“የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች”
“የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች”
መባረክ የማይፈልግ ሰው የለም። ዚ አሜሪካን ሄሪቴጅ ኮሌጅ ዲክሽነሪ እንደሚለው ከሆነ በረከት “ደስታ፣ ደህንነት ወይም ብልጽግና” ያስገኛል። ይሖዋ ‘የበጎ ስጦታና የፍጹምም በረከት ሁሉ’ ምንጭ በመሆኑ እያንዳንዱ እውነተኛና ዘላቂ በረከት የሚገኘው ከአፍቃሪው ፈጣሪያችን ነው። (ያዕቆብ 1:17) በረከቱን በሁሉም የሰው ዘር ላይ እንዲያውም በማያውቁት ላይ እንኳ ሳይቀር ያዘንባል። ኢየሱስ ስለ አባቱ የሚከተለውን ብሏል:- “እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባል።” (ማቴዎስ 5:44, 45) ይሁን እንጂ ይሖዋ ለሚወዱት ለየት ያለ ትኩረት ይሰጣል።—ዘዳግም 28:1-14፤ ኢዮብ 1:1፤ 42:12
መዝሙራዊው፣ ይሖዋ “በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 84:11) አዎን፣ ይሖዋን የሚያገለግሉ ሁሉ በረከት የሞላበትና ትርጉም ያለው ሕይወት ይኖራሉ። ‘የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ እንደምታደርግ፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር እንደማይጨምር’ ያውቃሉ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “[ይሖዋ] የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ።” (ምሳሌ 10:22፤ መዝሙር 37:22 NW , 29) ይህ እንዴት ያለ በረከት ነው!
ታዲያ የይሖዋን በረከት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የሚያስደስቱትን ባሕርያት ማፍራት ይኖርብናል። (ዘዳግም 30:16, 19, 20፤ ሚክያስ 6:8) ይህንን ሦስት የጥንት የይሖዋ አገልጋዮች ከተዉት ምሳሌ መረዳት እንችላለን።
ይሖዋ አገልጋዮቹን ይባርካል
ኖኅ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው የአምላክ አገልጋይ ሲሆን ዘፍጥረት 6:8 ላይ ስለ እርሱ እንዲህ የሚል እናነብባለን:- “ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ።” ለምን? ምክንያቱም ኖኅ ታዛዥ ነበር። ታሪኩ “ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” በማለት ይናገራል። ኖኅ የይሖዋን የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች የተከተለ ሲሆን መመሪያዎቹንም ታዝዟል። ዓለም በዓመፅና ልቅ በሆነ አኗኗር በተዘፈቀበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር ኖኅ ‘እንዲሁ ለማድረግ፣ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ ለማድረግ’ ተገፋፍቷል። (ዘፍጥረት 6:9, 22) ከዚህ የተነሣ ይሖዋ “ቤተ ሰዎቹን [የኖኅን] ለማዳን” የሚያስችል መርከብ እንዲሠራ አዘዘው። (ዕብራውያን 11:7) በዚህ መንገድ ኖኅና ቤተሰቡ እንዲሁም በእነርሱ አማካኝነት የሰው ዘር በዚያ ትውልድ ላይ ከደረሰው ጥፋት ሊተርፍ ችሏል። ኖኅ ትንሣኤ አግኝቶ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ በመያዝ አንቀላፍቷል። ኖኅ ምንኛ ተባርኳል!
አብርሃምም ይሖዋን የሚያስደስቱ ባሕርያት ነበሩት። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል እምነቱ በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው። (ዕብራውያን 11:8-10) አብርሃም በመጀመሪያ በዑር በኋላም በካራን የነበረውን የተደላደለ ኑሮ የተወው ይሖዋ ታላቅ ሕዝብ እንደሚያደርገውና በዘሩም የምድርን አሕዛብ እንደሚባርክ በገባው ቃል ላይ እምነት ስለነበረው ነው። (ዘፍጥረት 12:2, 3) ለብዙ ዓመታት የተፈተነ ቢሆንም ልጁ ይስሐቅ ሲወለድ እምነቱ ተክሷል። በይስሐቅ አማካኝነት የአምላክ የተመረጠ ሕዝብ ማለትም የእስራኤል ብሎም የመሲሑ አባት ለመሆን በቅቷል። (ሮሜ 4:19-21) በተጨማሪም አብርሃም “ለሚያምኑ ሁሉ አባት” ሲሆን “የእግዚአብሔርም ወዳጅ” ተብሎ ለመጠራትም በቅቷል። (ሮሜ 4:11፤ ያዕቆብ 2:23፤ ገላትያ 3:7, 29) ትርጉም ያለው ሕይወት ከመኖሩም በላይ በእጅጉ ተባርኳል!
ታማኝ የሆነውን ሙሴንም ተመልከት። ከሙሴ ግሩም ዕብራውያን 11:27) በምድያም 40 ዓመታት ካሳለፈ በኋላ ዕድሜው ገፍቶ ወደ ግብጽ በመመለስ በወቅቱ ኃያል የነበረውን ፈርኦንን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ወንድሞቹን እንዲለቅቅ ጠይቋል። (ዘጸአት 7:1-7) ሙሴ አሥሩ መቅሰፍቶች ሲወርዱ፣ ቀይ ባሕር ለሁለት ሲከፈልና የፈርኦን ሠራዊት ሲደመሰስ በዓይኑ ተመልክቷል። ይሖዋ ሕጉን ለእስራኤል የሰጠው በእሱ በኩል ከመሆኑም በላይ ከአዲሱ ብሔር ጋር በገባው ቃል ኪዳን መካከለኛ አድርጎ ተጠቅሞበታል። ሙሴ የእስራኤልን ብሔር 40 ለሚያክሉ ዓመታት በምድረ በዳ መርቷል። ሕይወቱ እውነተኛ ዓላማ የነበረው ሲሆን ብዙ ታላላቅ የአገልግሎት መብቶችም አግኝቷል።
ባሕርያት መካከል ለመንፈሳዊ ነገሮች የነበረው አድናቆት ጎልቶ ይታያል። ሙሴ ለግብጽ ብልጽግና ጀርባውን በመስጠት “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአል።” (በዘመናችን የሚገኝ በረከት
እነዚህ ታሪኮች እንደሚያሳዩት አምላክን የሚያገለግሉ ሁሉ እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት ይኖራሉ። የይሖዋ ሕዝቦች ታዛዥነት፣ እምነትና ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት ማሳየት የመሳሰሉትን ባሕርያት ሲያዳብሩ በብዙ ይባረካሉ።
ታዲያ እኛ የተባረክነው በምን መንገዶች ነው? በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በመንፈሳዊ ረሃብ ሲሰቃዩ እኛ ግን ‘በእግዚአብሔር ልግስና ደስ ይለናል።’ (ኤርምያስ 31:12 አ.መ.ት) ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስንና “ታማኝና ልባም ባሪያ”ን ተጠቅሞ ‘ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ’ መመላለሳችንን እንድንቀጥል የሚረዳንን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብልናል። (ማቴዎስ 7:13, 14፤ 24:45፤ ዮሐንስ 17:3) ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ወዳጅነት መመሥረት መቻላችን ደግሞ ሌላው በረከት ነው። በስብሰባዎችና በሌሎች አጋጣሚዎች ፍቅር ከሚያሳዩና “አዲሱን ሰው” ለመልበስ ልባዊ ጥረት ከሚያደርጉ ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር መሆን ከፍተኛ ደስታ ያስገኛል። (ቆላስይስ 3:8-10፤ መዝሙር 133:1) ይሁን እንጂ ከሁሉ ይበልጥ የተባረክነው ከይሖዋ አምላክ ጋር የግል ዝምድና የመመሥረትና የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን አርአያ የመከተል ውድ መብት በማግኘት ነው።—ሮሜ 5:1, 8፤ ፊልጵስዩስ 3:8
እንዲህ በመሳሰሉት በረከቶች ላይ ስናሰላስል ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት በእርግጥ ምን ያህል ውድ እንደሆነ እንገነዘባለን። ምናልባትም ኢየሱስ መልካምን ዕንቁ ስለሚሻ ነጋዴ የተናገረው ምሳሌ ትዝ ይለን ይሆናል። ኢየሱስ ስለዚህ ሰው የሚከተለውን ብሏል:- “ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቍ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።” (ማቴዎስ 13:46) በእርግጥም ከአምላክ ጋር ስለመሠረትነው ዝምድና፣ እርሱን ስለማገልገል መብታችን፣ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ስለመሠረትነው ወዳጅነት፣ ስለ ክርስቲያናዊው ተስፋችን እንዲሁም ከእምነታችን ጋር ስለተያያዙት ሌሎች በረከቶች በሙሉ የሚሰማን ልክ እንደዚህ ነው። በሕይወታችን ውስጥ ከዚህ ጋር የሚወዳደር አንድም ነገር የለም።
ለይሖዋ መልሳችሁ ስጡ
ይሖዋ የበጎ ስጦታ ሁሉ ምንጭ መሆኑን መገንዘባችን ላገኘናቸው በረከቶች ያለንን አመስጋኝነት እንድንገልጽ ይገፋፋናል። ታዲያ ይህንን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ሌሎች እነዚሁኑ በረከቶች እንዲያገኙ መርዳት ነው። (ማቴዎስ 28:19) ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ለጎረቤቶቻቸው ይህንኑ ለማድረግ ይጣጣራሉ። በዚህ መንገድ ሌሎች ‘እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ለመርዳት ውስን ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ቁሳዊ ንብረቶቻቸውን ይጠቀማሉ።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4
እስቲ በግሌንዴል ካሊፎርንያ ዩ ኤስ ኤ የሚኖሩትን አቅኚዎች ሁኔታ ተመልከት። ሁልጊዜ ቅዳሜ ጠዋት ወደ አንድ የፌዴራል እሥር ቤት ደርሰው ለመመለስ 100 ኪሎ ሜትር ያህል ይጓዛሉ። ከእሥረኞቹ ጋር ማሳለፍ የሚችሉት ጊዜ አነስተኛ ቢሆንም ተስፋ ግን አልቆረጡም። ከመካከላቸው አንደኛው እንዲህ ይላል:- “በዚህ ለየት ያለ ክልል ማገልገል እጅግ ይክሳል። ይህንን የምናደርገው እጅግ ደስ ብሎን ነው። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ብዙ በመሆናቸው ሁሉንም ማስጠናት አልቻልንም። በአሁኑ ጊዜ አምስት ሰዎች በማጥናት ላይ ሲሆኑ ሌሎች አራት ደግሞ ጥናት እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።”
ቅንዓት ያላቸው ክርስቲያን አገልጋዮች ይህንን ሕይወት አድን ሥራ አለክፍያ ለማከናወን ፈቃደኞች ናቸው። “በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ” በማለት የተናገረውን የኢየሱስን አመለካከት ያንጸባርቃሉ። (ማቴዎስ 10:8 አ.መ.ት.) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ያለውን ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ አገልግሎት በመስጠቱ ሥራ ላይ ተጠምደዋል። በውጤቱም ብዙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምላሽ በመስጠትና ደቀ መዛመርት በመሆን ላይ ናቸው። ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ወደ 1.7 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነዋል። ይህ ጭማሪ ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ማተምን እንዲሁም አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችና ሌሎች የመሰብሰቢያ ቦታዎች መገንባትን ጠይቋል። ታዲያ እነዚህን ነገሮች ለማከናወን የሚያስፈልገው ገንዘብ የሚመጣው ከየት ነው? በፈቃደኝነት ከሚሰጡ መዋጮዎች ነው።
በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች የከፋ ድህነት በመኖሩ ብዙዎች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች ለማቅረብ ሌት ከቀን ይሠራሉ። ኒው ሳይንቲስት መጽሔት እንዳለው ከሆነ 1 ቢልዮን የሚያክሉ ሰዎች ቢያንስ ቢያንስ የገቢያቸውን 70 በመቶ በምግብ ላይ ያውላሉ። ብዙ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚገኙት እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ሌሎች ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ካልረዷቸው በቀር ክርስቲያናዊ ጽሑፎችንም ሆነ ተስማሚ የመንግሥት አዳራሾችን ማግኘት አይችሉም።
እርግጥ ይህ ሲባል እንዲህ ያሉት ሰዎች ሸክማቸውን በሌሎች ላይ ይጥላሉ ማለት አይደለም። ሆኖም እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ሙሴ እስራኤላውያን ከይሖዋ ላገኙት በረከት ያላቸውን አድናቆት የሚገልጹበትን ቁሳዊ መዋጮ እንዲሰጡ እስራኤላውያንን ሲያበረታታ የሚከተለውን ብሎ ነበር:- “አምላክህ እግዚአብሔር በረከት እንደ ሰጠህ መጠን እያንዳንዱ ሰው እንደ ችሎታው ይስጥ።” (ዘዳግም 16:17) በመሆኑም ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አንዲት መበለት “ሁለት ሳንቲም” ስትሰጥ ባየ ጊዜ በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድናቆቱን ገልጿል። የቻለችውን ሁሉ አድርጋለች። (ሉቃስ 21:2, 3) በተመሳሳይም በድህነት ቀንበር ሥር ያሉ ክርስቲያኖች የቻሉትን ያደርጋሉ። እጥረት ሲኖር በተሻለ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖች ካዋጡት መስጠት ይቻላል።—2 ቆሮንቶስ 8:13-15
እንዲህ ባለው መንገድ ለአምላክ መልሰን ስንሰጥ ትክክለኛውን የልብ ዝንባሌ መያዙ በጣም አስፈላጊ ነው። (2 ቆሮንቶስ 8:12) ጳውሎስ የሚከተለውን በማለት ተናግሯል:- “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።” (2 ቆሮንቶስ 9:7) ከልባችን በነፃ በመስጠት በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለውን ቲኦክራሲያዊ ጭማሪ እንደግፋለን ብሎም የራሳችንን ደስታ እንጨምራለን።—ሥራ 20:35
በስብከቱ ሥራ መካፈልና ፈቃደኛ መዋጮ ማድረግ ይሖዋ ለሰጠን በረከት መልሰን መስጠት የምንችልባቸው ሁለት መንገዶች ናቸው። ይሖዋ ገና በማያውቁት ቅን ልብ ባላቸው ብዙ ተጨማሪ ሰዎች ላይ እንኳ ሳይቀር በረከቱን ለማፍሰስ ዝግጁ መሆኑን ማወቁ ምንኛ ያበረታታል! (2 ጴጥሮስ 3:9) ስለዚህ አሁንም ያለንን ነገር ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ለመፈለግና እንዲህ ያሉት ሰዎች ታዛዥነት፣ እምነትና አድናቆት የመሳሰሉትን ባሕርያት እንዲያፈሩ ለመርዳት እንጠቀምበት። በዚህ መንገድ ይሖዋ ‘ቸር መሆኑን እንዲቀምሱና እንዲያዩ’ በመርዳት የሚገኘውን ደስታ እናጭዳለን።—መዝሙር 34:8
[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንዶች ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚውል መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች
ብዙዎች “ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚውል መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” ተብሎ በተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩትን የተወሰነ የገንዘብ መጠን ያስቀምጣሉ ወይም ይመድባሉ።
ጉባኤዎች ይህን ገንዘብ በየወሩ በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወዳለው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በአካባቢው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ ይልካሉ። በፈቃደኛነት የሚደረጉ የገንዘብ እርዳታዎችን በቀጥታ Treasurer’s Office, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአገርህ ወደሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችን በእርዳታ መልክ መስጠትም ይቻላል። የተላከው ነገር ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ አብሮ መላክ ይኖርበታል።
ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት
አንድ ሰው የሰጠውን ገንዘብ ሊጠቀምበት በሚፈልግበት ጊዜ መልሶ ሊያገኝ የሚችልበትን ልዩ ዝግጅት በማድረግ ሊሰጥ ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ መጠየቅ ይቻላል።
በእቅድ የሚደረግ ስጦታ
ለማኅበሩ በቀጥታ የገንዘብ ስጦታ ከመለገስና ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ከመስጠት በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥት አገልግሎት ለመደጎም መስጠት የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ:-
ኢንሹራንስ:- የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአንድ የሕይወት ዋስትና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል።
የባንክ ሒሳብ:- የአገሩ ባንክ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል።
አክሲዮኖችና ቦንዶች:- አክሲዮኖችንና ቦንዶችን እንዳለ በስጦታ መልክ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር መስጠት ይቻላል።
የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች:- ሊሸጡ የሚችሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እንዳለ በስጦታነት ወይም ሰጪው በሕይወት እስካለ ድረስ በንብረቱ በመተዳደር እንዲቀጥል መብቱን በማስጠበቅ ለማኅበሩ በእርዳታ መስጠት ይቻላል። ማንኛውም የማይንቀሳቀስ ንብረት በሕግ ከማዛወርህ በፊት በአገሩ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ ማነጋገር ይኖርብሃል።
የስጦታ አበል:- የስጦታ አበል አንድ ሰው ገንዘቡን ወይም ንብረቱን ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለማስተላለፍ የሚያደርገውን ዝግጅት ያመለክታል። በምላሹም ለጋሹ ወይም እርሱ የወከላቸው ግለሰቦች በሕይወት እስከቆዩበት ጊዜ ድረስ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በየዓመቱ በአበል መልክ ይከፈላቸዋል። ለጋሹ የስጦታ አበሉን ለማስተላለፍ ከተስማማበት ጊዜ አንስቶ የገቢ ግብር ቅናሽ ያገኛል።
ኑዛዜዎችና አደራዎች:- ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተፈጻሚነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በውርሻ ሊሰጥ ወይም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዛወር ይችላል። አንድ የሃይማኖት ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ አንዳንድ ጥቅሞች አሉት።
“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች በሰጪው በኩል በትንሹም ቢሆን እቅድ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ። የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ ሥራ በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደጎም ለሚፈልጉ ግለሰቦች ዓለም አቀፉን የመንግሥት አገልግሎት ለመደጎም በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር በእንግሊዝኛና በስፓንኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ስጦታዎችን፣ ኑዛዜዎችንና አደራዎችን በተመለከተ ለቀረቡት በርካታ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ታስቦ ነው። በተጨማሪም ብሮሹሩ ከንብረት፣ ከገንዘብና ከታክስ ጋር በተያያዘ እቅድ ማውጣትን አስመልክቶ ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎች ይዟል። ከዚህም ሌላ ብሮሹሩ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩና በአሁኑ ጊዜ ልዩ ስጦታ ለመስጠት እቅድ ያላቸው ወይም በሚሞቱበት ጊዜ ውርስ ለመስጠት ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች የቤተሰባቸውና የግል ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውን ጠቃሚና ውጤታማ ዘዴ ለመምረጥ እንዲችሉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። የዚህን ብሮሹር አንድ ቅጂ በእቅድ የሚደረጉትን ስጦታዎች ጉዳይ ከሚከታተለው ቢሮ ጠይቆ ማግኘት ይቻላል።
ይህን ብሮሹር በማንበብና በእቅድ የሚደረጉትን ስጦታዎች ጉዳይ በሚከታተለው ቢሮ ውስጥ ከሚሠሩት ወንድሞች ምክር በመጠየቅ ብዙዎች በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች መርዳት ከመቻላቸውም በላይ ከቀረጥ ቅናሽ የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ችለዋል። በእቅድ የሚደረጉትን ስጦታዎች ጉዳይ የሚከታተለው ቢሮ ከእነዚህ ዝግጅቶች ጋር ግንኙነት ስላላቸው ሰነዶች ሊነገረውና የሰነዶቹ ቅጂ ሊላክለት ይገባል። ከእነዚህ በእቅድ የሚደረጉ ስጦታዎች በአንዱ ለመካፈል ከፈለግህ ከታች ያለውን አድራሻ በመጠቀም ወይም በአገርህ ወዳለው የማኅበሩ ቢሮ በመጻፍ ወይም በመደወል ማሳወቅ ይኖርብሃል።
CHARITABLE PLANNING OFFICE
Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
100 Watchtower Drive,
Patterson, New York 12563-9204
ስልክ:- (845) 306-0707