በሴኔጋል ክርስቲያናዊ ተስፋን ለሌሎች ማካፈል
ከሚያምኑት ወገን ነን
በሴኔጋል ክርስቲያናዊ ተስፋን ለሌሎች ማካፈል
ዓሣ ከጥንት ጀምሮ ዋና ምግብ ሆኖ ቆይቷል። ሰዎች ለብዙ ሺህ ዓመታት ከባሕር፣ ከሐይቆችና ከወንዞች ዓሣ ሲያጠምዱ ኖረዋል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አንዳንዶቹ በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ አጥማጆች ነበሩ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሌላ ዓይነት ዓሣ የማጥመድ ሥራ አስተዋወቃቸው። ይህም አጥማጆቹን ብቻ ሳይሆን ዓሣውንም የሚጠቅም መንፈሳዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ነው።
ኢየሱስ ዓሣ አጥማጅ የነበረውን ጴጥሮስን “ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” ብሎት ነበር። (ሉቃስ 5:10) ዛሬ ይህ ዓይነቱ የማጥመድ ሥራ ሴኔጋልን ጨምሮ ከ230 በሚበልጡ አገሮች በመከናወን ላይ ይገኛል። (ማቴዎስ 24:14) በዚህ ዘመን የሚገኙ “ሰዎችን አጥማጆች” ክርስቲያናዊ ተስፋቸውን በድፍረት ለሌሎች ያካፍላሉ።—ማቴዎስ 4:19
ሴኔጋል በምዕራብ አፍሪካ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ትገኛለች። በስተሰሜን ሳሃራን ከሚያዋስኑት አሸዋማ በረሃ ክልሎች አንስቶ በስተደቡብ እርጥበት አዘል እስከሆነው የካዛማንስ ጥቅጥቅ ደን ድረስ ተንጣሎ ይገኛል። ሴኔጋል ደረቅ የሆነው የበረሃ ንፋስ እንዲሁም ቀዝቃዛና ነፋሻማ የሆነው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ነፋስ የሚነፍስባት አገር ናት። በዚህች አገር ከዘጠኝ ሚልዮን የሚበልጥ ሕዝብ ይኖራል። የሴኔጋል ሕዝብ በእንግዳ ተቀባይነቱ ይታወቃል። አብዛኛው ሕዝብ ክርስቲያን ነን ከሚሉት ወገን አይደሉም። ብዙዎቹ በግ አርቢዎች ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ የቀንድ ከብቶች፣ ግመሎችንና ፍየሎችን ያረባሉ። በተጨማሪም ለውዝ፣ ጥጥና ሩዝ የሚያመርቱ ገበሬዎች ይገኛሉ። ዓሣ አጥማጆችም ከአትላንቲክ ውቅያኖስና በአገሪቱ እየተጠማዘዙ ከሚፈስሱ በርካታ ትላልቅ ወንዞች መረቦቻቸውን በዓሣ ሞልተው ያመጣሉ። የዓሣ ምርት ኢንዱስትሪ በሴኔጋል ኢኮኖሚ ውስጥ በጣም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። እንዲያውም ቺብ ጀን የሚባለው ጣፋጭ ምግብ ከሩዝ፣ ከዓሣና ከአትክልት የሚዘጋጅ ተወዳጅ ባህላዊ ምግብ ነው።
“ሰዎችን አጥማጆች”
ሴኔጋል ውስጥ የአምላክን መንግሥት በቅንዓት የሚሰብኩ 863 አስፋፊዎች ይገኛሉ። በዚህ አገር መንፈሳዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራ የተጀመረው በ1950ዎቹ መጀመሪያ ነበር። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በ1965 በዋና ከተማው ዳካር ቅርንጫፍ ቢሮ ከፈተ። ሚስዮናውያን “አጥማጆች” በጣም ሩቅ ከሆኑ አገሮች መምጣት ጀመሩ። በሴኔጋል “የማጥመዱ” እንቅስቃሴ በመጀመሩ ክርስቲያናዊ ተስፋን የማካፈሉ ሥራ ያለማቋረጥ ወደፊት ገፋ። ከጊዜ በኋላ ዳካር ዳርቻ አልማድየስ በተባለ ቦታ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ተገንብቶ ሰኔ 1999 ለይሖዋ አገልግሎት ተወሰነ። እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ነበር!
እውነትን ለመቀበል የሚያጋጥም ዕንቅፋት
ዘወትር የተለያየ አስተዳደግና ችሎታ ካላቸው ሰዎች ጋር የምንገናኝ ሲሆን አንዳንዶቹ የአምላክ ቃል ለያዘው የተስፋ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ። ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ባይኖራቸውም ይሖዋ አምላክ ጥንት ለነበሩት ታማኝ ነቢያት የሰጠው ተስፋ በቅርቡ እንደሚፈጸም ሲማሩ ደስ ይላቸዋል።
በተለይ የቤተሰብ ባህልና ልማድ ተጽዕኖ ሲያጋጥም ለክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የጸና አቋም መያዝ ድፍረት ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል በሴኔጋል ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት በጣም የተለመደ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲጀምር ሁለት ሚስቶች የነበሩትን የአንድ ሰው ሁኔታ ተመልከት። የአንዲት ሚስት ባል ይሁን ከሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ ጋር ተስማምቶ በመኖር ክርስቲያናዊውን እውነት የመቀበል ድፍረት ይኖረው ይሆን? (1 ጢሞቴዎስ 3:2) እንዲሁም ከጉብዝና ሚስቱ ማለትም መጀመሪያ ካገባት ሚስቱ ጋር ይቀጥል ይሆን? ያደረገው ይህንኑ ነው። አሁን ዳካር አካባቢ ከሚገኙ ትላልቅ ጉባኤዎች መካከል በአንዱ ቀናተኛ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነው። በተጨማሪም የመጀመሪያ ሚስቱ ከ12 ልጆቹ ጋር እውነትን የተቀበለች ሲሆን አሥሩ ከመጀመሪያ ሚስቱ ሁለቱ ደግሞ ሁለተኛ ሚስቱ ከነበረችው የተወለዱ ናቸው።
ክርስቲያናዊ ተስፋን ለመቀበል መሰናክል ሊሆን የሚችለው ሌላው ነገር ደግሞ መሃይምነት ነው። ያልተማረ ሰው እውነትን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ አይችልም ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። እስቲ ስምንት ትንንሽ ልጆች ያሏትን ማሪ የተባለች ትጉህ እናት ምሳሌ ተመልከት። በየዕለቱ ልጆቿ ወደ ትምህርት ቤት እርሷም ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ውይይት ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደባትም። ይሁን እንጂ ማንበብ ስለማትችል እንዴት ይህን
ማድረግ ትችላለች? በየዕለቱ ጧት በማለዳ እየተነሳች ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር የተባለውን ቡክሌት ይዛ ከቤቷ ፊት ለፊት በሚገኘው አሸዋማ መንገድ ላይ ትቆማለች። ሰዎች በዚያ ሲያልፉ ማንበብ ይችሉ እንደሆነ ትጠይቃቸዋለች። ማንበብ የሚችል ሰው ስታገኝ ቡክሌቱን ትሰጥና “እባክህ ማንበብ ስለማልችል ይህንን ክፍል ልታነብልኝ ትችላለህ?” ብላ አጥብቃ ትለምነዋለች። ሲነበብ በጥሞና ታዳምጣለች። ከዚያ መንገደኛውን ታመሰግንና ልጆቿ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት በጥቅሱ ላይ አስደሳች ውይይት ለማድረግ ፈጥና ወደ ቤት ትገባለች!ሁሉም ዓይነት ሰዎች ምላሽ ይሰጣሉ
በሴኔጋል ሰዎችን መንገድ ላይ ተቀምጠው ዓሣ፣ አትክልት ወይም ፍራፍሬ ሲሸጡ ወይም ግርማ ሞገስ በተላበሰው የባኡባብ ዛፍ ስር ጋደም ብለው ትንሽ መረር የሚለውን አታይ የተባለ አረንጓዴ ሻይ ሲጠጡ ማየት የተለመደ ነው። ሁለት ወንድሞች፣ ለሚያገኙት ሰው ሁሉ ምሥራቹን ማካፈል እንዳለባቸው በማሰብ መንገድ ላይ ተቀምጦ የሚለምን አንድን የአካል ጉዳተኛ አነጋገሩ። ሰላምታ ካቀረቡለት በኋላ እንዲህ አሉ:- “ብዙ ሰዎች ሳንቲም ወርወር አድርገውልህ ያልፋሉ እንጂ ቆመው አያነጋግሩህም። እኛ የመጣነው የወደፊቱ ጊዜህን በተመለከተ አንድ በጣም አስፈላጊ ነገር ልንነግርህ ነው።” ይህ ለማኝ በጣም ተገረመ። “አንድ ጥያቄ ልንጠይቅህ እንፈልጋለን” ሲሉ ወንድሞች ንግግራቸውን ቀጠሉ። “በዓለም ውስጥ መከራ የበዛው ለምንድን ነው ብለህ ታስባለህ?” ለማኙ “የአምላክ ፈቃድ ነው” በማለት መልስ ሰጠ።
ወንድሞች ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ካስረዱት በኋላ ራእይ 21:4ን አብራሩለት። ለማኙ በሰማው የተስፋ መልእክት እንዲሁም እርሱን ቆሞ ለማነጋገርና መጽሐፍ ቅዱስን ለማስረዳት ፍላጎት ያለው ሰው እንዳለ ሲገነዘብ በጥልቅ ተነካ። ዓይኖቹ እንባ አቀረሩ። ገንዘብ እንዲሰጡት በመጠየቅ ፋንታ በሚለምንበት ጣሳ ውስጥ ያጠራቀመውን ሳንቲም ሁሉ እንዲወስዱ ለመናቸው! አጥብቆ ይለምናቸው ስለነበር ሁኔታው በአካባቢው የሚያልፉ መንገደኞችን ትኩረት ሳበ። ወንድሞች ገንዘቡን ራሱ እንዲጠቀምበት ያሳመኑት በግድ ነበር። በመጨረሻ በዚህ ቢስማማም ተመልሰው እንዲጠይቁት አጥብቆ ለመናቸው።
በተጨማሪም በዳካር የሚገኘው ትልቅ ዩኒቨርሲቲ በመንፈሳዊው የማጥመጃ መረብ ተጨማሪ ዓሦችን ለመያዝ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ዣን ልዊ የተባለ የሕክምና ተማሪ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በአጭር ጊዜ ውስጥ እውነትን ተቀብሎ ሕይወቱን ለይሖዋ ወስኖ ተጠመቀ። ፍላጎቱ የሙሉ ጊዜ አቅኚ ሆኖ አምላክን ማገልገል ቢሆንም የሚማረውን የሕክምና ትምህርትም ይወደው ነበር። ከአገሩ ጋር አስቀድሞ በገባው ውል ምክንያት ትምህርቱን መጨረስ ግድ ሆነበት። ሆኖም ትምህርቱን እየተማረ በረዳት አቅኚነት ማገልገል ጀመረ። በሕክምና ሙያ ተመርቆ ዲፕሎማውን ካገኘ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአፍሪካ በሚገኝ አንድ ትልቅ የቤቴል ቤት ውስጥ የቤተሰብ ዶክተር ሆኖ እንዲያገለግል ተጋበዘ። ከዳካር ዩኒቨርሲቲ የተገኘው ሌላ ወጣትም እንዲሁ በዚያው በአገሩ በሚገኝ ቤቴል እያገለገለ ነው።
በሴኔጋል መንፈሳዊ ዓሣ የማጥመዱ ሥራ የሚክስ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁአቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በጣም ተወዳጅ ሲሆኑ ዎሎፍ በሚባል የአካባቢው ቋንቋም እየተዘጋጁ ነው። በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ምሥራቹን መስማታቸው ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች በአድናቆት ምላሽ እንዲሰጡ አደፋፍሯቸዋል። “ሰዎችን አጥማጆች” የሆኑት የሴኔጋል ቀናተኛ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ ተስፋቸውን በታማኝነትና በድፍረት ለሌሎች ማካፈላቸውን ሲቀጥሉ ይሖዋ ስለሚባርካቸው ብዙ ተጨማሪ ዓሣ መሰል ሰዎች እንደሚጠመዱ ምንም ጥርጥር የለውም።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሴኔጋል
[ሥዕል]
በሴኔጋል ክርስቲያናዊ ተስፋን ለሌሎች ማካፈል
[ምንጭ]
Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital wisdom, Inc.