ምንም ዓይነት አስተዳደግ ይኑርህ ስኬታማ መሆን ትችላለህ
ምንም ዓይነት አስተዳደግ ይኑርህ ስኬታማ መሆን ትችላለህ
ኒኮላስ ከልጅነቱ ጀምሮ የዓመፀኝነት ዝንባሌ ነበረው። a ከጊዜ በኋላ በውስጡ የሚረብሸውን ስሜት ለመቋቋም ሲል አደገኛ ዕፆችን መውሰድና አልኮል በብዛት መጠጣት ጀመረ። ኒኮላስ “አባቴ የመጠጥ ሱሰኛ ነበር፤ ይህም እኔንና እህቴን ለብዙ ስቃይ ዳርጎናል” ሲል ተናግሯል።
የማሊንዳ ወላጆች ከውጭ ለሚያያቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ የተከበሩ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ናቸው። ሆኖም በአንድ የኑፋቄ ቡድን ውስጥ በንቃት ይሳተፉ ነበር። አሁን በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው ማሊንዳ ወላጆቼ “የሚያደርጓቸው አንዳንድ ነገሮች በጣም የሚያስጸይፉ ነበሩ። እነዚህ ነገሮች ገና በልጅነቴ አእምሮዬን መርዘውብኛል” በማለት ሐዘኗን ገልጻለች። አክላም “ነፍስ ካወቅኩበት ጊዜ አንስቶ የሚሰማኝ የተስፋ ቢስነትና የከንቱነት ስሜት እስከ አሁን ድረስ አብሮኝ አለ።”
ዓመፅ፣ በደል፣ የወላጅ እንክብካቤ ማጣትና ይህን የመሰሉ ሌሎች አሉታዊ ተጽእኖዎች በብዙዎች የልጅነት ሕይወት ላይ ጠባሳ ጥለው ማለፋቸውን ማን ሊክድ ይችላል? መጥፎ የልጅነት ሕይወት የሚያስከትለው ቁስል ሥር የሰደደ ሊሆን ይችላል። ሆኖም እንዲህ ያለው ቁስል አንድ ሰው የአምላክን ቃል እውነት እንዳይቀበልና በተወሰነ ደረጃ ደስታ እንዳያገኝ ያግደዋል ማለት ነው? ኒኮላስና ማሊንዳ ጥሩ አስተዳደግ ባይኖራቸው እንኳ ጽኑ አቋም በመጠበቅ ረገድ ይሳካላቸው ይሆን? እስቲ በመጀመሪያ የይሁዳን ንጉሥ የኢዮስያስን ምሳሌ ተመልከት።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ
ኢዮስያስ በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ (659-629 ከዘአበ) ይሁዳን ለ31 ዓመታት ገዝቷል። ኢዮስያስ በሰው ተገድሎ በሞተው በአባቱ ምትክ ዙፋን ላይ በተቀመጠ ጊዜ በይሁዳ ያለው ሁኔታ እጅግ መጥፎ ነበር። ይሁዳና ኢየሩሳሌም በዓልን በሚያመልኩና የአሞናውያን ዋነኛ አምላክ በሆነው በሚልኮም በሚምሉ ሰዎች ተሞልተው ነበር። በዚያ ዘመን የአምላክ ነቢይ የነበረው ሶፎንያስ የይሁዳን አለቆች “እንደሚያገሱ አንበሶች” ፈራጆችዋንም “እንደማታ ተኩላዎች” አድርጎ ገልጿቸዋል። በዚህም የተነሣ ዓመፅና ማታለል በምድሪቱ በእጅጉ ተስፋፍተው ነበር። ብዙዎች በልባቸው “እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፣ ክፉም አያደርግም” ይሉ ነበር።—ሶፎንያስ 1:3–2:3፤ 3:1-5
ኢዮስያስ ምን ዓይነት ንጉሥ ይወጣው ይሆን? ዕዝራ የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል:- “[ኢዮስያስ] በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፣ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም።” (2 ዜና መዋዕል 34:1, 2) ኢዮስያስ በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ ረገድ እንደተሳካለት ከዚህ ለመረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ያደገበት ቤተሰብ ምን ይመስል ነበር?
ጥሩ ወይስ መጥፎ ዓይነት አስተዳደግ?
ኢዮስያስ በ667 ከዘአበ ሲወለድ አባቱ አሞጽ 16 ዓመቱ ነበር። አያቱ ምናሴ ደግሞ ይሁዳን ይገዛ ነበር። ምናሴ በይሁዳ ከነገሡት ሁሉ እጅግ ክፉ ንጉሥ ነበር። ለበዓል መሠዊያ በመሥራት “በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።” ልጆቹን በእሳት አሳልፏል፣ ሞራ ገላጭ ሆኗል፣ አስማትና መተትን አድርጓል፣ የመናፍስት ሥራዎችን አስፋፍቷል እንዲሁም እጅግ ብዙ ንጹህ ደም አፍስሷል። በተጨማሪም የማምለኪያ አፀድ ምስል ሠርቶ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ አቁሟል። ምናሴ “እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ” ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አስቷል።—2 ዜና መዋዕል 33:1-9
ይሖዋ፣ ምናሴ በጣም መጥፎ ከመሆኑ የተነሳ በሰንሰለት ታስሮ የአሦራውያን ነገሥታት መቀመጫ ከሆኑት ከተሞች አንዷ ወደሆነችው ወደ ባቢሎን እንዲወሰድ አድርጓል። ምናሴ በግዞት ሳለ ንስሐ በመግባትና ራሱን ዝቅ በማድረግ ይቅር እንዲለው ይሖዋን ተማጸነ። 2 ዜና መዋዕል 33:10-17
ይሖዋም ልመናውን በመስማት ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ንግሥናው መልሶታል። ከዚያም ምናሴ ባካሄደው ተሃድሶ አንዳንድ መልካም ውጤቶችን አግኝቷል።—የምናሴ መጥፎ ምግባርና ከዚያም ያሳየው የንስሐ መንፈስ በልጁ በአሞጽ ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ አሳድሮ ይሆን? አሞጽ በጣም ክፉ ሆነ። ምናሴ ንስሐ ገብቶ ቀደም ሲል በሕዝቡ ላይ ያመጣውን ርኩሰት ለማጥራት ጥረት ቢያደርግም ልጁ አሞጽ ምንም ዓይነት አዎንታዊ ምላሽ አልሰጠም። አሞጽ በ22 ዓመቱ ንግሥናውን በጨበጠ ጊዜ “አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።” በይሖዋ ፊት ራሱን ከማዋረድ ይልቅ “መተላለፉን እጅግ አበዛ።” (2 ዜና መዋዕል 33:21-23) አሞጽ የይሁዳ ንጉሥ ሲሆን ኢዮስያስ ገና የስድስት ዓመት ልጅ ነበረ። ኢዮስያስ በጣም አስከፊ የልጅነት ሕይወት አሳልፎ መሆን አለበት!
አሞጽ ባሪያዎቹ በእርሱ ላይ ተማምለው በገደሉት ጊዜ በክፋት የተሞላው የሁለት ዓመት አገዛዙ አከተመ። ይሁን እንጂ የአገሩ ሕዝብ በአሞጽ ላይ የተማማሉትን ሰዎች ገድለው ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት።—2 ዜና መዋዕል 33:24, 25
ኢዮስያስ በመጥፎ ሁኔታዎች ሥር ቢያድግም በይሖዋ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረጉን ቀጠለ። የንግሥናው ዘመን እጅግ ስኬታማ ከመሆኑ የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይናገርለታል:- “እንደ ሙሴም ሕግ ሁሉ በፍጹም ልቡ በፍጹምም ነፍሱ በፍጹምም ኃይሉ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ ከእርሱ አስቀድሞ አልነበረም፤ እንደ እርሱም ያለ ንጉሥ ከእርሱ በኋላ አልተነሣም።”—2 ነገሥት 23:19-25
በልጅነታቸው አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ላደጉ ግለሰቦች የኢዮስያስ ምሳሌ ምንኛ አበረታች ነው! ከእርሱ ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን? ኢዮስያስ ትክክለኛውን ጎዳና እንዲመርጥና በዚያው ጎዳና መጓዙን እንዲቀጥል የረዳው ምንድን ነው?
ይሖዋን ለማወቅ ጣር
በኢዮስያስ የልጅነት ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ያሳደረው ንስሐ የገባው አያቱ ምናሴ ነበር። 2 ዜና መዋዕል 34:1-3
ሁለቱ ምን ያህል ይቀራረቡ እንደነበረና ምናሴ ንስሐ ሲገባ ኢዮስያስ የስንት ዓመት ልጅ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። አይሁዳውያን ቤተሰቦች በጣም ይቀራረቡ ስለነበር ምናሴ በልጅ ልጁ ልብ ውስጥ ለእውነተኛው አምላክ ለይሖዋና ለቃሉ አክብሮትን በመትከል ዙሪያውን ከከበቡት መጥፎ ተጽእኖዎች ለመጠበቅ ሞክሮ ሊሆን ይችላል። ምናሴ በኢዮስያስ ልብ ውስጥ መትከል የቻለው የእውነት ዘር ምናልባትም ከሌሎች አዎንታዊ ተጽእኖዎች ጋር ተዳምሮ በመጨረሻ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። በይሁዳ ላይ መግዛት በጀመረ በስምንተኛው ዓመት የ15 ዓመቱ ኢዮስያስ የይሖዋን ፈቃድ ለማወቅና ለማድረግ ጥሯል።—አንዳንድ ሰዎች በልጅነታቸው ስለ መንፈሳዊ ነገሮች የማወቅ አጋጣሚ ያገኙት በሩቅ ዘመዳቸው፣ በአንድ በሚያውቁት ሰው ወይም በጎረቤታቸው አማካይነት ነው። ሆኖም በዚህ መንገድ የተዘሩ ዘሮች ከተኮተኮቱ ከጊዜ በኋላ ፍሬ ሊያፈሩ ይችላሉ። ቀደም ብላ የተጠቀሰችው ማሊንዳ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን ቤቷ ድረስ ይዞላት ይመጣ የነበረ አንድ በእድሜ የገፋ ጎረቤት ነበራት። እርሱን ስታስታውስ ፊቷ በደስታ ስሜት ተውጦ እንዲህ አለች:- “በጎረቤቴ ላይ ካየኋቸው ነገሮች መካከል በጣም የነካኝ ነገር በዓላትን የማያከብር መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ለእኔ በጣም አስፈላጊ ነበር። ምክንያቱም ሃሎዊንና ሌሎች በዓላት ወላጆቼ በሚሳተፉበት ኑፋቄ ውስጥ የአምልኮ ሥርዓቶች የሚከናወኑባቸው ወቅቶች ነበሩ።” ከአሥር ዓመታት በኋላ አንድ ጓደኛዋ በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ሲጋብዛት ማሊንዳ ያን ጎረቤቷን በማስታወስ ግብዣውን በደስታ ተቀበለች። ይህም እውነትን እንድትፈልግ ረድቷታል።
በአምላክ ፊት ራስህን አዋርድ
የኢዮስያስ ግዛት በይሁዳ ምድር ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ተሃድሶ የተካሄደበት ወቅት ነበር። ኢዮስያስ የይሁዳን ምድር ከጣዖት አምልኮ ለማጽዳት ስድስት ዓመት የፈጀ ዘመቻ ካካሄደ በኋላ የይሖዋን ቤት ማደሱን ቀጠለ። ቤተ መቅደሱን የማደሱ ሥራ እየተካሄደ ሳለ ሊቀ ካህኑ ኬልቅያስ አንድ ውድ የሆነ ነገር ማለትም “የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ” የመጀመሪያ ቅጂ አገኘ! ጸሐፊው ሳፋን የሕጉን መጽሐፍ ከኬልቅያስ በአደራ ከተቀበለ በኋላ ሁኔታውን ለንጉሡ ሪፖርት አደረገ። ይህ ግኝት የ25 ዓመቱን ኢዮስያስ እንዲኮራ አድርጎት ይሆን?—2 ዜና መዋዕል 34:3-18
ዕዝራ “ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ” በማለት ጽፏል። ይህ ልባዊ የሆነ የሃዘን መግለጫ ነበር። የቀድሞ አባቶቻቸው የአምላክን ሕጎች ሙሉ በሙሉ ሳይታዘዙ እንደቀሩ ተገንዝቦ ነበር። ይህ እንዴት ያለ የትሕትና ምልክት ነው! ወዲያውም ንጉሡ አምስት ሰዎችን ያቀፈ አንድ የልዑክ ቡድን በመላክ በነቢይቱ ሕልዳና በኩል ይሖዋን እንዲጠይቁ አዘዘ። የልዑክ ቡድኑም የሚከተለውን ይዞ ተመለሰ። ‘የይሖዋን ሕግ ሳይታዘዙ በመቅረታቸው ምክንያት ክፉ ነገርን አመጣለሁ። አንተ ግን [ንጉሥ ኢዮስያስ] ራስህን አዋርደሃልና በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ። ክፉ ነገር ሁሉ ዓይኖችህ አያዩም።’ (2 ዜና መዋዕል 34:19-28) ይሖዋ ኢዮስያስ ባሳየው ዝንባሌ ተደስቶ ነበር።
አስተዳደጋችን ምንም ይሁን ምን እኛም በእውነተኛው አምላክ በይሖዋ ፊት ራሳችንን ልናዋርድና ለእርሱና ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዳለን ልናሳይ እንችላለን። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ኒኮላስ ያደረገው ይህንኑ ነበር። እንዲህ ብሏል:- “እወስዳቸው በነበረው አደገኛ ዕፆችና የአልኮል መጠጦች ምክንያት ሕይወቴ ተመሰቃቅሎ የነበረ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስንና የሕይወትን ትርጉም የማወቅ ፍላጎት ነበረኝ። በመጨረሻም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁና ሕይወቴን አስተካክዬ እውነትን ተቀበልኩ።” አዎን፣ በዙሪያችን ያለው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ለአምላክና ለቃሉ አክብሮት ልናሳይ እንችላለን።
ከይሖዋ ዝግጅት ተጠቀም
ኢዮስያስ ለይሖዋ ነቢያትም ጭምር ጥልቅ አክብሮት ነበረው። ነቢይቱን ሕልዳናን መረጃ እንድትሰጠው ከመጠየቁም በላይ በጊዜው የነበሩት ሌሎች ነቢያት የሚናገሩትንም ትኩረት ሰጥቶ ተከታትሏል። ለምሳሌ ያህል፣ ኤርምያስም ሆነ ሶፎንያስ ጣዖት አምላኪ በሆነችው በይሁዳ ላይ የሚወርደውን ቅጣት በማወጁ ሥራ ተጠምደው ነበር። ኢዮስያስ ለመልእክታቸው ትኩረት መስጠቱ የሐሰት አምልኮን ለማጥፋት እየወሰደ ባለው እርምጃ እንዲገፋበት ኃይል ሰጥቶት መሆን አለበት!—ኤርምያስ 1:1, 2፤ 3:6-10፤ ሶፎንያስ 1:1-6
ማቴዎስ 24:45-47) የባሪያው ክፍል በጽሑፎችና በጉባኤ ዝግጅቶች አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች በትኩረት መከታተል የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እንድንገነዘብ ያደርጋል። በተጨማሪም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንዴት ልንሠራባቸው እንደምንችል የሚያሳዩ ተግባራዊ ሐሳቦች ያቀርባል። ማንኛውንም ዓይነት ሥር የሰደደ ጎጂ ባሕርይ ለመዋጋት እንድንችል በይሖዋ ዝግጅቶች መጠቀማችን ምንኛ ተገቢ ነው! ኒኮላስ ከልጅነቱ ጀምሮ ለሥልጣን ከፍተኛ ጥላቻ ነበረው። የአምላክን ቃል እውነት ከተማረ በኋላም ቢሆን ይሖዋን ይበልጥ እንዳያገለግል ይህ ድክመቱ እንቅፋት ሆኖበት ነበር። ይህንን ባሕርይ መለወጥ ቀላል ሆኖ አላገኘውም። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ተሳክቶለታል። እንዴት? “የሰው ስሜት የሚገባቸው ሁለት ሽማግሌዎች ባደረጉልኝ እርዳታ ችግሩ እንዳለብኝ አምኜ የተቀበልኩ ሲሆን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የሰጡኝን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ጀመርኩ።” አክሎም “አልፎ አልፎ ትንሽ በስጨት ብልም አሁን የዓመፀኝነት ባሕርዬን መቆጣጠር ችያለሁ።”
“ጌታው” ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው እንዲያቀርብ ቅቡዕ ተከታዮቹን ያቀፈውን ቡድን ማለትም ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ ሾሟል። (ማሊንዳም ከበድ ያሉ ውሳኔዎች በምታደርግበት ጊዜ የሽማግሌዎችን ምክር ለማግኘት ትጥራለች። ከልጅነቷ ጀምሮ የሚሰማትን የተስፋ ቢስነትና የከንቱነት ስሜት ለመቋቋም በምታደርገው ጥረት በተለይ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ የሚወጡት የተለያዩ ርዕሶች ከፍተኛ እርዳታ አበርክተውላታል። “አንዳንድ ጊዜ በአንድ ርዕስ ውስጥ እኔን የሚነካኝ አንድ አንቀጽ ወይም አንድ ዓረፍተ ነገር አገኛለሁ። እንደነዚህ ያሉትን ርዕሶች ሌላ ጊዜ ቶሎ ማግኘት እንድችል በማስታወሻ ደብተሬ ላይ መጻፍ የጀመርኩት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ነበር።” ዛሬ የማሊንዳ ሦስት የማስታወሻ ደብተሮች 400 የሚያክሉ ርዕሶች ይዘዋል!
ሰዎች መጥፎ የቤተሰብ ሕይወት ያስከተለባቸው ጎጂ ተጽዕኖ ቋሚ ተጠቂዎች መሆን አይኖርባቸውም። በይሖዋ እርዳታ በመንፈሳዊ ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ። ጥሩ አስተዳደግ አንድ ሰው የጸና አቋም እንዲይዝ ዋስትና እንደማይሆነው ሁሉ መጥፎ አስተዳደግም አንድ ሰው አምላክን የሚፈራ እንዳይሆን አያግደውም።
በቤተ መቅደሱ እደሳ ወቅት የሕጉ መጽሐፍ ከተገኘ በኋላ ኢዮስያስ ‘እግዚአብሔርን ተከትሎ ለመሄድ፣ ትእዛዙን በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ለመጠበቅ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ገባ።’ (2 ዜና መዋዕል 34:31) ኢዮስያስ በሞት እስካንቀላፋበት ቀን ድረስ ከዚህ ውሳኔው ፈቀቅ አላለም። ማሊንዳና ኒኮላስም ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ለመቆምና ጽኑ አቋምን በመጠበቅ ረገድ የተሳካላቸው ሰዎች ሆነው ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። አንተም ወደ አምላክ ተጠግተህ ለመኖርና እርሱን በታማኝነት ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። በዚህም እንደሚሳካልህ እርግጠኛ ሁን። ምክንያቱም ይሖዋ እንዲህ በማለት ቃል ገብቷል:- “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፣ እረዳህማለሁ፣ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።”—ኢሳይያስ 41:10, 13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮስያስ በመጥፎ ሁኔታዎች ሥር ቢያድግም ይሖዋን ለማወቅና ሕይወቱን ስኬታማ ለማድረግ ጥረት አድርጓል
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች ያለብህን ሥር የሰደደ የባሕርይ ችግር እንድታሸንፍ ሊረዱህ ይችላሉ
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“መጠበቂያ ግንብ” እና “ንቁ!” ጽኑ አቋምህን ጠብቀህ እንድትኖር ሊረዱህ ይችላሉ