የማይታየውን እንደሚታይ አድርጋችሁ ጽኑ!
የማይታየውን እንደሚታይ አድርጋችሁ ጽኑ!
“[ሙሴ] የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና።”—ዕብራውያን 11:27
1. ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ አምላክን በተመለከተ ምን ትኩረት የሚስብ ነገር ተናገረ?
ይሖዋ የማይታይ አምላክ ነው። ሙሴ ክብሩን ለማየት በጠየቀ ጊዜ ይሖዋ “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም” በማለት መልሶለታል። (ዘጸአት 33:20) እንዲሁም ሐዋርያው ዮሐንስ “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም” በማለት ጽፏል። (ዮሐንስ 1:18) ኢየሱስ እንኳ ሰው ሆኖ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አምላክን ማየት አይችልም ነበር። ይሁን እንጂ በተራራ ስብከቱ ላይ ኢየሱስ “ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፣ እግዚአብሔርን ያዩታልና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:8) እንዲህ ብሎ ሲናገር ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር?
2. አምላክን በሰብዓዊ ዓይናችን ልናየው የማንችለው ለምንድን ነው?
2 ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋ መንፈስ እንደሆነና በዚህም የተነሳ ሊታይ እንደማይችል ይገልጻሉ። (ዮሐንስ 4:24፤ ቆላስይስ 1:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:17) በመሆኑም ኢየሱስ በሰብዓዊ ዓይናችን ይሖዋን ማየት እንደምንችል አድርጎ መናገሩ አልነበረም። እርግጥ ነው፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ፍጥረታት ሆነው ትንሣኤ ካገኙ በኋላ በሰማይ ይሖዋ አምላክን ያዩታል። ይሁን እንጂ ‘ልበ ንጹሕ’ የሆኑና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎችም አምላክን ‘ማየት’ ይችላሉ። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
3. ሰዎች አንዳንዶቹን የአምላክን ባሕርያት ማስተዋል የሚችሉት እንዴት ነው?
3 የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች በጥንቃቄ በመመልከት ስለ እርሱ ልንማር የምንችለው ነገር አለ። ይህም በኃይሉ እንድንደነቅና ፈጣሪ አምላክ እንደሆነ አድርገን እንድንቀበለው ሊገፋፋን ይችላል። (ዕብራውያን 11:3፤ ራእይ 4:10, 11) ይህን በማስመልከት ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና።” (ሮሜ 1:20) ስለዚህ ኢየሱስ አምላክን ስለማየት የተናገራቸው ቃላት የይሖዋን አንዳንድ ባሕርያት የመገንዘብ ችሎታን የሚጨምር ነው። እንዲህ ያለው የማየት ችሎታ በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ‘በልብ ዓይኖች’ አማካኝነት የሚከናወን መንፈሳዊ ማስተዋል ነው። (ኤፌሶን 1:18) ኢየሱስ የተናገራቸውና ያደረጋቸው ነገሮችም ስለ አምላክ ብዙ ይናገራሉ። በዚህም የተነሳ ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:9) ኢየሱስ የይሖዋን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። ስለዚህ የኢየሱስን ሕይወትና ትምህርቶች ማወቅ የአምላክን አንዳንድ ባሕርያት እንድናይ ወይም እንድናስተውል ይረዳናል።
መንፈሳዊነት ወሳኝ ነው
4. በዛሬው ጊዜ ብዙዎች መንፈሳዊነት እንደሚጎድላቸው የታየው እንዴት ነው?
4 በዛሬው ጊዜ እምነትና እውነተኛ መንፈሳዊነት በአብዛኛው ጠፍተዋል። ጳውሎስ ‘እምነት ለሁሉ አይደለም’ በማለት ተናግሯል። (2 ተሰሎንቄ 3:1, 2) ብዙዎች ሙሉ በሙሉ የግል ጉዳዮችን በማሳደድ ተግባር የተዋጡ ከመሆናቸውም በላይ በአምላክ ላይ እምነት የላቸውም። የኃጢአተኝነት አኗኗራቸውና መንፈሳዊነት የጎደላቸው መሆናቸው አምላክን በማስተዋል ዓይናቸው እንዳያዩት ይጋርዳቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስም “ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም” ሲል ጽፏል። (3 ዮሐንስ 11) እንደነዚህ ያሉት ሰዎች አምላክን በሰብዓዊ ዓይናቸው ስለማያዩት አድራጎታቸውን ሁሉ እንደማያይ አድርገው ያስባሉ። (ሕዝቅኤል 9:9) መንፈሳዊ ነገሮችን ስለሚንቁ ‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት አይችሉም። (ምሳሌ 2:5) ጳውሎስ “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም” ብሎ መጻፉ ትክክል ነው።—1 ቆሮንቶስ 2:14
5. መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ምን ነገር ይገነዘባሉ?
5 ይሁን እንጂ መንፈሳዊ አመለካከት ካለን ምንም እንኳ ይሖዋ ስህተት የሚፈላልግ አምላክ ባይሆንም መጥፎ አስተሳሰቦችንና ምኞቶችን የሚያውቀው ገና በውስጣችን ማቆጥቆጥ ሲጀምሩ እንደሆነ እንገነዘባለን። በእርግጥም፣ “የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና፣ አካሄዱንም ሁሉ እርሱ ይመለከታልና።” (ምሳሌ 5:21) በኃጢአት ብንሸነፍ እንኳ ይሖዋን ስለምንወድደውና እርሱን ማሳዘን ስለማንፈልግ ንስሐ ገብተን ምሕረት እንዲያደርግልን እንጠይቀዋለን።—መዝሙር 78:41፤ 130:3
እንድንጸና የሚያደርገን ምንድን ነው?
6. ጽኑ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?
6 ምንም እንኳ ይሖዋን ማየት ባንችልም በእርሱ ፊት የተሰወርን አለመሆናችንን ፈጽሞ አንዘንጋ። እርሱ እንዳለ ማወቃችንና ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ እንደሆነ ጽኑ እምነት ማዳበራችን እንድንጸና ማለትም ለእርሱ ባለን ታማኝነት የማንወላውልና ከአቋማችን ፍንክች የማንል እንድንሆን ይረዳናል። (መዝሙር 145:18) ጳውሎስ “የንጉሡን ቊጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና” ሲል እንደጻፈለት እንደ ሙሴ ልንሆን እንችላለን።—ዕብራውያን 11:27
7, 8. ሙሴ በፈርዖን ፊት በድፍረት እንዲቀርብ ያደረገው ማን ነው?
7 ሙሴ እስራኤላውያንን እየመራ ከግብፅ ባርነት ነፃ እንዲያወጣ አምላክ የሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ሲል በሃይማኖት መሪዎችና በጦር ኃይል ሹማምንቶች በተከበበው በጨካኙ ፈርዖን ፊት ለመቅረብ በተደጋጋሚ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሄዶ ነበር። የቤተ መንግሥቱ ግድግዳዎች በጣዖት የተሞሉ እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ የማይታይ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ የግብፅን በድን አማልክት ከሚወክሉት ጣዖታት ይልቅ ለሙሴ እውን ነበር። ሙሴ ፈርዖንን አለመፍራቱ ሊያስገርመን አይገባም!
8 ሙሴ በተደጋጋሚ ጊዜ ፈርዖን ፊት እንዲቀርብ ድፍረት የሰጠው ምንድን ነው? ቅዱሳን ጽሑፎች “ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ” በማለት ይነግሩናል። (ዘኁልቁ 12:3) ሙሴ የነበረው ጠንካራ መንፈሳዊነትና አምላክ ከእርሱ ጋር እንዳለ የነበረው እምነት ‘የማይታየውን አምላክ’ ወክሎ ጨካኝ በነበረው የግብፁ ንጉሥ ፊት ለመቅረብ የሚያስችል ጥንካሬ ሰጥቶታል። የማይታየውን አምላክ “የሚያዩ” ሰዎች በዛሬው ጊዜ እምነታቸውን የሚያሳዩባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
9. በጽናት መቀጠል የምንችልበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?
9 እምነት የምናሳይበትና የማይታየውን እንደሚታይ አድርገን መጽናት የምንችልበት አንደኛው መንገድ ስደት እያለም ቢሆን በድፍረት በመስበክ ነው። ኢየሱስ “በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስጠንቅቋል። (ሉቃስ 21:17) በተጨማሪም “ባርያ ከጌታው አይበልጥም . . . እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:20) ልክ ኢየሱስ እንደተናገረው እርሱ ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ተከታዮቹ በማስፈራራት፣ በእስራትና በድብደባ ስደት ደርሶባቸዋል። (ሥራ 4:1-3, 18-21፤ 5:17, 18, 40) የኢየሱስ ሐዋርያትና ሌሎች ደቀ መዛሙርት በስደት ማዕበል ውስጥ እያሉም እንኳ ምሥራቹን በድፍረት ከመስበክ ፈጽሞ ወደኋላ አላሉም።—ሥራ 4:29-31
10. በይሖዋ ጥበቃ ላይ መተማመናችን በአገልግሎቱ የሚረዳን እንዴት ነው?
10 እንደ ሙሴ ሁሉ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ተከታዮችም በሚታዩ በርካታ ጠላቶች ምክንያት አልፈሩም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በአምላክ ላይ እምነት ስለ ነበራቸው የደረሰባቸውን ከባድ ስደት መቋቋም ችለዋል። አዎን፣ የማይታየውን እንደሚታይ አድርገው ጸንተዋል። ዛሬም የይሖዋ ጥበቃ እንዳለን ሁልጊዜ ማስታወሳችን በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ያለ አንዳች ፍርሃት በድፍረት እንድንካፈል ይረዳናል። የአምላክ ቃል “ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 29:25) በዚህም የተነሳ ስደት ይደርስብናል ብለን በመፍራት ወደኋላ አንልም፤ ወይም በአገልግሎታችን አናፍርም። ያለን እምነት ለጎረቤቶቻችን፣ ለሥራ ባልደረቦቻችን፣ ለትምህርት ቤት ጓደኞቻችንና ለሌሎች ሰዎች በድፍረት እንድንመሰክር ያነሳሳናል።—ሮሜ 1:14-16
የማይታየው አምላክ ሕዝቡን ይመራል
11. ጴጥሮስና ይሁዳ በተናገሩት መሠረት ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ይተባበሩ የነበሩ አንዳንዶች መንፈሳዊነት እንደሚጎድላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?
11 እምነት ምድራዊ ድርጅቱን የሚመራው ይሖዋ መሆኑን እንድናስተውል ይረዳናል። ስለዚህ በጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙትን ከመንቀፍ እንርቃለን። ሐዋርያው ጴጥሮስና የኢየሱስ ግማሽ ወንድም ይሁዳ በክርስቲያኖች መካከል ግንባር ቀደም ሆነው በሚያገለግሉት ወንዶች ላይ የስድብ ቃል የሚናገሩትን መንፈሳዊነት የጎደላቸው አንዳንድ ሰዎች በማስጠንቀቅ ጽፈዋል። (2 ጴጥሮስ 2:9-12፤ ይሁዳ 8) እነዚህ ስህተት የሚለቃቅሙ ሰዎች ይሖዋ በሰብዓዊ ዓይን የሚታይ ቢሆን ኖሮ በእርሱ ፊት ተመሳሳይ ነገር ያደርጉ ነበር? እንደማያደርጉት የታወቀ ነው! ሆኖም አምላክ የማይታይ በመሆኑ ምክንያት ሥጋዊ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው እነዚህ ሰዎች በእርሱ ፊት ተጠያቂ መሆናቸውን መገንዘብ ሳይችሉ ቀሩ።
12. በጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው ለሚሠሩት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
12 ክርስቲያን ጉባኤ የተገነባው ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች መሆኑ እሙን ነው። ሽማግሌ ሆነው የሚያገለግሉት ወንድሞች አልፎ አልፎ እኛን በግለሰብ ደረጃ ሊነካን የሚችል ስህተት ይሠሩ ይሆናል። የሆነ ሆኖ፣ ይሖዋ እነዚህን ሰዎች መንጋውን ለመንከባከብ ይጠቀምባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:1, 2) መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ይሖዋ ሕዝቡን የሚመራበት አንደኛው መንገድ ይህ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ስለዚህ ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ከነቀፋና ከማማረር መንፈስ እንርቃለን እንዲሁም ለአምላክ ቲኦክራሲያዊ አደረጃጀት አክብሮት እንዳለን እናሳያለን። በመካከላችን ግንባር ቀደም ሆነው ለሚሠሩት ታዛዥ በመሆን የማይታየውን እንደምናየው አድርገን እንደምናምን እናሳያለን።—ዕብራውያን 13:17
አምላክን እንደ ታላቅ አስተማሪያችን አድርጎ መመልከት
13, 14. ይሖዋን እንደ ታላቅ አስተማሪ አድርጎ መመልከት ለአንተ ምን ማለት ነው?
13 መንፈሳዊ ማስተዋል ማሳየት የሚጠይቅ ሌላም መስክ አለ። ኢሳይያስ “ዓይኖችህ ግን [“ታላቅ፣” NW ] አስተማሪህን ያያሉ” በማለት ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 30:20) በምድራዊ ድርጅቱ በኩል እያስተማረን ያለው ይሖዋ እንደሆነ አድርጎ መቀበል እምነት ይጠይቃል። (ማቴዎስ 24:45-47) አምላክን እንደ ታላቅ አስተማሪ አድርጎ መመልከት ማለት ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልማድ ማዳበርና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ማለት ብቻ አይደለም። በአምላክ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ መጠቀም ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በመንፈሳዊ ከመወሰድ መጠበቅ እንችል ዘንድ ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ለሚያቀርብልን መመሪያ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል።—ዕብራውያን 2:1
14 ከሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ ሙሉ ተጠቃሚ መሆን እንችል ዘንድ አንዳንድ ጊዜ ልዩ ጥረት ማድረግ ሊጠይቅብን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ለመረዳት አስቸጋሪ ሆነው ያገኘናቸውን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንዲሁ ገረፍ ገረፍ አድርገን አንብበን ብቻ ማለፍ ይቀናን ይሆናል። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በምናነብበት ጊዜ ርዕሰ ጉዳዩ በተለይ የእኛን ትኩረት የማይስብ ሆኖ ካገኘነው አንዳንድ ርዕሶችን ሳናነብ እንዘል ይሆናል። ወይም በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ተገኝተን ዝም ብለን ሐሳባችን እንዲባዝን እንፈቅድ ይሆናል። ይሁን እንጂ ትኩረት ሰጥተን እየተብራሩ ባሉት ነጥቦች ላይ የምናስብ ከሆነ በንቃት መከታተል እንችላለን። ለምናገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ጥልቅ አድናቆት ማዳበራችን ይሖዋን እንደ ታላቅ አስተማሪያችን አድርገን እንደተቀበልነው ያሳያል።
መልስ እንሰጣለን
15. አንዳንዶች ይሖዋ እንደማያያቸው አድርገው እንደሚያስቡ ያሳዩት እንዴት ነው?
15 በተለይ በዚህ ‘የፍጻሜ ዘመን’ ክፋት በጣም በመስፋፋቱ ምክንያት በማይታየው አምላክ ላይ እምነት ማሳደር እጅግ ወሳኝ ነው። (ዳንኤል 12:4) እምነት ማጉደልና የጾታ ብልግና በእጅጉ ተስፋፍቶ ይገኛል። ሰዎች ሊያዩን በማይችሉበት ጊዜ እንኳ ይሖዋ እያንዳንዱን ድርጊታችንን እንደሚመለከት ማስታወሱ ጥበብ ነው። አንዳንዶች ይህን ሃቅ ዘንግተዋል። ሰዎች በማያዩአቸው ጊዜ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ጎጂ የሆኑ መዝናኛዎችንና በኢንተርኔት፣ በቴሌቪዥን እንዲሁም በሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት የሚተላለፉ ወሲባዊ ምስሎችን በመመልከት ረገድ የገጠማቸውን ፈተና መቋቋም ሳይችሉ ቀርተዋል። እነዚህን ድርጊቶች የሚፈጽሙት ማንም ሰው ሳያያቸው በስውር በመሆኑ አንዳንዶች ድርጊታቸው በይሖዋ ፊት የተሰወረ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ።
16. ይሖዋ ካወጣቸው ከፍ ካሉት የአቋም ደረጃዎቹ ጋር ተስማምተን እንድንኖር ምን ነገር ሊረዳን ይገባል?
16 ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ማስታወሱ ጥሩ ነው። (ሮሜ 14:12) ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ኃጢአቱን የምንፈጽመው በይሖዋ ላይ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። ይህን ማወቃችን ከፍ ካሉት የአቋም ደረጃዎቹ ጋር ተስማምተን እንድንኖርና ርኩስ ከሆኑ ድርጊቶች እንድንርቅ ሊረዳን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ያሳስበናል:- “እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ፣ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።” (ዕብራውያን 4:13) በእርግጥም፣ ለይሖዋ መልስ እንሰጣለን፤ ሆኖም የእርሱን ፈቃድ የምናደርግበትና ጻድቅ ከሆኑት የአቋም ደረጃዎቹ ጋር ተስማምተን የምንኖርበት ዋነኛው ምክንያት ለይሖዋ ፍቅር ስላለን ነው። ስለዚህ በመዝናኛ ምርጫችንና ከተቃራኒ ጾታ ጋር በምናሳየው ጠባይ ረገድ አስተዋዮች እንሁን።
17. ይሖዋ እኛን የሚመለከተን ከምን አንጻር ነው?
17 ይሖዋ የእኛን ሁኔታ አንድ በአንድ ይከታተላል፤ ያ ማለት ግን እኛን ለመቅጣት ስህተት እስክንሠራ ድረስ ይጠብቃል ማለት አይደለም። ከዚያ ይልቅ ታዛዥ ለሆኑ ልጆቹ ወሮታ ለመክፈል እንደሚፈልግ አባት በፍቅራዊ አሳቢነት ይመለከተናል ማለት ነው። የሰማዩ አባታችን በምናሳየው እምነት እንደሚደሰትና ‘ለሚፈልጉትም ዋጋ እንደሚሰጥ’ ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! (ዕብራውያን 11:6) ስለዚህ በይሖዋ ላይ ፍጹም እምነት ይኑረን እንዲሁም ‘በፍጹም ልብ እናገልግለው።’—1 ዜና መዋዕል 28:9
18. ይሖዋ የሚመለከተንና ታማኝነታችንን የማይረሳ መሆኑን ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ማረጋገጫ ይሰጡናል?
18 ምሳሌ 15:3 “የእግዚአብሔር ዓይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፤ ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ” በማለት ይናገራል። አዎን፣ አምላክ ክፉ ሰዎችን ይመለከታል እንዲሁም እንደ ሥራቸው ይከፍላቸዋል። ይሁን እንጂ “ደጎች” ከተባሉት መካከል የምንገኝ ከሆነ ይሖዋ እያንዳንዱን በታማኝነት የምንፈጽመውን ድርጊት እንደሚመለከት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ‘ድካማችን በጌታ ከንቱ እንደማይሆንና’ የማይታየው አምላክ ‘ያደረግነውን ሥራ ለስሙም ያሳየነውን ፍቅር የማይረሳ’ መሆኑን ማወቁ ምንኛ እምነት የሚያጠነክር ነው!—1 ቆሮንቶስ 15:58፤ ዕብራውያን 6:10
ይሖዋ እንዲመረምረን መፍቀድ
19. በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት መገንባት የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
19 ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን በእርሱ ፊት ውድ ነን። (ማቴዎስ 10:29-31) አምላክ የማይታይ ቢሆንም እንኳ እውን ሊሆንልን ይችላል፤ እንዲሁም ከእርሱ ጋር የመሠረትነውን ውድ ዝምድና ከፍ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን። ለሰማዩ አባታችን እንዲህ ያለ አመለካከት ማዳበራችን በርካታ ጥቅሞችን ያስገኝልናል። ያዳበርነው ጠንካራ እምነት በይሖዋ ፊት ንጹሕ ልብና በጎ ሕሊና እንዲኖረን ይረዳናል። ግብዝነት የሌለበት እምነት ሁለት ዓይነት ኑሮ ከመምራት ይጠብቀናል። (1 ጢሞቴዎስ 1:5, 18, 19) በአምላክ ላይ የማይናወጥ እምነት ማዳበራችን በአካባቢያችን ላሉ ሰዎች ጥሩ ምሳሌ ሊሆንና አዎንታዊ ተጽዕኖም ሊያሳድር ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:11, 12) ከዚህም በላይ እንዲህ ያለው እምነት አምላካዊ አኗኗር እንዲኖረን ስለሚያደርግ የይሖዋን ልብ ያስደስታል።—ምሳሌ 27:11
20, 21. (ሀ) የይሖዋ ዓይኖች በእኛ ላይ መሆናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) መዝሙር 139:23, 24ን በእኛ ላይ እንዲሠራ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
20 እኛ በእርግጥ ጥበበኞች ከሆንን ይሖዋ ሁልጊዜ እንደሚመለከተን ማወቃችን ያስደስተናል። ይሖዋ እንዲመለከተን ብቻ ሳይሆን አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን አንድ በአንድ እንዲመረምርም እንፈልጋለን። ይሖዋ እንዲመረምረንና በውስጣችን ተገቢ ያልሆነ ዝንባሌ መኖር አለመኖሩን እንዲመለከት በጸሎት ብንጠይቀው እንጠቀማለን። ችግሮቻችንን መቋቋም እንድንችልና አስፈላጊ የሆኑ ማስተካከያዎችን እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። መዝሙራዊው ዳዊት እንደሚከተለው ብሎ መዘመሩ የተገባ ነው:- “አቤቱ፣ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ ፍተነኝ መንገዴንም እወቅ፤ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፤ የዘላለምንም መንገድ ምራኝ።”—መዝሙር 139:23, 24
21 ዳዊት በውስጡ ‘በደል’ ያለ መሆኑን እንዲያይ ይሖዋ እንዲመረምረው ተማጽኗል። እኛም እንደ መዝሙራዊው አምላክ ልባችንን እንዲመረምርና በውስጣችን ተገቢ ያልሆነ አስተሳሰብ ያለ መሆን አለመሆኑን እንዲመለከት መጓጓት አይኖርብንም? ስለዚህ እንዲመረምረን ይሖዋን በእምነት እንጠይቅ። ይሁን እንጂ አንድ ዓይነት ስህተት በመፈጸማችን ምክንያት የምንጨነቅ ብንሆን ወይም ጎጂ የሆነ አንድ ነገር በውስጣችን ቢኖርብን ምን እናደርጋለን? እንደዚያ ከሆነ አፍቃሪ ወደሆነው አምላካችን ወደ ይሖዋ አምርረን መጸለያችንን እንቀጥል፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱሱ የሚሰጠንን መመሪያና በቃሉ ውስጥ የሰፈረውን ምክሩን በትሕትና እንታዘዝ። እርዳታ እንደሚሰጠን እርግጠኞች ልንሆንና የዘላለም ሕይወት በሚያስገኘው ጎዳና መጓዛችንን እንድንቀጥል እንደሚረዳን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—መዝሙር 40:11-13
22. የማይታየውን አምላክ በተመለከተ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?
22 አዎን፣ ይሖዋ ብቃቶቹን የምናሟላ ከሆነ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርከናል። እርግጥ ነው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን” በማለት እንዳረጋገጠው ኃይሉንና ሥልጣኑን መቀበል ይገባናል። (1 ጢሞቴዎስ 1:17) ለይሖዋ ሁልጊዜ እንዲህ የመሰለ ከልብ የመነጨ አክብሮት እናሳይ። ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን የማይታየውን እንደምናየው አድርገን ለመጽናት ካደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ፈጽሞ ንቅንቅ አንበል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ሰዎች አምላክን ሊያዩ የሚችሉት እንዴት ነው?
• ይሖዋ እውን ከሆነልን ስደት በሚያጋጥመን ጊዜ ምን እናደርጋለን?
• ይሖዋን እንደ ታላቅ አስተማሪያችን አድርጎ ማየት ሲባል ምን ማለት ነው?
• ይሖዋ እንዲመረምረን መፈለግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴ ፈርዖንን ሳይፈራ የማይታየውን አምላክ ይሖዋን እንደሚያየው አድርጎ ተመላልሷል
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ የምናደርገውን ሁሉ ሊያይ እንደማይችል አድርገን ፈጽሞ አናስብ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክን እንደ ታላቅ አስተማሪያችን አድርገን ስለምንመለከተው የእርሱን እውቀት ለማግኘት እንጣጣራለን