በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን በፈቃደኛነት መንፈስ አገልግሉ

አምላክን በፈቃደኛነት መንፈስ አገልግሉ

አምላክን በፈቃደኛነት መንፈስ አገልግሉ

ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለ እናንተ እንኳን ገንዘቤን፣ ራሴንም አሳልፌ ብሰጥ ደስ ይለኛል” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 12:​15 የ1980 ትርጉም ) እነዚህ ቃላት የይሖዋ አገልጋዮች ለማዳበር መጣር ስላለባቸው አመለካከትና ዝንባሌ ምን ነገር ያስገነዝቡሃል? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዳሉት ከሆነ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስቲያኖች እነዚህን ቃላት ሲጽፍ እንዲህ ማለቱ ነበር:- “አንድ አባት ለልጆቹ በደስታ እንደሚያደርገው ሁሉ ለእናንተ ደህንነት ስል ጉልበቴን፣ ጊዜዬን፣ ሕይወቴንና ያለኝን ሁሉ ለመሠዋት ፈቃደኛ ነኝ።” ጳውሎስ ክርስቲያናዊ አገልግሎቱን ለመፈጸም ሲል አስፈላጊ ከሆነ ‘ራሱን አሳልፎ ለመስጠት’ ወይም “አንዳች ሳይቆጥብ ሁለመናውን ለመስጠት” ዝግጁ ነበር።

ከዚህም በላይ ጳውሎስ ይህን ሁሉ ያደረገው ‘ደስ እያለው’ ነበር። ዘ ጀሩሳሌም ባይብል እንደሚለው ይህን ለማድረግ “ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ” ነበር። አንተስ? አንዳንድ ጊዜ “አንዳች ሳትቆጥብ ሁለመናህን መስጠት” የሚጠይቅብህ ሊሆን ቢችልም እንኳ ይሖዋ አምላክን ለማገልገልና የሌሎችን ፍላጎት ለማሟላት ስትል ጊዜህን፣ ጉልበትህን፣ ችሎታህንና ሀብትህን ለመሠዋት ፈቃደኛ ነህን? ይህንንስ የምታደርገው ‘ደስ እያለህ’ ነውን?

ጭራሽ ለማገልገል ፈቃደኞች አይደሉም

አብዛኞቹ ሰዎች ከማቅማማትም አልፈው አምላክን ለማገልገል ጭራሽ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ፊት ለፊት ይገልጻሉ። የምስጋና ቢስነት፣ በራስ የመመራት አልፎ ተርፎም የዓመፀኝነት መንፈስ ያሳያሉ። ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ገፋፍቷቸዋል። ‘እንደ እግዚአብሔር መልካምንና ክፉን በማወቅ’ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ አድርጎ ነገራቸው። (ዘፍጥረት 3:​1-5) በዛሬው ጊዜ እንዲህ ዓይነት መንፈስ ያላቸው ሰዎች በአምላክ ፊት ምንም ዓይነት ግዴታ ሳይኖርባቸው ወይም ያለ እሱ ጣልቃ ገብነት የፈለጉትን ነገር ለማድረግ የተሟላ ነፃነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ይሰማቸዋል። (መዝሙር 81:​11, 12) ያላቸውን ነገር ሁሉ የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ።​—⁠ምሳሌ 18:​1

እንዲህ ዓይነት የለየለት አመለካከት አይኖርህ ይሆናል። አሁን ያገኘኸውን የሕይወት ስጦታና ከዚህ ይበልጥ አስደናቂ የሆነውን ወደ ገነትነት በተለወጠች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ከልብ ሳታደንቅ አትቀርም። (መዝሙር 37:​10, 11፤ ራእይ 21:​1-4) ይሖዋ ላሳየህ ጥሩነት ጥልቅ የአመስጋኝነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሰይጣን አስተሳሰባችንን በማዛባት አገልግሎታችን በአምላክ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እንዲያጣ ሊያደርግ የሚችል በመሆኑ ሁላችንም ንቁ መሆን ይኖርብናል። (2 ቆሮንቶስ 11:​3) ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

የፈቃደኝነት አገልግሎት ይፈለግብናል

ይሖዋ በፈቃደኝነትና በሙሉ ልብ የሚቀርብ አገልግሎት ይፈልጋል። ፈቃዱን እንድናደርግ በፍጹም አያስገድደንም። ሰይጣን፣ ሰዎች ፍላጎቱን እንዲያሟሉለት ጫና ለማሳደር ወይም ለመገፋፋት የቻለውን ሁሉ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን ከማገልገል ጋር በተያያዘ ስለ ግዴታ፣ ትእዛዝ፣ መሥፈርት እንዲሁም ሌሎች ነገሮች ይናገራል። (መክብብ 12:​13፤ ሉቃስ 1:​6) ሆኖም አምላክን እንድናገለግል የሚገፋፋን ዋነኛው ምክንያት ለእሱ ያለን ፍቅር ነው።​—⁠ዘጸአት 35:​21፤ ዘዳግም 11:​1

ጳውሎስ በአምላክ አገልግሎት ምንም ያህል ቢደክም ‘ፍቅር ከሌለው’ ድካሙ ከንቱ እንደሚሆን አውቋል። (1 ቆሮንቶስ 13:​1-3) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ክርስቲያኖች የአምላክ ባሪያዎች መሆናቸውን ሲጠቅሱ በግዳጅ ላይ የተመሠረተ ባርነትን ማመልከታቸው አይደለም። (ሮሜ 12:​11፤ ቆላስይስ 3:​24) ይህ አባባል የሚያመለክተው ለአምላክና ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥልቅ በሆነ ልባዊ ፍቅር ላይ ተመሥርቶ በፈቃደኝነት መገዛትን ነው።​—⁠ማቴዎስ 22:​37፤ 2 ቆሮንቶስ 5:​14፤ 1 ዮሐንስ 4:​10, 11

ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት ለሰዎችም ያለንን ጥልቅ ፍቅር ማንጸባረቅ አለበት። ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚገኘው ጉባኤ “ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትንከባከብ፣ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን” ሲል ጽፏል። (1 ተሰሎንቄ 2:​7) በዛሬው ጊዜ በበርካታ አገሮች እናቶች ልጆቻቸውን የመንከባከብ ሕጋዊ ግዴታ አለባቸው። ሆኖም አብዛኞቹ እናቶች ልጆቻቸውን የሚንከባከቡት ሕጉን ለማክበር ብቻ ብለው ነውን? እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ይህን የሚያደርጉት ልጆቻቸውን በጣም ስለሚወዷቸው ነው! አንዲት ሞግዚት እንኳ በደስታ ለልጆችዋ ከፍተኛ መሥዋዕቶች ትከፍላለች። ጳውሎስ ለሚያገለግላቸው ሰዎች ተመሳሳይ የሆነ ‘ፍቅር’ ስለነበረው ሕይወቱን እነሱን ለመርዳት ሊጠቀምበት “ዝግጁ፣” [የ1980 ትርጉም ] (“ፈቃደኛ፣” ኪንግ ጀምስ ቨርሽን፤ “ደስተኛ” ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) ነበር። (1 ተሰሎንቄ 2:​8) ፍቅር የጳውሎስን ምሳሌ እንድንኮርጅ ያነሳሳናል።​—⁠ማቴዎስ 22:​39

በግማሽ ልብ ስለሚቀርብ አገልግሎትስ ምን ማለት ይቻላል?

ለራሳችን ያለን ፍቅር ለአምላክና ለሰዎች ካለን ፍቅር መብለጥ የለበትም። አለዚያ በግማሽ ልብ የማገልገል ልማድ ሊጠናወተን ይችላል። ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ በራሳችን ፍላጎት መምራት ሳንችል በመቅረታችን እየተበሳጨን በውስጣችን የቅሬታ ስሜት ማቆጥቆጥ ሊጀምር ይችላል። ይህ ሁኔታ ለአምላክ የነበራቸውን ፍቅር ቢያጡም ግዴታ እንዳለባቸው ተሰምቷቸው መጠነኛ አገልግሎት ያቀርቡ በነበሩ አንዳንድ እስራኤላውያን ላይ ታይቷል። ውጤቱ ምን ነበር? አምላክን ማገልገል “አሰልቺ” ሆነባቸው።​—⁠ሚልክያስ 1:​13 የ1980 ትርጉም

ለአምላክ የሚቀርብ ማንኛውም ዓይነት መሥዋዕት ምንጊዜም ‘ነውር የሌለበት’ እና “የተመረጠ” መሆን ይኖርበታል። (ዘሌዋውያን 22:​17-20፤ ዘጸአት 23:​19) በሚልክያስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ከእንስሶቻቸው መካከል ምርጦቹን ለይሖዋ ከማቅረብ ይልቅ የማይፈልጓቸውን እንስሳት መስጠት ጀመሩ። ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠ? ካህናቱን እንዲህ አላቸው:- “ዕውር መሥዋዕትንም ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? አንካሳውንና የታመመውን ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? ያንን ለአለቃህ አቅርብ፤ በውኑ በአንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ፊትህን ይቀበላልን? . . . በቅሚያ የያዛችሁትንም አንካሳውንም የታመመውንም አቅርባችኋል፤ እንዲሁ ቁርባንን ታመጣላችሁ፤ በውኑ ከእጃችሁ ይህን ልቀበለውን?”​—⁠ሚልክያስ 1:​8, 13

ይህ በማናችንም ላይ ሊደርስ የሚችለው እንዴት ነው? ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ የሆነ ልብና መንፈስ ከሌለን የምናቀርበው መሥዋዕት “አሰልቺ” ሊሆንብን ይችላል። (ዘጸአት 35:​5, 21, 22፤ ዘሌዋውያን 1:​3፤ መዝሙር 54:​6፤ ዕብራውያን 13:​15, 16) ለምሳሌ ያህል ለይሖዋ የምንሰጠው ትርፍራፊ ጊዜያችንን ነውን?

ቅን ልቦና ያለው አንድ የቤተሰብ አባል ወይም ቀናተኛ ሌዋዊ አንድን እስራኤላዊ በሆነ መንገድ አስገድዶ ፈጽሞ መስጠት ያልፈለገውን ምርጥ እንስሳውን እንዲሠዋ ቢያደርግ መሥዋዕቱ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል ብሎ የሚያስብ ሰው ይኖራልን? (ኢሳይያስ 29:​13፤ ማቴዎስ 15:​7, 8) ይሖዋ እንዲህ ዓይነት መሥዋዕቶችን ሳይቀበል ከመቅረቱም በላይ መሥዋዕቱን ያቀረቡትን ሰዎች ትቷቸዋል።​—⁠ሆሴዕ 4:​6፤ ማቴዎስ 21:​43

የአምላክን ፈቃድ በደስታ መፈጸም

በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ መከተል አለብን። ኢየሱስ “የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻም” ብሏል። (ዮሐንስ 5:​30) ኢየሱስ አምላክን በፈቃደኝነት በማገልገል ታላቅ ደስታ አግኝቷል። ኢየሱስ “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ” የሚሉትን የዳዊትን ትንቢታዊ ቃላት ፈጽሟል።​—⁠መዝሙር 40:​8

ኢየሱስ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ያስደስተው የነበረ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረጉ ሁልጊዜ ቀላል ነበር ማለት አይደለም። ከመያዙ፣ ለፍርድ ከመቅረቡና ከመገደሉ በፊት የነበረውን ሁኔታ ተመልከት። ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ በነበረበት ወቅት ‘እጅግ አዝኖ፣’ “በፍርሃትም ሲጣጣር” ነበር። ከፍተኛ የስሜት ውጥረት አድሮበት ስለነበር በሚጸልይበት ጊዜ “ወዙ በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ።”​—⁠ማቴዎስ 26:​38፤ ሉቃስ 22:​44

ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ጭንቀት የደረሰበት ለምንድን ነው? ለራሱ ደህንነት በማሰብ ወይም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ባለመፈለጉ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ለመሞት ዝግጁ ነበር። ሌላው ቀርቶ “አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም” ለሚሉት የጴጥሮስ ቃላት ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 16:​21-23) ኢየሱስን ያሳሰበው ነገር እንደ ተናቀ ወንጀለኛ ተቆጥሮ መሞቱ በይሖዋና በቅዱስ ስሙ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ነቀፋ ነበር። ውድ ልጁ እንዲህ ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊት ሲፈጸምበት ማየቱ አባቱን በእጅጉ እንደሚረብሸው ኢየሱስ ያውቅ ነበር።

በተጨማሪም ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ወሳኝ ወደሆነ ጊዜ እየተቃረበ መሆኑን ተገንዝቧል። የአምላክን ሕጎች በታማኝነት መከተሉ አዳምም ተመሳሳይ ምርጫ ማድረግ ይችል እንደነበር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ይሆናል። ኢየሱስ ታማኝ መሆኑ ሰዎች ፈተና ሲያጋጥማቸው አምላክን በፈቃደኝነትና በታማኝነት አያገለግሉትም የሚለው የሰይጣን አባባል ሙሉ በሙሉ ውሸት መሆኑን ያጋልጣል። በመጨረሻ ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ሰይጣንን የሚደመስሰው ሲሆን የእሱ ዓመፅ ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶችም ያስወግዳል።​—⁠ዘፍጥረት 3:​15

በኢየሱስ ጫንቃ ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት ወድቋል! የአባቱ ስም፣ የአጽናፈ ዓለሙ ሰላምና የሰው ዘር ቤተሰብ መዳን ባጠቃላይ በኢየሱስ ታማኝነት ላይ የተመካ ነበር። ኢየሱስ ይህን በመገንዘብ እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “አባቴ፣ ቢቻልስ፣ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን።” (ማቴዎስ 26:​39) ኢየሱስ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እያለም ለአባቱ ፈቃድ በውዴታ ከመገዛት አላፈገፈገም።

“መንፈስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው”

ኢየሱስ ይሖዋን ሲያገለግል ከፍተኛ ጭንቀት እንደደረሰበት ሁሉ እኛም የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ሰይጣን ጫና ያደርስብናል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። (ዮሐንስ 15:​20፤ 1 ጴጥሮስ 5:​8) ከዚህም በላይ ከፍጽምና የራቅን ነን። በመሆኑም አምላክን በፈቃደኝነት ብናገለግልም እንኳ ይህን ማድረግ ቀላል አይሆንልንም። ኢየሱስ እንዲያደርጉ የነገራቸውን ሁሉ ለማድረግ ደቀ መዛሙርቱ ምን ያህል ይጥሩ እንደነበር ያውቃል። ከዚህም የተነሳ “መንፈስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው” ብሏል። (ማቴዎስ 26:​41) ፍጹም በሆነ ሰብዓዊ ሥጋው ላይ በተፈጥሮ የወረሰው ድካም አልነበረበትም። ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርቱ ፍጹም ካልሆነው አዳም የወረሱትን አለፍጽምና ማለትም የሥጋቸውን ድካም በአእምሮው ይዞ ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በውርስ ባገኙት አለፍጽምናና ይህ በሚያስከትልባቸው ሰብዓዊ ገደብ የተነሳ በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን የሚፈልጉትን ሁሉ ለማድረግ ትግል እንደሚጠይቅባቸው ያውቃል።

ከዚህ የተነሳ አምላክን በተሟላ መልኩ እንዳያገለግል አለፍጽምና ችሎታውን በገደበበት ጊዜ ከፍተኛ ጭንቀት ተሰምቶት እንደነበረው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ይሰማን ይሆናል። ጳውሎስ “ፈቃድ አለኝና፣ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 7:​18) እኛም ማድረግ የምንፈልጋቸውን መልካም ነገሮች ሁሉ አሟልተን ማከናወን እንደማንችል እንገነዘብ ይሆናል። (ሮሜ 7:​19) ይህ የሆነው ማድረግ ባለመፈለጋችን ሳይሆን ደካማ ሥጋችን የምናደርገውን ከፍተኛ ጥረት ሳይቀር ስለሚገድብብን ነው።

ተስፋ መቁረጥ የለብንም። የቻልነውን ሁሉ ለማድረግ ከልባችን ከተዘጋጀን አምላክ አገልግሎታችንን እንደሚቀበል የተረጋገጠ ነው። (2 ቆሮንቶስ 8:​12) ለአምላክ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ በመገዛት ረገድ ክርስቶስ ያሳየውን መንፈስ ለመኮረጅ ‘እንትጋ።’ (2 ጢሞቴዎስ 2:​15፤ ፊልጵስዩስ 2:​5-7፤ 1 ጴጥሮስ 4:​1, 2) ይሖዋ ለእንዲህ ዓይነቱ የፈቃደኝነት መንፈስ ወሮታ ይከፍላል፤ ድጋፍም ይሰጣል። ድካማችንን መሸፈን እንድንችል “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 4:​7-10 NW ) በይሖዋ እርዳታ እኛም እንደ ጳውሎስ ውድ ለሆነው አገልግሎቱ ‘ገንዘባችንንም ሆነ ራሳችንን ደስ እያለን አሳልፈን እንሰጣለን።’

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ አቅሙ በፈቀደለት መጠን አምላክን በፈቃደኝነት አገልግሏል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በአስጨናቂ ሁኔታ ሥር በነበረበት ጊዜ እንኳ የአባቱን ፈቃድ አድርጓል