የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
ቤት የሌላቸውና ድሆች ምን ተስፋ አላቸው?
ጆ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር የቀድሞ ወታደር ነው። በራሱም ሆነ በቤተሰቡ ላይ በደረሱ አሳዛኝ ሁኔታዎች የተነሳ መኖሪያ ቤት ካጣ 18 ዓመታት አልፈዋል። በአንድ ወቅት በአካባቢው ወደሚገኝ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት መሄድ ጀመረ፤ እዚያም ከአንዲት የቤተ መጻሕፍቱ ሠራተኛ ጋር ይወያይ ነበር። ይህ ውይይት ለሕይወቱ መለወጥ ምክንያት ሆኗል።
ማርቲን የተባለ በአርጀንቲና የሚኖር ወጣት በመንፈሳዊ ባዶ እንደሆነ ይሰማው ነበር። ሕይወቱ ትርጉም የለሽ ሆኖበት ነበር። በመሆኑም የሕይወትን ትርጉም ለመፈለግ ተነሳ፤ ቤቱን ትቶም በባሕር ዳርቻ መኖር ጀመረ። ይሁን እንጂ ይፈልግ የነበረውን ነገር ማግኘት አልቻለም፤ እንደውም በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ይሠቃይ ጀመር። በዚህም ምክንያት አምላክን “በእርግጥ ካለህ አንተን እንዳውቅህ እርዳኝ” በማለት እያለቀሰ ለመነ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? በኋላ ላይ እናየዋለን።
ሰዎች ለመኖሪያ ቤት ችግር እንዲዳረጉ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው። አንዳንዶች ጆ የደረሰበት ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ሌሎች ደግሞ እንደ ማርቲን፣ ሕይወት ትርጉም የሌለው ድግግሞሽ ይሆንባቸውና “ከተለመደው” ዓይነት አኗኗር ወጣ ያለ ሕይወት ይመራሉ። በድህነት፣ በተፈጥሮ አደጋ፣ በቤት ውስጥ በሚፈጸም ጥቃት፣ በዕፅ ወይም በአልኮል ሱሰኝነት፣ በአእምሮ መታወክ፣ ቤት ለማግኘት የሚያስችል አቅም በማጣት አሊያም ሥራ አጥ በመሆናቸው የተነሳ ለቤት ችግር የሚዳረጉም አሉ።
በአንድ ወቅት በታዳጊ አገሮች ወይም በጦርነት በተመቱ አሊያም የኢኮኖሚ ድቀት በደረሰባቸው አገሮች ብቻ የሚከሰት ችግር እንደሆነ ተደርጎ ይታይ የነበረው የቤት እጦት “በአብዛኞቹ የበለጸጉ አገሮች ጭምር ዋነኛ ችግር ሆኗል” በማለት ፖል ቶሮ የተባሉ የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር ተናግረዋል። * ለችግሩ አስተዋጽኦ አድርገዋል ተብለው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች በሚሰጥ እርዳታ ረገድ መንግሥታት የሚከተሏቸው ፖሊሲዎችና የገቢ አለመመጣጠን ይገኙበታል።
ብዙ ሰዎች ስለ ነገ ይጨነቃሉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን እንደሚል በማወቃቸው ጭንቀታቸው ቀለል ብሎላቸዋል፤ በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ሐሳብ ቆየት ብለን እንመለከታለን። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጆ እና ማርቲን
በሕይወታቸው መመልከት እንደቻሉት በኢኮኖሚ ረገድ የተረጋጋ ሕይወት እንድንመራና የአእምሮ ሰላም እንድናገኝ የሚያስችሉ መመሪያዎች በመስጠት ዛሬም ቢሆን ሊረዳን ይችላል።መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቱን እንዲለውጥ ረዳው
በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ትሠራና ጆ ወደ ቤተ መጻሕፍቱ ሲመጣ አዘውትራ ትመለከተው የነበረችው ሲንዲ “ጆ የተማረ፣ ጨዋና ትሑት ሰው ይመስላል” ብላለች። የይሖዋ ምሥክር ስለሆነች መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔት ሰጠችው፤ በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ጋበዘችው። በዚያ ያገኛቸው ሰዎች በደግነትና በአክብሮት ስለተቀበሉት አዘውትሮ ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረ። በተጨማሪም በጉባኤው ውስጥ የሚገኝ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ያቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ።
ጆ የተማረው ነገር ስላጽናናው በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማድረግ የሚጠይቅበት ቢሆንም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ሥራ ላይ ማዋል ጀመረ። ለምሳሌ ሕይወት በአክብሮት ሊያዝ የሚገባው ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደሆነና ማጨስ ደግሞ ሰውነትን እንደሚያቆሽሽ አወቀ። (መዝሙር 36:9) በመሆኑም “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” በሚለው የ2 ቆሮንቶስ 7:1 መሠረታዊ ሥርዓት መሠረት ማጨስ አቆመ። በእርግጥም የጆ ውሳኔ ጤንነቱን ያሻሻለለት ከመሆኑም ሌላ ገንዘቡን አድኖለታል።
ጆ ለኑሮ የሚያስፈልገንን ለማግኘት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንደሚኖርብን መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር በመከተል ሥራ መፈለግ ጀመረ። * (1 ተሰሎንቄ 4:11, 12) መክብብ 2:24 “ሰው ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት የሚሻለው ነገር የለም” ይላል። ሥራን በሐቀኝነት መሥራት ስለሚያስከብረን ለራሳችን ያለን አክብሮት ከፍ ይላል፤ ይህም ደስታችን እንዲጨምር ያደርጋል። በተጨማሪም ችግረኞችን ለመርዳት ያስችለናል።—ኤፌሶን 4:28
ሲንዲ ጉባኤው ጆ ያደረገውን ልባዊ ጥረት ሲመለከት “በደስታ ተቀበለው፤ አንዳንዶች ሕጉ የሚፈቅድለትን ተስማሚ መኖሪያና ሌሎች ነገሮች ለማግኘት እንዲያመለክት ረዱት” በማለት ተናግራለች። ጆ እድገት አድርጎ የይሖዋ ምሥክር ሆኖ ተጠመቀ። አሁን ሌሎች ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው መለኮታዊ ጥበብ እንዲመሩ በሚመክርበት ጊዜ የራሱን ተሞክሮ ሊጠቅስላቸው ይችላል።—ምሳሌ 3:13, 14
የሕይወትን ትርጉም አወቀ
ማርቲን የሕይወትን ትርጉም መፈለግ የጀመረው የ20 ዓመት ወጣት ሳለ ነበር። “በውስጤ ይሰማኝ የነበረውን የባዶነት ስሜት ለማሸነፍ የተለያዩ ሃይማኖቶችንና ፍልስፍናዎችን ብመረምርም አልተሳካልኝም” በማለት ተናግሯል። ለተወሰነ ጊዜ በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከኖረ በኋላ ወደ ሃዋይ ሄደ። በዚህ ጊዜ “ገነት የገባሁ መስሎኝ ነበር” ብሏል። ይሁንና የተፈጥሮ ውበት ብቻውን ያደረበትን የባዶነት ስሜት እንዲያሸንፍ አልረዳውም። “በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት በመዋጤ ራሴን ለማጥፋት እስከ ማሰብ ደርሼ ነበር” በማለት ተናግሯል። ማርቲን ስቅስቅ ብሎ ያለቀሰውና አምላክን “በእርግጥ ካለህ አንተን እንዳውቅህ እርዳኝ” ብሎ የለመነው በዚህ ጊዜ ነበር።
ማርቲን ከዚህ በፊት “የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ” የሚል ምልክት አንብቦ እንደነበረ አስታወሰ። ወደዚያ በመሄድ በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወሰነ። እንዲህ ብሏል፦ “ፀጉሬና ጺሜ አድጎ ለበርካታ ወራት ከላዬ ላይ ያልወለቀውን ልብሴን እንደለበስኩ ወደ አዳራሹ ገባሁ። ቢሆንም ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገልኝ።” ማርቲን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ፤ በባሕሩ ዳርቻ ከሚገኘው “ቤቱ” ተነስቶ ወደ ከተማ እየሄደ ያጠና ነበር።
በመጨረሻም ማርቲን ለጥያቄዎቹ አጥጋቢ መልስ ማግኘት ቻለ። በውጤቱም የነበረበት የመንፈስ ጭንቀት ተወግዶለት ኢየሱስ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው” በማለት የተናገረለትን ደስታ ማጣጣም ቻለ።—ማቴዎስ 5:3
“ሰዎች እያደረግኩ ባለሁት ለውጥ በጣም እየተደነቁ ነው”
ማርቲን ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆ ሕይወቱን እንዲያስተካክል የረዱትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል ሲጀምር ስለ ሕይወት የነበረው አመለካከት መለወጡ በግልጽ እየታየ መጣ። ከዚያም ማርቲን ስለ ቁመናው ማሰብ ጀመረ፤ በይሖዋ ምሥክሮች እርዳታም ሥራና የሚኖርበት ቤት አገኘ። “ከዚህ በፊት የምታወቀው ጎዳና ተዳዳሪ በመሆኔ ነበር፤ አሁን ግን የአካባቢው ሰዎች እያደረግኩ ባለሁት ለውጥ በጣም እየተደነቁ ነው” በማለት ተናግሯል።
ከጊዜ በኋላ ማርቲን ወደ አርጀንቲና ተመልሶ የይሖዋ ምሥክር በመሆን ተጠመቀ። አሁን በመንፈሳዊ የተጠሙ ሰዎች በአእምሯቸው ለሚጉላሉ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ የመርዳት መብት በማግኘቱ ደስተኛ ነው።
የመኖሪያ ቤት እጦትና ድህነት የማይኖሩበት ጊዜ
የአምላክ አገልጋይ የነበረው ኤርምያስ ይኖር የነበረበት ዘመን በመከራና በችግር የተሞላ ነበር። ጨካኝ የሆነ ጠላት አገሪቱን በመውረሩ የተነሳ ብዙ ሰዎች ለግዞትና ለባርነት ተዳርገው ነበር። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 1:3) ኤርምያስ ከጥፋቱ በሕይወት ቢተርፍም የነበረውን ንብረት በሙሉ አጥቷል። በዚህ ጊዜ በምሬት ተውጦ “መጎሳቆሌንና ዱር አዳሪ መሆኔን አስታውስ” ሲል ጸልዮአል።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:19
ኤርምያስ 1:8) ሁለተኛ፣ ድህነትና ሥቃይ ተወግዶ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት የሚሰፍንበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚናገረውን ጥቅስ ያውቅ ነበር።—መዝሙር 37:10, 11
ኤርምያስ ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስበትም ተስፋ አልቆረጠም። ለምን? አንደኛ ነገር፣ ይሖዋ ጨርሶ እንደማይተወው ያውቅ ነበር። (እነዚህ ሁኔታዎች የሚፈጸሙት ፍጹም መስተዳድር በሆነው በአምላክ መንግሥት እንጂ በሰው ልጆች ጥረት አይደለም። (ዳንኤል 7:13, 14) የዚህ መንግሥት ንጉሥ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለድሆች ርኅራኄ ያሳየው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ሉቃስ 7:22፤ 14:13) በእሱ አገዛዝ ሥር “ጻድቅ ይለመልማል። . . . ሰላም ይበዛል። እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ፣ እንዲሁም ችግረኛውንና ረዳት የሌለውን ሁሉ [ይታደጋል]። ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል።”—መዝሙር 72:7, 12, 14
ኢየሱስ ትምህርቱ በዋነኝነት ያተኮረው በአምላክ መንግሥት ላይ ነበር። (ሉቃስ 4:43) እንዲያውም ሰዎች “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ መንግሥት ምድርን ሙሉ በሙሉ በሚገዛበት ጊዜ ሕይወት ምን ይመስል ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጊዜ በዓይነ ሕሊናችን ለመሳል የሚያስችሉ ጥቅሶች ይዟል። ለምሳሌ የአምላክ መንግሥትን ተገዢዎች በተመለከተ እንዲህ ይላል፦
-
“ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። እነሱ በሠሩት ቤት ሌላ ሰው አይኖርም፤ እነሱ የተከሉትንም ሌላ ሰው አይበላውም። . . . የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ።”—ኢሳይያስ 65:21, 22
-
“እያንዳንዱም ከወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም፤ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ አፍ ተናግሯልና።”—ሚክያስ 4:4
ይህ የተረጋገጠ ተስፋ ፈተና በሚደርስብን ጊዜ መንፈሳችን እንዲታደስ ያደርጋል። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጆ፣ ማርቲንና ሌሎች ሰዎች እንደተገነዘቡት አሁንም እንኳ ትርጉም ያለው አርኪ ሕይወት እንድንኖር ይረዱናል። ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ “እኔን የሚሰማ ሰው . . . ተረጋግቶ ይኖራል፤ መከራ ይደርስብኛል የሚል ስጋትም አያድርበትም” የሚል ዋስትና ይሰጠናል። (ምሳሌ 1:33) አንተም በሕይወትህ እንዲህ እንዲሰማህ እንመኛለን!
^ አን.6 በግጭት፣ በዓመፅ ወይም በስደት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስደተኞች ወይም ተፈናቃዮች ለመሆን ተገደዋል።
^ አን.11 አንዳንዶች የመሥራት ፍላጎት ቢኖራቸውም በአካል ጉዳት፣ በጤና ችግር ወይም በእርጅና ምክንያት መሥራት ሳይችሉ ይቀራሉ። አምላክ “መሥራት የማይፈልግ” ሰው አይወድም።—2 ተሰሎንቄ 3:10