አሳዳጁ ሰው ታላቅ ብርሃን አየ
አሳዳጁ ሰው ታላቅ ብርሃን አየ
ሳውል በኢየሱስ ተከታዮች ላይ በጣም ተቆጥቷል። በድንጋይ ተወግሮ የሞተውን እስጢፋኖስን ጨምሮ ኢየሩሳሌም በሚኖሩት ላይ የደረሰው ስደት አላረካ ብሎት አሁን ደግሞ ስደቱን ለማፋፋም የሚያስችል ፈቃድ ጠየቀ። “[ሳውል] ደቀ መዛሙርት[ን] እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፣ በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፣ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ።”—ሥራ 9:1, 2
መቼም ሳውል ወደ ደማስቆ የሚያደርገውን ጉዞ የተያያዘው የተሰጠውን ሥልጣን እንዴት ውጤታማ በሆነ መንገድ እንደሚጠቀምበት እያወጣና እያወረደ መሆን አለበት። ከሊቀ ካህናቱ የተቀበለው ሥልጣን በዚያች ከተማ በሚኖረው ትልቅ የአይሁድ ማኅበረሰብ መሪዎች በሚሰጡት ትብብር የተጠናከረ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። የእነርሱ እርዳታ ያስፈልገው ነበር።
ሳውል ወደ መድረሻው እየተቃረበ ሲሄድ መቼ በደረስኩ እያለ ሳይጓጓ አልቀረም። 220 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለውና በእግር ጉዞ ሰባት ወይም ስምንት ቀናት የሚፈጀው ከኢየሩሳሌም እስከ ደማስቆ ያለው ጉዞ ኃይል የሚያሟጥጥ መሆን አለበት። ወደ ቀትር አካባቢ ፀሐይዋ ከምትሰጠው ብርሃን ይበልጥ ደማቅ የሆነ ብርሃን በሳውል አካባቢ በድንገት አንጸባረቀና ሳውል መሬት ላይ ወደቀ። አንድ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ሳውል ሳውል፣ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል” ብሎ ሲናገረው ሰማ። እርሱም መልሶ “ጌታ ሆይ፣ ማን ነህ?” ብሎ ጠየቀ። “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ” የሚል መልስ መጣለት። “ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና። . . . ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።” “ጌታ ሆይ፣ ምን ላድርግ?” በማለት ሳውል ጠየቀ። “ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድና ታደርገው ዘንድ ስለ ታዘዘው ሁሉን በዚያ ይነግሩሃል” አለው።—ሥራ 9:3-6፤ 22:6-10፤ 26:13-17
ከሳውል ጋር አብረው ይጓዙ የነበሩት ሰዎች ድምፅ ሥራ 9:7-9፤ 22:11
የሰሙ ቢሆንም ተናጋሪውን አላዩም ወይም የተናገረውን ነገር አልተረዱም። ብርሃኑ ኃይለኛ ነጸብራቅ ስለነበረው ሳውል ከወደቀበት ሲነሳ ማየት ተስኖት ነበር። በዚህም የተነሳ እጁን ይዞ መምራት የግድ አስፈላጊ ሆነ። “ሳያይም ሦስት ቀን ኖረ፤ አልበላምም አልጠጣምም።”—ለሦስት ቀን ማሰላሰል
ሳውል ቅን በተባለ መንገድ በሚኖረው በይሁዳ ቤት እንግድነት ተቀመጠ። a (ሥራ 9:11) ይህ መንገድ በአረብኛ ደርብ አል-ሙስታኪም ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን አሁንም በደማስቆ ዋና ጎዳና ሆኖ ያገለግላል። ሳውል በይሁዳ ቤት ሳለ በአእምሮው ውስጥ ምን ነገር ይመላለስ እንደነበር ገምት። ሳውል የደረሰበት ሁኔታ ለዓይነ ስውርነት የዳረገው ከመሆኑም በላይ በጣም ደንግጧል። ይህ የደረሰው ነገር ምን ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ለማሰላሰል የሚያስችል ጊዜ አግኝቷል።
አሳዳጁ ፈጽሞ ካልገመተው አካል ጋር አሁን ተፋጥጧል። በአይሁድ ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት ዘንድ የተወገዘውና ‘በሰዎች ተንቆና ተጠልቶ’ የተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን በሕይወት አለ። እንዲያውም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ “ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን” በአምላክ ቀኝ ቆሟል! ኢየሱስ መሲሕ ነበር። እስጢፋኖስና ሌሎች የተናገሩት ነገር ትክክል ነበር። (ኢሳይያስ 53:3፤ ሥራ 7:56፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:16) ኢየሱስ ራሱን ሳውል ከሚያሳድዳቸው ሰዎች እንደ አንዱ አድርጎ መናገሩ ሳውል ሙሉ በሙሉ ተሳስቶ እንደነበር የሚያሳይ ነበር! እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች እያሉ ሳውል ‘የመውጊያውን ብረት መቃወሙን’ እንዴት ሊቀጥል ይችላል? አበያ በሬ እንኳ ከኋላ ወጋ ወጋ ሲደረግ ባለቤቱ እንዲሄድ በሚፈልገው መንገድ መሄዱ የማይቀር ነው። ስለዚህ ሳውል የኢየሱስን ማሳሰቢያ ለመቀበል አሻፈረኝ ቢል የሚጎዳው ራሱን ይሆናል።
ኢየሱስ መሲሕ እንደመሆኑ መጠን በአምላክ ዘንድ የተረገመ ሊሆን አይችልም። ሆኖም ይሖዋ ከሁሉም በሚከፋ የውርደት ሞት እንዲሞትና “በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነው” በሚለው የሞት ሕግ ሥር እንዲያልፍ ፈቅዷል። (ዘዳግም 21:23) ኢየሱስ የሞተው በተሰቀለበት እንጨት ላይ እንዳለ ነበር። ኢየሱስ ኃጢአት ያልነበረበት እንደመሆኑ መጠን በራሱ ኃጢአት ሳይሆን ለሰው ዘሮች ኃጢአት ሲል የተረገመ ሆነ። ከጊዜ በኋላ ሳውል እንዲህ በማለት አብራርቶታል:- “ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። . . . በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን።”—ገላትያ 3:10-13
የኢየሱስ መሥዋዕት የመቤዠት ዋጋ አለው። ይሖዋ ይህን መሥዋዕት መቀበሉ ሕጉንና እርግማኑን በምሳሌያዊ መንገድ በእንጨት ላይ የጠረቀው ያህል ነበር። ሳውል ይህን ሃቅ መቀበሉ “ለአይሁድ ማሰናከያ” የሆነውን የመከራ እንጨት እንደ “እግዚአብሔር ጥበብ” አድርጎ ከፍ አድርጎ ሊመለከተው ችሏል። (1 ቆሮንቶስ 1:18-25፤ ቆላስይስ 2:14) ስለዚህ መዳን የሚገኘው በሕጉ ሥራ ሳይሆን እንደ ሳውል ላሉ ኃጢአተኞች አምላክ በሚያሳየው ይገባናል በማንለው ደግነቱ ከሆነ ከጊዜ በኋላ ከሕጉ ውጭ ለሚገኙ ሰዎችም ክፍት መሆኑ የማይቀር ነበር። ኢየሱስም ሳውልን የላከው ወደ አሕዛብ ነበር።—ኤፌሶን 3:3-7
ሳውል በተለወጠበት ወቅት ከዚህ ውስጥ ምን ያክሉን ተገንዝቦ እንደነበር የምናውቀው ነገር የለም። ወደ አሕዛብ እንዲሄድ የተሰጠውን ተልዕኮ በተመለከተ ኢየሱስ እንደገና ምናልባትም ከአንድ ጊዜ በላይ ሳይነግረው አልቀረም። ከዚህም በላይ ሳውል በመንፈስ አነሳሽነት ይህን ሁሉ ዘገባ በጽሑፍ ከማስፈሩ በፊት በርካታ ዓመታት አልፈዋል። (ሥራ 22:17-21፤ ገላትያ 1:15-18፤ 2:1, 2) ሳውል ከአዲሱ ጌታው ተጨማሪ መመሪያዎችን ከማግኘቱ በፊት የተወሰኑ ቀናት አልፈዋል።
ሐናንያ ያደረገው ጉብኝት
ኢየሱስ ለሳውል ከተገለጠለት በኋላ ለሐናንያም ተገለጠለትና እንዲህ አለው:- “ተነሥተህ ቅን ወደሚባለው መንገድ ሂድ፣ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤ እነሆ፣ እርሱ ይጸልያልና፤ ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቶአል [“በራእይ ተመልክቷል፣” NW ] አለው።”—ሥራ 9:11, 12
ሐናንያ ሳውልን በዝና ያውቀው ስለነበር ኢየሱስ በተናገራቸው ቃላት መደነቁ የሚያስገርም አይደለም። እርሱም “ጌታ ሆይ፣ በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤ በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው አለ።” ሆኖም ኢየሱስ “ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ” አለው።—ሥራ 9:13-15
ይህን ማረጋገጫ ያገኘው ሐናንያ፣ ኢየሱስ በሰጠው አድራሻ መሠረት ጉዞውን ጀመረ። ሐናንያ ሳውልን ፈልጎ ካገኘው በኋላ እጁን ጫነበት። “ወዲያውም” ይላል ዘገባው “እንደ ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፣ ያን ጊዜም ደግሞ አየ።” አሁን ሳውል ለማዳመጥ ተዘጋጀ። ሐናንያ የተናገራቸው ቃላት ሳውል ቀደም ሲል ከኢየሱስ ቃላት የተረዳቸውን ነገሮች ሳያጠናክርለት አልቀረም። “የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና ጻድቁን ታይ ዘንድ ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ አስቀድሞ መርጦሃል ባየኸውና በሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆንለታለህና። አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ።” ውጤቱስ ምን ሆነ? “ተነሥቶም ተጠመቀ፣ መብልም በልቶ በረታ።”—ሥራ 9:17-19፤ 22:12-16
ታማኙ ሐናንያ የተሰጠውን ተልዕኮ ከፈጸመ በኋላ ከታሪክ መድረክ የጠፋ ሲሆን ከዚያ በኋላ ዳግመኛ ስለ እርሱ የሚናገር ነገር የለም። ሆኖም ሳውልን የሰሙት ሁሉ በጣም ተገረሙ! የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ለመያዝ ወደ ደማስቆ የመጣው የቀድሞው አሳዳጅ በምኩራብ ውስጥ መስበክና ኢየሱስ፣ ክርስቶስ መሆኑን ማስረዳት ጀመረ።—ሥራ 9:20-22
“የአሕዛብ ሐዋርያ”
ሳውል ወደ ደማስቆ በመጓዝ ላይ ሳለ የገጠመው ነገር የአሳዳጅነት ዓላማውን አስለውጦታል። ሳውል የመሲሑን ማንነት ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት በርካታ ሐሳቦችና ትንቢቶች እንዴት በኢየሱስ ላይ እንደሚሠሩ ሊያብራራ ይችላል። ኢየሱስ ለእርሱ መገለጡና ‘እርሱን መያዙ’ እንዲሁም “የአሕዛብ ሐዋርያ” የመሆንን ተልዕኮ ለእርሱ መስጠቱ የሳውል ሕይወት በእጅጉ እንዲለወጥ አድርጓል። (ፊልጵስዩስ 3:12፤ ሮሜ 11:13) አሁን ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የሚታወቀው ሰው በምድር ላይ ያሳለፈውን የቀረውን የሕይወት ዘመኑን ብቻ ሳይሆን የክርስትናን ታሪክ የመለወጥ መብትና ሥልጣን አግኝቷል።
ከዓመታት በኋላ በጳውሎስ ሐዋርያነት ላይ ጭቅጭቅ በተነሳ ጊዜ ወደ ደማስቆ ይጓዝ በነበረበት ወቅት ያጋጠመውን ተሞክሮ በመጥቀስ ለሥልጣኑ ተሟግቷል። “ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንስ አላየሁትምን?” በማለት ጠየቀ። ኢየሱስ ትንሣኤ አግኝቶ ለሌሎች መታየቱን ከገለጸ በኋላ ሳውል (ጳውሎስ) “ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ” በማለት ተናገረ። (1 ቆሮንቶስ 9:1፤ 15:8) ሳውል የኢየሱስን ሰማያዊ ክብር መመልከቱ ጊዜው ከመድረሱ በፊት ተወልዶ ወይም ትንሣኤ አግኝቶ መንፈሳዊ ሕይወት ያገኘ ያህል ነበር።
ሳውል ይህን መብቱን ከፍ አድርጎ የተመለከተው ከመሆኑም በላይ ከዚህ መብት ጋር ተስማምቶ ለመኖር ታግሏል። “እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፣ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤ ነገር ግን . . . ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው [የእግዚአብሔር] ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው [ከሌሎቹ ሐዋርያት] ይልቅ ግን ደከምሁ” በማለት ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 15:9, 10
ምናልባት እንደ ሳውል አንተም የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ለረዥም ጊዜ ይዘኸው የነበረውን ሃይማኖታዊ አመለካከት ማስተካከል እንደሚኖርብህ የተገነዘብክበትን ጊዜ ታስታውስ ይሆናል። እውነትን መቅሰም ትችል ዘንድ ይሖዋ ላደረገልህ እርዳታ አመስጋኝ እንደነበርክ ምንም ጥርጥር የለውም። ሳውል ብርሃኑን ሲያይና ከእርሱ ምን እንደሚጠበቅበት በተገነዘበ ጊዜ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ አላመነታም። እንዲሁም በቀሪው የሕይወት ዘመኑ በሙሉ ይህንን በቅንዓትና በቁርጠኝነት አድርጓል። ዛሬም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ይህ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ይሆናቸዋል!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድ ምሁር ይሁዳ የአካባቢው የአይሁድ ማኅበረሰብ መሪ ወይም የአንድ ትንሽ ሆቴል ባለቤት ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ በደማስቆ የሚገኘው ቅን የተባለው ጎዳና
[ምንጭ]
Photo by ROLOC Color Slides