በሕይወቴ ሙሉ የይሖዋ ድጋፍ አልተለየኝም
የሕይወት ታሪክ
በሕይወቴ ሙሉ የይሖዋ ድጋፍ አልተለየኝም
ፎረስት ሊ እንደተናገረው
ፖሊስ በቅርቡ የሸክላ ማጫወቻችንንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ወረሰብን። ተቃዋሚዎች ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው አዲሱ የካናዳ አስተዳዳሪ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ሕገ ወጥ መሆኑን የሚገልጽ ዓዋጅ እንዲያወጡ አሳመኗቸው። ይህ የሆነው ሐምሌ 4, 1940 ነበር።
በተከሰተው ሁኔታ ተስፋ ባለመቁረጥ ተጨማሪ ጽሑፎችን ካስቀመጥንበት አወጣንና ስብከታችንን ቀጠልን። አባባ በዚያ ወቅት “የፈለገው ይምጣ እንጂ መስበካችንን አናቆምም። ይሖዋ እንድንሰብክ አዝዞናል” በማለት የተናገራቸው ቃላት ምንጊዜም አይረሱኝም። በወቅቱ ገና የአሥር ዓመት ጎረምሳ ነበርኩ። ይሁን እንጂ የአባባ ቆራጥነትና ለአገልግሎት የነበረው ቅንዓት አምላካችን ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዴት እንደሚደግፍ ዘወትር ያስታውሰኛል።
በሚቀጥለው ጊዜ ፖሊሶች ሲያስቆሙን ጽሑፎቻችንን መቀማት ብቻ ሳይሆን አራት ልጅ እማማ ላይ ትተው አባባን ወደ እስር ቤት ወሰዱት። ይህ የሆነው መስከረም 1940 በሳስካችዋን ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በመጽሐፍ ቅዱስ በሰለጠነው ሕሊናዬ ምክንያት ለባንዲራ ሰላምታ አልሰጥም ወይም የሕዝብ መዝሙር አልዘምርም በማለቴ ከትምህርት ቤት ተባረርኩ። ትምህርቴን በተልዕኮ መቀጠሌ በራሴ ፕሮግራም እንድመራ ስላስቻለኝ በስብከቱ ሥራ ይበልጥ መካፈል ጀመርኩ።
በ1948 አቅኚዎች (የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች) ወደ ምሥራቃዊ የካናዳ የባሕር ዳርቻ ሄደው እንዲያገለግሉ ጥሪ ቀረበላቸው። ስለዚህ በሃሊፋክስ፣ በኖቫ ስኮሺያ እና የፕሪንስ ኤድዋርድ ደሴት በሆነችው በኬፕ ዎልፍ በአቅኚነት ለማገልገል ወደዚያ ሄድኩ። በቀጣዩ ዓመት ቶሮንቶ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለሁለት ሳምንት እንዳገለግል ተጠራሁ። ከሁለት ሳምንት በኋላ ጊዜው ስለተራዘመልኝ
በቤቴል ከስድስት ለሚበልጡ ዓመታት በአርኪ ሁኔታ አገለገልኩ። በመጨረሻ እንደ እኔ ይሖዋን ከምታፈቅር ሚረን ከምትባል እህት ጋር ተዋወቅኩና ታኅሣሥ 1955 ተጋባን። ሚልተን፣ ኦንታሪዮ ውስጥ መኖር የጀመርን ሲሆን ብዙም ሳንቆይ አዲስ ጉባኤ ተቋቋመ። ምድር ቤታችንን መንግሥት አዳራሽ አደረግነው።አገልግሎታችንን ለማስፋት የነበረን ፍላጎት
በቀጣዮቹ ዓመታት ስድስት ልጆችን ራስ በራስ ወለድን። የመጀመሪያ ልጃችን ሚርያም ስትሆን ቀጥሎ ቻርሜን፣ ማርክ፣ አኔት፣ ግራንትና በመጨረሻም ግሊን ተከታትለው ተወለዱ። ሁልጊዜ ከሥራ ስመለስ ሚረንና ልጆቹ እሳት ዳር ቁጭ ብለው እሷ መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብላቸው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ስትነግራቸው እንዲሁም በልባቸው ውስጥ ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር ለመትከል ስትጥር እደርሳለሁ። ስላበረከተችው ፍቅራዊ ድጋፍ ምስጋና ይድረሳትና ልጆቻችን በሙሉ ገና ከለጋ ዕድሜያቸው አንስቶ ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አግኝተዋል።
አባቴ ለአገልግሎት የነበረው ቅንዓት በአእምሮዬና በልቤ ውስጥ እንደማይፋቅ ሆኖ ተቀርጿል። (ምሳሌ 22:6) በመሆኑም በ1968 የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች በስብከቱ ሥራ ለማገዝ ወደ ማዕከላዊውና ደቡብ አሜሪካ እንዲሄዱ ጥሪ በቀረበ ጊዜ ቤተሰባችን ለጥሪው ምላሽ መስጠት ፈለገ። በወቅቱ ልጆቻችን ከ5 እስከ 13 ዓመት ይሆናቸው የነበረ ሲሆን ማናችንም ብንሆን አንዲት የስፓንኛ ቃል እንኳ አናውቅም ነበር። በተሰጠን መመሪያ መሠረት ስለ ኑሮው ሁኔታ ለማወቅ ወደ ተለያዩ አገሮች ተጓዝኩ። ከዚያም በቤተሰብ ሆነን አማራጮቹን በጸሎት ከመረመርን በኋላ ወደ ኒካራጓ ለመሄድ ቆረጥን።
በኒካራጓ ማገልገል
ጥቅምት 1970 አዲሱ ቤታችን የገባን ሲሆን ከሦስት ሳምንት በኋላ በጉባኤ ስብሰባ ላይ የማቀርበው አጠር ያለ ክፍል ተሰጠኝ። ባጠናኋቸው ጥቂት የስፓንኛ ቃላት ክፍሌን እንደምንም አቀረብኩና ሁሉም የጉባኤው አባላት ቅዳሜ ጠዋት በ3:30 ለሰርቬሳ እኛ ቤት እንዲመጡ ጋብዤ ንግግሬን ደመደምኩ። መስክ አገልግሎት ለማለት ሰርቪስዮ እላለሁ ብዬ ለካስ የጋበዝኳቸው እኛ ቤት መጥተው ቢራ እንዲጠጡ ነበር። ቋንቋውን መማር በእርግጥ ትልቅ ፈተና ነበር!
መጀመሪያ አካባቢ አንድ አቀራረብ በእጄ ላይ እጽፍና አንድ ቤት ከማንኳኳቴ በፊት መንገድ ላይ እለማመደዋለሁ። “በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ያለ ክፍያ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይደረጋል” እላለሁ። መጽሐፉን የተቀበለ አንድ ሰው ከጊዜ በኋላ እንደተናገረው ምን ለማለት እንደፈለግኩ ለማወቅ ስብሰባ ወደምናደርግበት ቦታ መምጣት እንዳለበት ተሰምቶት ነበር። ይህ ሰው አሁን የይሖዋ ምሥክር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ትሁት በሆኑ ሰዎች ልብ ውስጥ የእውነትን ዘር የሚያሳድገው አምላክ መሆኑ ምንኛ ግልጽ ነው!—1 ቆሮንቶስ 3:7
በዋና ከተማዋ በማናጉዋ ሁለት ዓመት ያክል ካገለገልን በኋላ ወደ ደቡብ ኒካራጉዋ እንድንዛወር ተጠየቅን። እዚያም ሪቫስ ከሚገኘው ጉባኤና በአቅራቢያው ከሚገኙ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ካቀፉ ገለልተኛ ቡድኖች ጋር እናገለግል ነበር። እነዚህን ቡድኖች ስንጎበኝ ፔድሮ ፔና የሚባል ታማኝ አረጋዊ ወንድም አብሮኝ ይሄድ ነበር። አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ብቻ ያለበት አንደኛው ቡድን በኒካራጓ ሐይቅ ላይ ባለች የእሳተ ገሞራ ደሴት ላይ ይገኛል።
ምንም እንኳ ቤተሰቡ ኑሯቸው ዝቅተኛ ቢሆንም በጉብኝታችን መደሰታቸውን ለማሳየት የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ማታ ቤት ስንገባ እራት ተዘጋጅቶ ጠበቀን። እዚያ በቆየንበት የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ያላቸው ብዙ ተወዳጅ ሰዎች የምንበላው ምግብ ያመጡልን ነበር። እሁድ ቀን ባደረግነው የሕዝብ ስብሰባ ላይ 101 ሰዎች ሲገኙ በጣም ደስ አለን።
በኮስታ ሪካ ድንበር አቅራቢያ በሚገኙት ተራራማ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን በጎበኘን ጊዜ የይሖዋ ድጋፍ እንዳልተለየኝ በግልጽ ለማየት ችያለሁ። ወደዚያ በምንሄድበት ዕለት ፔድሮ ሊወስደኝ ሲመጣ ወባ አሞኝ ተኝቼ ነበር። “ፔድሮ መሄድ አልችልም” አልኩት። መዳፉን ግንባሬ ላይ አደረገና “በጣም ታተኩሳለህ ሆኖም መሄድ አለብህ! ወንድሞች ይጠብቁናል” አለኝ። በመቀጠልም ልዩ የሆነ ልባዊ ጸሎት አቀረበ።
እኔም “እስከዚያው ፍሬስኮ (የፍራፍሬ ጭማቂ) እየጠጣህ ቆየኝ። በአሥር ደቂቃ ውስጥ እነሳለሁ” አልኩት። በዚህ ክልል ሁለት የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች የነበሩ ሲሆን ጥሩ መስተንግዶ አድርገውልናል። በትኩሳት ምክንያት ሰውነቴ ቢዝልም በማግስቱ ከእነርሱ ጋር ተያይዘን አገልግሎት ወጣን። በእሑዱ ስብሰባችን ላይ ከመቶ የሚበልጡ ሰዎች መገኘታቸው ምንኛ የሚያበረታታ ነበር!
ሌላ ዝውውር
በ1975 ቮን የተባለውን ሰባተኛ ልጃችንን ወለድን። በቀጣዩ ዓመት በገንዘብ ችግር ምክንያት ወደ ካናዳ ለመመለስ ተገደድን። ኒካራጉዋ በቆየንባቸው ጊዜያት የይሖዋ ድጋፍ እንዳልተለየን ስለተመለከትን አገሪቱን ጥለን መውጣት ቀላል አልሆነልንም። ከዚያ ለቅቀን በወጣንበት ወቅት በጉባኤያችን የአገልግሎት ክልል ውስጥ የሚኖሩ ከ500 የሚበልጡ ሰዎች ስብሰባ ላይ መገኘት ጀምረው ነበር።
ቀደም ሲል ኒካራጉዋ እያለን እኔና ሴት ልጃችን ሚርያም ልዩ አቅኚ ስንሆን ሚርያም “አባባ፣ ወደፊት እናንተ ወደ ካናዳ ብትመለሱ እንኳ እኔ እዚሁ እንድቆይ ትፈቅድልኛለህ?” ስትል ጠይቃኝ ነበር። እመለሳለሁ የሚል ሐሳብ ስላልነበረኝ “አዎን፣ ምን ጥያቄ አለው!” ብያት ነበር። ስለዚህ እኛ ወደ ካናዳ ስንመለስ ሚርያም እዚያው ቀርታ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቷን ቀጠለች። ከጊዜ በኋላ ከአንድሪው ሪድ ጋር ተጋቡ። በ1984 በወቅቱ ብሩክሊን ኒው ዮርክ በነበረው በጊልያድ (የይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናውያን ትምህርት ቤት) 77ኛ ክፍል ተማሩ። አሁን ሚርያም ከባለቤቷ ጋር በዶሚኒካን ሪፑብሊክ በማገልገል ኒካራጉዋ የነበሩ ትጉ ሚስዮናውያን የቀረጹባትን ፍላጎት በማርካት ላይ ትገኛለች።
በዚህ ጊዜም ቢሆን “የፈለገው ይምጣ እንጂ መስበካችንን አናቆምም” የሚለው የአባቴ አነጋገር ከውስጤ አልጠፋም። ስለዚህ ወደ መካከለኛው አሜሪካ የምንመለስበትን በቂ ገንዘብ ካጠራቀምን በኋላ በ1981 ወደ ኮስታ ሪካ ሄድን። እዚያ እያገለገልን እያለ በአዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ላይ እንድንካፈል ተጠራን። ይሁን እንጂ በ1985 ልጃችን ግራንት የሕክምና ክትትል ስላስፈለገው ወደ ካናዳ ተመለስን። ግሊን በቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ላይ ለመሥራት አኔት እና ቻርሜን ደግሞ በልዩ አቅኚነት ለማገልገል እዚያው ኮስታ ሪካ ቀሩ። ከኮስታ ሪካ ስንወጣ እንመለሳለን የሚል ሐሳብ ጨርሶ አልነበረንም።
መከራን መቋቋም
መስከረም 17, 1993 ጠዋት ፀሐይዋ ፍንትው ብላ ወጥታለች። እኔና ትልቁ ልጃችን ማርክ ጣሪያችንን እየከደንን ነበር። ጎን ለጎን እየሠራን እያለ እንደ ልማዳችን መንፈሳዊ ጉዳዮች አንስተን እንጫወት ነበር። ብቻ ምን እንደሆንኩ እንጃ ሚዛኔን ስቼ ከጣሪያው ላይ ወደቅኩ። ራሴን ሳውቅ ደማቅ መብራቶችንና ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሰዎች አየሁ። ያለሁት በሆስፒታሉ ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ትዝ ስላለኝ በመጀመሪያ የተናገርኩት “ደም አልወስድም፣ ደም አልወስድም!” የሚሉትን ቃላት ነበር። (ሥራ 15:28, 29) ቻርሜን “ችግር የለም አባባ። ሁላችንም እዚህ ነን” ስትል ስሰማ እፎይታ ተሰማኝ። ከጊዜ በኋላ እንደነገሩኝ ዶክተሮቹ የሕክምና ሰነዴን አይተው ከዚያ በኋላ ስለ ደም ጉዳይ አላነሱም። አንገቴ ተሰብሮ ሙሉ በሙሉ ሽባ ስለሆንኩ መተንፈስ እንኳ አልችልም ነበር።
መንቀሳቀስ ስለማልችል ከምን ጊዜውም ይበልጥ የይሖዋ ድጋፍ አስፈልጎኝ ነበር። በጉሮሮዬ ላይ በቀዶ ሕክምና ለመተንፈስ የሚረዳ ቱቦ ተደረገልኝ። መናገር አልችልም ነበር። ሰዎች ለማለት የፈለግኩትን ለመረዳት ከንፈሮቼን ማንበብ ነበረባቸው።
የተለያዩ ወጪዎች በአንድ ጊዜ ተቆለሉብን። ባለቤቴን ጨምሮ አብዛኞቹ ልጆቼ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ስለነበሩ እነዚህን ወጪዎች ለመሸፈን የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ማቋረጥ ይኖርባቸው ይሆን ብዬ አሰብኩ። ይሁን እንጂ ማርክ ሥራ አገኘና በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ አብዛኞቹን ወጪዎች መሸፈን ቻልን። በዚህም ምክንያት ከእኔና ከባለቤቴ በስተቀር ሁሉም የሙሉ ጊዜ አገልግሎታቸውን ቀጠሉ።
ከስድስት የተለያዩ አገሮች የተላኩልኝ በመቶ የሚቆጠሩ ካርዶችና ደብዳቤዎች የተኛሁበትን የሆስፒታል ክፍል ሞሉት። ይሖዋ በእርግጥም ደግፎ አቁሞኛል። ልዩ የሕክምና ክትትል በሚሰጥበት ክፍል በቆየሁባቸው የአምስት ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ጉባኤውም ቤተሰቤን በመመገብ ረድቶኛል። ሁልጊዜ ከሰዓት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የሚያነብልኝ እንዲሁም የሚያጽናኑ ተሞክሮዎችን የሚነግረኝ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ከጎኔ አላጣም ነበር። ሁለት የቤተሰቤ አባላት እያንዳንዱን የጉባኤ ስብሰባ ከእኔ ጋር ስለሚዘጋጁ በጣም አስፈላጊ የሆነው መንፈሳዊ ምግብ አምልጦኝ አያውቅም።
ሆስፒታል ተኝቼ እያለሁ በልዩ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ዝግጅት ተደረገልኝ። ሆስፒታሉ ቀኑን ሙሉ ከእኔ ጋር የምትውል አንዲት ነርስና ለመተንፈስ እንዲረዳኝ ተብሎ ለተገጠመልኝ መሣሪያ ባለሞያ መደበልኝ። ከክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር እንደገና መሰብሰብ መቻሌ ምንኛ አስደሳች ነበር! በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች እኔን
ሰላም ለማለት ተሰልፈው ሲጠብቁ የነበረበትን ያንን ጊዜ መቼም አልረሳውም።መንፈሳዊነቴን መጠበቅ
ምንም እንኳ የ24 ሰዓት የነርስ ክትትል ቢያስፈልገኝም አደጋው ከተከሰተ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ቤት ተመለስኩ። በተለየ መንገድ የተሠራ መኪና ወደ ስብሰባ ስለሚወስደኝ ጉባኤ አምልጦኝ አያውቅም። እውነቱን ለመናገር ወደ ጉባኤ መሄድ ቆራጥነትን ይጠይቅ ነበር። ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋላ በሁሉም የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ችያለሁ።
ከጊዜ በኋላ በ1997 የካቲት ወር ውስጥ በተወሰነ መጠን እንደገና መናገር ቻልኩ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው ተስፋ ስናገር አንዳንድ ነርሶች በአድናቆት ያዳምጡኛል። አንዲት ነርስ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ከዳር እስከ ዳርና ሌሎች የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎችን አንብባልኛለች። ሁኔታው አሰልቺ ቢሆንም ከሰዎች ጋር ለመነጋገር ስፈልግ በዘንግ ኮምፒውተር ላይ የምጽፍ ሲሆን በዚህ መንገድ በአገልግሎት መካፈል መቻሉ መልሶ የሚክስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
የነርቭ ሕመም በጣም ያሰቃየኛል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ሳካፍል ወይም መጽሐፍ ቅዱስ በሚነበብልኝ ጊዜ ትንሽ ሻል ይለኛል። ድጋፍ ከሆነችኝ ከባለቤቴ ጋር በመንገድ ላይ ምሥክርነት አልፎ አልፎ የምካፈል ሲሆን እርዳታ በሚያስፈልገኝ ጊዜ ታስተረጉምልኛለች። በተለያዩ ጊዜያት በረዳት አቅኚነት ለማገልገል ችያለሁ። ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኜ ማገልገሌ በተለይ ወንድሞች ስብሰባ ላይ ወደ እኔ በሚቀርቡበት ወይም ቤቴ በሚመጡበት ጊዜ መርዳትና ማበረታታት መቻሌ ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልኛል።
በግልጽ ለመናገር በቀላሉ ጭንቀት ውስጥ እገባለሁ። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሲሰማኝ ደስታዬን እንዳላጣ ቶሎ ብዬ እጸልያለሁ። የይሖዋን ድጋፍ ምንጊዜም እንዳይለየኝ ቀን ከሌት እጸልያለሁ። ደብዳቤ ሲደርሰኝ ወይም አንድ ሰው መጥቶ ሲጠይቀኝ ሁልጊዜ ያስደስተኛል። እንዲሁም መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! መጽሔቶችን ማንበብ የሚያንጹ ነገሮችን እንዳስብ ይረዳኛል። አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ ነርሶች እነዚህን መጽሔቶች ያነብቡልኛል። ከአደጋው መከሰት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ሰባት ጊዜ በቴፕ ክር አዳምጫለሁ። ይሖዋ በእነዚህ ነገሮች አማካኝነት ደግፎ አቁሞኛል።—መዝሙር 41:3
ያጋጠመኝ ለውጥ ታላቁ አስተማሪያችን ይሖዋ ሕይወታችንን እንድንመራ እንዴት እንደሚረዳን የማሰላስልበትን በቂ ጊዜ አስገኝቶልኛል። ፈቃዱንና ዓላማውን የሚያስታውቅ ትክክለኛ እውቀት፣ ትርጉም ያለው አገልግሎት፣ የቤተሰብ ደስታ ቁልፉን የምናገኝበት ምክር እንዲሁም መከራ ሲደርስብን ማድረግ ያለብንን የሚያሳውቅ ማስተዋል ሰጥቶናል። ይሖዋ ታማኝና ግሩም ሚስት በመስጠት ባርኮኛል። ልጆቼም በታማኝነት ከጎኔ የቆሙ ሲሆን ሁሉም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲካፈሉ በማየቴ ተደስቻለሁ። እንዲያውም ልጃችን ማርክና ባለቤቱ አሊሰን መጋቢት 11, 2000 ከጊልያድ ትምህርት ቤት 108ኛው ክፍል ተመርቀው ኒካራጉዋ ተመድበዋል። እኔና ባለቤቴ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተን ነበር። በእርግጥ፣ የደረሰብኝ መከራ ሕይወቴን እንጂ ልቤን አልለወጠውም ብዬ መናገር እችላለሁ።—መዝሙር 127:3, 4
የተቀበልኩትን መንፈሳዊ ውርሻ ለቤተሰቤ ማስተላለፍ የሚያስችል ጥበብ ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ልጆቼ “የፈለገው ይምጣ እንጂ መስበካችንን አናቆምም። ይሖዋ እንድንሰብክ አዝዞናል” የሚለውን የአባቴን ዓይነት ዝንባሌ በመያዝ ፈጣሪያቸውን ሲያገለግሉ ማየቴ የሚያበረታታና የሚያጽናና ሆኖልኛል። እርግጥ ነው፣ እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ ዕድሜያችንን ሁሉ የይሖዋ ድጋፍ አልተለየንም።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአቅኚነት በሠራንባቸው ዓመታት እንጠቀምበት በነበረው ተንቀሳቃሽ ቤት አጠገብ ከአባቴ፣ ከወንድሞቼ እና ከእህቴ ጋር። እኔ በስተቀኝ ያለሁት ነኝ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከሚረን ጋር
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቤተሰባችን በቅርቡ የተነሳው ፎቶ ግራፍ
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሁንም ደብዳቤ በመጻፍ መመሥከሬን አልተውኩም