በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በትዕግሥት መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

በትዕግሥት መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

በትዕግሥት መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ሰዎች በመጠበቅ ብቻ በየዓመቱ ምን ያህል ሰዓት እንደሚያጠፉ መገመት ትችላለህ? በገበያ አዳራሽ ወይም በነዳጅ ማደያ ሰልፍ ይዘው ይጠብቃሉ። ምግብ ቤት ገብተው ያዘዙት እስኪቀርብላቸው ድረስ ይጠብቃሉ። ሐኪም ዘንድ ለመቅረብ ተራ ይጠብቃሉ። አውቶቡስና ባቡር ይጠብቃሉ። አዎን፣ አንድ ሰው በመጠበቅ ብቻ በሕይወቱ ውስጥ ይህ ነው የማይባል ጊዜ ያጠፋል። በአንድ ግምት መሠረት ጀርመናውያን በተሽከርካሪ መጨናነቅ ሳቢያ ብቻ በዓመት 4.7 ቢልዮን ሰዓት ያጠፋሉ! አንድ ሰው ባሰላው መሠረት ይህ ሰዓት ወደ 7, 000 የሚያህሉ ሰዎች ከሚኖራቸው የሕይወት መቆያ ዘመን ድምር ጋር እኩል ነው።

መጠበቅ በጣም ሊያበሳጭ ይችላል። በዛሬው ጊዜ ሁሉን ነገር ለመሥራት የሚያስችል በቂ ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። በመሆኑም ልንሠራቸው ስለሚገቡ ሌሎች ነገሮች ስናስብ አንድን ነገር በትዕግሥት መጠበቅ ከባድ ፈተና ሊሆንብን ይችላል። በአንድ ወቅት ደራሲው አሌክሳንደር ሮስ “በሕይወታችን ከሚገጥሙን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ከመጠበቅ ጋር የተቆራኙ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

አሜሪካዊው የሀገር መሪ ቤንጃሚን ፍራንክሊን መጠበቅ ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቅ ሊሆን እንደሚችልም ተገንዝበዋል። ከዛሬ 250 ዓመት በፊት “ጊዜ ገንዘብ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በንግድ ሥራ የተሠማሩ ሰዎች በሥራ ሂደት ላይ አላስፈላጊ መጓተቶችን የሚያስቀሩበትን ዘዴ የሚፈልጉት ከዚህ የተነሳ ነው። በአጭር ጊዜ ብዙ ማምረት መቻል ይበልጥ ትርፋማ መሆን ማለት ሊሆን ይችላል። ወዲያው ተዘጋጅተው የሚቀርቡ ምግቦች የሚሸጡ፣ ከመኪና ሳይወርዱ የገንዘብ ዝውውር የሚያስፈጽሙና ይህን የመሰሉ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የንግድ ድርጅቶች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ የሚያደርጉት ደንበኞችን ማስደሰት ጉዳያቸው እስኪፈጸም ድረስ በመጠበቅ የሚያጠፉትን ጊዜ ማሳጠርን እንደሚያካትት ስለሚገነዘቡ ነው።

የሕይወት ዘመናችንን ማባከን

የአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን አሜሪካዊው ባለቅኔ ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን “በመጠበቅ የሚባክነው የሰው ልጅ ዕድሜ እጅግ ከፍተኛ ነው!” ሲሉ በአንድ ወቅት አማርረው ተናግረዋል። በቅርቡ ደግሞ ደራሲው ላንስ ማሮ መጠበቅ ስለሚያስከትለው የመሰላቸት ስሜትና እንግልት ምሬታቸውን ከገለጹ በኋላ “መጠበቅ ስለሚያስከትለው ስውር ሥቃይ” ተናግረዋል። ሥቃዩ ምንድን ነው? “አንድ ሰው ውድ ሀብቱን፣ ጊዜውንና የሕይወቱን የተወሰነ ክፍል ሊተካ በማይችል መንገድ ያጣል።” ይህ ሁኔታ የሚያሳዝን ቢሆንም እውነት ነው። በመጠበቅ ምክንያት ጊዜ ለዘላለም ይጠፋል።

እርግጥ ነው፣ ሕይወት አጭር ባይሆን ኖሮ መጠበቅ ያን ያህል አሳሳቢ ጉዳይ ባልሆነ ነበር። ሆኖም ሕይወት አጭር ነው። ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙራዊ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል:- “የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፣ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፣ እኛም እንገሠጻለንና።” (መዝሙር 90:​10) የትም እንኑር፣ ምንም ዓይነት ሰው እንሁን ሕይወታችን ማለትም በምንወለድበት ጊዜ ከፊታችን ያሉት ቀናት፣ ሰዓታትና ደቂቃዎች በቶሎ ያልፋሉ። ይሁን እንጂ በዚህም ሆነ በዚያ ሰዎችን ወይም አንድን ክንውን በመጠበቅ ከዚህ ውድ ጊዜ ውስጥ የተወሰነው እንዲባክን ማድረጋችን አይቀርም።

እንዴት በትዕግሥት መጠበቅ እንደሚቻል መማር

የተሳፈርንበት መኪና አሽከርካሪ ከፊቱ ያለውን መኪና ለመቅደም ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ አብዛኞቻችን ተመልክተን ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ምንም የሚያጣድፈው ነገር አይኖረው ይሆናል። ሆኖም ሌላ አሽከርካሪ ከፊቱ ሆኖ እንቅስቃሴውን እንዲገድብበት አይፈልግም። ትዕግሥት ማጣቱ በትዕግሥት መጠበቅን እንዳልተማረ ያሳያል። መማር? አዎን፣ በትዕግሥት መጠበቅ ልናውቀው የሚገባ አንድ ራሱን የቻለ ትምህርት ነው። ማንም ሰው ይህን ችሎታ ይዞ አይወለድም። ሕፃናት ሲርባቸው ወይም ምቾታቸው ትንሽ ሲጓደል ወዲያው ትኩረት እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት አንዳንድ ጊዜ መጠበቅ እንዳለባቸው የሚገነዘቡት እያደጉ ሲሄዱ ብቻ ነው። በእርግጥም፣ መጠበቅ ሊወገድ የማይችል የሕይወት ክፍል ስለሆነ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በትዕግሥት መጠበቅ መቻል የጉልምስና ምልክት ነው።

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ፋታ የማይሰጡ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ የታወቀ ነው። ምጥ የያዛት ሚስቱን ሆስፒታል ለማድረስ እየከነፈ ያለ ባል የሚያዘገዩ ሁኔታዎች ቢገጥሙትና ትዕግሥት አጥቶ ቢበሳጭ አያስገርምም። ከሰዶም እንዲወጣ ያጣድፉት የነበሩት መላእክት ከተማዋን ጥሎ ለመውጣት የዘገየውን ሎጥን ለመጠበቅ ዝግጁ አልነበሩም። ጥፋት በደጅ ስለቀረበ የሎጥና የቤተሰቡ ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል። (ዘፍጥረት 19:​15, 16) ይሁን እንጂ ሰዎች እንዲጠብቁ የሚገደዱባቸው አብዛኞቹ ሁኔታዎች ሕይወት አደጋ ላይ የወደቀባቸው አይደሉም። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሰዎች ለመጠበቅ የተገደዱት በሌላ ሰው ቅልጥፍና ማነስ ወይም ፍላጎት ማጣት ቢሆንም እንኳ ሁሉም ሰው ትዕግሥተኛ መሆን ቢማር ነገሮች ይበልጥ አስደሳች ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም ሁሉም ሰው በመጠበቅ የሚያጠፋውን ጊዜ እንዴት ጠቃሚ በሆነ መንገድ ሊጠቀምበት እንደሚችል ቢያውቅ በትዕግሥት መጠበቅን ይበልጥ ቀላል ሊያደርግለት ይችላል። በገጽ 5 ላይ የሚገኘው ሣጥን በትዕግሥት እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ብቻ ሳይሆን ያንን ጊዜ እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ጭምር አንዳንድ ሐሳቦች ይሰጣል።

ትዕግሥት የማጣት መንፈስ አንድ ሰው በጣም ተፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ እንዲጠብቅ መደረግ እንደሌለበት ያለውን ስሜት በሌላ አባባል የኩራት ዝንባሌውን የሚያሳይ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ያለው ማንኛውም ሰው “ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል” ለሚሉት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ቃላት ትኩረት መስጠቱ ጠቃሚ ነው። (መክብብ 7:​8) ትዕቢት ወይም ኩራት ጉልህ የባሕርይ ድክመት ከመሆኑ የተነሳ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “በልቡ የታበየ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነው” ይላል። (ምሳሌ 16:​5) በመሆኑም ትዕግሥትን ማለትም እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል መማር ራሳችንን እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት በጥሞና እንድንመረምር ሊጠይቅብን ይችላል።

ትዕግሥተኛ መሆን ወሮታ ያስገኛል

እየጠበቅን ያለነው ነገር ቢዘገይም የማያስቆጭና በመጨረሻም መምጣቱ የማይቀር መሆኑን ካመንን በትዕግሥት መጠበቁ ይበልጥ ቀላል እንደሚሆንልን የታወቀ ነው። በዚህ ረገድ እውነተኛ የአምላክ አምላኪዎች በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን አምላክ የሰጠውን አስደናቂ ተስፋ ፍጻሜ በመጠበቅ ላይ የመሆናቸውን ጉዳይ ማስታወሱ መልካም ነው። ለምሳሌ ያህል በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈ መዝሙር ላይ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” ተብሎ ተነግሮናል። ሐዋርያው ዮሐንስ ‘የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘላለም ይኖራል’ ብሎ በመናገር ይህን ተስፋ አስተጋብቷል። (መዝሙር 37:​29፤ 1 ዮሐንስ 2:​17) ለዘላለም መኖር ብንችል ኖሮ በትዕግሥት መጠበቅ የጎላ ችግር እንደማይሆንብን የታወቀ ነው። ሆኖም አሁን ለዘላለም እየኖርን አይደለንም። ደግሞስ ስለ ዘላለም ሕይወት ማውራት ከእውነታው መራቅ አይሆንምን?

ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን ሲፈጥር ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ከፊታቸው ዘርግቶላቸው እንደነበር አስታውስ። እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው (እኛን ጨምሮ) ይህን ተስፋ ያጡት ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ነው። ሆኖም ወዲያው ኃጢአት ከሠሩ በኋላ አምላክ የእነሱ አለመታዘዝ ያስከተለውን ውጤት ለመቀልበስ ዓላማ እንዳለው አስታውቋል። አንድ ‘ዘር’ እንደሚመጣ ቃል የገባ ሲሆን በመጨረሻም ዘሩ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ተገኘ።​—⁠ዘፍጥረት 3:​15፤ ሮሜ 5:​18

በግለሰብ ደረጃ ይሖዋ ተስፋ የገባቸው ነገሮች ሲፈጸሙ ተጠቃሚ መሆን አለመሆናችን ራሳችን በምናደርገው ውሳኔ ላይ የተመካ ነው። ተጠቃሚ ለመሆን በትዕግሥት መጠበቅን ይጠይቃል። እንዲህ ዓይነቱን ትዕግሥት ለመማር እንዲረዳን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አንድ ገበሬ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንድናሰላስል ያበረታታናል። ዘሩን ከዘራ በኋላ የመከር ወቅት እስኪደርስ ድረስ ሰብሉን ከአደጋ ለመከላከል የተቻለውን ሁሉ እያደረገ በትዕግሥት ከመጠበቅ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለውም። ከዚያም ትዕግሥቱ ወሮታ ያስገኝለትና የድካሙን ፍሬ ያያል። (ያዕቆብ 5:​7) ሐዋርያው ጳውሎስ ትዕግሥትን አስመልክቶ ሌላ ምሳሌ ጠቅሷል። በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ ወንዶችንና ሴቶችን እንድናስታውስ አድርጎናል። የአምላክ ዓላማ ሲፈጸም ለመመልከት በጉጉት እየተጠባበቁ የነበረ ቢሆንም እንኳ አምላክ የቀጠረውን ጊዜ መጠበቅ ነበረባቸው። ጳውሎስ “በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን” እነዚህን ሰዎች እንድንመስል አበረታትቶናል።​—⁠ዕብራውያን 6:​11, 12

አዎን፣ መጠበቅ መቅረት የማይችል የሕይወት እውነታ ነው። ሆኖም መጠበቅ ምንጊዜም የጭንቀት ምንጭ መሆን የለበትም። አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች ሲፈጸሙ ለማየት ለሚጠብቁ ሰዎች የደስታ ምንጭ ሊሆንላቸው ይችላል። በመጠበቅ የሚያሳልፉትን ጊዜ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና በማዳበርና እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሥራዎች በማከናወን ማስያዝ ይችላሉ። እንዲሁም በጸሎት፣ በጥናትና በማሰላሰል አምላክ ተስፋ የሰጠው ነገር ሁሉ በወሰነው ጊዜ እንደሚፈጸም የማያወላውል ትምክህት ማዳበር ይችላሉ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መጠበቅ የሚያስከትለውን ውጥረት ቀንሱ!

አስቀድመህ ዕቅድ አውጣ! መጠበቅ እንዳለብህ አስቀድመህ ካወቅህ ለማንበብ፣ ለመጻፍ፣ ዳንቴል ለመሥራት፣ ጥልፍ ለመ​ጥለፍ ወይም በአንድ ዓይነት ጠቃሚ ሥራ ለመጠመድ ዝግጅት አድርግ/ጊ።

ጊዜውን ለማሰላሰል ተጠቀምበት። ጥድፊያ በሞላበት በዚህ ባለንበት ዓለም ለማሰላሰል የሚሆን ጊዜ ማግኘት ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳጋች እየሆነ የመጣ ነገር ነው።

የስልክ ጥሪ መጠበቅ ካለብህ ማንበብ እንድትችል ስልኩ አጠገብ የሚነበብ ጽሑፍ አስቀምጥ። በአምስት ወይም በአሥር ደቂቃ ውስጥ ብዙ ልታነብ ትችላለህ።

ከሌሎች ጋር ሆነህ በምትጠብቅበት ጊዜ ሁኔታው አመቺ ከሆነ አጋጣሚውን ውይይት ለመጀመርና የሚያንጹ ሐሳቦችን ለማካፈል ተጠቀምበት።

እንድትጠብቅ የሚያደርግ ያልታሰበ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ የምትጠቀምበት ማስታወሻ መጻፊያ ደብተር ወይም የሚነበብ ጽሑፍ መኪናህ ውስጥ አስቀምጥ።

ዓይንህን ጨፍነህ ዘና በል ወይም ጸልይ።

ስኬታማ በሆነ መንገድ መጠበቅ በአመዛኙ የአመለካከትና አርቆ የማሰብ ጉዳይ ነው።