በኤጂያን ባሕር ሰዎችን ማጥመድ
በኤጂያን ባሕር ሰዎችን ማጥመድ
በስተ ሰሜንና በስተ ምዕራብ ከግሪክ፣ በስተ ደቡብ ከቀርጤስ ደሴት እንዲሁም በስተ ምሥራቅ ከቱርክ የሚዋሰነው የኤጂያን ባሕር ምሥራቃዊ ሜዲትራንያንን በስፋት የሚሸፍን ክልል ነው። የአንዳንድ ትላልቅ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች መገኛ የሆነው የኤጂያን ባሕር ተበታትነው የሚገኙ ትላልቅና ትናንሽ ደሴቶችን አካልሎ የያዘ ነው። የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍባቸው የሚያንጸባርቁ እዚያና እዚህ ተበታትነው የሚገኙ ትናንሽ ነጫጭ ጎጆዎች የሚገኙባቸውን ወጣ ገባ ደሴቶች አንድ ገጣሚ “ጋማቸው የሚዘናፈል የድንጋይ ፈረሶች” ሲል ገልጿቸዋል።
እነዚህ ደሴቶች በዓለም ላይ ከሚገኙት የታወቁ የቱሪስት መስህቦች መካከል መሆናቸው ምንም አያስገርምም! በዚያ የሚኖሩና የሚሠሩ ወንዶችና ሴቶች ያሏቸው ግሩም የሆኑ ባሕርያት የእነዚህን ደሴቶች መልከዓ ምድራዊ ውበት ይበልጥ አጉልተውታል። በጣም ግልጽ፣ እንግዳ ተቀባይና በራሳቸው የሚመሩ የሆኑት የደሴቶቹ ነዋሪዎች አካባቢውን ይበልጥ ልዩ አድርገውታል።
አብዛኞቹ የደሴቶቹ ነዋሪዎች የሚተዳደሩት ከኤጂያን ባሕር ውኃዎች ዓሣ በማስገር ነው። ሆኖም በጣም አስፈላጊ የሆነ ሌላ ዓይነት “የማጥመድ” ሥራ በአካባቢው አመርቂ ውጤት እያስገኘ ነው። “ሰዎችን አጥማጆች” የሆኑት የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚሰብኩት ወንጌላውያን በኤጂያን ደሴቶች በመንቀሳቀስ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት በማፍራት ላይ ናቸው።—ማቴዎስ 4:18, 19፤ ሉቃስ 5:10
ከ19 መቶ ዓመታት በፊት ክርስቲያን ወንጌላውያን የኤጂያንን ደሴቶች ጎብኝተው ነበር። በ56 እዘአ ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ ከሦስተኛ የሚስዮናዊ ጉዞው ሲመለስ እግረ መንገዱን ወደ ሌስቮስ፣ ኪዩ፣ ሳሞን፣ ቆስ እና ሩድ ደሴቶች ለአጭር ጊዜ ጎራ ብሎ ነበር። ምንጊዜም ቀናተኛ ሰባኪ የነበረው ጳውሎስ ለአንዳንዶቹ የደሴቶቹ ነዋሪዎች ሰብኮላቸው መሆን አለበት። (ሥራ 20:14, 15, 24፤ 21:1, 2) ጳውሎስ በሮም ለሁለት ዓመት በእስር ከቆየ በኋላ ወደ ቀርጤስ እንደሄደና በዚያ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴውን እንደቀጠለ የታወቀ ነው። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሊያበቃ ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ሐዋርያው ዮሐንስ “ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር” በፍጥሞ ደሴት ታስሮ ነበር። (ራእይ 1:9) ዛሬ ያሉ የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪዎች በእነዚህ ደሴቶች እያደረጉ ያለው እንቅስቃሴስ ምን ይመስላል?
አስደሳች የስብከት ዘመቻ
በእነዚህ ደሴቶች መስበክ አስቸጋሪና ተፈታታኝ ነው። ከፍተኛ ጥረትና መሥዋዕትነት ይጠይቃል። አንዳንዶቹ ደሴቶች በጣም የተራራቁ ናቸው። ከእነዚህ ደሴቶች ወደ አንዳንዶቹ የሚሄድ የአየርም ሆነ የባሕር ትራንስፖርት የሚገኘው እንደ አጋጣሚ ከስንት አንዴ ሲሆን ወደ ተቀሩት ደግሞ በተለይ በክረምት ወቅት ጭራሽ መጓጓዣ የሚባል አይገኝም። በተለይ ሜልተምያ የተባለው የሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ኃይለኛ ነፋስ በሚነፍስበት ወቅት የባሕሩ ሞገድ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ በደሴቶቹ ላይ ያሉት መንደሮች የተበታተኑ ሲሆኑ አቧራማና ኮረኮንቻማ የሆኑት መንገዶች ለጉዞ በጣም አስቸጋሪ ናቸው። በትናንሽ ጀልባ ካልሆነ በስተቀር ወደ አንዳንዶቹ መንደሮች መሄድ ፈጽሞ አይቻልም።
ለምሳሌ ያህል የኢካሪያን ደሴት እንውሰድ። እዚያ በሚገኘው አነስተኛ ጉባኤ ውስጥ ያሉ 11 የመንግሥቱ ምሥራች አስፋፊዎች በደሴቲቱና በአቅራቢያዋ ባሉ ትናንሽ ደሴቶች ላይ የሚገኙ መንደሮችን በሙሉ መሸፈን አልቻሉም።
ስለሆነም በኢካሪያ እንዲሁም በፈርኖይ፣ በፍጥሞና በሊፕሶስ ለሚገኙ ሰዎች በመስበክ ይረዷቸው ዘንድ በሳሞን የሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞችና እኅቶች መጡ። በቅርቡ በተደረገ በእንዲህ ዓይነቱ የሁለት ቀን ዘመቻ ምሥክሮቹ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገሩ 650 መጽሔቶችን፣ 99 ብሮሹሮችን እንዲሁም 25 መጻሕፍትን አበርክተዋል! ይሖዋ ማን እንደሆነ ጨርሶ የማያውቁና እዚያ ሰንብተው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ እንዲያስተምሯቸው የሚለምኗቸው ሰዎች በማግኘታቸው ወንድሞች በጣም ተገርመዋል። አንዲት ሴት ለአንዲት ምሥክር “እሺ እናንተ አሁን ጥላችሁን ልትሄዱ ነው። ሆኖም እኔ ገና ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች አሉኝ። ታዲያ ማን ይረዳኛል?” ስትል ጠይቃታለች። እኅትም በስልክ እንደምታወያያት ቃል የገባችላት ሲሆን ይህች ሴት በዚህ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልትጀምር ችላለች።አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ኢካሪያን በጎበኘበት ወቅት መላ ደሴቲቱን በአንድ ቅዳሜና እሁድ ለመሸፈን ዝግጅት አደረገ። ከሳሞን ደሴት መጥተው የሚረዱ 30 የሚያክሉ የመንግሥቱ አስፋፊዎችን መዝግቦ ነበር። ከሳሞን የመጡት ወንድሞች ሁለት ቀን እዚያ ለሚያድሩበት ለሆቴል እንዲሁ ለአስቸጋሪ መንገድ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ መኪና ለመከራየት የሚጠይቀውን ወጪ ራሳቸው መሸፈን ነበረባቸው። ለሁለት ቀን ዶፍ ዝናብ የጣለ ሲሆን ስለ ቅዳሜና እሁድ የተሰጠው የአየር ሁኔታ ትንበያም መጥፎ ነበር። ሆኖም ወንድሞች “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፣ ደመናትንም የሚመለከት አያጭድም” የሚሉትን የመክብብ 11:4 ቃላት በማስታወስ ይህ ሁኔታ እንቅፋት እንዲሆንባቸው አልፈቀዱም። በመጨረሻም የአየሩ ጠባይ በመጠኑ መሻሻል ያሳየ ሲሆን ወንድሞች በጣም አስፈላጊ በሆነው መልእክታቸው መላ ደሴቲቱን ካዳረሱ በኋላ ተደስተውና ረክተው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።
በአንድሮስ ደሴት ያሉት 16 አስፋፊዎች መላ ደሴቲቱን ለመሸፈን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ሁለት ወንድሞች ገለል ብሎ ወደሚገኝ አንድ መንደር ሲደርሱ ለነዋሪዎቹ በሙሉ ለመስበክ ወሰኑ። ሰዎችን ቤታቸው፣ መንገድ ላይና በእርሻ ቦታቸው አነጋገሩ። ፖሊስ ጣቢያ ሳይቀር ገብተው ጽሑፍ አበረከቱ። የመንደሩን ነዋሪዎች በሙሉ እንዳነጋገሩ በማመን ከመንደሩ ሊወጡ ሲሉ አንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ሲመጣ ተመለከቱ። ምሥክርነቱ እንዳልተሰጠው በመገንዘብ አንድ አነስተኛ ጽሑፍ አበረከቱለት፤ እሱም በደስታ ተቀበለ። አሁን ለመስበክ ባደረጉት ጥረት ማንንም ሰው እንዳላለፉ እርግጠኛ ሆኑ!
ጋቨደስ (ወይም ቄዳ) የደቡባዊ አውሮፓ ጫፍ እንደሆነች ተደርጋ የምትታይ 38 ነዋሪዎች ብቻ ያላት በቀርጤስ አቅራቢያ የምትገኝ አነስተኛ ደሴት ናት። (ሥራ 27:16) አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካችና ሚስቱ ከሌላ አንድ ባልና ሚስት ጋር ሆነው በዚያ ሦስት ቀን ሰበኩ። ወጪ ለመቀነስ ሲሉ በድንኳን ይተኙ ነበር። ነዋሪዎቹ በሙሉ ምሥራቹ የደረሳቸው ሲሆን በዚያ የሚኖሩት ሰዎች መሠረተቢስ ጥላቻ የሌላቸው መሆናቸው ወንድሞችን በጣም አስደሰታቸው። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ጥሩም ሆነ መጥፎ ምንም የሰሙት ነገር አልነበረም። አንድን ቄስ ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች 19 መጻሕፍትንና 13 ብሮሹሮችን ወስደዋል። ምሥክሮቹ በጀልባ ወደ ቀርጤስ እየተመለሱ ሳሉ ባሕሩ በመናወጡ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወደቀ። “በሕይወት ወደ ቤት ለመመለስ በመቻላችን ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ ደቡባዊ ጫፍ ስሙን እንድናስከብር ስለፈቀደልን ይሖዋን አመሰገንነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ፍጥሞ፣ ዮሐንስ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የራእይን መጽሐፍ የጻፈባት ደሴት ናት። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በፍጥሞ ደሴት አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። በሳሞን የሚገኙ ወንድሞች በዚህች ደሴት ላይ አንዴ በዘመቻ የሚሰብኩበትን መንገድ ጥሩ አድርገው አደራጁ። ደሴቲቱ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠንካራ ይዞታ ስለሆነች ወንድሞች ከባድ ተቃውሞ እንደሚገጥማቸው ያውቁ ነበር። ሁለት እኅቶች ለአንዲት ሴት ምሥራቹን እየነገሯት ሳሉ ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። የሴትዬዋ ባል እኅቶችን ማን ወደ ቤቱ እንደላካቸው አጥብቆ ጠየቀ። እያንዳንዱን
ቤት እያዳረሱ እንዳለ ቢነግሩትም “ከጎረቤት ወደ እኛ የላካችሁ ሰው የለም ነው የምትሉኝ?” ሲል በድጋሚ ጠየቃቸው። ዛየር በነበረችበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችን ታውቅ የነበረችው ሚስቱ በዚያን ዕለት ጠዋት ምን እንደተከሰተ ነገረቻቸው። “በሌሎች ቀናት አደርግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬ ጠዋትም የይሖዋ ምሥክሮችን ወደዚህ ደሴት እንዲልክ ወደ ይሖዋ ስጸልይ ነበር። ባለቤቴ በዚህ የተነሳ ሲስቅብኝ ነበር። በሩን ስከፍት እናንተን ስናይ እኔም ባለቤቴም በጣም ተገረምን። ወደ እዚህ የላካችሁ ማን ነው እያለ አጥብቆ የጠየቃችሁ ለዚህ ነው” ስትል አጫወተቻቸው። ለሴትየዋ ወዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላት። ምንም እንኳ ለእኅትም ሆነ ለሴትየዋ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም ከአሥር ለሚበልጡ ወራት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ የተመራው በስልክ ነበር። ይህች ሴት የተጠመቀች ሲሆን ከ1, 900 ዓመታት በፊት ሐዋርያው ዮሐንስ በተገለለባት በዚህች ደሴት በአሁኑ ጊዜ የምትገኝ ብቸኛ የይሖዋ ምሥክር እሷ ነች።በወደቦች ላይ ‘ማጥመድ’
የበጋ ዕረፍታቸውን በዚያ ለማሳለፍ የሚመጡ ተጓዦችን የጫኑ የመጓጓዣ መርከቦች በኤጂያን ደሴቶች በሚገኙ በርካታ ወደቦች ይቆማሉ። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ከተለያዩ አገሮች የመጡና የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን የማግኘት ልዩ አጋጣሚ አላቸው። ጉባኤዎች በተለያየ ቋንቋ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የሚያዝዙ ሲሆን አስፋፊዎች በሺዎች የሚቆጠሩ መጽሔቶችን ለቱሪስቶች ያበረክታሉ። አንዳንድ የመጓጓዣ መርከቦች በየሳምንቱ በተደጋጋሚ ወደ አንድ ወደብ ይመጣሉ። ይህም ወንድሞች ለአንዳንድ የመርከቡ ሠራተኞች ተመላልሶ መጠየቅ እንዲያደርጉ አልፎ ተርፎም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመሩ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።
በሩድ ደሴት የሙሉ ጊዜ ሰባኪ የሆነች አንዲት እኅት ሁልጊዜ ዓርብ ዓርብ እዚያ ወደብ መጥቶ በሚቆም የመጓጓዣ መርከብ ላይ ለሚሠራ ጃማይካዊ ወጣት በ1996 የበጋ ወቅት መሰከረችለት። በሚቀጥለው ዓርብ ይህ ወጣት በደሴቲቱ ላይ ሊካሄድ በታቀደው የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ተጋበዘ አቅኚዋ እኅት የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ይዛ በፕሮግራሙ ላይ የሚቀርቡትን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች እንዲያስተውሉ ረዳችው። በስብሰባው ላይ የተገኙት ምሥክሮች ሞቅ ያለ ፍቅር የዚህን ወጣት ልብ በእጅጉ ነካው። በሚቀጥለው ዓርብ ሁለት አቅኚዎች ወደ መርከቡ እንዲመጡ ጋበዛቸው። አቅኚዎቹ በእንግሊዝኛና በስፓንኛ የተዘጋጁ ጽሑፎችን ይዘው ሄዱ። ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በአገልግሎት ቦርሳቸው ውስጥ የያዙትን ጽሑፍ በሙሉ ጨረሱ! ጃማይካዊው ወጣት የበጋው ወቅት እስኪያበቃ
ድረስ ሁልጊዜ ዓርብ ዓርብ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱን ቀጠለ። በቀጣዩ የበጋ ወቅት ተመልሶ መጣና ጥናቱን ካቆመበት እንደገና ቀጠለ። ሆኖም በዚህ ወቅት ተጨማሪ መንፈሳዊ ዕድገት ማድረግ ይችል ዘንድ ሥራውን ለመቀየር ወሰነ። ከዚያም ሄደ። በሩድ የሚገኙ ወንድሞች ይህ ወጣት በ1998 መጀመሪያ ላይ መጠመቁን ሲሰሙ ምንኛ ተደስተው ይሆን!ስደተኛ “ዓሣ” ማጥመድ
የኤጂያን ባሕር እንደ ሰርዲንና ስዎርድፊሽ ያሉት ስደተኛ ዓሦች በብዛት የሚገኙበት ባሕር ሲሆን እነዚህ ዓሦች ተሰድደው ወደዚህ ባሕር ከገቡ በኋላ ከፍተኛ ችሎታ ባላቸው ዓሣ አስጋሪዎቸ መረብ ውስጥ ይገባሉ። በተመሳሳይም የመንግሥቱ ወንጌላውያን ከበርካታ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ተሰድደው ወደ ግሪክ ከመጡ ስደተኛ ሠራተኞች መካከል በርካታ ተቀባይ ልብ ያላቸው ሰዎች አግኝተዋል።
ሪዚ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች አማካኝነት ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበበችው ገና የአሥር ዓመት ልጅ ሳለች ነበር። ይህም በአልባንያ እያለች ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ ሩድ ደሴት መጣች። በዚያም ከሕዝቦቹ ጋር እንዲያገናኛት አንድ ቀን ወደ ይሖዋ ጸለየች። ደስ የሚለው በሚቀጥለው ቀን የሪዚ አባት እነዚያን የምታውቃቸውን መጽሔቶች (መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ማለት ነው) ይዞ መጣ። ሪዚ ለአባቷ መጽሔቶቹን ከሰጡት እኅቶች ጋር ተዋወቀችና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ወዲያው ጥናት ጀመረች። አንዳንዴ በቀን ሦስት ጊዜ እንዲያስጠኗት ትጠይቅ ነበር! ከሁለት ወር በኋላ ያልተጠመቀች አስፋፊ ሆነች። ከዚያም መጋቢት 1998 በ14 ዓመት ዕድሜዋ ተጠመቀች። በዚያው ዕለት ረዳት አቅኚ ሆነች፤ ከስድስት ወር በኋላ ለዘወትር አቅኚነት ወይም ለሙሉ ጊዜ አገልጋይነት ተመዘገበች።
በቆስ ደሴት የሚገኝ አንድ ወንድም ከሩሲያ የመጡ ሰዎችን ያስጠና ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚፈልጉ ሌሎች ጓደኞች እንዳሏቸው ሲጠይቃቸው 30 ኪሎ ሜትር ርቀው ወደሚገኙት ሊአንደስ እና ኦፍሊ የተባሉ አርመናውያን ባልና ሚስት መሩት። ወንድሞች እዚያ ሲደርሱ ያጋጠማቸው ነገር የሚያስገርም ነበር። አርመናውያኑ ባልና ሚስት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ያሳተማቸውን በአርመንኛና በሩሲያ ቋንቋ የተዘጋጁ አንድ ሻንጣ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አሳዩአቸው! ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ እንደነበረና ያልተጠመቁ አስፋፊዎች እስከ መሆን ደርሰው እንደነበር ነገሯቸው። ወደዚህ የመጡት አገራቸው በተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋትና የኢኮኖሚ ችግር የተነሳ ነበር። ወንድሞች ወደ ቆስ እንደደረሱ መጀመሪያውንም እዚያ ይኖሩ የነበሩትን የሊአንደስን እናትና እኅት ጥናት አስጀመሯቸው። ወንድም በአንድ ጊዜ ሦስት አዳዲስ ጥናቶች አገኘና ኦፍሊን፣ ሊአንደስን እንዲሁም የሊአንደስን እናትና እኅት ማስጠናት ጀመረ። እነዚህን ጥናቶች ለመምራት በሳምንት ሦስት ጊዜ ሲሄድ ወይ ሲመለስ ብቻ 30 ኪሎ ሜትር በሞተር ብስክሌት መጓዝ ነበረበት። ሊአንደስ እና ሚስቱ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ተጠመቁ። በደሴቲቱ ላይ የሚኖሩት ወንድሞች የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረጋቸው ምንኛ ክሷቸዋል!
ይሖዋ ያሳድጋል
በኤጂያን ደሴቶች የሚገኙ 2, 000 የሚያክሉ ንቁ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ያለመታከት ያደረጉትን ጥረት ይሖዋ እንደባረከው ግልጽ ነው። በአሁኑ ጊዜ በእነዚህ አካባቢዎች 44 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎችና 25 ቡድኖች ይገኛሉ። የይሖዋ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ” እንደመሆኑ መጠን ከቡድኖቹ መካከል 17ቱ በሌላ አገር ቋንቋ የሚመሩ ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) በተጨማሪም በእነዚህ ተበታትነው በሚገኙ የአገልግሎት ክልሎች የሚኖሩ ብዙ ተጨማሪ ሰዎችን ለማነጋገር 13 ልዩ አቅኚዎች ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የኤጂያን ባሕር ለበርካታ መቶ ዘመናት የባሕላዊ ዕድገትና የንግድ ልውውጥ ማዕከል ሆኖ ቆይቷል። ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ለመዝናናት የሚጎርፉበት አካባቢ ሆኗል። ከሁሉም በላይ ግን የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች “ሰዎችን አጥማጆች” እንደመሆናቸው መጠን በእነዚህ ደሴቶች ላይ ይሖዋን የሚያወድሱ በርካታ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ማግኘት ችለዋል። “ለእግዚአብሔር ክብር ይስጡ፣ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ” ለሚለው ትንቢታዊ ግብዣ ከፍተኛ ምላሽ ሰጥተዋል።—ኢሳይያስ 42:12
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የኤጂያን ባሕር
ግሪክ
ሌስቮስ
ኪዩ
ሳሞን
ኢካሪያ
ፈርኖይ
ፍጥሞ
ቆስ
ሩድ
ቀርጤስ
ቱርክ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሌስቮስ ደሴት
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፍጥሞ ደሴት
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቀርጤስ ደሴት