ጽዋዎች በጋራ ከመጠቀም ይልቅ የየራሳቸው ጽዋዎች እንዲኖሯቸው ጥረት ተደርጓል። አዎን፣ እነዚህ ፈር ቀዳጅ የሆኑ ሰዎች ብዙሐኑ ስለ ንጽሕና ያለውን አመለካከት በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ያገኙ ይመስላል።
የሰዎች አመለካከት በጣም ከመለወጡ የተነሣ አንዲት ጸሐፊ ሁኔታውን ሰዎች “ከንጽሕና ጋር ፍቅር ይዟቸዋል” ሲሉ ገልጸውታል።ይሁን እንጂ ይህ “ፍቅር” እውነተኛ ሳይሆን የወረት ነበር። ነጋዴዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ተራውን ሳሙና ወደ ውበት ማሣመሪያነት ለመለወጥ ጊዜ አልወሰደባቸውም። በረቀቀ መንገድ የተዘጋጁ ማስታወቂያዎች ሰዎች አንድ ዓይነት የንጽሕና መጠበቂያ ሳሙና ከተጠቀምን ሌሎችን ሊያስቀና የሚችል ማኅበራዊ ቦታ ይኖረናል ብለው እንዲያምኑ አድርገዋቸዋል። ቴሌቪዥንም ይህን ዓይነቱን ቅዠት በማራገብ ረገድ አስተዋጽዖ አድርጓል። በንግድ ማስታወቂያዎችና በቴሌቪዥን በሚቀርቡ ተከታታይ ፊልሞች ላይ የሚታዩት የተሳካላቸውና የሚያማምሩ ግለሰቦች አብዛኛውን ጊዜ ቤትና ግቢ ሲያጸዱ፣ ቆሻሻ ሲያነሱ አሊያም የድመቶቻቸውንና የውሾቻቸውን እዳሪ ሲያጸዱ አይታዩም።
ወደ ሥራ መሄድ ኑሮን ለማሸነፍ ይረዳል። ቤት ማጽዳትም ሆነ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወን ግን ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አይሰጥም ብለው የሚያስቡም አሉ። የአካባቢውን ንጽሕና በመጠበቃቸው የሚሰጣቸው የገንዘብ ሽልማት የለ! ታዲያ ለምን ብለው ነው ስለ አካባቢው ንጽሕና የሚጨነቁት? ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ካስከተላቸው ውጤቶች መካከል አንደኛው ዛሬ አንዳንዶች ንጽሕና ለየግለሰቡ የተተወ ጉዳይ ነው የሚል አመለካከት እንዲይዙ ማድረጉ ነው።
አምላክ ስለ ንጽሕና ያለው አመለካከት
ቀደም ሲል ስለ ንጽሕና ለማስተማር የተደረጉት ጥረቶች የሰዎችን አኗኗር እንዳሻሻሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም ንጽሕና፣ ቅዱስና ንጹሕ ከሆነው አምላክ ከይሖዋ የተገኘ ባሕርይ ነው። ይሖዋ በመንገዳችን ሁሉ ቅዱስና ንጹሕ በመሆን ራሳችንን እንድንጠቅም ያስተምረናል።—ኢሳይያስ 48:17፤ 1 ጴጥሮስ 1:15
በዚህ ረገድ ይሖዋ አምላክ ጥሩ ምሳሌ ነው። ንጽሕናውን ጨምሮ ሌሎች የማይታዩ ባሕርያቱን ከፍጥረት ሥራዎቹ መመልከት እንችላለን። (ሮሜ 1:20) ፍጥረት በራሱ ምንም ዓይነት ዘላቂ ብክለት እንደማያስከትል መገንዘብ እንችላለን። የብዙ ሥነ ምህዳራዊ ዑደቶች ባለቤት የሆነችው ምድር ራሷን በራሷ ማጽዳት የምትችል ድንቅ ፍጥረት ናት። ንጹሕና ጤናማ ለሆነ አኗኗር እንድትመች ተደርጋ ተዘጋጅታለች። እንዲህ ያለውን ንጹሕ ሥራ ሊሠራ የሚችለው ንጹሕ አእምሮ ያለው ንድፍ አውጪ ብቻ ነው። ስለዚህ የይሖዋ አምላኪዎች በሁሉም የኑሮአቸው ዘርፍ ንጹሖች እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል ብለን መደምደም እንችላለን።
አራቱ የንጽሕና ዘርፎች
መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ አራት የንጽሕና ዘርፎች ይገልጻል። እስቲ አንድ በአንድ እንመልከታቸው።
መንፈሳዊ ንጽሕና። ይህ የንጽሕና ዘርፍ የአንድን ሰው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ስለሚነካበት ከሁሉም የንጽሕና ዘርፎች የላቀ ነው ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ከሌሎቹ ይልቅ ትኩረት የሚነፈገው የንጽሕና ዘርፍም ነው። በአጭሩ በመንፈሳዊ ንጹሕ መሆን ማለት ይሖዋ በእውነተኛው አምልኮና በሐሰተኛው መካከል ካስቀመጠው ድንበር አለማለፍ ማለት ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት አምላክ የትኛውንም ዓይነት የሐሰት አምልኮ ርኩስ አድርጎ ስለሚመለከተው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ:- እኔም እቀበላችኋለሁ።” (2 ቆሮንቶስ 6:17) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብም “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው . . . በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው” በማለት በዚህ ረገድ ቀጥተኛ መልእክት አስተላልፏል።—ያዕቆብ 1:27
አምላክ የሐሰት አምልኮ ከእርሱ እውነተኛ አምልኮ ጋር እንዲቀላቀል እንደማይፈልግ በግልጽ አሳይቷል። የሐሰት አምልኮ አብዛኛውን ጊዜ ንጹሕ ያልሆኑ ድርጊቶች መፈጸምን እንዲሁም አስጸያፊ ጣዖታትና አማልክት ማምለክን ይጨምራል። (ኤርምያስ 32:35) በዚህም ምክንያት እውነተኛ ክርስቲያኖች ከማንኛውም ዓይነት የሐሰት አምልኮ እንዲርቁ ታዝዘዋል።—1 ቆሮንቶስ 10:20, 21፤ ራእይ 18:4
ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና። በዚህ ረገድም አምላክ ንጹሕ የሆነውንና ያልሆነውን በተመለከተ የማያሻማ መመሪያ ሰጥቷል። በአጠቃላይ ሲታይ ዓለም በኤፌሶን 4:17-19 ላይ የተገለጸውን ዓይነት መንፈስ የሚያሳይ ሆኗል:- “እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፣ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ . . . ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ።” እንዲህ ያለው ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ አስተሳሰብ በረቀቁና ገሃድ በወጡ መንገዶች ይገለጻል። ስለዚህ ክርስቲያኖች ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
አምላክን የሚወዱ ሁሉ ዝሙት አዳሪነት፣ ግብረ ያዕቆብ 3:17
ሰዶማዊነት፣ ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸምና ወሲባዊ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን መመልከት ይሖዋ የሥነ ምግባር ንጽሕናን አስመልክቶ ያወጣውን ደንብ መጣስ እንደሆነ ያውቃሉ። ይሁን እንጂ በመዝናኛውና በፋሽኑ ዓለም ይህን የመሳሰሉ ድርጊቶች የሚገለጹባቸው ሁኔታዎች የተለመዱ ናቸው። ስለሆነም ክርስቲያኖች እነዚህን ከመሰሉ ዝንባሌዎች መራቅ ይኖርባቸዋል። በጣም አጭርና እርቃንን የሚያጋልጥ ልብስ ለብሶ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አሊያም በማኅበራዊ ዝግጅቶች ላይ መገኘት ወደ ግለሰቡ አላስፈላጊ ትኩረት የሚስብ ከመሆኑም በላይ ግለሰቡ ቢያንስ በዚህ ጊዜ እንኳ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናውን በመጠበቅ ረገድ ልል እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ይህ ዓይነቱ አለባበስ ወደ ጉባኤው ዓለማዊ አስተሳሰብ ሰርጎ እንዲገባ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ሌሎች ንጹሕ ያልሆኑ ሐሳቦች እንዲያውጠነጥኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። ይህ ክርስቲያኖች ‘የላይኛይቱን ጥበብ’ ለማንጸባረቅ ከፍተኛ ጥረት ሊያደርጉበት የሚገባ የንጽሕና ዘርፍ ነው።—አእምሮአዊ ንጽሕና። የአንድ ሰው የአእምሮ ጓዳ ንጹሕ ያልሆኑ ሐሳቦች ማጠራቀሚያ መሆን አይኖርበትም። ኢየሱስ ንጹሕ ያልሆነ አስተሳሰብን በሚመለከት የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:- “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።” (ማቴዎስ 5:28፤ ማርቆስ 7:20-23) እነዚህ ቃላት ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞች መመልከትን፣ አሳፋሪ ስለሆኑ ጾታዊ ድርጊቶች የሚናገሩ ታሪኮችን ማንበብንና የጾታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ሙዚቃዎች ማዳመጥን በተመለከተም ይሠራሉ። ስለዚህ ክርስቲያኖች ንጹሕና ቅዱስ ያልሆኑ አነጋገሮችን እንዲጠቀሙና ንጹሕ ያልሆኑ ተግባራትን እንዲፈጽሙ ሊያደርጋቸው ከሚችል ንጹሕ ያልሆነ አስተሳሰብ በመራቅ ራሳቸውን ከማርከስ መቆጠብ ይኖርባቸዋል።—ማቴዎስ 12:34፤ 15:18
አካላዊ ንጽሕና። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቅድስናና አካላዊ ንጽሕና በቅርብ የተሳሰሩ ነገሮች ናቸው። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ “ወዳጆች ሆይ፣ . . . በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁኔታቸው በፈቀደ መጠን ሰውነታቸውን፣ ቤታቸውንና አካባቢያቸውን ንጹሕና ሥርዓታማ አድርገው ለመያዝ መጣር ይኖርባቸዋል። ለመታጠቢያ የሚሆን ውኃ እንደልብ በማይገኝበት ቦታ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ጭምር ንጹሕና ሥርዓታማ ሆነው ለመቅረብ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
አካላዊ ንጽሕና ትንባሆን በማንኛውም መልኩ ከመጠቀም መራቅን፣ የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ አለመጠጣትንና አደገኛ ዕፆች አለመውሰድን ይጨምራል። እነዚህ ነገሮች አካልን ሊያቆሽሹና ሊጎዱ ይችላሉ። በመኃልየ መኃልይ መጽሐፍ ላይ የተገለጸው እረኛ የሱነማይቷ ልጃገረድ ልብስ ያለውን ጥሩ መዓዛ አድንቋል። (መኃልየ መኃልይ 4:11) አብረውን ያሉ ሰዎች መጥፎ ጠረን እንዲሸታቸው ስለማንፈልግ የግል ንጽሕናችንን መጠበቃችን ፍቅራዊ ድርጊት ነው። ሽቶ መቀባት ጥሩ ሊሆን ቢችልም አዘውትሮ የመታጠብንና ንጹሕ ልብስ የመልበስን አስፈላጊነት በምንም ዓይነት አይቀንሰውም።
ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
አካላዊ ንጽሕናን በተመለከተ ሰዎች ወደ ሁለት የተለያዩ ጽንፎች ሊሄዱ ይችላሉ። በአንድ በኩል ለንጽሕና ከልክ በላይ መጨነቅ ከሕይወት የምናገኘውን ደስታ ሊነጥቀን
ይችላል። ውድ ጊዜያችንንም ሊያጠፋብን ይችላል። በሌላው በኩል ደግሞ ቆሻሻና የተዝረከረኩ ቤቶችን መጠገን ከፍተኛ ወጪ ሊጠይቅ ይችላል። ወደ ሁለቱም ጽንፎች ሳንሄድ ቤታችንን ንጹሕና ሥርዓታማ ለማድረግ የሚያስችለንን ተግባራዊና ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ እንችላለን።ኮተት አታብዙ። ኮተት የበዛበትን ቤት ወይም ክፍል ማጽዳት የሚከብድ ከመሆኑም በተጨማሪ እፍንፍን ባለ ቤት ውስጥ የሚገኘውን ቆሻሻ ማጽዳት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ልከኛ የሆኑና ኮተት ያልበዛባቸውን ቤቶች ማጽዳት የሚወስደው ጊዜ አነስተኛ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” በማለት ቀለል ያለ አኗኗርን ያበረታታል።—1 ጢሞቴዎስ 6:8
ዕቃ አታዝረክርኩ። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ቤቱን በንጽሕና የመያዝ ኃላፊነት አለበት። አብዛኛውን ጊዜ የተዝረከረኩ ቤቶች የሚፈጠሩት የተዝረከረኩ ክፍሎች ሲኖሩ ነው። ሥርዓት ማስያዝ ማለት እያንዳንዱን ነገር በተገቢው ቦታ ማስቀመጥ ማለት ነው። ለምሳሌ የቆሸሹ ልብሶች መኝታ ቤት ወለል ላይ መጣል የለባቸውም። ሌላው ቸል ሊባል የማይገባው ነገር ደግሞ በየቦታው ተዝረክርከው የሚተዉ የልጆች መጫዎቻዎችና ሌሎች ነገሮች አደጋ ሊያስከትሉ መቻላቸው ነው። በቤት ውስጥ የሚከሰቱት ብዙዎቹ ድንገተኛ አደጋዎች ከሥርዓታማነት ጉድለት የሚመጡ ናቸው።
ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ንጽሕናና ክርስቲያናዊ ሕይወት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። ነቢዩ ኢሳይያስ አምላካዊውን የሕይወት መንገድ አስመልክቶ ሲጽፍ “የተቀደሰ መንገድ” በማለት ጠርቶታል። ቀጥሎም “ንጹሐንም ያልሆኑ አያልፉበትም” በማለት አንድ ሊጤን የሚገባው ሐሳብ አክሏል። (ኢሳይያስ 35:8) አዎን፣ ጥሩ የንጽሕና አጠባበቅ ልማድ ማዳበር አምላክ በቅርቡ የጸዳች ምድራዊ ገነት እንደሚያቋቁም በገባው ተስፋ ላይ እምነት እንዳለን የሚያሳይ ጠንካራ ማረጋገጫ ነው። በመጨረሻም ገነት በሆነችው ውብ ምድር ላይ የመኖር አጋጣሚ ያገኙ ሰዎች በሙሉ ይሖዋ አምላክ ንጽሕናን አስመልክቶ ካወጣቸው ፍጹም የንጽሕና ደንቦች ጋር ተስማምተው በመኖር እርሱን ያስከብራሉ።—ራእይ 7:9
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ቤቱን በንጽሕና የመያዝ ኃላፊነት አለበት
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምድር ራሷን በራሷ ማጽዳት የምትችል ድንቅ ፍጥረት ናት