በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የሙጫ እሳት ራት አስደናቂ የመስማት ችሎታ

የሙጫ እሳት ራት አስደናቂ የመስማት ችሎታ

ትልቁ የሙጫ እሳት ራት እስከ ዛሬ ከሚታወቁት ፍጥረታት ሁሉ በተሻለ፣ በጣም ቀጭን (high pitch) የሆኑ ድምፆችን መስማት ይችላል። ይሁንና የስፒል አናት የሚያክሉት የዚህ ነፍሳት ጆሮዎች የተሠሩበት መንገድ በጣም ቀላል ነው።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ተመራማሪዎች ይህ የእሳት ራት ያለውን የመስማት ችሎታ ለብዙ ዓመታት ሲያጠኑ ቆይተዋል። በቅርቡ ደግሞ በስኮትላንድ በሚገኘው ስትራትክላይድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ የሳይንስ ምሁራን የተለያየ መጠን ያላቸውን ድምፆች በመጠቀም የዚህን የእሳት ራት የመስማት ችሎታ ለመለካት ሞክረዋል። “የጆሮ ታምቡሮቹን” እርግብግቢት ከለኩ በኋላ ለመስማት በሚጠቀሙባቸው የነርቭ ሴሎች ላይ የታየውን እንቅስቃሴ መዘገቡ። የእሳት ራቶቹ እስከ 300 ኪሎ ኸርዝ የሚደርስ ድምፅ መስማት እንደሚችሉ በዚህ መንገድ አወቁ። በሌላ በኩል የሌሊት ወፎች መስማት የሚችሉት እስከ 212 ኪሎ ኸርዝ የሚደርስ ድምፅ ሲሆን ዶልፊኖች ደግሞ እስከ 160 ኪሎ ኸርዝ የሚደርስ ድምፅ ነው፤ የሰው ልጆች ግን ከ20 ኪሎ ኸርዝ የሚበልጥ ድምፅ መስማት አይችሉም።

ተመራማሪዎች የዚህን የእሳት ራት ከፍተኛ የመስማት ችሎታ መሠረት በማድረግ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መሥራት ይፈልጋሉ። በስትራትክላይድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ጄምስ ዊንድሚል የእነዚህን ነፍሳት የመስማት ችሎታ በማየት “የተሻለ ጥራት ያላቸውና መጠናቸው አነስተኛ የሆነ የድምፅ ማጉያዎችን መሥራት” እንደሚቻል ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ የድምፅ ማጉያዎች በሞባይል ስልኮች፣ መስማት የሚቸግራቸውን ሰዎች በሚረዱ መሣሪያዎችና በሌሎች መሣሪያዎች ውስጥ ሊገጠሙ ይችላሉ።”

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ትልቁ የሙጫ እሳት ራት ያለው አስደናቂ የመስማት ችሎታ የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?