በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘እስከ መጨረሻው ጸንቷል’

‘እስከ መጨረሻው ጸንቷል’

‘እስከ መጨረሻው ጸንቷል’

ላይመን አሌክሳንደር ስዊንግል በይሖዋ ምሥክሮች ዋናው መሥሪያ ቤት ለሚሠሩ አዳዲስ አባላት በ1993 በቪዲዮ በቀረበ ትምህርት ላይ “እስከ መጨረሻዋ እስትንፋስ ድረስ አገልግሉ!” በማለት ይሖዋን ስለማገልገል የሚሰማውን ስሜት ገልጿል።

የዘጠና ዓመት ዕድሜ ባለ ጸጋ የነበረው ወንድም ስዊንግል ሌሎች እንዲያደርጉ ያበረታታውን ነገር እሱ ራሱ አድርጓል። ‘እስከ መጨረሻው ጸንቷል።’ (ማቴዎስ 24:​13) ምንም እንኳ በጠና ታምሞ የነበረ ቢሆንም አባል የሆነበት የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ረቡዕ መጋቢት 7 ዕለት ባደረገው ስብሰባ ላይ ተገኝቷል። በቀጣዩ ማክሰኞ ሕመሙ በጣም የባሰበት ሲሆን መጋቢት 14 ከሌሊቱ 10:​26 ላይ መሞቱን ዶክተሩ አስታውቋል።

ላይመን ስዊንግል ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ዋና መሥሪያ ቤት ማገልገል የጀመረው ሚያዝያ 5, 1930 ነው። ሰባ አንድ ለሚያክሉ ዓመታት በዚያ አገልግሏል። ወንድም ስዊንግል መጀመሪያ በመጽሐፍ መጠረዣ ክፍል ከዚያም ጽሑፍ ማተሚያ ክፍል የተመደበ ሲሆን በተጨማሪም ቀለም መበጥበጫ ክፍል ውስጥ ይሠራ ነበር። እንዲያውም ወንድም ስዊንግል በቀለም መበጥበጫ ክፍል ውስጥ 25 ለሚያክሉ ዓመታት ሠርቷል። እንዲሁም በዋናው መሥሪያ ቤት የጽሑፍ ዝግጅት ክፍል አባል በመሆን 20 ለሚያክሉ ዓመታት አገልግሏል። የሕይወቱን የመጨረሻ 17 ዓመታት በገንዘብ ያዥ ቢሮ ውስጥ ሠርቷል።

ወንድም ስዊንግል ደፋር የአምላክ መንግሥት ሰባኪ ነበር። ገና ወጣት እያለ ብሩክሊን ውስጥ እሱና አርተር ዋርዝሌ የሚባል አብሮት የሚኖር ጓደኛው በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጀልባ በሃድሰን ወንዝ ላይ ይጓዙ ነበር። የድምፅ ማጉያ መሣሪያዎች በመጠቀም በወንዙ ዳር ዳር ለሚኖሩ ሕዝቦች የመንግሥቱን መልእክት እየሰበኩ ብዙ ቅዳሜና እሁዶችን ያሳልፉ ነበር።

ወንድም ስዊንግል ኅዳር 6, 1910 በሊንከን ኔብራስካ ተወለደ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ቤተሰቡ ወደ ሶልት ሌክ ሲቲ ዩታ ተዛወረ። እዚያም በ1913 ወላጆቹ በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች ይጠሩበት እንደነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሆኑ። የስዊንግል ቤተሰብ ለብዙ ዓመታት ብሩክሊን ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚመጡ ብዙ ጎብኚ ተናጋሪዎች ተቀብሎ ያስተናገደ ሲሆን እነዚህ ወንዶች በስዊንግል ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድረውበታል። በ1923 በ12 ዓመቱ ራሱን ለአምላክ መወሰኑን ለማሳየት ተጠመቀ።

ወንድም ስዊንግል ሳያገባ ከ26 ለሚበልጡ ዓመታት ብሩክሊን በሚገኘው ቤቴል ካገለገለ በኋላ ሰኔ 8, 1956 ያገባት ክሪስትል ዘርቸር ለሕይወቱ ቅመም ሆናለት ነበር። ክሪስትል በ1998 እስከ ሞተችበት ጊዜ ድረስ በአገልግሎት አብረው በመካፈል ምንግዜም አይነጣጠሉም ነበር። ክሪስትል ከመሞቷ ከሦስት ዓመት በፊት በአንጎሏ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት የአካል ጉዳተኛ ሆነች። ወንድም ስዊንግል እሷን ለማስታመም በየዕለቱ የሚያደርገው ጥረት ለሚያውቋቸው ሁሉ በተለይ ደግሞ ክሪስትል በአቅራቢያው በሚገኘው የእግረኞች መንገድ ላይ ለሚተላለፉ ሰዎች መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንድታበረክት ተሽከርካሪ ወንበሯን በፍቅር ሲገፋ ለሚመለከቱ ሰዎች ግሩም የታማኝነት ምሳሌ ነው።

ወንድም ስዊንግል የሚያውቁት ሁሉ እንዲወዱት የሚያደርግ ባሕርይ ያለው ግልጽና አሳቢ ሰው ነበር። እሱም እንደ አባቱና እንደ እናቱ በሰማይ በተቋቋመው መንግሥት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የመኖር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋ አለው። በአሁኑ ጊዜ ይህ ተስፋው እንደተፈጸመለት እርግጠኞች ነን።​—⁠1 ተሰሎንቄ 4:​15-18፤ ራእይ 14:​13

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድም ስዊንግል በቀለም መበጥበጫ ክፍል ውስጥ 25 ለሚያክሉ ዓመታት አገልግሏል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስዊንግል እና ክሪስትል አይነጣጠሉም ነበር