የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?
ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?
“ኑሮ እንዳያያዙ ነው” የሚል አባባል አለ። በዛሬው ጊዜ ሁሉም ነገር የተመቻቸለት አንድም ሰው የለም። ሕይወትህን መቆጣጠር ችለሃል የሚባለው ያለህበትን ሁኔታ አምነህ የምትቀበልና ሁኔታህ የሚፈቅድልህን ያህል ብቻ የምታደርግ ከሆነ ነው። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነህም ሕይወትህን በተወሰነ መጠን መቆጣጠር ከቻልክ ጥሩ ነው። ሁኔታዎችህ እያደር ከተሻሻሉ ደግሞ እሰየው ነው። ይበልጥ አስደሳች የሆነው ግን ወደፊት የሚጠብቅህ ነገር ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰው ሕይወቱን በሚፈልገው መንገድ መምራት የሚችልበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጽ ተስፋ ይዟል። በዚያን ጊዜ ሰዎች ተስፋ አስቆራጭ ከሆኑ ሁኔታዎች፣ በየዕለቱ ከሚደርሱባቸው ጫናዎችና ከአሉታዊ ስሜቶች ነፃ ሆነው አርኪ ሕይወት ይመራሉ። (ኢሳይያስ 65:21, 22) መጽሐፍ ቅዱስ ‘እውነተኛው ሕይወት’ በማለት የሚጠራው ይህንን ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:19
“ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። እነሱ በሠሩት ቤት ሌላ ሰው አይኖርም፤ እነሱ የተከሉትንም ሌላ ሰው አይበላውም። የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፤ የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ።” —ኢሳይያስ 65:21, 22