የዛፍ ጠር
የዛፍ ጠር
መጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ዛፎች ጠቃሚ ንብረቶች ተደርገው ይታዩ ነበር። ለምሳሌ ያህል አብርሃም ለውድ ሚስቱ ለሣራ የሚሆን የመቃብር ቦታ ለመግዛት ውል ሲዋዋል በንብረቱ ዝርዝር ውስጥ ዛፎችም ተጠቅሰው ነበር።—ዘፍጥረት 23:15-18 አ.መ.ት
ዛሬም በተመሳሳይ ዛፎች ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ሲሆን የደን ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቷል። ስቴት ኦቭ ዘ ወርልድ 1998 የተባለው መጽሐፍ እንዳለው ከሆነ “በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ የሚገኙ ብዙ ሰዎች በሞቃታማው የሐሩር ክልል የሚገኙት ደኖች ሁኔታ ያሳስባቸዋል። ሆኖም መካከለኛ የሆነ የአየር ንብረት ባላቸው ቦታዎች ማለትም በገዛ አገራቸው የሚገኙት ደኖች በየትኛውም ቦታ ከሚገኙት ደኖች ይበልጥ የተራራቁና ጎጂ ለሆኑ ተጽእኖዎች የተጋለጡ መሆናቸውን አልተገነዘቡ ይሆናል።” በእነዚህ የሰሜን አውሮፓና የሰሜን አሜሪካ አገሮች ውስጥ የሚገኙትን ደኖች አደጋ ላይ የጣለው ምንድን ነው? ብዙዎች የደን መመንጠር ነው ቢሉም ዛፎቹን በረቀቀ መንገድ አንድ በአንድ የሚያወድሙ ሌሎች ኃይሎችም አሉ። እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው? የአየር ብክለትና የአሲድ ዝናብ ናቸው። እነዚህ ብክለት የሚያስከትሉ ነገሮች ዛፎቹ መርዘኛ ተባዮችንና በሽታን እንዳይቋቋሙ በማድረግ ቀስ በቀስ ሊያዳክሟቸው ይችላሉ።
በርከት ላሉ አሥርተ ዓመታት የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችና ሌሎች ተቆርቋሪ ግለሰቦች የምድርን ሥርዓተ ምህዳር የመጠበቁን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርገው ሲገልጹ ቆይተዋል። በ1980ዎቹ የጀርመን ሳይንቲስቶች የአየር ብክለትና የአሲድ ዝናብ በአካባቢ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ ካጠኑ በኋላ የሚከተለው ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል:- ‘አንድ ነገር ካልተደረገ በ2000 ዓመት አካባቢ ሰዎች ደኖችን የሚያደንቁት በዓይናቸው እየተመለከቱ ሳይሆን የቆዩ ፎቶዎችን አሊያም ፊልሞችን በመመልከት ይሆናል።’ የሚያስደስተው ግን ምድር ያላት ራሷን በራሷ የማደስና ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ የመመለስ ችሎታ በጣም ከፍተኛ መሆኑ እስካሁን ድረስ አስቀድሞ የተተነበየውን ያህል ጥፋት እንዳይደርስባት አድርጓል።
ሆኖም የምድርን ሥርዓተ ምህዳር በዘላቂነት በመንከባከብ ረገድ አብዛኛውን ድርሻ የሚያበረክተው አምላክ ይሆናል። “ተራሮችን ከላይ” ያጠጣቸዋል። “ለምለሙን ለሰው ልጆች ጥቅም፣ ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል።” እንዲሁም አምላክ “ምድርንም የሚያጠፉትን” ለማጥፋት ቃል ገብቷል። (መዝሙር 104:13, 14፤ ራእይ 11:18) የምድር ነዋሪዎች ከብክለት ነጻ በሆነ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር ሲችሉ ምንኛ ያስደስታል!—መዝሙር 37:9-11