የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
አንደኛ ነገሥት 8:8 የቃል ኪዳኑን ታቦት ለመሸከም የሚያገለግሉት መሎጊያዎች ከቅድስቱ ውስጥ ይታያሉ የሚለው አቀማመጣቸው እንዴት ቢሆን ነው?
በምድረ በዳ የሚሠራውን የማደሪያ ድንኳን ንድፍ ይሖዋ ለሙሴ ሲሰጠው የዚህ ማደሪያ ድንኳን ዋነኛ ገጽታ የቃል ኪዳኑ ታቦት ነበር። ይህ የአራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው በወርቅ የተለበጠ ሣጥን ሕጉ የተቀረጸባቸውን ጽላቶችና ሌሎች ነገሮች ይይዝ ነበር። በውስጠኛው ክፍል በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ይቀመጣል። በታቦቱ ክዳን ላይ ክንፋቸውን የዘረጉ ሁለት የወርቅ ኪሩቦች ነበሩ። ከጎንና ከጎኑ ከግራር እንጨት ተሠርተው በወርቅ በተለበጡ ሁለት መሎጊያዎች አማካኝነት ታቦቱን ለመሸከም የሚያገለግሉ ሁለት ቀለበቶች አሉ። መሎጊያዎቹ ጫፍና ጫፍ ባሉት ቀለበቶች ውስጥ እንደሚሾልኩ ግልጽ ነው። ስለሆነም ፊቱ ወደ ምሥራቅ በሆነው የማደሪያው ድንኳን ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የሚገኘው ታቦት መሎጊያዎች ጫፋቸው ወደ ሰሜንና ደቡብ አቅጣጫ ነበር። ታቦቱ ሰሎሞን በገነባው ቤተ መቅደስ ውስጥ ከገባ በኋላም አቀማመጡ ተመሳሳይ ነበር።—ዘጸአት 25:10-22፤ 37:4-9፤ 40:17-21 a
በቅድስተ ቅዱሳኑና በቅድስቱ (በውጨኛው ክፍል) መካከል መጋረጃ አለ። በቅድስቱ ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት መጋረጃው ስለሚከልላቸው በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ያለው የአምላክን በዚያ መገኘት የሚያመለክተው ታቦት አይታያቸውም። (ዕብራውያን 9:1-7) በዚህ ምክንያት “መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩ፤ በቅድስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ በውጭ ያለ ግን አያያቸውም ነበር” የሚሉት የ1 ነገሥት 8:8 ቃላት ግራ የሚያጋቡ ይመስላሉ። በ2 ዜና መዋዕል 5:9 ላይ ተመሳሳይ አገላለጽ ይገኛል። ታዲያ መሎጊያዎቹ በቤተ መቅደሱ ቅድስት ውስጥ ላለ ለማንኛውም ሰው የሚታዩት እንዴት ነው?
አንዳንዶች መሎጊያዎቹ መጋረጃውን ስለሚነኩት መጋረጃው አበጥ ብሎ ይታያል የሚል አመለካከት አላቸው። ሆኖም መሎጊያዎቹ ከመጋረጃው ትይዩ ሆነው ጫፋቸው ወደ ሰሜንና ደቡብ አቅጣጫ ከሆነ መጋረጃውን ሊነኩት አይችሉም። (ዘኁልቍ 3:38) ከዚህ የተሻለ ምክንያታዊ ሐሳብ ማቅረብ ይቻላል። መሎጊያዎቹ በመጋረጃውና በመቅደሱ ግድግዳ መካከል ትንሽ ክፍተት ከነበረ በዚያ በኩል አሊያም ሊቀ ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ በሚገባበት ጊዜ ይታዩ ይሆናል። መጋረጃው ታቦቱ እንዳይታይ ሙሉ በሙሉ ቢከልልም በሁለቱም በኩል ረጃጅም የነበሩት መሎጊያዎች ግን በተፈጠረው ክፍተት መካከል ታይተው ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳ እዚህ ላይ የቀረበው ሐሳብ ምክንያታዊ ቢመስልም ከዚህ የተለየ ማብራሪያ አይኖረውም ማለት አንችልም።
ወደፊት ዝርዝር ሁኔታዎችን እንደምንማር ግልጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ አንዳንድ ገጽታዎቹን ጠቆም አድርጓል። ከዚያም “ስለ እነዚህም ስለ እያንዳንዳቸው ልንናገር አሁን አንችልም” ብሏል። (ዕብራውያን 9:5) የታመኑ ሰዎች ከሞት የሚነሱበት መጪው ትንሣኤ ስለ ማደሪያው ድንኳን ንድፍና አሠራር በቅርብ ከሚያውቁት ከሙሴ፣ ከአሮን፣ ከባስልኤል እንዲሁም ከሌሎች የበለጠ ለመማር አጋጣሚውን ይከፍትልናል።—ዘጸአት 36:1
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ታቦቱ ማደሪያው ድንኳን ውስጥ ገብቶ ከተቀመጠ በኋላም መሎጊያዎቹ ከቀለበቶቹ ውስጥ አይወጡም ነበር። በዚህም ምክንያት መሎጊያዎቹ ለሌላ ለምንም ዓላማ አይውሉም። በተጨማሪም ታቦቱ በእጅ መነካት አይኖርበትም። መሎጊያዎቹ ከቀለበቶቹ ውስጥ ይወጡ የነበረ ቢሆን ኖሮ ታቦቱን ማጓጓዝ ባስፈለገ ጊዜ ሁሉ መሎጊያዎቹን በቀለበቶቹ ውስጥ ለማስገባት ቅዱስ የሆነውን ታቦት በእጅ መንካት የግድ ይሆን ነበር። በዘኁልቊ 4:6 ላይ ‘መሎጊያዎቹን ስለማስገባት’ የሚናገረው ሐሳብ ክብደት ያለውን ታቦት ወደ አዲስ ሠፈር ተሸክሞ ለማድረስ በቅድሚያ መሎጊያዎቹን ስለ ማዘጋጀት ወይም ስለ ማስተካከል የሚገልጽ ሊሆን ይችላል።