በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ድህነት

ድህነት

ድህነትን ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም በድህነት እየማቀቁ ነው።

ድሆች ደስተኛ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

ሰዎች ምን ይላሉ?

ብዙ ሰዎች ደስታና እርካታ የሚገኘው በቁሳዊ ሀብት እንደሆነና እውነተኛ ስኬት የሚለካው ደግሞ አንድ ሰው ባለው የገንዘብ መጠን እንደሆነ ይሰማቸዋል። ስለሆነም በድህነት እየማቀቁ ያሉ ሰዎች የመማር አጋጣሚና በቂ ሕክምና እንደ ልብ ማግኘት ሳይችሉ እንዲሁም ሌሎች የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ሳይሟሉላቸው ደስታና እርካታ ያለው ሕይወት ሊኖሩ አይችሉም ብለው ያስባሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አንድ ሰው እውነተኛ ደስታ ማግኘቱ የተመካው በኑሮ ደረጃው ሳይሆን ከፈጣሪው ጋር ባለው ዝምድና እንደሆነ ያስተምራል። መጽሐፍ ቅዱስ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው” ይላል። (ማቴዎስ 5:3) የኑሮ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን መንፈሳዊ ነገሮች እንደሚያስፈልጓቸው የሚሰማቸው ሰዎች አምላክ ስለተለያዩ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ለማወቅ ስለሚፈልጉ እውነተኛ ማጽናኛና የአእምሮ ሰላም የሚያስገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለመማር ይነሳሳሉ። ይህም እውነተኛ ደስታ ያስገኝላቸዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ተምረው ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ ድህነትን መቋቋም ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሰዎች ሲጋራ እንደማጨስና የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ እንደመጠጣት ካሉ ጎጂ ልማዶች እንዲርቁ ይረዳቸዋል። እነዚህ ልማዶች ገንዘብ የሚያባክኑ ከመሆናቸውም በላይ ከፍተኛ ወጪ ለሚጠይቅ ሕክምና ሊዳርጉ ይችላሉ።—ምሳሌ 20:1፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስግብግብነትና ቁሳዊ ሀብትን ማሳደድ ስላለው ጎጂ ውጤት ያስጠነቅቃል። (ማርቆስ 4:19፤ ኤፌሶን 5:3) እንዲህ ያለው ምክር አንድ ሰው ቁማር በመጫወት ገንዘቡን ከማባከን እንዲቆጠብ ሊረዳው ይችላል፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር” እንደሆነ ስለሚናገር እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ከማዳበር እንዲርቅ ይረዳዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:10) መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ንብረቱ ሕይወት ሊያስገኝለት አይችልም” የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (ሉቃስ 12:15) በአጭር አነጋገር የቱንም ያህል ገንዘብ ቢኖረን ሕይወትን መግዛት አንችልም። በሌላ በኩል ግን ጥበብ ካዘለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጋር ተስማምቶ መኖር ትርጉም ያለው ሕይወትና እውነተኛ ደስታ ያስገኛል።

በድህነት የሚኖሩ ሰዎች ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ለማግኘት ብዙ እንደሚደክሙ አይካድም፤ ያም ቢሆን ባላቸው ነገር ረክተው ለመኖር ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ ሕይወታቸው ፈጣሪያቸውን በማስደሰትና ከፈቃዱ ጋር ተስማምቶ በመኖር ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ደስታ ማግኘት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፤ እሱም ከበረከቱ ጋር ሥቃይን አይጨምርም” በማለት የገባውን ቃል እውነተኝነት ይገነዘባሉ።—ምሳሌ 10:22

ቁልፍ ጥቅስ፦ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው።”ማቴዎስ 5:3

ድህነት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሰዎች ድህነትን ለማስወገድ ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም፤ ሆኖም ጊዜው ሲደርስ አምላክ የችግሩ መንስኤ የሆኑትን የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ የሚያራምዱ ራስ ወዳድ ሰዎችንና መንግሥታትን ያስወግዳል። (መክብብ 8:9) ፈጣሪያችን የግል ፍላጎታቸውን የሚያስቀድሙ ሰብዓዊ መንግሥታትን ያስወግዳል። በእነዚህ መንግሥታት ምትክ በሰማይ የሚገኘው የአምላክ መንግሥት ለሁሉም የምድሪቱ ነዋሪዎች ያለምንም አድልዎ የተትረፈረፈ በረከት ያፈስሳል። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ መንግሥት ንጉሥ ለድሆች እንደሚራራና ችግራቸውንም እንደሚያስወግድ ይናገራል። “እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ . . . ይታደጋልና። ለችግረኛውና ለድሃው ያዝናል፤ የድሆችንም ሕይወት ያድናል” በማለት ቃል ገብቷል።—መዝሙር 72:12-14

ምድር ገነት ስትሆን ድህነት ፈጽሞ አይኖርም፤ እንዲሁም ሁሉም ሰው መኖሪያ ቤትና የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ አምላክ ለሕዝቦቹ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል፦ “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። . . . የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ።” (ኢሳይያስ 65:21, 22) ወደፊት ሰዎች ያለቻቸውን እንደምንም አብቃቅተው በመኖር ፋንታ “ምርጥ ምግቦች የሚገኙበት ታላቅ ግብዣ” ተቋዳሽ ይሆናሉ፤ እንዲሁም ይሖዋ ካዘጋጃቸው ተጨማሪ መልካም ነገሮች ተካፋይ ይሆናሉ። —ኢሳይያስ 25:6

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ ያሉ ሰዎች አምላክ ድህነት የማይኖርበት ዓለም እንደሚመጣ በገባው ቃል ላይ ማሰላሰላቸው አምላክ እንደሚያስብላቸውና እፎይ የሚሉበት ጊዜ ቅርብ እንደሆነ እርግጠኞች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። አንድ ሰው እንዲህ ባለው ተስፋ ላይ ትኩረት ማድረጉ አሁን ያሉበትን ችግሮች በጽናት እንዲቋቋም ጥንካሬ ይሰጠዋል።

ቁልፍ ጥቅስ፦ “እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ . . . ይታደጋልና። ለችግረኛውና ለድሃው ያዝናል፤ የድሆችንም ሕይወት ያድናል።”መዝሙር 72:12, 13