ታስታውሳለህን?
ታስታውሳለህን?
በቅርቡ የወጡ የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን አንብበሃልን? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-
• በኢዮብ ምዕራፍ 38 ውስጥ የቀረቡት ጥያቄዎች ዛሬም ቢሆን ልንመረምራቸው የሚገቡ የሆኑት ለምንድን ነው?
አምላክ ኢዮብ ትኩረት እንዲያደርግባቸው የጠቀሰለትን አብዛኞቹን ድንቅ ሥራዎች በዚህ ዘመን ያሉ ሳይንቲስቶች እንኳ ሙሉ በሙሉ አልተረዷቸውም። ከእነዚህ ድንቅ ሥራዎች መካከል ስበት ምድር ምህዋሯን ጠብቃ እንድትዞር የሚያደርጋት እንዴት እንደሆነ፣ የብርሃን ምንነት፣ የበረዶ ቅንጣቶች በቅርጽና በመልክ የተለያዩበት ምክንያት፣ የዝናብ ጠብታዎች የሚፈጠሩት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ነጎድጓዳማ ወዥቦች ያላቸው ኃይል ይገኙበታል።—4/15 ገጽ 4-11
• የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች አሉታዊ ስሜቶችን እንድንቋቋም ሊረዱን ይችላሉ?
አሳፍ፣ ባሮክ እና ኑኃሚን ተስፋ መቁረጥ ወይም ሌሎች አሉታዊ ስሜቶች ያጋጠማቸው ወቅት የነበረ ሲሆን ችግሩን በተሳካ ሁኔታ እንደተቋቋሙ የሚገልጹት ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘገባዎች እኛንም ሊረዱን ይችላሉ።—4/15 ገጽ 22-24
• ክርስቲያን መበለቶችን መርዳት የሚቻልባቸው አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
ወዳጆች ደግነትና ግልጽነት በተሞላበት ሁኔታ እነርሱን ለመርዳት ራሳቸውን ማቅረብ ይችላሉ። የቤተሰብ አባላት ወይም ሌሎች ሰዎች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የገንዘብ ወይም ቁሳዊ እርዳታ መስጠት ይችላሉ። ክርስቲያኖችም በመንፈሳዊ በመደገፍና በማጽናናት ፍቅራዊ አሳቢነታቸውን ማሳየት ይችላሉ።—5/1 ገጽ 5-7
• በአንደኛ ቆሮንቶስ 7:39 ላይ በሚገኘው ምክር መሠረት “በጌታ ብቻ” ማግባት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ከማያምን ሰው ጋር በትዳር መቆራኘት በአብዛኛው ውጤቱ መራራ ነው። ከዚህም በላይ ይህን መለኮታዊ ምክር መከተሉ ለይሖዋ አምላክ ታማኝ የመሆን ጉዳይ ነው። ከአምላክ ቃል ጋር ተስማምተን ስንሄድ ልባችን አይፈርድብንም። (1 ዮሐንስ 3:21, 22)—5/15 ገጽ 20-1
• ኃጢአታችንን ይቅር ለማለት የሚችለው ይሖዋ ሆኖ ሳለ ክርስቲያኖች ከባድ ኃጢአቶችን በጉባኤው ውስጥ ላሉ ሽማግሌዎች የሚናዘዙት ለምንድን ነው?
አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ሲሠራ ማግኘት የሚፈልገው የይሖዋን ይቅርታ መሆኑ ግልጽ ነው። (2 ሳሙኤል 12:13) ሆኖም ነቢዩ ናታን ዳዊትን እንደረዳው ሁሉ በጉባኤ ውስጥ ያሉ የጎለመሱ ሽማግሌዎችም ከልብ ጸጸት የተሰማቸውን ኃጢአት የሠሩ ሰዎች መርዳት ይችላሉ። ኃጢአት የሠራ አንድ ሰው ወደ ሽማግሌዎች መሄድ ያለበት በያዕቆብ 5:14, 15 ላይ የተሰጠውን መመሪያ ለመታዘዝ ነው።—6/1 ገጽ 31
• ወላጆች የሌላቸው ልጆችና መበለቶች ችግር ላይ ሲወድቁ መርዳት እንደሚገባ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን መርዳት በጥንት ዕብራውያንም ሆነ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ዘንድ እውነተኛው አምልኮ ተለይቶ የሚታወቅበት ምልክት እንደነበር የታሪክ መዝገብ ያሳያል። (ዘጸአት 22:22, 23፤ ገላትያ 2:9, 10፤ ያዕቆብ 1:27) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ችግር ላይ የወደቁ መበለቶችን እንዲረዱ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ግልጽ መመሪያ አስቀምጧል። (1 ጢሞቴዎስ 5:3-16)—6/15 ገጽ 9-11
• ደስተኛና ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት ቁልፉ ምንድን ነው?
የሰማዩ አባታችን ከሆነው ከይሖዋ ጋር ተገቢ የሆነ ዝምድና ማዳበርና ይህንንም ጠብቀን ማቆየት ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይህን እንድናደርግ ያግዘናል።—7/1 ገጽ 4-5
• እያንዳንዱ ሰው ከሞት በኋላ በሕይወት የሚቀጥል መንፈስ አለውን?
አንዳንድ ሰዎች የማይሞተው ነፍስ ሳይሆን መንፈስ ነው ብለው ቢያምኑም መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሐሳብ አይደግፍም። አንድ ሰው ሲሞት ወደ አፈር እንደሚመለስ ይኸውም ከሕልውና ውጪ እንደሚሆን ይናገራል። ይሁን እንጂ ሰውዬውን እንደገና ወደ ሕይወት የመመለስ ችሎታ ያለው አምላክ ስለሆነ ወደፊት በትንሣኤ አማካኝነት ሕይወት የማግኘት ተስፋው የተመካው በአምላክ ላይ ይሆናል። (መክብብ 12:7)—7/15 ገጽ 3-6
• ሦስቱ ዕብራውያን በዱራ ሜዳ በተፈተኑ ጊዜ ዳንኤል የት ነበር?
መጽሐፍ ቅዱስ የት እንደነበረ አይናገርም። ዳንኤል በነበረው ሥልጣን ምክንያት ወደዚያ እንዲሄድ ሳይገደድ ቀርቶ ወይም ደግሞ በመንግሥት ሥራ ምክንያት ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ለይሖዋ ታማኝ ከመሆን ዝንፍ እንዳላለ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—8/1 ገጽ 31