“ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የምታውቁት አላችሁ”
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የምታውቁት አላችሁ”
ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ በኢየሩሳሌም ከነበሩ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በድፍረት ሲነጋገር ‘የሰሙት ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገርመዋል።’ (ሉቃስ 2:47) ዛሬም በተመሳሳይ ብዙ ወጣት የይሖዋ አገልጋዮች ለአስተማሪዎቻቸውና አብረዋቸው ለሚማሩ ተማሪዎች በድፍረት ስለ አምላክና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገሩ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የዚያኑ ያህል አስደሳች ውጤቶች ያጋጥሟቸዋል።
የ14 ዓመቷ ቲፈኒ ባለችበት ክፍል ውስጥ በዳንኤል 9:24-27 ላይ ስለሚገኘው የ70ዎቹ ሳምንታት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውይይት ተነሣ። አስተማሪው ስለ እነዚህ ቁጥሮች ጥቂት ነገር ተናግሮ ለማለፍ ሞከረ።
በመጀመሪያ ቲፈኒ እጇን ለማውጣት አመንትታ ነበር። “ሆኖም ጥቅሶቹ በሚገባ አለመብራራታቸው ከነከነኝ። ከዚያም ሳላስበው እጄን አወጣሁ” ብላለች። አብዛኞቹ ተማሪዎች ጥቅሱን ለመረዳት ተቸግረው ስለነበረ በዚህ ርዕስ ላይ ሐሳብ ለመሰንዘር የሚፈልግ ሰው በመኖሩ አስተማሪው ተደነቀ።
ቲፈኒ ትንቢቱን ለማብራራት አጋጣሚው ስለተሰጣት ከመቀመጫዋ ተነስታ ድንገተኛ ንግግር አቀረበች። ስትጨርስ በክፍሉ ውስጥ ፍጹም ጸጥታ ሰፍኖ የነበረ ሲሆን ቲፈኒም ትንሽ ፈርታ ነበር። ወዲያው ክፍሉ በደማቅ ጭብጨባ ተናወጠ።
አስተማሪው ደግሞ ደጋግሞ “በጣም የሚደነቅ ነው ቲፈኒ በጣም የሚደነቅ ነው” አለ። ምንም እንኳን ተጨማሪ ማብራሪያ ሊኖረው እንደሚችል ቢያውቅም እነዚህን ቁጥሮች በግልጽ ያብራራችለት የመጀመሪያዋ ሰው ቲፈኒ እንደሆነች ሳይሸሽግ ተናግሯል። አስተማሪው ከትምህርቱ በኋላ ቲፈኒ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል እንዴት ልታውቅ እንደቻለች ጠየቃት።
“የይሖዋ ምሥክር ስለሆንኩ ነው” በማለት መልስ ሰጠች። “ወላጆቼ ትንቢቱ ግልጽ እስኪሆንልኝ ድረስ ደጋግመው አስረድተውኛል።”
አብረዋት የሚማሩትም ቢሆኑ ቲፈኒ ባላት የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በጣም ተደንቀዋል። አንዲት ተማሪ “እናንተ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት የምትሄዱት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የምታውቁት ነገር ስላላችሁ መሆኑን የተገነዘብኩት አሁን ነው” ብላታለች። ሌሎችም ከዚህ በኋላ በእምነቷ ምክንያት ፈጽሞ እንደማያሾፉባት ቃል ገቡ።
ቲፈኒ ያጋጠማትን ለወላጆቿ ስትነግራቸው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ለአስተማሪዋ እንድታበረክት ሐሳብ አቀረቡላት። እርሷም መጽሐፉን ወስዳ የዳንኤልን ትንቢት የሚያብራራውን ክፍል ለአስተማሪዋ ስታሳየው ወዲያው ተቀበላትና ስለ መጽሐፉ አመሰገናት።
በእርግጥም ክርስቲያን ወጣቶች ስለ አምላክና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆቻቸው ያስተማሯቸውን ለሌሎች በድፍረት የሚናገሩ ከሆነ ለይሖዋ ምስጋናና ክብር ለራሳቸው ደግሞ በረከትን ያተርፋሉ።—ማቴዎስ 21:15, 16