ልጆቻችሁን ስታሠለጥኑ ይሖዋን ምሰሉ
ልጆቻችሁን ስታሠለጥኑ ይሖዋን ምሰሉ
“አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?”—ዕብራውያን 12:7
1, 2. በዛሬው ጊዜ ወላጆች ልጆችን በማሳደግ ረገድ ችግር የገጠማቸው ለምንድን ነው?
ከጥቂት ዓመታት በፊት በጃፓን የተደረገ አንድ ጥናት ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው አዋቂ ሰዎች መካከል ግማሽ የሚያክሉት በወላጆችና በልጆች መካከል ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንደሌለና ወላጆችም ልጆቻቸውን ከመጠን በላይ እንደሚያሞላቅቋቸው ይፋ አድርጓል። በዚህ አገር የተደረገ ሌላ ጥናት እንዳሳየው ጥያቄ ከቀረበላቸው መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት ከልጆች ጋር መግባባት እንደሚቸግራቸው ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። እንዲህ ያለው ሁኔታ በሩቅ ምሥራቅ አገሮች ብቻ የተወሰነ አይደለም። “በርካታ ካናዳውያን ወላጆች እንዴት ጥሩ ወላጅ መሆን እንደሚቻል እንደማያውቁ ተናግረዋል” በማለት ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። በየትኛውም የምድር ክፍል የሚገኙ ወላጆች ልጆችን ማሳደግ አስቸጋሪ እየሆነባቸው መጥቷል።
2 ወላጆች ልጆችን በማሳደግ ረገድ ችግር የሚገጥማቸው ለምንድን ነው? የዚህ ዋነኛው ምክንያት “የሚያስጨንቅ ዘመን” በተባለው “በመጨረሻው ቀን” ውስጥ የምንኖር መሆናችን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነው” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 8:21) በተለይ ወጣቶች ተሞክሮ የሌላቸውን አድኖ ለመያዝ “እንደሚያገሳ አንበሳ” ለሚዞረው ለሰይጣን ጥቃት ዋነኛ ዒላማ ናቸው። (1 ጴጥሮስ 5:8) ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ለማሳደግ ቆርጠው የተነሱ ክርስቲያን ወላጆች በእርግጥም በርካታ ችግሮች አሉባቸው። (ኤፌሶን 6:4) ወላጆች ልጆቻቸው “መልካሙንና ክፉውን” መለየት የሚችሉ የጎለመሱ የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑላቸው መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?—ዕብራውያን 5:14
3. ልጆችን በተሳካ ሁኔታ አርሞና ኮትኩቶ ለማሳደግ ወላጆች የሚሰጡት ሥልጠናና መመሪያ ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?
3 ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ስንፍና በሕፃን ልብ ታስሮአል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 13:1፤ 22:15) ልጆች እንዲህ ያለውን ስንፍና ከልባቸው ውስጥ ነቅለው ለማስወጣት ከወላጆቻቸው የሚሰጣቸው ፍቅራዊ እርምት ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም ልጆች እንደዚህ ያለውን እርምት ሁልጊዜ በደስታ ላይቀበሉት ይችላሉ። እንዲያውም ከማንም ይምጣ ከማን የሚሰጣቸውን ምክር ለመቀበል ብዙውን ጊዜ ሲያንገራግሩ ይታያሉ። ስለዚህ ወላጆች ‘ልጅን በሚሄድበት መንገድ መምራት’ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ አለባቸው። (ምሳሌ 22:6) ልጆች የሚሰጣቸውን እንዲህ ያለውን ምክር በጥብቅ ከተከተሉ ሕይወት ሊያስገኝላቸው ይችላል። (ምሳሌ 4:13) ወላጆች፣ ልጅን ማሠልጠን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ማወቃቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!
ተግሣጽ ምንድን ነው?
4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተሠራበት መሠረት “ተግሣጽ” የሚለው ቃል ዋነኛ ትርጉም ምንድን ነው?
4 አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ይደበድቧቸዋል፣ ይሰድቧቸዋል ወይም ሥነ ልቦናዊ በደል ይፈጽሙባቸዋል ተብለው እንዳይከሰሱ በመፍራት ልጆቻቸውን ከመቅጣት ወደኋላ ይላሉ። እኛ ግን እንዲህ ያለ ፍርሃት ሊሰማን አይገባም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት “ተግሣጽ” የሚለው ቃል የትኛውንም ዓይነት በደል ወይም የጭካኔ ድርጊት አያመለክትም። “ተግሣጽ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛው ቃል በዋነኛነት የሚያመለክተው መመሪያ፣ ትምህርት፣ እርማትና አንዳንድ ጊዜም ጥብቅ ሆኖም በፍቅር ላይ የተመሠረተ ቅጣት መስጠትን ነው።
5. ይሖዋ ሕዝቡን እንዴት አድርጎ እንደያዘ መመርመሩ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
5 እንዲህ ያለውን ተግሣጽ በመስጠት ረገድ ይሖዋ አምላክ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋን ከአንድ ሰብዓዊ አባት ጋር በማወዳደር እንዲህ በማለት ጽፏል:- “አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? . . . እነርሱ [የሥጋችን አባቶች] መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፣ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል።” (ዕብራውያን 12:7-10) አዎን፣ ይሖዋ ሕዝቡን የሚቀጣው ቅዱስ ወይም ንጹሕ እንዲሆኑ ነው። ይሖዋ ሕዝቡን ያሠለጠነበትን መንገድ በመመርመር ልጆችን ስለመገሠጽ ብዙ መማር እንችላለን።—ዘዳግም 32:4፤ ማቴዎስ 7:11፤ ኤፌሶን 5:1
ፍቅር—አንቀሳቃሽ ኃይል
6. ወላጆች ይሖዋን በፍቅሩ መምሰል ቀላል ሆኖ የማያገኙት ለምን ሊሆን ይችላል?
6 ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት ተናግሯል። ስለሆነም ይሖዋ ምንጊዜም ስልጠና የሚሰጠው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። (1 ዮሐንስ 4:8፤ ምሳሌ 3:11, 12) ታዲያ እንዲህ ሲባል ወላጆች ልጆቻቸውን በተፈጥሮ የሚወዷቸው በመሆኑ በዚህ ረገድ ይሖዋን መምሰል ቀላል ሆኖ ያገኙታል ማለት ነው? እንደዚያ ማለት ላይሆን ይችላል። የአምላክ ፍቅር በመሠረታዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ፍቅር ነው። እንዲሁም አንድ ግሪካዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዳመለከቱት እንዲህ ያለው ፍቅር “ብዙውን ጊዜ ከተፈጥሮ ዝንባሌ ጋር አይጣጣምም።” አምላክ በስሜት አይመራም። ምንጊዜም የሚያስበው ሕዝቡን የሚጠቅማቸውን ነገር ነው።—ኢሳይያስ 30:20፤ 48:17
7, 8. (ሀ) ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር በነበረው ግንኙነት በመሠረታዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ፍቅር በማሳየት ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል? (ለ) ወላጆች ልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የመከተል ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ በሚረዱበት ጊዜ ይሖዋን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?
7 ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት ያሳየውን ፍቅር ተመልከት። ሙሴ ልብ የሚነካ ምሳሌያዊ አነጋገር በመጠቀም ይሖዋ ጨቅላ ለነበረው ለእስራኤል ብሔር ያሳየውን ፍቅር ገልጿል። እንዲህ እናነባለን:- “ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፣ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፣ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፣ በክንፎቹም አዘላቸው። እግዚአብሔር ብቻውን [ያዕቆብን] መራው።” (ዘዳግም 32:9, 11, 12) አንዲት እናት ንስር ጫጩቶቿ እንዲበርሩ ለማስተማር ክንፎቿን እያማታችና እያርገፈገፈች እንዲሁም ጎጆዋን እየነቀነቀች ‘እንዲወጡ’ ታነሳሳቸዋለች። በመጨረሻም አንዱ ጫጩት ብዙውን ጊዜ ገደል ላይ ከሚገኘው ጎጆው ውስጥ ዘሎ ሲወጣ እናትየው ‘ከላዩ እየተንሳፈፈች’ ትከተለዋለች። ጫጩቱ መሬት ደርሶ የሚፈጠፈጥ ከመሰላት በፍጥነት ተወርውራ ከሥሩ በመግባት በክንፎቿ ‘ታዝለዋለች።’ ይሖዋም አዲስ ለተወለደው የእስራኤል ብሔር በተመሳሳይ መንገድ ፍቅራዊ እንክብካቤ አድርጎለታል። የሙሴን ሕግ ለሕዝቡ ሰጥቷል። (መዝሙር 78:5-7) ከዚያም ብሔሩን በጥንቃቄ እየተንከባከበ በሕዝቡ ላይ ሊደርስ ከሚችል አደጋ ታድጎታል።
8 ክርስቲያን ወላጆች ይሖዋን በፍቅሩ ሊመስሉት የሚችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶችና የአቋም ደረጃዎች ለልጆቻቸው ማስተማር አለባቸው። (ዘዳግም 6:4-9) እንዲህ የሚያደርጉበት ዓላማ ልጆቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ውሳኔ ማድረግን እንዲማሩ ለመርዳት ነው። ይህን ሲያደርጉም አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች በምሳሌያዊ አነጋገር በላያቸው ላይ እያንዣበቡ ልጆቹ የተማሯቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ እንዴት እያዋሏቸው እንዳሉ ይመለከታሉ። ልጆቹ እያደጉና ቀስ በቀስ ተጨማሪ ነፃነት እያገኙ ሲሄዱ አሳቢ የሆኑ ወላጆች አደጋ በሚኖርት ጊዜ ሁሉ ‘በፍጥነት ተወርውረው በክንፋቸው ለመሸከም’ ዝግጁዎች ናቸው። አደጋዎቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
9. አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች በተለይ ለየትኛው አደጋ ንቁ መሆን አለባቸው? ምሳሌ ስጥ።
9 ይሖዋ አምላክ ክፉ ባልንጀርነት የሚያስከትለውን መዘዝ በተመለከተ እስራኤላውያንን አስጠንቅቋቸዋል። (ዘኁልቊ 25:1-18፤ ዕዝራ 10:10-14) ዛሬም ከመጥፎ ሰዎች ጋር መግጠም አደጋ አለው። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ክርስቲያን ወላጆች በዚህ ረገድ ይሖዋን መምሰል ይገባቸዋል። ሊዛ የተባለች አንዲት የ15 ዓመት ልጅ ወላጆቿ የሚከተሉትን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ አቋም ከማይከተል ልጅ ጋር መቀራረብ ጀመረች። “ወላጆቼ ጠባዬ እየተቀየረ እንዳለ ወዲያው ከማስተዋላቸውም በላይ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጡት” በማለት ሊዛ ትናገራለች። “አንዳንድ ጊዜ እርማት ይሰጡኛል በሌላ ጊዜ ደግሞ በርኅራኄ ያበረታቱኛል።” ከሊዛ ጋር ተቀምጠው በትዕግሥት ካዳመጧት በኋላ የችግሯ ዋነኛ መንሥኤ ሆኖ ያገኙትን በውስጧ ያለውን በእኩዮቿ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ምኞቷን እንድታሸንፍ ረዷት። a
የሐሳብ ግንኙነት መሥመሩ ክፍት ይሁን
10. ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?
10 ልጆችን በማሳደግ ረገድ ስኬታማ ለመሆን ወላጆች በእነሱና በልጆቻቸው መካከል ያለው የሐሳብ ግንኙነት መስመር ክፍት እንዲሆን ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል። ይሖዋ በልባችን ውስጥ ያለውን ሁሉ ጠንቅቆ የሚያውቅ ቢሆንም እንኳ ሐሳባችንን እንድንገልጽለት ያበረታታናል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) ይሖዋ ለእስራኤላውያን ሕጉን ከሰጣቸው በኋላ እንዲያስተምሯቸው ሌዋውያንን የመደበላቸው ከመሆኑም በላይ እንዲያስረዷቸውና እንዲያስተካክሏቸው ነቢያትን ልኮላቸዋል። የሚያቀርቡትን ጸሎት ለመስማትም ፈቃደኛ መሆኑን ገልጾላቸዋል።—2 ዜና መዋዕል 17:7-9፤ መዝሙር 65:2፤ ኢሳይያስ 1:1-3, 18-20፤ ኤርምያስ 25:4፤ ገላትያ 3:22-24
11. (ሀ) ወላጆች በእነርሱና በልጆቻቸው መካከል ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜ ጥሩ አዳማጭ መሆናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
11 ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሐሳብ ግንኙነት በሚያደርጉበት ጊዜ ይሖዋን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ለልጆቻቸው ጊዜ መመደብ አለባቸው። በተጨማሪም ወላጆች “በቃ ለዚህችው ነው? እኔ ደግሞ ቁም ነገር መስሎኝ”፤ “ይሄማ የማይረባ ነገር ነው”፤ “ድሮስ ምን ፈለግህ? አንተ ገና ልጅ ነህ” እንደሚሉት ያሉ ልጁ እንዲያፍር የሚያደርጉ ሐሳቦችን ከመሰንዘር መቆጠብ ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 12:18) ጠቢብ የሆኑ ወላጆች ልጆች የልባቸውን አውጥተው እንዲነግሯቸው ለማድረግ ጥሩ አድማጭ ለመሆን ይጥራሉ። ልጆቻቸውን በልጅነታቸው ወቅት ችላ የሚሉ ወላጆች ልጆቹ አድገው ትላልቅ በሚሆኑበት ጊዜ በተራቸው ችላ ይሏቸዋል። ይሖዋ ሕዝቡን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሳይሆን የቀረበት ጊዜ የለም። ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ እርሱ የሚጸልዩትን ሁሉ ሁልጊዜ ያዳምጣቸዋል።—መዝሙር 91:15፤ ኤርምያስ 29:12፤ ሉቃስ 11:9-13
12. ወላጆች ልጆቻቸው በቀላሉ እንዲቀርቧቸው የትኞቹን ባሕርያት ማዳበር ይረዳቸዋል?
12 አንዳንዶቹ የአምላክ ባሕርያት ሕዝቡ በቀላሉ እንዲቀርቡት ያደረጋቸው እንዴት እንደሆነ ተመልከት። ለምሳሌ ያህል የጥንቱ እስራኤል ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር በመፈጸም ከባድ ኃጢአት ሠርቶ ነበር። ዳዊት ፍጹም ያልሆነ ሰው እንደመሆኑ መጠን በሕይወቱ ውስጥ ሌሎች ከባድ ኃጢአቶችንም ፈጽሟል። ሆኖም የይሖዋን ምሕረትና ተግሣጽ ሳይፈልግ የቀረበት ጊዜ የለም። የአምላክ ፍቅራዊ ደግነትና ምሕረት ዳዊት ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ቀላል እንዳደረገለት ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 103:8) ወላጆችም እንደ ርኅራኄና ምሕረት ያሉ አምላካዊ ባሕርያትን ማንጸባረቃቸው ልጆች በሚያጠፉበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር የሐሳብ ግንኙነት መሥመራቸውን ክፍት አድርገው እንዲቆዩ ሊረዳቸው ይችላል።—መዝሙር 103:13፤ ሚልክያስ 3:17
ምክንያታዊ ሁኑ
13. ምክንያታዊ መሆን ምንን ይጨምራል?
13 ወላጆች ልጆቻቸውን በሚያዳምጡበት ጊዜ ምክንያታዊና ‘ላይኛይቱን ጥበብ’ የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው። (ያዕቆብ 3:17) “ገርነታችሁ [“ምክንያታዊነታችሁ፣” NW ] ለሰው ሁሉ ይታወቅ።” (ፊልጵስዩስ 4:5) ምክንያታዊ መሆን ምን ማለት ነው? “ምክንያታዊ” ለሚለው የግሪክኛ ቃል ከተሰጡት ፍቺዎች መካከል አንዱ “በሕጉ ፊደል ላይ ድርቅ አለማለት” የሚል ነው። ወላጆች ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ የአቋም ደረጃዎችን ሳያላሉ ምክንያታዊ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?
14. ከሎጥ ጋር በተያያዘ ይሖዋ ምክንያታዊነትን ያሳየው እንዴት ነው?
14 ምክንያታዊ በመሆን ረገድ ይሖዋ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ምሳሌ ትቶልናል። (መዝሙር 10:17) ሎጥና ቤተሰቡ ጥፋት ከተፈረደባት ከሰዶም ከተማ እንዲወጡ ማሳሰቢያ በተሰጣቸው ጊዜ ሎጥ ‘ዘገየ።’ ከጊዜ በኋላ የይሖዋ መልአክ ወደ ተራራማው አካባቢ እንዲሸሽ በነገረው ጊዜ ሎጥ “ወደ ተራራ ሸሽቼ አመልጥ ዘንድ አልችልም፤ እነሆ ይህች ከተማ [ዞዓር] ወደ እርስዋ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፣ እርስዋም ትንሽ ናት፤ . . . ወደ እርስዋ ሸሽቼ ላምልጥ፤ እርስዋ ትንሽ ከተማ አይደለችምን?” በማለት ተናገረ። ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠ? “የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ” አለው። (ዘፍጥረት 19:16-21, 30) ይሖዋ የሎጥን ጥያቄ ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኗል። እርግጥ ነው፣ ወላጆች ይሖዋ አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሰፈራቸውን የአቋም ደረጃዎች በጥብቅ መከተል ይገባቸዋል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ የልጆችን ፍላጎት ግምት ውስጥ ማስገባት ይቻል ይሆናል።
15, 16. በኢሳይያስ 28:24, 25 ላይ ከሚገኘው ምሳሌ ወላጆች ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?
15 ምክንያታዊ መሆን ልጆች የሚሰጣቸውን ምክር ይሰሙ ዘንድ ልባቸውን ማዘጋጀትን ይጨምራል። ኢሳይያስ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ይሖዋን ከአንድ ገበሬ ጋር በማወዳደር እንዲህ ብሏል:- “በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ ሁልጊዜ እርሻውን ይገለግላልን? ጓሉንስ ይከሰክሳልን? እርሻውን ባስተካከለ ጊዜ ጥቁሩን አዝሙድ፣ ከሙኑንም፣ ስንዴውንም በተርታ፣ ገብሱንም በስፍራው፣ አጃንም በደረጃው የሚዘራ አይደለምን?”—ኢሳይያስ 28:24, 25
16 ይሖዋ ዘርን ‘ለመዝራት ያርሳል እንዲሁም ጓሉን በመከስከስ መሬቱን ያለሰልሳል።’ ተግሳጽ ከመስጠቱ በፊት በዚህ መንገድ የሕዝቡን ልብ ያዘጋጅ ነበር። ወላጆች ልጆቻቸውን በሚያርሙበት ጊዜ የልጆቻቸውን ልብ ‘ማረስ’ የሚችሉት እንዴት ነው? አንድ አባት የአራት ዓመት ልጁን በሚያርምበት ጊዜ የይሖዋን ምሳሌ ተከትሏል። ልጁ አንድን የጎረቤት ልጅ በመታ ጊዜ በመጀመሪያ አባትየው ልጁ የሚሰጠውን ምክንያት በትዕግሥት አዳመጠ። ከዚያም የልጁን ልብ ‘የማረስ’ ያህል ጉልበተኛ ልጆች ሁልጊዜ ይመቱት ስለነበረ አንድ ልጅ የሚገልጽ ታሪክ ነገረው። ልጁ ታሪኩን ካዳመጠ በኋላ ጉልበተኞቹ ልጆች መቀጣት እንዳለባቸው ተናገረ። አባትየው በዚህ መንገድ ‘በማረስ’ የልጁን ልብ አዘጋጅቶ የጎረቤት ልጅ መምታትም የጉልበተኝነት ድርጊት እንደሆነና ይህ ደግሞ ተገቢ እንዳልሆነ በቀላሉ እንዲታየው አድርጓል።—2 ሳሙኤል 12:1-14
17. ወላጆች ስለሚሰጡት እርማት በኢሳይያስ 28:26-29 ላይ ምን ትምህርት ሰፍሯል?
17 በተጨማሪም ኢሳይያስ ይሖዋ የሚሰጠውን እርማት ከሌላ የግብርና ሥራ ማለትም እህል ከመውቃት ጋር አነጻጽሮታል። አንድ ገበሬ እንደ እህሉ የገለባ ጥንካሬ የተለያዩ የመውቂያ መሣሪያዎችን ይጠቀማል። ጥቁር አዝሙድን ለመውቃት በትር ይጠቀማል እንዲሁም ከሙን ለመውቃት ሽመል ይጠቀማል። ይሁን እንጂ ጠንከር ያለ ገለባ ያለውን እህል ለመውቃት ጋሪ ወይም ሰረገላ ይጠቀማል። ሆኖም ከገለባው አልፎ እህሉ እስኪሰባበር ድረስ አያስኬድበትም። በተመሳሳይም ይሖዋ አንድን የማይፈለግ ነገር ከሕዝቡ መካከል ለማስወገድ በሚፈልግበት ጊዜ ጉዳዩን የሚይዝበትን መንገድ እንደሁኔታው ይለዋውጣል። አምባ ገነን ወይም ጨካኝ አይደለም። (ኢሳይያስ 28:26-29) አንዳንድ ልጆች ወላጆቻቸው ገና ኮስተር ሲሉባቸው ብቻ ይበቃቸዋል፣ ከዚያ ያለፈ ነገር አያስፈልጋቸውም። አንዳንዶች ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሌሎች ደግሞ ትንሽ ጠንከር ያለ ተግሳጽ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ምክንያታዊ የሆኑ ወላጆች እንደ ልጆቹ ሁኔታ እርማት ይሰጣሉ።
የቤተሰብን ውይይት አስደሳች አድርጉት
18. ወላጆች ዘወትር የሚደረግ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ጊዜ መመደብ የሚችሉት እንዴት ነው?
18 ቋሚ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና በየዕለቱ የሚደረግ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ልጆቻችሁን ለማስተማር ከሚያስችሏችሁ ከሁሉ የተሻሉ መንገዶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ዘወትር የሚደረግ ከሆነ ከቤተሰብ ጥናት ከፍተኛ ጥቅም ይገኛል። በተመቸ ጊዜ ወይም ድንገት ትዝ ሲል ብቻ የሚደረግ ከሆነ ቋሚ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው። ስለዚህ ወላጆች ለጥናቱ የሚሆን ‘ጊዜ መዋጀት’ አለባችሁ። (ኤፌሶን 5:15-17) ለሁሉም አመቺ የሆነ ቋሚ ጊዜ መምረጥ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። አንድ የቤተሰብ ራስ ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ ፕሮግራማቸው በመለያየቱ ምክንያት ቤተሰቡ አንድ ላይ መሰባሰብ እንዳስቸገረው ተገነዘበ። ሆኖም የጉባኤ ስብሰባዎች ባሉበት ምሽት ቤተሰቡ ሁልጊዜ አንድ ላይ ይሰባሰባል። ስለዚህ አባትየው ከእነዚህ ምሽቶች በአንዱ የቤተሰብ ጥናት ለማድረግ ዝግጅት አደረገ። ይህም ውጤት አስገኘ። አሁን ሦስቱም ልጆቹ የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው።
19. ወላጆች የቤተሰብ ጥናት በሚመሩበት ጊዜ የይሖዋን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?
19 ይሁን እንጂ በጥናቱ ወቅት ቅዱስ ጽሑፋዊ ጽሑፎችን መሸፈን ብቻውን በቂ አይደለም። ይሖዋ ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱትን እስራኤላውያን በካህናቱ አማካኝነት አስተምሯቸዋል። ካህናቱም ‘የሚያነቡትን እያብራሩ ያስረዷቸው ነበር።’ (ነህምያ 8:8 NW ) ሰባቱም ልጆቹ ለይሖዋ ፍቅር እንዲኖራቸው በመርዳት ረገድ የተሳካለት አንድ አባት የቤተሰብ ጥናቱ ከመጀመሩ በፊት ወደ ክፍሉ ይገባና ትምህርቱን ከእያንዳንዱ ልጅ ሁኔታ ጋር እንደሚስማማ አድርጎ ለማቅረብ ይዘጋጃል። ጥናቱን ልጆቹ እንደሚወዱት አድርጎ ያቀርበው ነበር። ትልቅ ከሆኑት ልጆቹ መካከል አንዱ “ጥናቱ ሁልጊዜ የሚያስደስት ነበር” በማለት ያስታውሳል። “ውጪ ኳስ እየተጫወትን ሳለ ለቤተሰብ ጥናት ስንጠራ ወዲያው ኳሳችንን ትተን ሮጠን ወደ ቤት እንሄድ ነበር። በሳምንቱ ውስጥ በጣም አስደሳች ከሆኑት ምሽቶች መካከል አንዱ ይህ ወቅት ነው።”
20. ልጆችን በማሳደግ ረገድ ሊያጋጥም የሚችል ምን ነገር እንመረምራለን?
20 መዝሙራዊው “እነሆ፣ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፣ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 127:3) ልጆችን ማሠልጠን ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ሆኖም ተገቢ በሆነ መንገድ እንዲህ ማድረጉ ልጆቻችን የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ደግሞ ምንኛ የሚክስ ነው! ስለዚህ ልጆቻችንን በምናሠለጥንበት ጊዜ የይሖዋን ምሳሌ ለመኮረጅ ጥረት እናድርግ። ‘ልጆቻቸውን በይሖዋ ምክርና በተግሣጽ የማሳደግ’ ኃላፊነት በወላጆች ላይ የተጣለ ቢሆንም እንኳ ሁልጊዜ ይሳካላቸዋል ማለት ግን አይደለም። (ኤፌሶን 6:4) ከፍተኛ ጥረት ተደርጎም አንድ ልጅ ዓመፀኛ ሊሆንና ይሖዋን ማገልገል ሊያቆም ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ምን ማድረግ ይቻላል? በሚቀጥለው ርዕስ ይህ ጉዳይ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህም ሆነ በቀጣዩ ርዕስ ላይ የሠፈሩት ተሞክሮዎች ከእናንተ ባሕል ከተለየ አካባቢ የተገኙ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ለመረዳትና ከእናንተ ባሕል ጋር ሊስማማ በሚችል መንገድ በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርጉ።
ምን መልስ ትሰጣለህ?
• ወላጆች በዘዳግም 32:11, 12 ላይ የተገለጸውን የይሖዋን ፍቅር ሊኮርጁ የሚችሉት እንዴት ነው?
• ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር ከነበረው የሐሳብ ግንኙነት ምን ትማራለህ?
• ይሖዋ ሎጥ ያቀረበውን ልመና መቀበሉ ምን ያስተምረናል?
• ለልጆች እርማት በመስጠት ረገድ ከኢሳይያስ 28:24-29 ምን ትምህርት አግኝተሃል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ሕዝቡን የሚያሠለጥንበትን መንገድ ሙሴ አንዲት ንስር ለጫጩቶቿ ከምታደርግላቸው ሥልጠና ጋር አመሳስሎ ገልጾታል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች ለልጆቻቸው ጊዜ መመደብ ይኖርባቸዋል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በሳምንቱ ውስጥ በጣም አስደሳች ከሆኑት ምሽቶች መካከል አንዱ ይህ ወቅት ነው”