የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
በዕብራውያን 4:9-11 ላይ የተጠቀሰው “ዕረፍት” ምንድን ነው? አንድ ሰው “ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት” የሚችለውስ እንዴት ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። ወደ ዕረፍቱ የገባ፣ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፣ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና። እንግዲህ . . . ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ።”—ዕብራውያን 4:9-11
ጳውሎስ፣ አምላክ ከሥራው እንዳረፈ ሲናገር በዘፍጥረት 2:2 ላይ “እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ” ተብሎ የተገለጸውን ማመልከቱ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይሖዋ ‘በሰባተኛው ቀን ያረፈው’ ለምን ነበር? “ከሠራው ሥራ ሁሉ” የተነሳ ኃይሉን ማደስ አስፈልጎት እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። ከዚያ ቀጥሎ ያለው ጥቅስ የሚሰጠን ፍንጭ አለ:- “እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና።”—ዘፍጥረት 2:3፤ ኢሳይያስ 40:26, 28
“ሰባተኛውን ቀን” አምላክ ስለባረከውና ስለቀደሰው ማለትም ለአንድ ልዩ ዓላማ የተለየ ወይም የተወሰነ ቀን ስላደረገው አስቀድሞ ከነበሩት ከስድስቱ ቀናት የተለየ ነበር። ይህ ዓላማ ምን ነበር? ቀደም ሲል አምላክ የሰው ልጆችንና ምድርን በተመለከተ ያለውን ዓላማ አሳውቆ ነበር። አምላክ ለመጀመሪያው ሰውና ለሚስቱ እንዲህ ብሏቸዋል:- “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” (ዘፍጥረት 1:28) ምንም እንኳ አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር ፍጹም ጅምር ቢያደርግላቸውም በአምላክ ዓላማ መሠረት መላዋን ምድር መግዛትና ፍጹም በሆነ ሰብዓዊ ቤተሰብ የተሞላች ገነት ማድረግ ጊዜ የሚጠይቅ ሥራ ነበር። በመሆኑም ‘በሰባተኛው ቀን’ አምላክ አስቀድሞ የፈጠራቸው ነገሮች ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ እያደጉ እንዲሄዱ ለማስቻል ተጨማሪ ምድራዊ የፍጥረት ሥራዎች ከመሥራት አርፏል ወይም ተቆጥቧል። ሰባተኛው “ቀን” ሲያበቃ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የተካተተው ነገር ሁሉ እውን ይሆናል። የዕረፍቱ ቀን ምን ያህል ርዝመት ይኖረዋል?
በዕብራውያን መጽሐፍ ላይ ወደሚገኘው የጳውሎስ ሐሳብ ስንመለስ “የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል” ብሎ መናገሩን የምናስተውል ከመሆኑም በላይ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ “ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት” ትጋት እንዲያሳዩ አሳስቧቸዋል። ይህም ማለት ጳውሎስ እነዚህን ቃላት በጻፈበት ወቅት 4, 000 ዓመታት ገደማ ያስቆጠረው አምላክ ያረፈበት ‘ሰባተኛው ቀን’ ገና አላበቃም ማለት ነው። ይህ ቀን “የሰንበት ጌታ” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ንግሥና ማብቂያ ላይ አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር ያለው ዓላማ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እስከሚያገኝበት ጊዜ ድረስ ይዘልቃል።—ማቴዎስ 12:8፤ ራእይ 20:1-6፤ 21:1-4
ጳውሎስ አንድ ሰው ይህን አስደናቂ ተስፋ በመያዝ እንዴት ወደ አምላክ ዕረፍት መግባት እንደሚችል ገልጿል። “ወደ ዕረፍቱ የገባ፣ . . . እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና” ሲል ጽፏል። ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ምንም እንኳ ፍጹም ጅምር ቢኖራቸውም የሰው ልጆች ባጠቃላይ ወደ አምላክ ዕረፍት አልገቡም። ይህ የሆነበት ምክንያት አዳምና ሔዋን አምላክ ለእነሱ ያደረገውን ዝግጅት ተቀብለው የአምላክ ዕረፍት የሆነውን ‘ሰባተኛውን ቀን’ ረዘም ላለ ጊዜ ሳይጠብቁ በመቅረታቸው ነው። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ አገዛዝ ነፃ መውጣት ስለፈለጉ ዓመፁ። እንዲያውም የአምላክን ፍቅራዊ መመሪያ ከመቀበል ይልቅ የሰይጣንን ዕቅድ ደገፉ። (ዘፍጥረት 2:15-17) ከዚህ የተነሳ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ አጡ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የሰው ልጅ በሙሉ የኃጢአትና የሞት ባሪያ ሆነ።—ሮሜ 5:12, 14
የሰው ልጅ ዓመፅ የአምላክን ዓላማ አላጨናገፈውም። የአምላክ ዕረፍት ቀን እንደቀጠለ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ በእምነት የተቀበሉት ሁሉ ከኃጢአትና ከሞት ቀንበር የመላቀቅና ዕረፍት የማግኘት ተስፋ እንዲኖራቸው ሲል በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የቤዛውን ፍቅራዊ ዝግጅት አደረገ። (ሮሜ 6:23) ጳውሎስ የእምነት ጓደኞቹን ‘ከሥራቸው እንዲያርፉ’ ያሳሰባቸው በዚህ ምክንያት ነው። የአምላክን የደኅንነት ዝግጅት መቀበልና አዳምና ሔዋን እንዳደረጉት የራሳቸውን የወደፊት ሕይወት በራሳቸው ጥረት ከማመቻቸት መቆጠብ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም የራሳቸውን የጽድቅ ተግባር ከመከተል መራቅ አለባቸው።
አንድ ሰው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሲል የስስት ወይም ዓለማዊ ግቦቹን መተዉ በእርግጥ የመንፈስ ጥንካሬና ዕረፍት ያስገኝለታል። ኢየሱስ የሚከተለውን ግብዣ አቅርቧል:- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”—ጳውሎስ ስለ አምላክ ዕረፍትና አንድ ሰው ወደ ዕረፍቱ እንዴት ሊገባ እንደሚችል የሰጠው ማብራሪያ ለእምነታቸው ሲሉ ብዙ ስደትና ነቀፋ በጽናት ላሳለፉ በኢየሩሳሌም ለነበሩ ዕብራውያን ክርስቲያኖች የብርታት ምንጭ እንደሆነላቸው የተረጋገጠ ነው። (ሥራ 8:1፤ 12:1-5) በተመሳሳይ የጳውሎስ ቃላት በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች የብርታት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። አምላክ ጽድቅ በሰፈነበት መንግሥቱ አማካኝነት ምድርን ገነት ለማድረግ የገባው ቃል ፍጻሜውን የሚያገኝበት ጊዜ በጣም ቅርብ መሆኑን በመገንዘብ እኛም ከራሳችን ሥራ ማረፍና ወደ አምላክ ዕረፍት ለመግባት መትጋት ይኖርብናል።—ማቴዎስ 6:10, 33፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግ የገባው ቃል በዕረፍቱ ቀን መጨረሻ ላይ ፍጻሜውን ያገኛል